ገብርኄር
በጎ አገልጋይ ለጌታው ታምኝ እንደመሆኑ ‹‹ገብር ኄር›› ይባላል፡፡ ይህም ስያሜ ለዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት እንደተሰጠ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ይገልጻል፡፡ የስያሜው መነሻ የሚገኘው ደግሞ በዕለቱ ሥርዓተ ቅዳሴ ከሚነበበው በማቴዎስ ወንጌል ክፍል ነው፡፡ (ማቴ.፳፭፥፲፬-፴)
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምሳሌ ካስተማራቸው ትምህርቶች መካከል አንዱ የሆነው ይህ ወንጌል አስተማሪ የሆኑ መሠረታዊ ጉዳዮችን በውስጡ ይዟል፡፡ በተለይ ምንም እንኳን የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት የእገሌና የእገሊት ተብሎ ባይወሰንም ቤተ ክርስቲያን ባላት የአገልግሎት መዋቅር መሠረት የኃላፊነትን ቦታ ይዘው ለሚያገለግሉ ሰዎች አትኩሮት ሊሰጡባቸው የሚገባቸውን ነጥቦች ይጠቁማል፡፡ ይህን ለማየት ያመቸን ዘንድ ከታሪኩ የመጀመያ ክፍል በመነሣት ዋና ዋና የሆኑ ሐሳቦችን በአትኩሮት መመርመር ጠቃሚ ነው፡፡
በምሳሌያዊው ታሪክ መጀመሪያ ላይ የምናገኘው አንድ መንገድ ሊጀምር ያሰበ ሰው ከመሄዱ በፊት አገልጋዮቹን ጠርቶ ለእያንዳንዳቸው እንደ ችሎታቸው መጠን ለአንዱ አምስት፣ ለአንዱ ሁለት እንዲሁም ለሌላኛው አንድ መክሊት ነግደው ያተርፉበት ዘንድ እንደሰጣቸው ነው፡፡ ገና ከታሪኩ መጀመሪያ እንደምንረዳው የአገልጋዮቹ ጌታ ምንም እንኳን እርሱ ለመንገድ ቢዘጋጅም ሀብቱ ግን በተዘጋ ቤት ውስጥ ተቆልፎበት እንዲቀመጥ አልፈለገም፡፡ በዚህም አገልጋዮቹን ጠርቶ ገንዘቡን በአደራ ተቀብለው እንዲያተርፉበት ማዘዙን እንደማስረጃ ልናቀርብ እንችላለን፡፡ ሆኖም ግን ማትረፍ በመፈለጉ ብቻ ገንዘቡን ያለአግባብ አልበተነም፡፡ ነገር ግን ለእርሱ ቀረቤታ የነበራቸውን አገልጋዮቹን ጠርቶ ያውም እንደየችሎታቸው መጠን ኃላፊነቱ ሳይከብዳቸው እንዲሠሩበት ገንዘቡን አከፋፈላቸው፡፡
ይህ ጌታ ቅንነትና ርኅራኄ የበዛለት እንደሆነ የሚያመላክተን ነገር አለ፡፡ ይኸውም ለአገልጋዮቹ ኃላፊነትን ቢሰጥም እንኳን ከእነርሱ ጋር በነበረው ቀረቤታ ማን ምን መሥራት እንደሚችል ከግምት ውስጥ በማስገባት ለእያንዳንዳቸው እንደ ኃላፊነት የመሸከም አቅማቸው አምስት፣ ሁለኃ አንድ እያደረገ መስጠቱ ነው፡፡ ምናልባት ስስት ባልተላቀቀው ስሜት ለሚያስብ ሰው የዚህ ጌታ መክሊት አሰጣጥ አድልዎ ያለበት ሊመስለው ይችላል፡፡ ታሪኩን እስከ መጨረሻው ብንከታተለው ግን የሚያሳየን የባለ መክሊቱን ባለቤት ቅንነት ነው፡፡ ይህ ጌታ ለአገልጋዮቹ እንዲያተርፉበት መክሊቱን ሰጥቷቸው በሄደበት ሀገር አልቀረም፡፡ ይልቁንም እያንዳንዱ በተሰጣቸው መክሊት ምን እንደሠሩበት ሊቆጣጠራቸው እንደመጣ እናነባለን፡፡ ስለዚህ አገልጋዮቹ በሰጣቸው መክሊት ምን እንደሠሩ እንደሚጠይቃቸው እያወቀ ከአቅማቸው በላይ የሆነ መክሊትን በመስጠት ምን ሢሰሩ የተሰጣቸውን መክሊት ያህል ማትረፍ እንደሚችሉ በማሰብ እንዲጨነቁ አልፈለገም፡፡ በተቃራኒው የምናየው ያለምንም ጭንቀት ከአእምሯቸው በላይ ሳይሆን ባላቸው ኃይል ተጠቅመው መሥራትና ማትረፍ የሚችሉትን ያህል መክሊት እንደሰጣቸው ነው፡፡
ከብዙ ጊዜም በኋላ የእነዚያ አገልጋዮች ጌታ በሰጣቸው መክሊት ምን እንደሠሩበት ሊቆጣጠራቸው ሲመጣ አምስት መክሊት ተቀብሎ የነበረው ሌላ አምስት እንዲሁም ሁለት መክሊት ተቀብሎ የነበረው ሌላ ሁለት መክሊት አትርፎ ጌታቸው ፊት እንደቆሙ፣ ያ ጌታም በእነዚህ አገልጋዮቹ ታማኝነት ተደስቶ ወደ ደስታው እንዳስገባቸው እናያለን፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ያ አንድ መክሊት ተቀብሎ የነበረው ምድርን ቆፍሮ ያተርፍባት ዘንድ የተሰጠችውን መክሊት እንደቀበረ ከዚህም አልፎ ምን እንዳደረገበት ሲጠየቅ የአመጽ ንግግር እንደተናገረና በዚህ ከፊቱ ያዘነው ጌታውም ያን ክፉ አገልጋይ እንዲቀጣ እንዳደረገው እናነባለን፡፡
በዚህኛው ክፍል ከተጠቀሰው ታሪክ ሦስቱን አካላት ማለት የመክሊቱን ሰጪ ጌታ፣ በጎ የተባሉ አገልጋዮችና ክፉ እና ሰነፍ የተባለውን አገልጋይ በተናጥል እንመልከታቸው፡፡
፩. የአገልጋዮቹ ጌታ
ይህ ሰው ለገንዘቡ ጠንቃቃ ከመሆኑ ባሻገር በአገልጋዮቹ ላይ ሙሉ ሥልጣን እንዳለው እንመለከታለን፡፡ በክፉው አገልጋይ ላይ ባለመታዘዙ ምክንያት የፈረደበትን ፍርድ (ልቅሶና ጥርስ ማፏጨት ወዳለበት በውጪ ወዳለ ጨለማ እንደከተቱት) ስንመለከት የሚያሳየን የአገልጋዮቹን ጌታ ትላቅ ሥልጣን ነው፡፡ ምንም እንኳን ሥልጣኑ ጽኑ ቢሆንም ይህ ጌታ ፍርዱ ግን በእውነት ላይ የተመረኮዘ መሆኑን ደግሞ በድካማቸው ታግዘው በተሰጣቸው መክሊት ላተረፉት በጎ አገልጋዮች የሰጣቸውን ፍጹም ደስታ መጥቀስ ይቻላል፡፡
፪. በጎ አገልጋዮች
በአገልጋዮቹ ጌታ በጎ አገልጋዮች የተባሉት አምስት መክሊት የተቀበለውና ሁለት መክሊት የተቀበለው ናቸው፡፡ እዚህ ጋር ማስተዋል የሚገባው እነዚህ ሁለቱ አገልጋዮች በጎ አገልጋዮች ለመባል ያበቃቸው አስቀድመው ብዙ ወይንም የተሻለ ቁጥር ያለው መክሊት ለመቀበል መብቃታቸው አይደለም፡፡ ጉዳዩ የመክሊቱ ቁጥር ሳይሆን በተሰጣቸው መክሊት መጠን የሚገባቸውን ያህል ደክመው ማትረፍ መቻላቸው ነው፡፡ ወይንም ያ ባለ አንድ መክሊት አገልጋይ ከሁለቱ ያሳነሰው ከአንድ በላይ መክሊት መቀበል የማይችል መሆኑ ሳይሆን በዚያችው በአንዷ መክሊት እንኳን መሥራት አለመቻሉ ነው፡፡
፫. ክፉና ሰነፍ አገልጋይ
ክፉና ሰነፍ የሆነው አገልጋይ በታሪኩ ውስጥ የተጠቀሱ ሦስት መሠረታዊ ችግሮች አሉበት፡፡ የአገልጋዮቹ ጌታ ወደ መንገድ ሊሄድ በተዘጋጀበት ወቅት አገልጋዮቹን ጠርቶ ለእያንዳንዳቸው እንደችሎታቸው ገንዘቡን ሲሰጣቸው አትርፈው እንዲቆዩት ነው፡፡ ከላይ እንደተመለከትነው የተለያየ መክሊት መስጠቱም አቅማቸው በሚፈቅደው የሥራ ደረጃ እንዲሰማሩ በማሰብ ነበር፡፡ ይህ ሰነፍ አገልጋይ ግን ያደረገው ከታዘዘበት ዓላማ በተቃራኒው መልኩ ነው፡፡ ሊሠራበት የሚገባውን መክሊት ቀበረው፡፡ ይህም ለጌታው ትእዛዝ ያለውን ቸልተኝነት ያሳያል፡፡
ጌታው በመጣ ጊዜ አመጽ የተመላበት የሐሰት ንግግር ተናግሯል፤ ከሄደበት ቦታ ተመልሶ ጌታው በተሰጠው መክሊት ምን እንዳደረገ ሲጠይቀው «አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበትም የምትሰበሰብ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንህ አውቃለሁ፤ ስለፈራሁም ሄድሁና መክሊትህን በምድር ውስጥ ቀበርሁ» በማለት መለሰለት፡፡ ይህ ንግግር ከአመጽ ንግግርነቱ በተጨማሪ ሐሰት አለበት፡፡ ምክንያቱም እርሱ እንዳለው ጌታው ካልዘራበት የሚያጭድና ካልበተነበት የሚሰበሰብ ጨካኝ ሰው ቢሆን ኖሮ ያደርግ የነበረው ምንም መክሊት ሳይሰጠው ከነትርፉ ሁለት መክሊቶችን ይጠይቀው ነበር፡፡ ነገር ግን ተጽፎ የምናነበው ትርፉን ከመጠየቅ በፊት አንድ መክሊት ሰጥቶት እንደበረ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ አስቀድሞ ገንዘቡን ዘርቶ ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ጌታ ዘርቷልና ማጨድ በትኗልና መሰብሰብም ይገባዋል፡፡
እርሱ መሥራት ሲሳነው እንኳን ዕድሉን ለሌሎች አልሰጠም፤ ይህ ሰው የተሰጠው መክሊት በትርፍ ሊመለስ እንደሚገባው ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ምክንያቱም ገና መክሊቱን ሲቀበል ከጌታው የተሰጠው ትእዛዝ ነውና፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳን መውጣትና መውረዱ ቢከብደውም ወጥተው ወርደው ማትረፍ ለሚችሉ ሰዎች አለመስጠቱ ተጨማሪ ጥፋቱ ነው፡፡ ይህን እንዳያደርግ ያሰረው ደግሞ ውስጡ የተቀረጸው የአመጽ መንፈስ ነው፡፡ ጌታው መጥቶ ስለ ትርፉ ሲጠይቀው የሚመልስለትን ረብ የለሽ ምክንያት እንደ መከላከያ አድርጎ ማሰቡ አእምሮው ሌላ አማራጭ እንዳያስብ የዘጋበት ይመስላል፡፡
በመጀመሪያውም ይሁን በሁለተኛው ዓይነት ስጦታ ተቀባዮች ዘንድ ግን ብዙ የሚያሳዝኑ ችግሮች አሉ፡፡ በዳግመኛ መወለድ ምሥጢር (በ4፵ ና ፹ ቀን ጥምቀት) ስላገኘነው የልጅነት ጸጋ ጊዜ ሰጥቶ የሚያስብ ክርስቲያን ማግኘት በዚህ ዘመን በጣም አዳጋች ነው፡፡ በዓመት ውስጥ ክርስቲያንነቱ ለጥምቀት በዓልና ለመስቀል ደመራ ካልሆነ ትዝ የማይለው ቁጥሩ ቀላል አይደለም፡፡ ከዚህ የከፋው ደግሞ ከቤተ ዘመድ አንድ ሰው ምናልባትም ራሱም ሊሆን ይችላል ነፍሱ ከሥጋው ካልተለየች ወደ ቤተ ክርስቲያን ደጅ ብቅ አይልም፡፡
እግዚአብሔር የልጅነትን ጸጋ በመስጠት ለእኛ ያለውን ፍቅሩን አሳይቶናል፡፡ ምክንያቱም ልጅነታችን ዋጋ ተከፍሎበታልና፡፡ ልጆች የተባልነው እንዲሁ አይደለም፡፡ እኛ ልጅነትን እንድንቀበል አምላክ መከራን ተቀብሏል፡፡ የጥምቀታችን ውኃ የፈሰሰው በጦር ከተወጋው ከጌታ ጎን ነው፡፡ (ዮሐ.፲፱፥፳፬) ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ይሄንን ሁሉ ሲያመለክት እንዲህ በማለት ተናግሯል፤‹‹የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ልንጠራ አብ እንዴት ያለውን ፍቅር እንደሰጠን እዩ፡፡›› (፩ኛ.ዮሐ.፫-፩) እኛ ልጆቹ እንሆን ዘንድ እግዚአብሔር ካሳየን የአባትነት ፍቅር በተጨማሪ ልጆቹ ስለመሆናችን የገባልንም ተስፋ ከአእምሮ በላይ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ምእመናን በላከው መልእክቱ ‹‹እንኪያስ እናንተ ልጆች ናችሁ እንጂ ባሮች አይደላችሁም፡፡ ልጆች ከሆናችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሾች ናችሁ›› (ገላ.፬፥፯) በማለት ስለሚጠብቀን ተስፋ ነግሮናል፡፡ ስለዚህ በጣም ልንጠነቀቅበት የሚገባን የመጀመሪያው መክሊታችን ልጅነታችን መሆኑን መረዳት ያስፈልገናል፡፡ በዚህም መክሊት እንድንሠራ የታዘዝናቸውን ምግባራት እንድናፈራ የሚጠበቅብንን ፍሬዎች ማፍራት አለብን፡፡ ያለበለዚያ መክሊቱን እንደቀበረው ሰው መሆናችን ነው፡፡
ቃሉን የሰማንና የምናውቅ ሁላችን በሞቱ ላዳነን፣ በልጅነት ጸጋም ላከበረን፣ በትንሣኤውም ላረጋጋን፣ በመስቀሉ ጥልን ገድሎ ከራሱ ጋር ላስታረቀን፣ በውኂዘ ደሙም ሕይወትን፣ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ በረከትንና ዘለዓለማዊ ደስታን ለሰጠን አምላካችን በመታዘዝ አቅማችን በሚፈቅደው አገልግሎት ጸንቶ መገኘት ተገቢ ነው፡፡ በአገልግሎት የመጽናት ምልክቱ ደግሞ አትራፊነት ነው፡፡ ቅዱሳን ነቢያት፣ ቅዱሳን ሐዋርያት እንዲደሁም ቅዱሳን ሊቃውንት በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ በአትራፊነት ይታወቃሉ፡፡ ለማትረፍ ግን ራሳቸውን ለእውነት ለአገልግሎት ለመከራ አሳልፈው በመስጠት ነው፤ በትንሹ መታመን ሲባል የእኛ አገልግሎት ከፈጣሪ ቸርነት ጋር ስለማይመጣጠን ነው፤ ‹‹በብዙ እሾምሃለሁ›› ማለቱም በመንግሥተ ሰማያት ለዘለዓለም ከብሮ መኖርን ነው፡፡
ከቅዱሳን ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ሰብአ አርድእት፣ ሊቃውንትም የሰማነውና ያየነው እውነት ምንጊዜም ትጉህ ሠራተኛ የሚሠራው መልካም ሥራ ሁሉ ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለሀገር የሚሰጠው ጥቅም እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ዘመን ልዑል እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን፣ ምእመናንን፣ ሀገርንና ሕዝብን ለመምራት የጠራንና የመረጠ እንዲሁም በአገልግሎት ዐደባባይ ያስቀመጠን ሰዎች እጅግ ዕድለኞች ነን፤ ምክንያቱም የሕዝብን ችግርና አቤቱታ ሰምቶና ተቀብሎ መፍትሔ መስጠት ትርፋማነት ነውና፤ ትርፋማነት ደግሞ ወደ ትልቁ የሹመት መሰላል መውጣት ነው፤ ይህ ሳይሆን ቀርቶ አገልግሎታችን ተደናቅፎ የሕዝባችን ችግር ሳይፈታ ቀርቶ የአገልግሎታችን ተቆጣጣሪ አምላካችን ቢጎበኘን ‹‹አንተ ሰነፍ አገልጋይ›› ተብለን ወደ ውርደት አዘቅት እንዳንላክ መጠንቀቁ አይከፋም፡፡ የመሾም፣ የመሻር፣ የማሳደግና የማውረድ ሥልጣን የእግዚአብሔር ነውና፡፡ ‹‹ከእናንተ መካከል አንዱን እንኳ እንዳናስቸግር ቀንም ሌሊትም እንሠራ ነበር፡፡›› (፩ኛተሰ.፪፥፱) በጎና ታማኝ አገልጋዮች ሆነን እንድንገኝ መጠንከር ያስፈልጋል፡፡
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
✝ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together
https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━⊱✿⊰━━
Comments
Post a Comment