✝" ታኅሣሥ 10 "
<<< እንኩዋን ለቅዱሳን ሊቃውንት "አባ ኒቆላዎስ" : "አባ ሳዊሮስ" እና "ቅድስት ሱርስት" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ >>>
+*" ቅዱስ ኒቆላዎስ ሊቅ "*+
=>ቅዱስ ኒቆላዎስ:-
*ሃይማኖቱ የቀና::
*ምግባሩ የጸና ሊቅ::
*ብዙ መከራን የተቀበለ ሰማዕት::
*ብዙዎችን ያሳመነ ሐዋርያ::
*በበርሐ ለዘመናት የተጋደለ ጻድቅ::
*በዽዽስና ያገለገለ እረኛ እና:
*ከ318ቱ ሊቃውንት አንዱ ነው::
+የተወለደው በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን ሲሆን ሃገሩ ሜራ ትባላለች:: ይህች ሃገር ዛሬ የት እንዳለች ማወቅ ባንችልም ታሪክ ግን የቀድሞዋ ሮም ግዛት እንደ ነበረች ይነግረናል:: የቅዱስ ኒቆላዎስ ወላጆች የዘመኑ ጥሩ ክርስቲያኖች ነበሩ::
+በሕጉ: በሥርዓቱ: በሥጋ ወደሙና በምጽዋት ቢኖሩም ልጅ አልነበራቸውም:: እግዚአብሔርን ሲለምኑ የጉብዝናቸው ዘመን አልፎ አረጁ:: ልጅ መጠየቁንም ተውት:: ልክ እነሱ መጠየቁን ሲያቆሙ ግን እግዚአብሔር ይሕንን ቅዱስ ፍሬ በዮና ማሕጸን ላይ ፈጠረ::
+እነርሱም ተገርመው ፈጣሪን እያመሰገኑ ተወለደ:: እንደ ተወለደ ግን ዓይናቸው ድንቅ ነገርን ተመለከቱ:: አትበው ሊያነሱት ሲጐነበሱ በራሱ ጊዜ ብደግ ብሎ ፈጣሪውን ሲያመሰግን ሰሙት::
+ለ2 ሰዓት ያሕልም ምንነቱን ያላወቁትን ጸሎት ሲያደርስ ቆየ:: መቼም የዕለት ሕጻን ይሕንን ማድረጉ እጅግ ድንቅ ነው:: ከዚህ በሁዋላም የሕጻኑ ቅዱስ ኒቆላዎስ አስገራሚ ነገሮቹ ቀጠሉ::
+ለምሳሌ:- በአጽዋማት: በረቡዕና በዓርብ ዕለታት 9 ሰዓት ካልሆነ የእናቱን ጡት አይጠባም:: ሁሌም ደግሞ የፈለገውን ያህል ቢፈስ የእናቱን የግራ ጡት አይጠባም ነበር:: ሁሌም የሚጠባው በስተቀኝ ያለውን ጡቷን ብቻ ነበር እንጂ::
+እንዲህ እንዲህ እያለ ቅዱስ ኒቆላዎስ አደገ:: እርሱ ወጣት በሆነ ጊዜ አረጋውያን ወላጆቹ ብዙ ሃብት: 400 የወርቅ ዲናርና የመሳሰለውን ትተውለት ዐረፉ:: እርሱ ግን ሁሉንም ትቶት በ16 ዓመቱ በርሃ ገባ::
+በዚያ ሲጾም: ሲጸልይ: ሲሰግድ ያዩ አበው ሁሉ ይገረሙ ነበር:: ሲሠራም: ሲታዘዝም: ሲሰግድም እንደ መንኮራኩር ፈጣን ነበርና:: በሕጻን ገላው ይሕንን ማድረጉ በእርግጥ ይደነቃል:: የቀናውን የሃይማኖት ትምሕርትንም ቶሎ በማጠናቀቁ ገና በ19 ዓመቱ ቀሲስ አድርገው ሾሙት::
+ቅስናን ከተሾመ በሁዋላ ተጋድሎውንም: አገልግሎቱንም አስፋፋ:: ካለበት ገዳም እየተነሳ ብዙ አካባቢዎችን በስብከት ያደርስ ነበር:: በወንጌል አገልግሎቱ ጊዜም ብዙ ተአምራትን ሲሠራ በተለይ በአንድ ቀን የአንድን አካባቢ ሕዝብ ጥቂት ሕብስትን እንደ ፈጣሪው አበርክቶ አብልቷል::
+የተረፈውም ብዙ መሶብ ተነስቷል:: (ዮሐ. 6:5) ጌታችን "በእኔ የሚያምን እኔ የምሠራውን እርሱ ደግሞ ይሠራል" ብሏልና:: (ዮሐ. 14:12) በተረፈም ፈዋሴ ዱያን: መንስኤ ሙታን ሆኖ ዘመናትን አሳልፏል::
+አንድ ቀን ግን በበአቱ እያለ የአንድ ሰውና የ4 ሴት ልጆቹ ነፍስ ሊጠፋ መሆኑ ይታወቀዋል:: ይሔውም በአቅራቢያው ባለ ከተማ የሚኖር አንድ ባለ ጠጋ ሃብቱ አልቆበት ተቸግሯልና ሰይጣን ክፉን እንዲሠራ ሹክ አለው:: ሰውየውም ለ4 ሴት ልጆቹ 4 ቤት አሰናድቶ በዝሙት ሊሸጣቸው ተዘጋጀ::
+ይሕንን በጸጋ ያወቀው ቅዱስ ኒቆላዎስ "ከመገስጽ መርዳት ይቀድማል" ብሎ: ማንም ሳያየው ወላጆቹ ከተውለት 400 የወርቅ ዲናር 100ውን ከፍሎ በሌሊት ከሰውየው በር ላይ ጥሎለት ተሰወረ:: ሰውየውም ተገርሞ የኃጢአት ሃሳቡን ተወ::
+ያ ሥራ ፈት ሰው ግን እንደ ገና ገንዘቡን በልቶ ተመሳሳይ ድርጊት ሊፈጽም ማሰቡን ቅዱሱ አወቀ:: አሁንም ተደብቆ 100 የወርቅ ዲናር ጣለለት:: ይህ ነገር 3ኛና 4ኛም ተደገመ:: በ4ኛው ግን ሰውየው ወደ ልቡናው ተመልሶ ይሕንን ያሕል ቸርነት የሚያደርግለትን ሰው ተደብቆ አየው::
+ሩጦም ሒዶ ከቅዱስ ኒቆላዎስ እግር ላይ ወደቀ:: "አባቴ! ነፍሴን ከእሳት አወጣሃት" አለው:: ቅዱሱም መልሶ መክሮ: ምሥጢሩን ግን ለማንም እንዳይናገር አሳስቦት ተመለሰ:: ያ ሰው ከዚያ በሁዋላ በጐ ክርስቲያን መሆን ችሏል::
+ለቅዱስ ኒቆላዎስ ግን አንድ ቀን ጌታችን: እመቤታችን: ቅዱስ መልአክ መጥተው ስጦታን አበረከቱለት:: መልአኩ ዙፋን: እመ ብርሃን የክብር ልብስን ሲሰጡት ጌታ ደግሞ ወንጌሉን ሰጠው::
+ወዲያውም አበው ካለበት በርሃ መጥተው የሜራ ዻዻስ እንዲሆን ሾሙት:: የተሾመበት ጊዜ ዘመነ ሰማዕታት ነበርና የሜራን ሕዝብ አጽንቶ ለሰማዕትነት በማብቃት ትልቁ ሃላፊነትም ተወጥቷል::
+ነገር ግን ዜና ሕይወቱ በነገሥታቱ ዘንድ ሲሰማ ለፍርድ አቀረቡት:: ስለ ክርስቶስ ሰብከሃል በሚል ስቃይና ሞት ተፈረደበት:: ወደ አውደ ስምዕ (የሰማዕታት አደባባይ) ወስደው ገረፉት: በእሳት አቃጠሉት: ደሙንም አፈሰሱት::
+ነገር ግን እግዚአብሔር ለሌላ ሙያ ይፈልገዋልና አልሞተም:: እነርሱ ግን በጭካኔ ለዘመናት አሰቃዩት:: በመጨረሻም እስር ቤት ውስጥ ጣሉት:: እርሱ በእስር ቤት ሳለም ዘመነ ሰማዕታት ተፈጸመ:: ቆስጠንጢኖስ ነገሠ::
+በዚህ ጊዜም ምዕመናን ቅዱስ አባታቸውን ከእስር ፈትተው በመንበሩ ላይ አኖሩት:: ለ13 ዓመታት ሕዝቡን ሲመራ ቆይቶ አርዮስ በካደ ጊዜ ወደ ኒቅያ አመራ:: በዚያም ለቅዱሳን ሊቃውንት 318ኛ ሆኖ ተቆጠረ:: በጉባኤው ፊትም ተአምራትን አሳየ::
+በኒቅያ ከባልንጀሮቹ ጋር አርዮስን አውግዞ: ሥርዓትን ሠርቶ: መጻሕፍትን ጽፎም ወደ ሃገሩ ተመልሷል:: በመንበሩ ላይ 40 ዓመታት ሲሞሉትም ዐርፎ በዚህች ቀን ተቀብሯል::
<<ኒቆላዎስ ማለት "መዋኤ ሕዝብ - ሕዝብን የሚያሸንፍ" ማለት ነው>>
+"+ ቅድስት ሱርስት +"+
=>ይህቺ ቅድስት እናት በዘመነ ጻድቃን ከተነሱ ስመ ጥር እናቶች አንዷ ናት:: ገና ከልጅነቷ በቤተ መንግስት ውስጥ ብታድግም ከመልካም እናቷ መልካምነትን ወርሳለች:: እጅግ በተቀማጠለ ኑሮ ውስጥ ሆና ሕይወቷን ክርስቶስን አልዘነጋችውም::
+ደም ግባቷ እጅግ የተወደደ ነበርና ገና በ12 ዓመቷ ለነገሥታቱ ልጆች ሚስት ትሆን ዘንድ ታጨች:: መቼም ሃብትን: ክብርን እንኩዋን እንዲህ በለጋ እድሜ አርጅተንም ቢሆን መናቁ አይሳካም::
+ቅድስት ሱርስት ግን አንድ ቅን ሃሳብ መጣላት:: ወደ አባቷ ዘንድ ሔዳም "ወደ አድባራት ሔጄ ከሠርጌ በፊት እንድሳለም ፍቀድልኝ" ስትል ጠየቀችው:: እርሱ ግን "ከሠርግሽ በሁዋላ ይደርሳል" ቢላት "በድንግልናየ ሳለሁ መቃብርህን እስማለሁ ብዬኮ ለፈጣሪየ ተስያለሁ" አለችው::
+አባቷም ከ300 ዲናር ወርቅና ከብዙ ሠራዊት ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ላካት:: ቅድስቷ ሕጻንም በዚያ የጌታን መቃብር ተሳልማ ወታደሮችን ጠፋቻቸው:: ከዚያ በሁዋላ የት እንደ ደረሰች ያወቀ የለም:: ሱርስት ግን ከኢየሩሳሌም ግብጽ ወርዳ ወርቁ ገዳም እንዲታነጽበት አደረገች::
+እርሷ ግን መንኩሳ ወደ በርሃው ገባች:: በዚያም 27 ዓመት ሙሉ ማንንም ሳታይ: በጭንቅ: በመከራ: በአርምሞ ተጋደለች:: አንድ ቀን ግን ባሕታውያንን የሚመግብ ሲላስ የሚሉት ካህን አግኝቶ ዜናዋን ከነገረችው በሁዋላ ሰግዳ ዐርፋለች:: በ39 ዓመቷም በዚህች ቀን ቀብሯታል::
+*" ✝ታላቁ ቅዱስ ሳዊሮስ "*+✝
=>ቅዱስ ሳዊሮስ በ6ኛው መቶ ክ/ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በሶርያ አንጾኪያ የተነሳ አባት ነው:: ወቅቱ መለካውያን (2 ባሕርይ ባዮች) የሰለጠኑበት እንደ መሆኑ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን ያነሱበትና የሚሰደዱበት ጊዜ ነበር:: በዚህ ጊዜ ነበር ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ሳዊሮስ በሥላሴ ፈቃድ ለቤተ ክርስቲያን የተነሳው:: ሊቃውንት አንበሳ ሲሉ ይጠሩታል::
+ቅዱሱ ለተዋሕዶ ብዙ ሆኖላታል:: የመናፍቃን ጸር በመሆኑ ብዙ ድርሰቶችን ደርሷል:: ንጉሡን ዮስጢያኖስን (Justinian) ሳይቀር በይፋ ይገስጸው ነበርና ንጉሡ ሊገድለው ቆረጠ::
+ሃይማኖቷ የቀና ንግሥቲቱ ታኦድራ ግን ይህንን ስትሰማ በሌሊት ወደ ሊቁ ሒዳ "እባክህን ሽሽ" አለችው:: እርሱ ግን "ሞት ለእኔ ክብር ነውና አልሔድም" ሲል መለሰላት:: አባቶችን ሰብስባ "ስለ ቤተ ክርስቲያን ስትል" ብለው ለምነው ወደ ግብጽ ሸኙት::
+እርሱ እየሔደ ገዳዮቹ ያሳድዱት ገቡ:: መንገድ ላይ ቢደርሱበትም ተሰወረባቸው:: ለብዙ ቀናትም አብሯቸው ተጉዋዘ:: እነርሱ ተስፋ ቆርጠው ሲመለሱ እርሱ ግን ምድረ ግብጽ ደረሰ::
+በምድረ ግብጽም የዽዽስና ልብሱን ትቶ የመነኮሳትን አሮጌ ልብስ ለብሶ ሕዝቡንና መነኮሳቱን አስተማረ: አጸና:: በየቦታውም ብዙ ተአምራትን ሠራ::
+አባቶች መነኮሳትም ማንነቱን ባወቁ ጊዜ ሰገዱለት:: ዶርታኦስ (ዱራታኦስ) በሚባል አንድ ደግ ሰው ቤትም በ6ኛው መቶ ክ/ዘ አጋማሽ አካባቢ የካቲት 14 ቀን ዐርፏል:: ዛሬ የታላቁ ሊቅ በዓለ ፍልሠቱ ነው::
=>አምላከ ቅዱሳን ይርዳን: ይቅርም ይበለን:: ከበረከታቸውም ያሳትፈን::
=>ታሕሳስ 10 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ኒቆላዎስ ሊቅ
2.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
3.ቅድስት ሱርስት ገዳማዊት
4.ቅዱስ ጥዋሽ ሕጽው
5.ቅዱሳን ተላስስና አልዓዛር
=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ናትናኤል ሐዋርያ
2.አቡነ መልክዐ ክርስቶስ
3.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ እልፍዮስ)
4.ቅድስት ዕሌኒ ንግስት
5.ቅዱስ ዕፀ መስቀል
6.ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ
✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞
✞ ወለወላዲቱ ድንግል ✞
✞ ወለመስቀሉ ክቡር አሜን ✞
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ::" /ማቴ ፫:፫/
ዝክረ ቅዱሳንን ተማሩ ብለን እንለምናችኋለን!!።
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
✝ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Togethellettps://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━━━
Comments
Post a Comment