✝✞✝ እንኩዋን ለነቢየ እግዚአብሔር "ቅዱስ ሐጌ" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✝✞✝
+*" ቅዱስ ሐጌ ነቢይ "*+
=>ነቢይ ማለት በቁሙ ኃላፍያትን (አልፎ የተሠወረውን ምሥጢር) : መጻዕያትን (ገና ለወደ ፊት የሚሆነውን) የሚያውቅ ሰው ማለት ነው:: ሃብተ ትንቢት የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ሲሆን እርሱ ለወደደው ደግሞ በጸጋ ይሰጠዋል:: እነዚህም ከጌታ ሃብተ ትንቢት የተሰጣቸው አባቶችና እናቶች "ቅዱሳን ነቢያት" በመባል ይታወቃሉ::
+"ዘመነ ነቢያት" ተብሎ የሚታወቀው ብሉይ ኪዳን ቢሆንም እስከ ምጽዓት ድረስ ጸጋውን እግዚአብሔር ለፈቀደላቸው አይነሳቸውም:: በሐዋርያት መካከልም ቅዱስ አጋቦስን የመሰሉ ነቢያት ነበሩ:: (ሐዋ. 11:27) ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር እየተላኩ ሰውን ከፈጣሪው እንዲታረቅ ይመክራሉ: ይገስጻሉ::
+ከበጐ ሃይማኖታቸውና ንጽሕናቸው የተነሳም እግዚአብሔርን በተለያየ አርአያና አምሳል አይተውታል::
"እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር: ወተናጸሩ ገጸ በገጽ" እንዳለ አባ ሕርያቆስ:: (ቅዳሴ ማርያም)
+የብዙ ነቢያት ፍጻሜአቸው መከራን መቀበል ነው:: እውነትን ስለ ተናገሩ: አንዳንዶቹም በእሳት: አንዳንዶቹም በሰይፍ: አንዳንዶቹም በመጋዝ ተፈትነዋል:: ሌሎቹ ለአናብስት ሲጣሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በድንጋይ ተወግረዋል::
+ስለዚህም መከራቸው ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ተብለዋል:: ጌታም ለደቀ መዛሙርቱ "ሌሎች ደከሙ: እናንተ በድካማቸው ገባችሁ" ብሎ የነቢያቱን መከራ ተናግሯል:: (ዮሐ. 4:36)
+ነቢያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና እና ድንግል እናቱን ለማየት ብዙ ጥረዋል: ሽተዋልም:: "ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ሹ" እንዳለ ጌታ በወንጌል:: (ማቴ. 13:16, 1ዼጥ. 1:10) ዛሬ ግን በሰማያት ጸጋ በዝቶላቸው : ክብር ተሰጥቷቸው ሐሴትን ያደርጋሉ::
+ቅዱሳን ነቢያት በዋነኝነት "15ቱ አበው ነቢያት" : "4ቱ ዐበይት ነቢያት" : "12ቱ ደቂቀ ነቢያት" ና "ካልአን ነቢያት" ተብለው በ4 ይከፈላሉ::
=>"15ቱ አበው ነቢያት" ማለት:-
*ቅዱስ አዳም አባታችን
*ሴት
*ሔኖስ
*ቃይናን
*መላልኤል
*ያሬድ
*ኄኖክ
*ማቱሳላ
*ላሜሕ
*ኖኅ
*አብርሃም
*ይስሐቅ
*ያዕቆብ
*ሙሴና
*ሳሙኤል ናቸው::
=>"4ቱ ዐበይት ነቢያት"
*ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
*ቅዱስ ኤርምያስ *ቅዱስ ሕዝቅኤልና
*ቅዱስ ዳንኤል ናቸው::
=>"12ቱ ደቂቀ ነቢያት"
*ቅዱስ ሆሴዕ
*አሞጽ
*ሚክያስ
*ዮናስ
*ናሆም
*አብድዩ
*ሶፎንያስ
*ሐጌ
*ኢዩኤል
*ዕንባቆም
*ዘካርያስና
*ሚልክያስ ናቸው::
=>"ካልአን ነቢያት" ደግሞ:-
*እነ ኢያሱ
*ሶምሶን
*ዮፍታሔ
*ጌዴዎን
*ዳዊት
*ሰሎሞን
*ኤልያስና
*ኤልሳዕ ሌሎችም ናቸው::
=>ነቢያት በከተማም ይከፈላሉ::
*የይሁዳ (ኢየሩሳሌም):
*የሰማርያ (እሥራኤል)
*የባቢሎን (በምርኮ ጊዜ) ተብለው ይጠራሉ:: በዘመን አከፋፈል ደግሞ:-
*ከአዳም እስከ ዮሴፍ (የዘመነ አበው ነቢያት):
*ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል (የዘመነ መሳፍንት ነቢያት)
*ከቅዱስ ዳዊት እስከ ዘሩባቤል ያሉት (የዘመነ ነገሥት ነቢያት):
*ከዘሩባቤል ዕረፍት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ያሉት ደግሞ (የዘመነ ካህናት ነቢያት) ይባላሉ::
+ስለ ቅዱሳን ነቢያት በጥቂቱ ይህንን ካልን ወደ ዕለቱ በዓል እንመለስ::
+ቅዱስ ሐጌ ቁጥሩ ከ12ቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን ዘመነ ትንቢቱም ቅ.ል. ክርስቶስ በ450 ዓ/ዓ አካባቢ ነው:: "ደቂቀ ነቢያት" ማለት በጥሬው "የነቢያት ልጆች" ማለት ነው:: አንድም የጻፏቸው ትንቢቶች ሲበዙ 14 ምዕራፍ: ሲያንስ አንድ ምዕራፍ ያላቸው ናቸው::
=>"ሐጌ" ማለት መልአከ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር መልእክተኛ) ማለት ነው:: አንዳንዴም "በዓል" ተብሎ ይተረጐማል:: ትውልዱ ከነገደ ጋድ ሲሆን አባቱ አግታ: እናቱ ሲን ይባላሉ::
+በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከደኃርት (ከሁዋለኛው ዘመን ነቢያት) አንዱ ነው ይባላል:: ቁጥሩም ከ12ቱ ደቂቀ ነቢያት ነው:: ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
+እሥራኤል ከተከፈለችበት ከመንግስተ ሮብዓም (ከክርስቶስ ልደት 931 ዓመታት በፊት) በሁዋላ 10ሩ ነገድ "እሥራኤል": 2ቱ ነገድ "ይሁዳ" ተብለው በሰሜንና በደቡብ አቅጣጫ ተለያዩ:: መናገሻቸውም ኢየሩሳሌምና ሰማርያ ሆኑ::
+ከዕለት ዕለት ግን የሁሉም ኃጢአት እየበዛ በመሔዱ እግዚአብሔር አዘነባቸው:: ለአሕዛብም አሳልፎ ሰጣቸው:: አስቀድሞ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በ722 ዓመት የአሦሩ ንጉሥ ስልምናሶር መጥቶ ሰማርያን አጠፋት:: 10ሩን ነገድም በባርነት አሦር አወረዳቸው::
+ከዚህ ትምሕርት መውሰድ የተሳናቸው 2ቱ ነገድም ሊገሰጹ አልቻሉምና ተመሳሳይ ዕጣ ደረሰባቸው:: የእግዚአብሔርንና የነቢያቱን ድምጽ: ይልቁኑ የኤርምያስን ምክር አልሰሙምና ከክርስቶስ ልደት 586 ዓመታት በፊት ኃይለኛው የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር መጣ::
+የሚገድለውን ገድሎ: ሕዝቡንም ማርኮ ወደ ፋርስ ባቢሎን ሲያወርዳቸው ኢየሩሳሌምን ምድረ በዳ አደረጋት:: (2ነገ. )
+እግዚአብሔርን የማይሰማ ሕዝብ ምን ጊዜም እጣ ፈንታው ይሔው ነው:: በተለይ ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔር ቸርነት የበዛለት ሕዝብ እንዲህ አንገተ ደንዳና ሲሆን ይገርማል:: በእርግጥ ዛሬ እስራኤል ያይደለ ሃገረ እግዚአብሔር ኢትዮዽያ ናትና ከመሰል መከራ ለመራቅ ድምጹን መስማት ያስፈልጋል::
+ሕዝቡ ግን ፋርስ : ባቢሎን ወርደው መከራን ሲቀበሉ : ነቢያት ያሉት ሁሉ ሲፈጸምባቸው ተጸጸቱ:: ፈጣሪም ተስፋ እንዳይቆርጡ በዚያው ዳንኤልን የመሰሉ ነቢያትን አስነሳላቸው:: እነ ኤርምያስንም ከግብጽ ላከላቸው::
+ሕዝቡም (በተለይ "ትሩፋን" የተባሉት) "እግዚአብሔር ሆይ! 'ወሰብዓ ዓም ኃሊቆ' ባልከው ቃልህ : 70ው ዘመን ሲፈጸም ወደ አባቶቻችን ርስት ብትመልሰን መቅደስህን እናንጻለን:: በጐ ምግባርን እንይዛለን" ሲሉ ተሳሉ::
+ልመናን የሚሰማ ቸሩ ፈጣሪም እንደ ቃሉ 70ው ዘመን ሲፈጸም እሥራኤል በነ ኤርምያስ ባሮክና እና ሌሎችም አማካኝነት በኃይል: በድንቅና በተአምራት ከፋርስ ባቢሎን ወጡ:: በድል ተጉዘውም ወደ ርስታቸው ገቡ::
+የሰው ነገር አስቸጋሪ ነውና ከርስታቸው ከገቡ በሁዋላ ግን ስዕለታቸውን ሳይፈጽሙ ቀሩ:: በዚህ ጊዜም እንደ ዘወትሩ ይገሥጻቸው ዘንድ እግዚአብሔር ነቢያቱን ሐጌን : ዘካርያስንና ሚልክያስን አስነሳቸው::
+ሕዝቡ "እስመ ኢኮነ ጊዜሁ ለሐኒጽ - ለማነጽ ወቅቱ አልረዳንም" እያሉ ቤተ መቅደሱ ሳይታነጽ ዘመናት አለፉ:: የሚገርመው ግን ቤተ መቅደሱ ምድረ በዳ ሆኖ የራሳቸውን ቤት አሳምረው ያንጹ ነበር::
+በዚህ ጊዜ በመካከላቸው የነበረው ቅዱስ ሐጌ ዘለፋቸው::
"እምጊዜሁ ለክሙ ከመ አንትሙ ትንበሩ ውስተ ቤት ጥፉር: ወቤትየሰ ምዝቡር? - ቤቴ ፈርሶ ሳለ እናንተ ባማሩ ቤቶቻችሁ ልትኖሩ ጊዜው ነውን?" (ሐጌ. 1:4) አላቸው::
+አክሎም "ቃላችሁን አልፈጸማችሁምና በረከቴን ከእናንተ አርቃለሁ" አላቸው:: ተግሣጹን ከልብ የሰሙት ሕዝቡም በዘሩባቤል መሪነት 46 ዓመታት የፈጀውን ቤተ መቅደስን አንጸዋል::
+ቅዱስ ሐጌም በሕጉ እየኖረ: ትንቢትን እየተናገረ ዘመኑን ፈጽሟል:: በትውፊት ትምሕርትም ቅዱሱ የተወለደው በ500 ዓ/ዓ ሲሆን ያረፈው በ70 ዓመቱ በ5,070 ዓ/ዓ ነው:: ከክርስቶስ ልደት 430 ዓመታት በፊት ማለት ነው::
=>አምላከ ሐጌ ለቤቱ የምናስብበትን ዘመን ያምጣልን:: ከቅዱሱ ነቢይ በረከትም ይክፈለን::
=>ታሕሳስ 20 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ሐጌ ነቢይ
2.አባ አውጋንዮስ
3.ታውፊና ንግሥት
=>ወርኀዊ በዓላት
1..ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር
2.ቅዱስ አክሎግ ቀሲስ
3.ቅዱስ አፄ ካሌብ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
4.አባ አሞንዮስ ዘሃገረ ቶና
5.ቅድስት ሳድዥ የዋሒት
6.ማር ቴዎድሮስ ኃያል ሰማዕት
=>+"+ 'ብሩ የእኔ ነው:: ወርቁም የእኔ ነው' ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር:: 'ከፊተኛው ይልቅ የዚህ የሁለተኛው ቤት ክብር ይበልጣል' ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር:: በዚህም ሥፍራ ሰላምን እሰጣለሁ:: +"+ (ሐጌ. 2:9)
✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞
✞ ወለወላዲቱ ድንግል ✞
✞ ወለመስቀሉ ክቡር አሜን ✞
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ::" /ማቴ ፫:፫/
ዝክረ ቅዱሳንን ተማሩ ብለን እንለምናችኋለን!!።
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together.https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━━━
Comments
Post a Comment