✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞
✞✞✞ ታኅሣሥ 6 ✞✞✞
✞✞✞ እንኩዋን "ለድንግልና ሰማዕት ቅድስት አርሴማ" : "አባ አብርሃም" እና "ቅዱስ ስምዖን ጫማ ሰፊው" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞
+*" ቅድስት አርሴማ ድንግል "*+
=>እናታችን ቅድስት አርሴማን በምን እንመስላታለን? እርሷ በአድማስ ላይ ተቀምጦ እንደሚያበራ እንቁ ናትና ክብሯ ብዙ ነው:: መድኃኒታችን ክርስቶስ በወንጌል እንዳለው "በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትምና" (ማቴ. 5:11) የሰማዕቷ ሕይወት በፊታችን እንደ ብርሃን ተገልጦ ይታያል::
*ቅድስት አርሴማ እንደ ልጅ ወላጆቿን በመታዘዝ ደስ ያሰኘች ቡርክት ናት::
*ቅድስት አርሴማ ይሕ ቀረሽ የማይሏት ውብ ናት::
*ቅድስት አርሴማ ድንግል ናት::
*ቅድስት አርሴማ ባሕታዊት ጻድቅ ናት::
*ቅድስት አርሴማ ኃያል ሰማዕት ናት::
¤ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:
+አበው በትውፊት እንደ ነገሩን ከሆነ ቅዱሱ ጐርጐርዮስ የታላቁዋ ሰማዕት ቅድስት አርሴማ ትልቅ ወንድም ነው:: በዜና ሰማዕታት ተጽፎ እንደሚገኘው በዚያ የመከራ ዘመን ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሦስት ኃላፊነቶች ነበሩበት:-
1.ቅድስት አርሴማን ጨምሮ ደናግሉን ማጽናት
2.ትምሕርተ ቤተ ክርስቲያንን በሚገባ ማጥናት
3.የሚመጣውን መከራ ለመቀበል ራሱን ማዘጋጀት::
+ቅዱሱ 3ቱንም ኃላፊነቶች በሚገባ በመወጣቱ ከራሱ አልፎ ለሌሎቹ አርአያ መሆን ቻለ:: ያቺን ንጽሕት አርበኛ ቅድስት አርሴማንም አጽንቶ የደናግሉ መሪ አደረጋት:: መከራው ገፍቶ እስከ መጣበት ጊዜ በአንድ የደናግል ገዳም ውስጥ ሆነው ይጸልዩ: ይጾሙ: ገዳማዊ ሥራንም ይሠሩ ነበር::
+ለዚህም ነው ቅድስት አርሴማና ቅዱስ ጐርጐርዮስ ጻድቃን የምንላቸው:: በሁዋላ ግን ማሕደረ ሰይጣን ዲዮቅልጢያኖስ በመልኩዋ ተማርኮ ቅድስት አርሴማን ካላገባሁ በማለቱ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ድንግሏን አርሴማን ጨምሮ ክርስቲያኖችን ይዞ ወደ አርማንያ ተሰደደ::
+በአርማንያም በአንድ ገዳም ውስጥ ተደብቀው በጾምና በጸሎት ለጥቂት ጊዜ ቆዩ:: ነገር ግን ረሃብ ፈጃቸው:: የሚላስ የሚቀመስ ነገር በአካባቢው ባለ መኖሩ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ወደ ከተማ ለመውጣት ተገደደ::
+በዚያም በድርጣድስ ቤተ መንግስት ውስጥ ባርነት ተቀጠረ:: በሚያገኛት ገንዘብም ወገኖቹን ይረዳ ነበር:: መከራው ግን አለቀቃቸውም:: ርጉም ዲዮቅልጢያኖስ ቅዱሳኑ ወደ አርማንያ መሔዳቸውን ስለ ሰማ ይዞ እንዲልክለት ድርጣድስን ላከው::
+ድርጣድስ ግን ቅድስት አርሴማን ባያት ጊዜ ከውበቷ የተነሳ መታገስ ባለመቻሉ "ካላገባሁሽ" አላት:: ድንግሊቱ ግን "እኔ የክርስቶስ ሙሽራ ነኝ: አይሆንም" አለችው:: ሊያስፈራራት ሞከረ:: ዐይኗ እያየ ደናግሉን ጨፈጨፋቸው::
+አልሳካልህ ቢለው በአደባባይ በግድ ሊያገባት ቢሞክር እጁን ጠምዝዛ በሰው ሁሉ ፊት መሬት ላይ ጣለችው:: እጅግ ስላፈረ አስገረፋት: አሰቃያት: ዐይኗንም አወጣ:: በመጨረሻም አንገቷን አስቆርጦ ከሰማዕታቱ ጋር ተራራ ላይ ጣላት::
+ከነገር ሁሉ በሁዋላ ድርጣድስና ባለሟሎቹ ለአደን በሔዱበት ርኩስ መንፈስ ወደ አውሬነት (እሪያነት) ቀየራቸው::
+የንጉሡ እንስሳ (አውሬ) መሆን በአርማንያ ታላቅ ድንጋጤን ፈጠረ:: የንጉሡ እህት ስታለቅስ በራዕይ "ለእመ ኢያዕረግምዎ ለጐርጐርዮስ አልብክሙ ድኂን-ጐርጐርዮስን ከተቀበረበት ካላወጣችሁት አትድኑም" አላቸው:: ወዲያውም ቆፍረው አወጡት::
+ቅዱሱ እንደ ወጣ ዕረፍትን አልፈለገም:: ለ15 ዓመታት ቀባሪ አጥቶ የተበተነውን የቅድስት አርሴማንና የሰማዕታቱን አጽም ሰብስቦ በክብር አኖረው::
ድርጣድስና ባለሟሎቹንም ወደ በርሃ ሒዶ ፈወሳቸው::
+የሰማዕቷ ቅድስት አርሴማ አጽም በ14ኛው መቶ ክ/ዘመን ከሌሎች ሰማዕታት አጽም ጋር ኢትዮዽያ እንደ መጣ አባቶቻችን በትውፊት ነግረውናል:: ለዚህም ይመስላል ቡርክቷ እናታችን ከሌሎች ሃገራት ለይታ ለኢትዮዽያውያን ልዩ ፍቅር ያላት:: በዋናው ገዳሟ (ወሎ /ኩላማሶ/ : ስባ : ውስጥ የሚገኝ ነው) ጨምሮ ስሟ በተራበት ሁሉ ኃይልን ታደርጋለችና::
+ነገር ግን ወንድሞቼና እሕቶቼ በቅድስቷ እናታችን ስም የሚነግዱ ሥጋውያን ሰዎች በዝተዋልና እንጠንቀቅ:: የሰማዕቷ ክብር ብዙ ነውና በሕልም ላይ ብቻ አንታመን:: አባ እንጦንስ እንዳሉት "በሕልሙ የሚታመን ሰው ከንቱ ነውና::" (መዝ. 75:5)
+በዚህ ዕለት ከሰማዕቷ ጋር የመንፈስ እናቷን ቅድስት አጋታን ልናስባት ይገባናል:: ይህች እናት እመ-ምኔት ስትሆን ቅድስት አርሴማን ታስተምራት: ታጸናት: ከጐኗም ትቆምላት ነበር:: ረሃቧን: ጥሟን: ስደቷን: መከራዋንም ሁሉ አብራት ተሳትፋለች:: በፍጻሜውም አብራት ተሰይፋለች::
+ይህች ዕለት ለቅድስት አርሴማና ለተከታዮቿ ሰማዕታት የፍሰትና የቅዳሴ ቤት መታሰቢያ ናት::
+"+አባ አብርሃምና ቅዱስ ስምዖን ጫማ ሰፊው+"+
=>እነዚህ 2 ኮከቦች በ11ኛው መቶ ክ/ዘመን አካባቢ በምድረ ግብጽ ተነስተው ለቤተ ክርስቲያን ድንቅ ተአምርን የሠሩ አበው ናቸው:: እመ ብርሃን ማርያም ለሥራ እስክታገናኛቸው ድረስም እርስ በርስ አይተዋወቁም ነበር::
+"+ አባ አብርሃም +"+
=>ይህ ቅዱስ ትውልዱ ከሶርያ ሲሆን እጅግ የታወቀ ነጋዴ ነበር:: ከሶርያ ግብጽ እየተመላለሰ ሲነግድ ባለ ጸጋ ሆኖም ነበር:: ነገር ግን ክርስትናን አጥብቆ የተማረ: ነዳያንን የማይዘነጋ: ጾምና ጸሎትን የማይገፋና እኔን ብቻ ይድላኝ የሚል ሰው ስላልነበረ እግዚአብሔር ለታላቅ ሥራ ጠራው::
+የግብጽ 61ኛ ፓትርያርክ አባ ፊላታዎስ ባረፈ ጊዜ አበው ተተኪ ፍለጋ ሱባኤ ቢገቡ "ሶርያዊ አብርሃምን ሹሙ" አላቸው:: እርሱ "እንቢ" ቢልም አለቀቁትም:: እርሱም ከሆነስ ብሎ ሃብቱን እኩሉን ለነዳያን: እኩሉን ለገዳማት ሰጥቶ ባዶ እጁን ወደ መንበረ ዽዽስናው ወጥቷል:: በዘመነ ሲመቱም ልማደ ኃጢአትን ያርቅ ዘንድ ብዙ ተግቷል::
+"+ ቅዱስ ስምዖን ሰፋዪ +"+
=>በዚያው ዘመን በምስር (በአሁኗ CAIRO) አካባቢ ራሱን ደብቆ: ጫማ እየጠገነ: ነዳያንን እየመገበ: ድኩማንን እየረዳ: በፍጹም ትሕትና: በጾምና በጸሎት የኖረ አባት ነው:: አንዲት ወጣት ልታስተው ብትመጣም ስለ ክርስቶስ ትዕዛዝ አንድ ዐይኑን በመሳፈቻ አውጥቶ ጥሏል::
+"+ በእምነት ተራራ ሲነቀል +"+
=>በወቅቱ የነበረው የግብጽ ከሊፋ ፍልስፍና ወዳጅ በመሆኑ ምሁራንን ያከራክር ነበር:: አንድ አይሁዳዊ "ምሑር" ነኝ ባይም ከክርስቲያኖች ጋር መከራከር ፈልጐ ጠየቀ:: አባ አብርሃምና አባ ሳዊሮስ መጥተው ድል ነስተው: አሳፍረውት ሔዱ::
+እርሱም በቂም በማቴ. 17:20 ላይ ያለችውን ቃል ይዞ ሒዶ በከሊፋው ፊት አቀረበ:: ቃሉም:- "የሰናፍጭ ቅንጣት ታሕል እምነት ቢኖራችሁ ይህንን ተራራ ተነቀል . . . ብትሉት ይቻላቹሃል" ይላል::
+ከሊፋውም አባ አብርሃምን ጠርቶ "መጽሐፍ ቅዱሳችሁ እንደዚህ ይላል?" አለው:: "አዎ!" ሲል መለሰለት:: "አድርገህ አሳየኝ" ቢለው 3 ቀናትን ለምኖት ወጣ:: ሁሉም ክርስቲያኖች የ3 ቀን ምሕላ ሲይዙ አባ አብርሃም በእመቤታችን መቅደስ ለ3 ቀናት ያለ ምግብና እንቅልፍ አለቀሰ::
+እመ ብርሃን በሞገስ መጥታ "ጫማ ሰፊው ስምዖን ይህንን ያደርግልሃል" አለችው:: በምልክት ሒዶ: በፊቱ አዘንብሎ "አቤቱ ለገኖችህ ክርስቲያኖች ራራላቸው?" አለው::+ቅዱሱ ደንግጦ እንቢ እንዳይለው የድንግል ማርያምን ስም ጠራበት:: ቅዱስ ስምዖንም ለአባ አብርሃም "ሰው እንዳያውቀኝ አደራ!" ብሎት ወደ አንድ ግዙፍ ተራራ ሔዱ::
+ሕዝቡ ባንድ ወገን: ከሊፋውና ሠራዊቱ በሌላ ወገን ቆሙ:: ቅዱሳኑ ከምዕመናን ጋር "41 ኪርያላይሶን" አድርሰው: ሰግደው ቀና ሲሉ ተራራው ተነቅሎ በዓየር ላይ ተንሳፈፈ:: ለማጽናትም 3 ጊዜ ተነቅሎ ተተከለ::
+በሁዋላም ወደ ሌላ ቦታ አልፎ ተቀመጠ:: በዚህች ዕለትም በድንግል ምልጃ: በቅዱሳኑ ጸሎት ታላቅ ሞገስ ሆነ:: ወዲያው ግን ቅዱስ ስምዖን ተሰወረ:: ውዳሴ ከንቱን ይጠላልና:: አባ አብርሃምም በቀሪ ዘመኑ ተግቶ ዐርፏል:: ዛሬ የ2ቱም መታሰቢያ ነው::
+ሊቃውንትም ቅዱስ ስምዖንን ሲያደንቁ:-
"ሰላም ለስምዖን በአፈ ማርያም ዘተአምረ::
እንበይነ ትዕዛዙ ለወልዳ ከመ ዐይኖ አዖረ::
ኢይሌብውዎ ሎቱ ወኢይጸግውዎ ክብረ::
ሶበ ጸለየ ቀዊሞ ለሊቀ ዻዻሳት ድኅረ::
ነቀለ ደብረ ወተከለ ደብረ" ብለዋል:: (አርኬ)
=>አምላከ ቅዱሳን ተራራ ያፈለሱበትን እምነታቸውን አይንሳን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::
=>ታሕሳስ 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅድስት አርሴማ ድንግል
2."119" ሰማዕታት (ማሕበሯ)
3.ቅዱስ ስምዖን ጻድቅ (ጫማ ሠፊው)
4.አባ አብርሃም ሶርያዊ
5.ቅዱስ እንጣልዮስ ሰማዕት
=> ወርኅዊ በዓላት
1.ቅድስት ደብረ ቁስቁዋም
2.አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
3.አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
4.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
5.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
6.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
7.ቅድስት ሰሎሜ
8.አባ አርከ ሥሉስ
9.አባ ጽጌ ድንግል
=>+"+ እውነት እላቹሃለሁ:: የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ ይህን ተራራ ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል:: የሚሳናችሁም ነገር የለም:: +"+ (ማቴ. 17:20)
✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞
✞ ወለወላዲቱ ድንግል ✞
✞ ወለመስቀሉ ክቡር አሜን ✞
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ::" /ማቴ ፫:፫/
ዝክረ ቅዱሳንን ተማሩ ብለን እንለምናችኋለን!!።
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
✝ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Togethellettps://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━━━
Comments
Post a Comment