✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ፡፡ አሜን፡፡ ✞✞✞
=>+"+ እንኩዋን ለታላቁ "ጻድቅና ገዳማዊ አባ በኪሞስ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ +"+
+*" ታላቁ አባ በኪሞስ "*+
=>በቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ "ታላቁ : ዓቢይ : (THE GREAT)" የሚል ስም የሚሰጣቸው አባቶች የተለዩ ናቸው:: አንድም እጅግ ብዙ ትሩፋቶችን የሠሩ ናቸው:: በሌላ በኩል ደግሞ በተመሳሳይ ስም ከሚጠሩ ሌሎች ቅዱሳን እንለይበታለን::
+ገዳማዊ ሕይወት ጥንቱ ብሉይ ኪዳን ነው:: በቀዳሚነትም በደብር ቅዱስ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ደቂቀ ሴት እንደ ጀመሩት ይታመናል:: ሕይወቱ በጐላ: በተረዳ መንገድ የታየው ግን በታላቁ ጻድቅ ሄኖክ: ከዚያም በቅዱሱ ካህን መልከ ጼዴቅ አማካኝነት ነው::
+ቀጥሎም እነ ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ : እነ ኤልሳዕ ደቀ መዝሙሩ ኑረውበታል:: በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ሙሉ ሕይወቱን በገዳም (በበርሃ) ያሳለፈው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቅድሚያውን ይይዛል::
+ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና መድኃኒታችን ክርስቶስ በገዳመ ቆረንቶስ ለ40 ቀናት በትሕርምት ኑሮ ገዳማዊ ሕይወትን ቀድሷል:: አስተምሯል:: በዘመነ ስብከቱም ያድርባት የነበረችው የደብረ ዘይቷ በዓቱ (ኤሌዎን ዋሻ) በራሷ ለዚህ ሕይወት ትልቅ ማሳያ ናት::
+ከጌታ ዕርገት በሁዋላም ክርስቲያኖቹ የዓለም ሁካታ ሲሰለቻቸው: አንድም በንጹሕና በተሸከፈ ልቡና ለፈጣሪያቸው መገዛትን ሲሹ ከከተማ ወጣ እያሉ ይኖሩ እንደ ነበር የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ:: አኗኗራቸውም በቡድንም: በነጠላም ሊሆን ይችላል::
+ዋናው ነገር ግን በጾምና በጸሎት መትጋታቸው ነው:: ይሕም ሲያያዝ እስከ 3ኛው መቶ ክ/ዘመን ደረሰ:: በዚህ ዘመን ግን አባ ዻውሊ የሚባል አንድ ንጹሕ ክርስቲያን ይሕንን ሕይወት ወደ ሌላ ደረጃ ከፍ አደረገው:: ለ80 (90) ዓመታት ሰው ሳያይ ተጋድሎ "የባሕታውያን አባት" ተባለ:: ደንብ ያለው ተባሕትዎም ጀመረ::
+ይህ ከሆነ ከ20 ዓመታት በሁዋላ ደግሞ አባ እንጦንስ የሚባሉ ደግ ክርስቲያን ይህንን ገዳማዊ ሕይወት በሌላ መንገድ አጣፈጡት:: በቅዱስ ሚካኤል አመንኩዋሽነት ገዳማዊ ሕይወት በምንኩስና ተቃኘ:: ስለዚህም አባ እንጦንስ "የመነኮሳት አባት" ተባሉ::
+እርሳቸውም ሕይወቱን ለማስፋፋት ከተለያዩ አሕጉር ደቀ መዛሙርትን እየተቀበሉ አመንኩሰዋል:: ቅዱሳን የአባ እንጦንስ ልጆችም ወደየ ሃገራቸው ተመልሰው: ሕይወቱን በተግባር አሳይተው ገዳማዊነትን አስፋፍተዋል::
=>አባ በኪሞስ ስም አጠራሩ እጅግ የከበረ: ሽምግልናው ያማረ ባሕታዊ: መነኮስና ሐዋርያዊ አባት ነው:: የነበረው በዘመነ ጻድቃን (በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን) ሲሆን ትውልዱ እንደ ብዙዎቹ የወቅቱ ቅዱሳን በላይኛው (በደቡብ) ግብጽ ነው::
+አባ በኪሞስ ከክርስቲያን ወላጆቹ ተወልዶ: በልጅነቱ ክርስትናን አጥንቶ በእረኝነት ተሰማራ:: በጐቹን ሲጠብቅም የእግዚአብሔር ጥሪ ወደ እርሱ መጣ:: ያኔም እድሜው ገና 12 ዓመት ነበር::
+አጠራሩም እንዲህ ነው:: በእረኝነት ሳለ መልአከ እግዚአብሔር ሰው መስሎ መጥቶ ተገናኘው:: ቁጭ ብሎም ስለ መናንያን ክብር ሲያጫውተው ከዋለ በሁዋላ "ለምን እኔና አንተ ለዚህ ክብር እንድንበቃ አንመንንም?" ሲል ጠየቀው::
+ሕጻኑ በኪሞስም ደስ ብሎት "እሺ!" አለው:: ወዲያውም መንጋውን ለወላጆቹ መልሶ ከመልአኩ ጋር ወደ ገዳም ሔዱ:: ቅዱሱ መልአክም በመንገድ ሳሉ ብዙ ምሥጢራትን ነገረው:: አጸናው:: ረድኤተ እግዚአብሔርንም አሳደረበት::
+ልክ ወደ አንድ ገዳም ሲደርሱ ግን ተሰወረበት:: ቅዱስ በኪሞስም ወደ ገዳሙ ገብቶ ይምናኔ ሕይወትን ጀመረ:: በዚያም እንደ ልጅነቱ አበውን እያገለገለ: ሥርዓተ ገዳምን: ትሕርምትን: አርምሞንና ተጋድሎን በደንብ አጠና::
+በዚያው ገዳም ሳለም ምንኩስናን ተቀበለ:: ለ24 ዓመታት አገልግሎ 36 ዓመት በሞላው ጊዜም ተባሕትዎን ተመኘ:: ከአባቶች ዘንድ ተባርኮም ጭው ወዳለው በርሐ እየዘመረ ተጉዋዘ::
+አንዲት ቦታ ላይም የቀኑን ሐሩር: የሌሊቱን ቁር ሳይሰቀቅ ለ3 ዓመታት ጸለየ:: እድሜው 39 ዓመት ሲሆን እንደ ገና ጭራሽ ፍጥረት ወደ ማይደርስበት በርሃ ተጉዞ ደረሰ::
+የደረሰበት አካባቢ ፀሐይ እንደ እሳት የምታቃጥልበት: ምድር እንደ ብረት ምጣድ የጋለችበት ነው:: ቸር እግዚአብሔር ግን ለዚህ ታላቅ ሰው አንዲት የተምር ዛፍ አበቀለለት:: ትንሽ ምንጭንም አፈለቀለት::
+አባ በኪሞስም ዋናውን ተጋድሎ በዚህ ሥፍራ ጀመረ:: ጾምን : ጸሎትን : ስግደትን ያዘወትር ነበር:: ጾሙ በመጀመሪያ 3 ቀን: ቀጥሎ 7 ቀን: በመጨረሻ ግን በ40 ቀን አንዴ ብቻ ማዕድ የሚቀምስ ሆነ::
+ለዛውም ምግቡ አንዲት እፍኝ ይቆረጥማል:: አንዲት ጉንጭ ውሃን ይጐነጫል:: ከዚህ በላይ ለሥጋው ምክንያትና ምቾትን ሊሰጣት አልፈለገም:: በዚህም ምክንያት አካሉ ደርቆ ከሰውነት ተራ ወጣ:: ግን ብርቱና ደስተኛ: የማይደክምም ተዋጊ ነበር::
+የሚገርመው ደግሞ ጸሎቱ ነው:: ሌሎች ጸሎቶቹ ሳይቆጠሩ በመዓልት (በቀን) 2,400 ጊዜ አቡነ ዘበሰማያትን በልዩ ተመስጦ ያደርሰው ነበር:: በሌሊትም በተመሳሳይ ቁጥር ይደግመዋል:: በድምሩ በየዕለቱ 4,800 ጊዜ አቡነ ዘበሰማያት ይል ነበር::
+ስግደቱንማ ማን ቆጥሮት! ታላቁ አባ በኪሞስ እንዲህ ባለ ገድል ለ24 ዓመታት ቆየ:: እድሜውም 63 ደረሰ:: አንድ ጊዜ ግን ሕማማተ ክርስቶስን እያሰበ ያለ ምግብ ለ80 ቀናት ቆየ:: ፈጽሞ በተራበ ጊዜም ቅዱስ መልአክ ከሰማይ ሕብስተ በረከቱን: ጽዋዐ አኮቴቱን ይዞለት ወረደ::
+ከሕብስቱ መግቦት: ከጽዋው አጠጥቶት ወደ ሰማይ ዐረገ:: ሲያርግ ግን ሕብስቱን ትቶለት ነበር:: "ዘወትርም ከዚህ ተመገብ" ብሎታል:: አባ በኪሞስም ከዚያች ቀን ጀምሮ እስከ ዕረፍቱ ድረስ የተመገበው ከዚያ ሕብስት ነው:: ግን አላለቀም ነበር::
+በታላቁ አባ በኪሞስ ዘመን እነ አቡነ ኪሮስና ታላቁ ሲኖዳን የመሰሉ አበው ነበሩ:: በተለይ የባሕታውያን ሁሉ አለቃ አባ ሲኖዳና አባ በኪሞስን መንፈስ ቅዱስ እንዲህ አስተዋውቁዋቸዋል::
+አንድ ቀን አባ ሲኖዳ የእንቁ ምሰሶ ከምድር እስከ ሰማይ ተዘርግቶ ያይና "ጌታየ! ምሥጢሩ ምንድን ነው?" ቢል "ይህ ምሰሶ አባ በኪሞስ ነውና ሒድ ተገናኘው" የሚል ቃልን ሰማ:: አባ ሲኖዳም በእግሩ ተጉዞ አባ በኪሞስን አገኘው::
+ሰላምታን ከተለዋወጡ በሁዋላ አባ በኪሞስ ታላቁ ሲኖዳን "እኔ ወጥ ልሥራ: አንተ ውሃ ቅዳ" አለው:: ቅዱስ ሲኖዳ ከበር ብቅ ብሎ ማሰሮውን በተአምራት ውሃ ሞልቶት ሲመለስ አባ በኪሞስ ደግሞ ያለ እሳት ወጡን አብስሎት ቆየው::
+2ቱም ተገርመው ፈገግታን ተለዋወጡ:: ማንነታቸውንም ተዋወቁ:: ለመናፈስ ወደ በርሃ ወጥተው ሳለም ደክሟቸው ቁጭ አሉ:: ከፊታቸው አንድ የሰው ራስ ቅል ነበርና በበትራቸው መታ : መታ አድርገው "አንተ! ተነስ አጫውተን" አሉት::
+ያ አጽምም ሥጋ ነስቶ: ተነስቶ ሰገደላቸው:: "ከወዴት መጣህ?" ቢሉት "ከሲዖል" አላቸው:: አረማዊ እንደ ነበርና የሲዖልን የመከራ ብዛት ነገራቸው:: አክሎም "ክርስቲያን ነን እያሉ በክርስትናቸው የሚቀልዱ ከእኛ በታች በብዛት አሉ:: መከራቸው ተነግሮ አያልቅም" አላቸው::+ድጋሚ በበትራቸው ነክተው ወደ ነበረበት መለሱ:: ከዚያም ቅዱሳኑ ወደየ በዓታቸው ተሰነባበቱ:: ታላቁ አባ በኪሞስ ከዚህ በሁዋላ ለ7 ዓመታት ያህል መልአክ በክንፉ እየወሰደው ወንጌልን ሰብኩዋል:: ብዙዎችንም ወደ ሃይማኖትና ንስሃ
አምጥቷል::
+ሁሌም እንቅቦችን እየሰፋ ይሸጥ: በዋጋውም ለነዳያን ይራራ ነበር:: መልአኩም ወደ ፈለገበት ቦታ ተሸክሞ ይወስደው ነበር:: ታላቁ ቅዱስ አባ በኪሞስ በርሃ በገባ በ58 ዓመቱ : በተወለደ በ70 ዓመቱ በዚህች ቀን ዐርፏል:: የክብር ክብርንም ወርሷል::
=>አምላከ አባ በኪሞስ ጸጋውን: ክብሩን አይንሳን:: ከበረከቱም ይክፈለን::
=>ታሕሳስ 11 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ታላቁ አባ በኪሞስ
2.ቅዱስ በርተሎሜዎስ
3.ቅዱስ ቴዎድሮስ
4.ቅዱስ በጥላን
=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ያሬድ ካህን
2.ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት
3.ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
4.አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ
5.ቅድስት ሐና ቡርክት
=>+"+ በእሸቅድምድም ሥፍራ የሚሮጡት ሁሉ እንዲሮጡ: ነገር ግን አንዱ ብቻ ዋጋውን እንዲቀበል አታውቁምን? እንዲሁም ታገኙ ዘንድ ሩጡ:: የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል:: እነዚያም የሚጠፋውን አክሊል ሊያገኙ ነው:: እኛ ግን የማይጠፋውን:: +"+ (1ቆሮ. 9:24)
✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞
✞ ወለወላዲቱ ድንግል ✞
✞ ወለመስቀሉ ክቡር አሜን ✞
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ::" /ማቴ ፫:፫/
ዝክረ ቅዱሳንን ተማሩ ብለን እንለምናችኋለን!!።
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
✝ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Togethellettps://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━━━
Comments
Post a Comment