††† እንኳን ለአእላፍ ሰማዕታት: ቅዱስ ጴጥሮስ እና ቅዱስ ቀሌምንጦስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††
††† ቅዱሳን ሰማዕታት †††
††† ቤተ ክርስቲያን ዛሬ (ኅዳር 29) የሁሉንም ሰማዕታት በዓል ታከብራለች:: አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ (ቅዱሱ ሊቅ) በመጽሐፈ ሰዓታት ሰማዕታትን:-
"መስተጋድላን ከዋክብት ብሩሃን::
ማኅትዊሃ ለቤተ ክርስቲያን::" ይላቸዋል::
በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን የሮም መንግስት ዓለምን የሚያስተዳድረው በሁለት ከተሞች: ማለትም በራሷ በሮምና በአንጾኪያ ነበር:: የወቅቱ ንጉሥ ኑማርያኖስ ሲሆን የቤተ መንግስቱ ልዑላንና የጦር አለቆች ቅዱሳኑ:- *ፋሲለደስ: *ገላውዴዎስ: *ፊቅጦር: *መቃርስ: *አባዲር: *ቴዎድሮስ (ሦስቱም): *አውሳብዮስ: *ዮስጦስ: *አቦሊ: ሌሎቹም ነበሩ::
ሴቶቹ ደግሞ ቅዱሳቱ:- *ማርታ: *ሶፍያ: *ኢራኢ: *ታኡክልያ: ሌሎቹም ነበሩ:: ለእነዚህ ሁሉ የበላይ ደግሞ ቅዱስ ፋሲለደስ ነበር:: ወቅቱ ከፋርስ: ከቁዝና ከበርበር ጦርነት የሚበዛበት ነበርና ባጋጣሚ ንጉሡ ኑማርያኖስ በሰልፍ መካከል ተመትቶ ወደቀ (ሞተ)::
የሮም መንግስትም ባዶ ሆነች:: ዙፋኑን መያዝ ለቅዱስ ፋሲለደስም ሆነ ለሌሎቹ ቅዱሳን ቀላል ነበር:: ግን እነሱ ዝም ብለው ጠላትን ለመዋጋት ወጡ::
በዘመኑ ደግሞ በግብጽ የፍየል እረኛ የነበረና ከልጅነቱ ሰይጣን የሚያናግረው አንድ አግሪጳዳ የሚሉት ጉልበተኛ ሰው ነበር:: ንጉሡ ከወለዳቸው ልጆች ሁለቱ ሴቶች ክፉዎች ነበሩና ትንሿ አግሪጳዳን ማንም በሌለበት አንግሣ ጠበቀቻቸው:: ስሙንም ዲዮቅልጢያኖስ አለችው::
በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሰይጣን ቀጥሎ እንደዚህ የከፋ ስም የለም:: የዓለም ክርስቲያኖችን የጨፈጨፈ ሰው ነው:: ትልቋ ደግሞ የትንሿን አይታ መክስምያኖስ የሚባል አውሬ አግብታ አነገሠችው:: ዓለምም በእነዚህ ጨካኝ ሰዎች እጅ ወደቀች::
ሠራዊቱ ሁሉ በሚሊየን ይቆጠራሉ:: የተደረገውን ሲያዩ ተበሳጩ:: ይህንን የተመለከተው ቅዱሱ ፋሲለደስ ግን ልዑላኑንና አለቆችን ሰብስቦ:- "ይህ ዓለም ከነ ክብሩ ጠፊ ነው:: ስለዚህ የተሻለውን የክርስቶስን መንግስት እንምረጥ" አላቸው:: ሁሉም እንደ አንድ ልብ መካሪ ደስ ተሰኝተው ምድራዊ ክብራቸውን ሊተው ወሰኑ::
ቀጥለውም በአንድ ቤት ተሰብስበው ይጾሙ: ይጸልዩ ገቡ:: ወደ ውጪ የሚወጡት ለምጽዋት ብቻ ነበር:: ከሃዲውም ይህንን ሲያይ የልብ ልብ ተሰማው:: ከድሮ ያሰበውንና ክርስቲያኖችን የማጥፋቱን እቅድ ሊፈጽም ምክንያት አገኘ::
አባ አጋግዮስ በሚባል መነኩሴ ምክንያት "አብያተ ክርስቲያናት ይትዐጸዋ: አብያተ ጣዖታት ይትረኀዋ - ቤተ ክርስቲያኖች ይዘጉ: ቤተ ጣዖቶችም ይከፈቱ" አለ:: አጵሎን: አርዳሚስ የሚባሉ ጣዖቶችንም አቆመ::
በዚህ አዋጅ ምክንያትም የክርስቲያኖች ሰቆቃ ጀመረ::
*ምድር በደም ታጠበች::
*ቅዱሳኑ ቀባሪ አጡ::
*እኩሉ ተገደለ:: እኩሉ ተቃጠለ:: እኩሉ ታሠረ:: እኩሉም ተሰደደ::
የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የተጻፈው በብራናና በብዕር አይደለም:: ይልቁኑ እንደ ቀለም የሰማዕታት ደማቸው: እንደ ብዕር አጥንታቸው: ቆዳቸው እንደ ብራና ሆኖ ተጽፏል እንጂ:: ሰማዕታት ለሃይማኖታቸው የከፈሉት ዋጋ እጅግ ታላቅ ነው::
ስለዚህም "ተጋዳዮች: የሚያበሩ ኮከቦች: የቤተ ክርስቲያን ሻማዎች" ተብለው: እነሱ እየቀለጡ አብርተዋል:: ሰማዕትነት በብሉይ ኪዳን የጀመረና እስከ ዳግም ምጽዐተ ክርስቶስም የሚቀጥል ቢሆንም "ዘመነ ሰማዕታት" የሚባለው ከ150 እስከ 312 ዓ/ም ድረስ ያለው ዘመን ነው::
በተለይ ግን ከ270ዎቹ እስከ 312 ዓ/ም ድረስ ያሉ ዓመታት እጅግ የከፉ ነበሩና: የአርባ ሰባት ሚሊየን (47,000,000) ክርስቲያኖች ደም በምድር ላይ ፈሷል:: የሰማዕታት ምሥጢራቸው ቃለ ወንጌል: የጌታ ስብከትና ሕይወት እንጂ ሌላ አይደለም:: (ማቴ. 10:16, ማር. 13:9, ሉቃ. 12:4, ዮሐ. 16:1, ሮሜ. 8:35, ራዕይ. 2:9)
የቅዱሳን ሰማዕታት መነሻቸው ቅዱስ እስጢፋኖስ ሲሆን ፍጻሜአቸው ደግሞ ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ጳጳሳት ነው::
††† ቅዱስ ጴጥሮስ ሰማዕት †††
††† ይህ ቅዱስ የሚታወቀው "ተፍጻሜተ ሰማዕት (የሰማዕታት መጨረሻ)" በሚለው ስሙ ነው::
ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
የቅዱሱ ሃገረ ሙላዱ ግብጽ ናት:: ዘመኑም 3ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው:: ወላጆቹ ካህን ቴዎድሮስና ቡርክት ሶፍያ ልጅ አጥተው ሐምሌ 5 ቀን ወደ ፈጣሪ ቢማጸኑ በራዕይ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ተገልጠው ብሥራትን ለሶፍያ ነገሯት:: በወለደችው ጊዜም በራዕዩ መሠረት "ጴጥሮስ" አለችው::
ሰባት ዓመት በሆነው ጊዜም ለቤተ እግዚአብሔር ሰጥተው በሊቀ ጳጳሳቱ ቅዱስ ቴዎናስ እጅ አደገና በወጣትነቱ ሊቅ: ጥዑመ ቃልና በጐ ሰው ሆነ:: ዲቁናና ቅስናን ተሹሞ ሲያገለግል ቅዱስ ቴዎናስ በማረፉ ቅዱስ ጴጥሮስን የግብጽ 17ኛ ፓትርያርክ አድርገው ሾሙት::
ዘመኑ ደግሞ እጅግ ጭንቅ ነበር:: ክርስቲያኖች በተገኙበት ስለሚገደሉ: አብያተ ክርስቲያናትም ስለ ተቃጠሉ የቅዱሱ መከራ የበዛ ነበር:: ለ14 ዓመታት በፍጹም ትጋት ከመንጋው ጋር ተጨነቀ::
አርዮስን (ተማሪው ነበር) አውግዞ ለየው:: ከጌታ ጋርም ብዙ ጊዜ ተነጋገረ:: ብዙ ተአምራትንም ሠራ:: በዚህ ሁሉ ጊዜ አንድም ቀን በመንበረ ጵጵስናው ላይ አልተቀመጠም:: በኋላ ግን ጨካኙ ንጉሥ እንዲገደል አዘዘ::
ሕዝቡ "ከእሱ በፊት እኛን ግደሉን" በማለታቸው ሁከት እንዳይነሳ ቅዱስ ጴጥሮስ ተደብቆ ሔደና በፈቃዱ ለወታደሮች ተሰጠ:: በዚያች ሌሊትም የእርሱ ደም የግፍ ማብቂያ እንዲሆን እያለቀሰ ጮኸ:: ከሰማይም "አሜን! ይሁን!" የሚል ቃል መጣ:: ያን ጊዜ የእርሱ አንገት ተሰየፈ:: ዘመነ ሰማዕታትም አለፈ::
††† ቅዱስ ቀሌምንጦስ ዘሮም †††
††† የዚህ ቅዱስ ሐዋርያ ስሙ እንደ ምን ያምር! እንደ ምንስ ይከብር! ለቤተ ክርስቲያን ትልቁ ድልድዩዋ ነውና:: ቅዱስ ቀሌምንጦስ የቅዱስ ቀውስጦስና የቅድስት አክሮስያ ልጅ ሲሆን ወንድምም ነበረው::
አባትና እናቱም የሮም መሳፍንት: በስብከተ ቅዱስ ጴጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት ያመኑ: ገንዘባቸውን በምጽዋት የጨረሱ የመጀመሪያዎቹ የሮም ክርስቲያኖች ናቸው:: ልጆቻቸው (ቀሌምንጦስና ወንድሙ) በመርዝ ቢሞቱባቸው በአምላከ ጴጥሮስ ተማጽነው ተነስተውላቸዋል::
አንድ ጊዜ ቀውስጦስ በሌለበት አንድ ሰው አክሮስያን ስላስቸገራት ልጆቿን ይዛ ተሰዳለች:: በመንገድም መርከባቸው ተሰብሮ ቅዱስ ቀሌምንጦስ በስባሪው ግብጽ ደርሷል:: በዚያም ቅዱስ ጴጥሮስን አግኝቶት የሊቀ ሐዋርያት ደቀ መዝሙሩ ሆኗል::
ቅዱስ ጴጥሮስንም ተከትሎ ለአገልግሎት ብዙ አሕጉራትን ዙሯል:: ብዙ ምሥጢራትንም ተካፍሏል:: የቅዱሳን ሐዋርያትን ዜናም ከቅዱስ ሉቃስ (ግብረ ሐዋርያት) ቀጥሎ የጻፈ እርሱ ነው::
ቅዱሳን ሐዋርያት ሙሉ ቀኖናቸውን ለቅዱስ ቀሌምንጦስ ሲሰጡት ቅዱስ ጴጥሮስ ደግሞ ሰብአ ሰገል ለክርስቶስ ያመጡትን ወርቅ: እጣን: ከርቤውን አስረክቦታል:: በተለይ ሁሉም ሐዋርያት ባረፉ ጊዜ እርሱ ቤተ ክርስቲያንን ተረከበ:: በሮም ሁለተኛው ፓትርያርክ ሆነ::
በጊዜው መጽሐፈ ቅዳሴ ባለ መደራጀቱ ሥጋውን ደሙን ሲፈትቱ ፈጣሪ እንዳመለከታቸው ይጸልዩ ነበር:: ቅዱሱ ግን የጌታንና የሐዋርያትን ቅዳሴ ዛሬ በምናየው መንገድ አደራጅቶ ጽፎታል:: በስሙ የሚጠራና "ቀሌምንጦስ" የሚባል መጽሐፉም (8 ክፍሎች አሉት) ከ81ዱ (አሥራው) መጻሕፍት ተቆጥሮለታል::
ቅዱሱ ሐዋርያ እንዲህ ሲመላለስ ኖሮ በ2ኛው መቶ ክ/ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በጠራብሎስ እጅ ወደቀ:: ንጉሡም "ክርስትናን አስተምረሃል" በሚል ብዙ አሰቃይቶ: ከትልቅ ድንጋይ ጋር አስሮ ባሕር ውስጥ አስጥሞታል:: በዚህም ዐርፏል::
ሁሌ ግን በዓመት በዓመት ባሕሩ እየተከፈለላቸው: ምዕመናን እየገቡ ከቅዱስ አካሉ ይባረካሉ:: ቅዱሱን ብዙ ጊዜ "ቀሌምንጦስ ዘሮም" የምንለው "ቀሌምንጦስ ዘእስክንድርያ" የሚባል መናፍቅ ስላለ ከእርሱ ለመለየት ነው::
የቅዱሱ ክብር በእውነት ታላቅ ነው!
††† አምላከ ሐዋርያት ወሰማዕት በመከራቸው ከመከራ ይሰውረን:: በረከታቸውንም ያብዛልን::
††† ኅዳር 29 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱሳን ሰማዕታተ ክርስቶስ (ሁሉም)
2.ቅዱስ ጴጥሮስ ተፍጻሜተ ሰማዕት
3.ቅዱስ ቀሌምንጦስ ሐዋርያ (ዘሮም)
††† ወርኀዊ በዓላት
1.የፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት
2.ቅዱስ ማርቆስ ዘቶርማቅ
3.ቅድስት ፍቅርተ ክርስቶስ ኢትዮጵያዊት
4.ቅዱስ ዘርዐ ክርስቶስ
5.ቅድስት አርሴማ ድንግል
††† "አቤቱ አሕዛብ ወደ ርስትህ ገቡ::
የቅድስናህንም መቅደስ አረከሱ::
ኢየሩሳሌምንም እንደ መደብ አደረጉአት::
የባሪያዎችህንም በድኖች ለሰማይ ወፎች አደረጉ::
የጻድቃንህንም ሥጋ ለምድር አራዊት::
ደማቸውንም በኢየሩሳሌም ዙሪያ እንደ ውኃ አፈሰሱ::
የሚቀብራቸውም አጡ::" †††
(መዝ. ፸፰፥፩)
✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞
✞ ወለወላዲቱ ድንግል ✞
✞ ወለመስቀሉ ክቡር አሜን ✞
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ::" /ማቴ ፫:፫/
ዝክረ ቅዱሳንን ተማሩ ብለን እንለምናችኋለን!!።
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
✝ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Togethellettps://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━━━
Comments
Post a Comment