††† እንኳን ለዕለተ ብርሃን: ለታላቁ ሰማዕት ቅዱስ መርምሕናም እና ቅድስት ነሣሒት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††
††† ዕለተ ብርሃን †††
††† ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስንና የቅዱስ ያሬድን አስተምሕሮ መሠረት አድርጋ ይህንን ዕለት (ታኅሳስ 14ን) "ዕለተ-ብርሃን" : ሳምንቱን (ከታኅሳስ 14-20 ያለውን) ደግሞ "ሰሙነ-ብርሃን" ስትል ታስባለች::
"ብርሃን" በቁሙ የእግዚአብሔር ስሙ: አንድም የባሕርይ ገንዘቡ ነው:: "እግዚአብሔር ብርሃን ነውና:: ጨለማም በእርሱ ዘንድ የለችምና::" (ዮሐ. 1:4)
~በዚህ ዕለት "ብርሃን" በሚል መነሻ ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ታስተምሠራለች:-
1.እግዚአብሔር ብርሃን መሆኑን:: (ዮሐ. 1:5)
2.አምላካችን በመጀመሪያው የፍጥረት ቀን (በዕለተ እሑድ) ዲያብሎስ ቅዱሳን መላእክትን ሲረብሽ "ለይኩን ብርሃን" ብሎ ብርሃንን መፍጠሩን:: (ዘፍ. 1:2, አክሲማሮስ)
3.ነቢያት አበው በጨለማው ዓለም ሆነው መከራ ሲበዛባቸው "ፈኑ ብርሃነከ - ብርሃንህን ላክልን" እያሉ መጮሃቸውን:: (መዝ. 42:3)
4.ጩኸታቸውን የሰማ ከሦስቱ አካላት አንዱ ወልድ (እውነተኛው ብርሃን) ወደዚህ ዓለም መምጣቱን:: (ሉቃ. 1:26)
5."እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ" ሲል የባሕርይ ብርሃንነቱን እንደ ነገረን:: (ዮሐ. 9:5)
6.ብርሃነ መለኮቱን በገሃድ መግለጡን:: (ማቴ. 17:1)
7.ብርሃን የሆነችውን ሕግ: ወንጌልን እንደ ሠራልን:: (1ዮሐ. 2:9)
8.ድንግል እመቤታችን ብርሃን : የብርሃንም እናቱ መሆኗን:: (ሉቃ. 1:26, ራዕ. 12:1)
9.ቅዱሳኑ ብርሃን መባላቸውን:: (ማቴ. 5:14)
10.እኛ በሰው ፊት ሁሉ እንድናበራ መታዘዛችን:: (ማቴ. 5:16) ሁሉ ይታሰባል::
እርሱ ፈጣሪያችን ክርስቶስ ጨለማውን በምሕረቱ አርቆልናልና ዳግመኛ ወደ ጨለማ እንዳንሄድ እየለመንን እናመስግነው::
"ክርስቶስ ብርሃን ዘአሰሰልከ ጽልመተ::
ላዕለ ኪሩቤል ነቢረከ ዘትሬኢ ቀላያተ::
ስቡሕኒ ወልዑል አንተ::" (መልክአ ኢየሱስ)
††† ቅዱስ መርምሕናም ሰማዕት †††
††† ሰማዕቱ በቤተ ክርስቲያን ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ዐበይት ቅዱሳን አንዱ ነው:: በየአብያተ ክርስቲያናቱ ከሚሳሉ ቅዱሳንም አንዱ ነው:: ሃገሩ አቶር (በፋርስ አካባቢ) ሲሆን አባቱ ሰናክሬም የሚባል ንጉሠ ነገሥት ነው::
እናቱ ምንም ክርስቲያን ብትሆንም ስለ ፈራች 2ቱን ልጆቿን (መርምሕናምና ሣራን) ክርስትናን አላስተማረቻቸውም:: 2ቱም ወጣት በሆኑ ጊዜም ከንጉሥ አባታቸው ጋር ይወጡ ይገቡ ነበርና እናታቸው በሐዘን ጸለየች:: ወዲያውም ወጣቷ ሣራ በለምጽ ተመታች::
የሚፈውሳት ጠፋ:: መርምሕናም ግን ጐበዝ ወጣት ነውና 40 የጦር አለቆችን ይመራ ነበር:: በዚያው በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ቅዱስ መርምሕናም 40 ተከታዮቹን ይዞ ለአደን ወደ ዱር ሲወጣ ከአባ ማቴዎስ ገዳማዊ ጋር ተገናኘ::
ጻድቁ ለብዙ ዓመታት በበርሃ የኖሩ አባት ናቸው:: አካላቸው በጸጉር ስለ ተሸፈነ ደንግጦ ሲሸሽ "ልጄ አትፍራ! እኔም እንዳንተ የክርስቶስ ፍጡር የሆንኩ ሰው ነኝ" አሉት::
እርሱ ግን "ደግሞ ክርስቶስ ማነው?" ሲል ጠየቃቸው:: አባ ማቴዎስም ምሥጢረ ክርስትናን ከመሠረቱ አስተምረው የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት ነገሩት::
ቅዱስ መርምሕናም ግን "ክርስቶስ አምላክ እንደ ሆነ አምን ዘንድ እህቴን አድንልኝ" አላቸው:: "አምጣት" ብለውት አመጣት:: ጻድቁ ጸሎት አድርሰው መሬትን ቢረግጧት ውሃን አፈለቀች:: "በእምነት: በስመ ሥላሴ ተጠመቁ" አሏቸው::
ቅዱሱ: እህቱ ሣራና 40 የጦር አለቆች ተጠምቀው ሲወጡ ሣራ ከለምጿ ነጻች:: ፈጽሞም ደስ አላቸው:: ወደ ቤተ መንግስት ተመልሰውም ቅዱስ መርምሕናም ከእናቱ: ከእህቱና ከ40 ተከታዮቹ ጋር ክርስቶስን ሊያመልኩ ጀመሩ::
ንጉሡ ሰናክሬም ግን ነገሩን ሲሰማ ተቆጣ:: እነርሱም ወደ ተራራ ሸሹ:: ንጉሡ "ልጆቼ! መንግስቴን ውረሱ" ብሎ ቢልካቸውም "እንቢ" አሉ:: ስለ ተበሳጨም ቅዱስ መርምሕናምን: ቅድስት ሣራንና 40ውን ቅዱሳን በሰይፍ አስመታቸው::
ሥጋቸውን በእሳት ሊያቃጥሉ ሲሉ ግን መነዋወጥ ሆኖ ብዙ አረማውያን ሞቱ:: ንጉሡም አብዶ አውሬ (እሪያ) ሆነ:: ያን ጊዜ አባ ማቴዎስ ከበርሃ ወጥተው ንጉሡን ሰናክሬምን ፈወሱት::
እርሱም አምኖ የልጆቹና የ40ውን ሥጋ በክብር አኖረ:: በሃገሩ አቶርም የእመ ብርሃን ማርያምን ቤተ መቅደስ አነጸ:: በክርስትና ኑሮም ዐረፈ:: እርሱ ከተቀበረ በሁዋላ ግን የከለዳውያን ንጉሥ መጥቶ አቶርን ወረራት::
ንግሥቲቱን (የቅዱሳኑን እናት) ከሕጻኑ ልጇ ጋርም ገደለ:: በሁዋላም "ለጣዖት ስገዱ" ማለቱን የሰሙት የቅዱስ መርምሕናም ወታደሮች ደርሰው በምስክርነት ተሰየፉ:: ቁጥራቸውም 170,000 ሆነ::
††† ቅድስት ነሣሒት ቡርክት †††
††† በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ከነበሩና አስደናቂ ታሪካቸው ከተጻፈላቸው ቅዱሳት እናቶቻችን አንዷ ነሣሒት ናት:: የእርሷን ገድል (ዜና ሕይወት) የጻፈው አባ ያዕቆብ የአውሲም ኤዺስ ቆዾስ ነው:: እርሱ እንዲህ ይላል:-
"አንድ ቀን በገዳም ሳለሁ: አመሻሽ ላይ የገዳሙ በር ሲጸፋ (ሲንኩዋኩዋ) ሰማሁ:: ማን እንደ ሆነ አውቅና እከፍት ዘንድ ተጠጋሁ" ይላል ቅዱሱ አባት::
በሩን ከፍቶ ሲመለከት ፊቱን የተሸፋፈነ አንድ መነኮስ ራሱን አዘንብሎ ቁሟል:: "ማነህ? ከወዴትስ መጣህ?" ሲል ጠየቀው:: መነኮሱም "እኔ ከገዳመ ቅዱስ መቃርስ የመጣሁ መንገደኛ ነኝ:: በዚህች ሌሊት በእናንተ ዘንድ ላድር: ሥጋውን ደሙንም እቀበል ዘንድም እፈልጋለሁ" አለው::
አባ ያዕቆብ ግን ለገዳሙ ደህንነት ሲል "መጐናፀፊያህን ግለጥና ፊትህን አሳየኝ" ቢለው መነኮሱ "አባቴ! በኃጢአቴ ብዛት ፊቴ ጠቁሯልና ኃጢአቴን አትመራመረኝ" ሲል መለሰለት::
አባ ያዕቆብ "አላስገባህም" ብሎ ትቶት ሔደ:: "ግን ምናልባት የራበው ሰው ቢሆን ፈጣሪየ ሊያዝንብኝ አይደል!" ብሎ ከፍቶ አስገባው:: አበው ራት ሲበሉ እንግዳው አልበላም ነበር:: እነርሱ ሲተኙ እንግዳው መነኮስ ይጸልይ ጀመር::
ከድምጹ ግርማ የተነሳም መነኮሳቱ ሁሉ ደንግጠው ተነሱ:: የዳዊትን መዝሙር ሲዘምር ነጐድጉዋድ ድምጹ እንደ መልአክ ድምጽ ነበርና ምድር ራደች:: አባ ያዕቆብም ተደነቀ:: እንዲህ አድረው ዕለተ ሰንበት ነበርና በነግህ ቅዳሴ ገቡ::
ስለ ክብሩም በቅዳሴ ሰዓት መልእክታቱንና ወንጌሉን እንግዳው አነበበ:: ቅዱስ መጽሐፍን ሊያነብ መጐናጸፊያው ሲገለጥ ግን ከመልኩ ግርማና ከፊቱ ብርሃን የተነሳ ሊመለከቱት አልቻሉም::
ሥጋውን ደሙን ከተቀበለ በሁዋላ እነ አባ ያዕቆብ በረከቱን ይነሱ ዘንድ ቢሔዱም ተሰወረባቸው:: እነርሱም አዘኑ::
እስካሁን ድረስ ያነበባችሁት ዜና የአንድ ወንድ መነኮስ ታሪክ ሳይሆን ወንድ መስላ ራሷን ሰውራ የኖረችውን የቅድስት ነሳሒትን ታሪክ ነው::
ቅድስቲቱ ከሮም ነገሥታት የአንዱ ልጅ ብትሆንም ስለ ጌታ ፍቅር በ12 ዓመቷ ከቤተ መንግስት ጠፍታ በርሃ ገብታለች:: ነገር ግን የአባቷ ሠራዊትና መነኮሳት ስለሚፈልጉዋት ወንድ መስላና ራሷን ሠውራ በደብረ አባ መቃርስ ኑራለች::
ከዚያም ከአንዱ ገዳም ወደ ሌላኛው ስትዘዋወር ኑራ ጸጋ እግዚአብሔር ቢበዛላት ድምጿም መልኩዋም ልዩ ሆነ:: እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነውና:: ቅድስት ነሣሒት በዚህች ዕለት በበርሃ ስታርፍ መንገደኛ አበው ቀብረዋታል::
††† አምላከ ቅዱሳን ብርሃን ፍቅሩን ይላክልን:: ከወዳጆቹ ክብርም ያሳትፈን::
††† ታሕሳስ 14 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ዕለተ ብርሃን
2.ቅዱስ መርምሕናምና እህቱ ሣራ
3."40" ሰማዕታት (የቅዱሱ ተከታዮች)
4."170,000" ሰማዕታት (የቅዱሱ ሠራዊት)
5.ቅድስት ነሣሒት ቡርክት
6.ቅዱስ ስምዖን ሰማዕት
7.ቅዱስ አሞንዮስ ሰማዕት
8.አባ ገብረ ክርስቶስ ሊቀ ዻዻሳት
††† ወርሐዊ በዓላት
1.አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል)
2.አባ ስምዖን ገዳማዊ
3.አባ ዮሐንስ ጻድቅ
4.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ (ከ72ቱ አርድእት)
5.ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ
6.ቅዱስ ሙሴ መርዓዊ
††† "ብርሃን ወደ ዓለም መጥቷልና:: ሰውም ሥራው ክፉ ስለ ሆነ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን መርጧልና:: ሥራው ክፉ የሆነ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና:: ክፉም ስለ ሆነ: ሥራው እንዳይገለጥበት ወደ ብርሃን አይመጣም:: እውነትን የሚሠራ ግን ሥራው ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል:: ስለ እግዚአብሔር ብሎ ይሠራልና::" †††
(ዮሐ. 3:19)
✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞
✞ ወለወላዲቱ ድንግል ✞
✞ ወለመስቀሉ ክቡር አሜን ✞
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ::" /ማቴ ፫:፫/
ዝክረ ቅዱሳንን ተማሩ ብለን እንለምናችኋለን!!።
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together.https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━━━
Comments
Post a Comment