<<< ታሕሳስ 15 >>>
=>+"+ እንኩዋን ለአበው ቅዱሳን "ጐርጐርዮስ ዘአርማንያ" እና "አቡነ ኤዎስጣቴዎስ" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ +"+
+*"ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘአርማንያ "*+
=>ይህ ቅዱስ አባት ከሰማዕታት: ከጻድቃን: ከሊቃውንትና ከዻዻሳት ዝርዝር ውስጥ ይገኛል:: በቤተ ክርስቲያንም ዓበይት ከሚባሉ አበው አንዱ ነው:: ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሮማዊ ሲሆን ከክርስቲያን ወላጆቹ የተወለደው በዘመነ ሰማዕታት (በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን) ነው::
+አበው በትውፊት እንደ ነገሩን ከሆነ ቅዱሱ የታላቁዋ ሰማዕት ቅድስት አርሴማ ትልቅ ወንድም ነው:: በዜና ሰማዕታት ተጽፎ እንደሚገኘው በዚያ የመከራ ዘመን ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሦስት ኃላፊነቶች ነበሩበት:-
1.ቅድስት አርሴማን ጨምሮ ደናግሉን ማጽናት:
2.ትምሕርተ ቤተ ክርስቲያንን በሚገባ ማጥናት:
3.የሚመጣውን መከራ ለመቀበል ራሱን ማዘጋጀት::
+ቅዱሱ 3ቱንም ኃላፊነቶች በሚገባ በመወጣቱ ከራሱ አልፎ ለሌሎቹ አርአያ መሆን ቻለ:: ያቺን ንጽሕት አርበኛ ቅድስት አርሴማንም አጽንቶ የደናግሉ መሪ አደረጋት:: መከራው በጣም ገፍቶ እስከ መጣበት ጊዜ ድረስ በአንድ የደናግል ገዳም ውስጥ ሆነው ይጸልዩ: ይጾሙ: ገዳማዊ ሥራንም ይሠሩ ነበር::
+ለዚህም ነው ቅድስት አርሴማና ቅዱስ ጐርጐርዮስ ጻድቃን የምንላቸው:: በሁዋላ ግን ማሕደረ ሰይጣን ዲዮቅልጢያኖስ በመልኩዋ ተማርኮ ቅድስት አርሴማን ካላገባሁ በማለቱ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ድንግሏን አርሴማን ጨምሮ ክርስቲያኖችን ይዞ ወደ አርማንያ ተሰደደ::
+በአርማንያም በአንድ ገዳም ውስጥ ተደብቀው በጾምና በጸሎት ለጥቂት ጊዜ ቆዩ: ነገር ግን ረሃብ ፈጃቸው:: የሚላስ የሚቀመስ ነገር በአካባቢው ባለ መኖሩ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ወደ ከተማ ለመውጣት ተገደደ::
+በዚያም በድርጣድስ ቤተ መንግስት ውስጥ ባርነት ተቀጠረ:: በሚያገኛት ገንዘብም ወገኖቹን ይረዳ ነበር:: መከራው ግን አለቀቃቸውም:: ርጉም ዲዮቅልጢያኖስ ቅዱሳኑ ወደ አርማንያ መሔዳቸውን ስለ ሰማ ይዞ እንዲልክለት ድርጣድስን ላከው::
+ድርጣድስ ግን ቅድስት አርሴማን ባያት ጊዜ ከውበቷ የተነሳ መታገስ ባለመቻሉ "ካላገባሁሽ" አላት:: ድንግሊቱ ግን "እኔ የክርስቶስ ሙሽራ ነኝ: አይሆንም" አለችው:: ሊያስፈራራት ሞከረ:: ዐይኗ እያየ ደናግሉን ጨፈጨፋቸው::
+አልሳካልህ ቢለው በአደባባይ በግድ ሊያገባት ቢሞክር እጁን ጠምዝዛ በሰው ሁሉ ፊት መሬት ላይ ጣለችው:: እጅግ ስላፈረ አስገረፋት: አሰቃያት: ዐይኗንም አወጣ:: በመጨረሻም አንገቷን አስቆርጦ ከሰማዕታቱ ጋር ተራራ ላይ ጣላት::
+ወዲያው ደግሞ የቅዱስ ጐርጐርዮስ ማንነቱ በመታወቁ ይዘው አካሉ እስኪያልቅ ገረፉት:: በእሳትም አቃጠሉት:: በብዙ ስቃይም አሰቃዩት::
+በመጨረሻ ግን ከነ ሕይወቱ እንዲቀበር ተወሰነበት:: ወደ መጸዳጃ ቤት ወስደውም ከነ ሕይወቱ ቀበሩት:: ነገር ግን የእግዚአብሔር መልአክ ወርዶ መተንፈሻ ቀዳዳን ሠራለት:: አንዲት ሽማግሌ ክርስቲያንም በዚያች ቀዳዳ ቂጣ እየጣለችለት ለ15 ዓመታት ተቀብሮ ኖረ::
+አካሉና አፈሩ ተጣበቀ:: እርሱ ግን ፈጣሪውን እያመሰገነ ቆየ:: ከነገር ሁሉ በሁዋላ ድርጣድስና ባለሟሎቹ ለአደን በሔዱበት ርኩስ መንፈስ ወደ አውሬነት (እሪያነት) ቀየራቸው::
+የንጉሡ እንስሳ (አውሬ) መሆን በአርማንያ ታላቅ ድንጋጤን ፈጠረ:: የንጉሡ እህት ስታለቅስ በራዕይ "ለእመ ኢያዕረግምዎ ለጐርጐርዮስ አልብክሙ ድኂን-ጐርጐርዮስን ከተቀበረበት ካላወጣችሁት አትድኑም" አላቸው:: ወዲያውም በዚያች ሽማግሌ መሪነት ቆፍረው አወጡት::
+አካሉንም እግዚአብሔር መለሰለት:: ቅዱሱ እንደ ወጣ ዕረፍትን አልፈለገም:: ለ15 ዓመታት ቀባሪ አጥቶ የተበተነውን የቅድስት አርሴማንና የሰማዕታቱን አጽም ሰብስቦ በክብር አኖረው:: ድርጣድስና ባለሟሎቹንም ወደ በርሃ ሒዶ ፈወሳቸው::
+ወደ ሰውነትም መልሶ መላ አርማንያን ወደ ክርስትና መለሰ:: የንጉሡን እግር ግን የአውሬ አድርጐት ቀርቷል:: በመጨረሻም ቅዱስ ጐርጐርዮስ የአርማንያ ሊቀ ዻዻሳት ሆኖ ተሹሞ ብዙ መጻሕፍትን ደረሰ:: ከ318ቱ ሊቃውንትም አንዱ ሆኖ ተቆጠረ:: ዛሬ ታሕሳስ 15 ቀን ዕረፍቱ ነው::
+*" አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ረባን "*+
=>ሐዋርያዊው ጻድቅ ኢትዮዽያዊ (ኤርትራዊ) ሲሆኑ በዓለም ደረጃ የሚታወቅ አገልግሎት ያላቸው አባት ናቸው:: በመካከለኛው ዘመን የኢትዮዽያ ታሪክ የኤወስጣቴዎስንና የተክለ ሃይማኖትን ያህል ስሙ የጐላ ጻድቅ አይገኝም::
+ጻድቁ በ1265 ዓ/ም አካባቢ እንደ ተወለዱ ሲታመን ወላጆቻቸው ክርስቶስ ሞዐና ስነ ሕይወት ይባላሉ:: የጻድቁ የመጀመሪያ ስም "ማዕቀበ እግዚእ" (ለጌታ የተጠበቀ) ነው:: ኤዎስጣቴዎስ የተባሉ በሁዋላ ነው::
+ገና ከልጅነታቸው መንፈሰ እግዚአብሔር አድሮባቸዋልና ለዚህ ዓለም ግድ አልነበራቸውም:: ከመምሕር ዘንድ ገብተው: ቅዱሳት መጻሕፍትን ተምረው: ዲቁናን ተቀብለው ያገለግሉ ገቡ:: በዲቁና አገልግሎታቸው ስሉጥ (ፈጣን) በመሆናቸውም የዘመኑ አበው "ዳግማዊ እስጢፋኖስ" እያሉ ይጠሯቸው ነበር::
+ከዚያ በወጣትነት እድሜአቸው ምናኔን መርጠው: ጾምና ጸሎትን ከስግደት ጋር አዘወተሩ:: እንዲህ ባለ ሕይወት ሳሉ አንድ ቀን ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ዘንድ መጣ::
+በዘባነ ኪሩብ: በግርማው ቢያዩት ደነገጡ:: ጌታ ግን "ወዳጄ ኤዎስጣቴዎስ! ገና ከእናትህ ማሕጸን መርጬሃለሁ:: ከኢትዮዽያ እስከ አርማንያም ሐዋርያ ትሆን ዘንድ ሹሜሃለሁ:: "ዘኪያከ ሰምዐ: ኪያየ ሰምዐ . . . አንተን የሰማ እኔን ሰማ:: አንተን እንቢ ያለ እኔን እንቢ አለ::" ብሏቸው: ባርኩዋቸው ዐረገ::
+ጻድቁ ፈጣሪያቸውን ስለ ስጦታው እያመሰገኑ ቅስናን ተቀብለው ስብከትን ጀመሩ:: ስም አጠራራቸውም ፈጥኖ በሃገሪቱ ተሰማ:: በየቦታው እየዞሩ ያላመነውን አሳምነው እያጠመቁ: ያመነውን በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን እያጸኑ: ሕይወተ ገዳምን እያስፋፉ ኖሩ::
+አሁን ኤርትራ ውስጥ የሚገኘውንና እርሳቸው የመሠረቱትን ገዳም ጨምሮ ለገዳማዊ ሕይወት መስፋፋት አስተዋጽኦ አድርገዋል:: በገዳማቸውም አባ አብሳዲን ጨምሮ በርካታ አርድእትን አስተምረዋል: አፍርተዋል::
+አቡነ ኤዎስጣቴዎስ በተለይ የሚታወቁት ቀዳሚት ሰንበት እንዳትናቅ (እንድትከበር) ባደረጉት ጥረት ነው:: ደግሞም ተሳክቶላቸዋል:: ቅርብ ጊዜ ከምናየው የድፍረት ሥራ በቀር በሃገራችን 2ቱም ሰንበቶች ክቡር ናቸው::
+አቡነ ኤዎስጣቴዎስ 2 ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም በእግራቸው ተጉዘዋል:: መሔዳቸው ግን ለመሳለም ብቻ አይደለም:: ይልቁኑ የወንጌል ዘርን እየዘሩ: ፍሬውንም እየለቀሙ እንጂ:: እርሳቸው መቼም ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ቸል አይሉምና::
+በመጨረሻ ሕይወታቸውም በገዳማቸው ላይ ደቀ መዝሙራቸውን አባ አብሳዲን ሹመው ለአዲስ ጉዞ ተነሱ:: እኩሎች ልጆቻቸውን በገዳማቸው ትተው እኩሎችን አስከትለው ጉዞ ወደ አርማንያ ተደረገ::
+በመንገድም ወደ ባሕረ ኢያሪኮ ሲደርሱ የሚሻገሩበት መርከብ አጡ:: ድንቅ አባት ናቸውና በእምነት አጽፋቸውን (ኩታቸውን) አውልቀው ባሕሩ ላይ ጣሉት:: በላዩ ላይም በትእምርተ መስቀል አማትበው ተቀመጡበት::
+ደቀ መዛሙርቶቻቸውም ባሕሩ ላይ በተነጠፈው ኩታ ላይ ከበው ተቀመጡ:: ከሰማይም ጌታችን ወርዶ በመካከላቸው ቆመ:: ሚካኤል በቀኝ ገብርኤልም በግራ ቆሙ:: ጻድቁ ደግሞ ልጆቻቸውን ያስተምሯቸው: ይተረጉሙላቸው ገቡ::+በመካከል ግን አንዱ (የማነ ብርሃን ይሉታል በቅኔ ቤት) በመጠራጠሩ እርሱ የተቀመጠባት ብቻ ተቀዳ ሰጠመ:: በሁዋላ ግን ጻድቁ ተመልሰው አውጥተው: ከሞት አስነስተውታል:: በዚህም ምክንያት 'ዘአደወ ባሕረ-ማዕበልን የተሻገረ' ይባላሉ::
+አቡነ ኤዎስጣቴዎስ በአርማንያ ለዘመናት ሰብከው: ሕይወተ ገዳምን አስፋፍተው: ብዙ ተአምራትን ሠርተው: በተወለዱ በ80 ዓመታቸው: በ1345 ዓ/ም ዐርፈዋል:: በብዙ ዝማሬ በመቅደሰ መርምሕናም ተቀብረዋል:: በኢትዮዽያ: ኤርትራ: ግብጽና አርማንያ ይከብራሉ:: ዛሬ ጻድቁ ማዕበሉን የተሻገሩበት መታሰቢያ ቀን ነው::
=>አምላከ ቅዱሳን ስለ አባቶቻችን ሲል በምሕረቱ ይጐብኘን:: ከበረከታቸውም ያሳትፈን::
=>ታሕሳስ 15 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሊቅ (ዘአርማንያ)
2.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ረባን
3.ቅዱስ ሉቃስ ዘዓምድ
4.አባ ይምላህ
=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት)
2.ቅድስት እንባ መሪና
3.ቅድስት ክርስጢና
4.ቅዱስ ሚናስ ሰማዕት
5.ቅዱስ ቂርቆስ ሰማዕት
4.ብጽዕት ኢየሉጣ ሰማዕት
=>+"+ ጻድቃን ጮሁ:: እግዚአብሔርም ሰማቸው::
ከመከራቸውም ሁሉ አዳናቸው::
እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው::
መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል::
የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው::
እግዚአብሔርም ከሁሉ ያድናቸዋል::
እግዚአብሔር አጥንቶቻቸውን ሁሉ ይጠብቃል:: +"+ (መዝ. 33:17)
✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞
✞ ወለወላዲቱ ድንግል ✞
✞ ወለመስቀሉ ክቡር አሜን ✞
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ::" /ማቴ ፫:፫/
ዝክረ ቅዱሳንን ተማሩ ብለን እንለምናችኋለን!!።
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together.https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━━━
Comments
Post a Comment