✞✞✞ እንኩዋን ለታላቁ "ቅዱስ መቃርስ" ዓመታዊ
የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞
+*"+ ታላቁ ቅዱስ መቃርስ +"*+
=>ታላቁ ቅዱስ መቃርስ (ቅዱስ መቃሬ) 'ጽድቅ እንደ መቃርስ' የተባለለት: የመነኮሳት ሁሉ አለቃ: ከ80 ዓመታት በላይ በበርሃ የኖረ: በግብፅ ትልቁን ገዳም (አስቄጥስን) የመሠረተ: ከ50,000 በላይ መነኮሳትን ይመራና ይመግብ የነበረ ፍፁም ጻድቅ ነው::
+በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን አርዮሳውያን ደጉን ታላቅ አባት በሰንሰለት አስረው ከግብፅ ወደ እስያ በርሃ ከጉዋደኛው ቅዱስ መቃርዮስ እስክንድርያዊ ጋር አሰድደውታል:: በዚያ ለ2 ዓመታት ስቃይን ከተቀበሉ በሁዋላ በአረማውያን ፊት ድንቅ ተአምር አድርገው አረማውያንን ከነንጉሳቸው አጥምቀዋል::
+በተሰደዱባት ሃገርም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ (ስም አጠራሩ ይክበርና) እመቤታችንን: ቅዱሳን ሐዋርያትን:
አዕላፍ መላእክትን: በተለይ ደግሞ ቅዱሳኑን ዳዊትን:
ዮሐንስ መጥምቁንና ወንጌላዊውን: ማርቆስን: ዼጥሮስን:
ዻውሎስን አስከትሎ ወርዶ ተገልጦላቸዋል:: በቅዱስ
አንደበቱም የምሕረት ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል::
+ታላቁ ቅዱስ መቃርስና ባልንጀራው መቃርዮስ ከ2
ዓመታት ስደትና መከራ በሁዋላ ስደት በወጡባት ዕለት
መልዐኩ ኪሩብ በክንፉ ተሽክሞ ወደ ግብፅ
መልሷቸዋል:: በወቅቱም ጻድቁን ለመቀበል ከ50,000
በላይ የሚሆኑ ልጆቻቸው መነኮሳት በዝማሬ ወጥተዋል::
+ስለ ታላቁ ቅዱስ መቃርዮስ ቅድስና ለመጻፍ መነሳት
በረከቱ ብዙ ነው:: ግን 'ዓባይን በጭልፋ' እንዲሉ አበው
ከብዛቱ የተነሳ የሚዘለቅ አይሆንም::
+ቅዱስ መቃርስ ከዘመናት በላይ በቆየበት የበርሃ
ሕይወቱ:-
1.አባ ብሶይ: አባ ባይሞይ: አባ ሳሙኤል: አባ በብኑዳን
ጨምሮ እርሱን የመሰሉ (ያከሉ) ቅዱሳንን ወልዷል::
2.ለሕይወታችን መንገድ የሚሆኑንን ብዙ ቃላትን
ተናግሯል::
3.ከገዳማት እየወጣ በብዙ ቦታዎች ቅዱስ ወንጌልን
ሰብኩዋል::
4.አጋንንትን ድል ከመንሳት አልፎ እንደ ባሪያ ገዝቷቸዋል::
5.ለዓይንና ጀሮ ድንቅ የሆኑ ብዙ ተአምራትን ሰርቷል:: . .
.
+በእነዚህና ሌሎች ምክንያቶችም ቤተ ክርስቲያን "ርዕሰ
መነኮሳት (የመነኮሳት ሁሉ አለቃ)" ስትል ትጠራዋለች::
በ97 ዓመቱ መጋቢት 27 ቀን ሲያርፍ መላእክት ብቻ
ሳይሆን አጋንንትም ስለ ድል አድራጊነቱ ዘምረውለታል::
=>ታላቁ ቅዱስ መቃርስ ካረፈ በሁዋላ ከክቡር ሥጋው
ብዙ ተአምራት ይታዩ ነበርና የሃገሩ (የሳስዊር) ሰዎች
ሊወስዱት ፈለጉ:: ሳስዊር ማለት ቅዱሱ ተወልዶ
ያደገባት: ወላጆቹ (አብርሃምና ሣራ ይባላሉ) የኖሩባት ቦታ
ናት:: የምትገኘውም ግብጽ ውስጥ ነው::
+በምድረ ግብጽ: በተለይም በገዳመ አስቄጥስ የአባ
መቃርስን ያህል ክቡርና ተወዳጅ የለምና የሃገሩ ሰዎች
የነበራቸው አማራጭ መስረቅ ነበር:: መሥረቅ ኃጢአት
ቢሆንም እነሱ ግን ስለ ፍቅር: አንድም ለበረከት (በረከትን
ሲሹ) አደረጉት::
+ወደ ሳስዊርም ወስደው: ቤተ ክርስቲያን በቅዱሱ ስም
አንጸው በክብር አኖሩት:: በዚያም ለ160 ዓመታት
ተቀመጠ:: በ7ኛው መቶ ክ/ዘመን ግን ተንባላት
(እስላሞች) መጥተው ቤተ ክርስቲያኑን አጠቁ:: በዚህ
ጊዜም ሕዝቡ የጻድቁን አጽም ይዘው ሸሹ:: በሌላ ቦታም
እንደ ገና በስሙ ቤተ ክርስቲያን አንጸው በዚያ አኖሩት::
+በእነዚህ ሁሉ ዓመታት የመንፈሳዊ አባታቸውን ሥጋ
ያጡት የገዳመ አስቄጥስ ቅዱሳን ያዝኑ ይጸልዩ ነበርና
ልመናቸውን ፈጣሪ ሰማ:: አባ ሚካኤል ሊቀ ዻዻሳት
በነበረበት ዘመን: ከገዳሙ ለሌላ ተግባር ወደ ሳስዊር
የተላኩ አበው ከታላቁ አባት ቤተ ክርስቲያን ሲደርሱ
ሰውነታቸው ታወከ::
+ይዘው ለመውሰድ ሙከራ ቢያደርጉ ሊሳካላቸው
አልቻለም:: ምክንያቱም የቤተ ክርስቲያኑ ጠባቂ ደወል
ደውሎ ሕዝቡን ሁሉ ጠርቶ ነበርና:: ሕዝቡና ሃገረ ገዢው
የሆነውን ሲሰሙ "የቅዱሱን ሥጋ ብትነኩ እንገላቹሃለን"
ብለው ሰይፍ: ዱላ: ጐመድና ጦር ይዘው መጡባቸው::
+መነኮሳቱ ግን ባዷቸውን ሊመለሱ አልፈቀዱምና ሌሊቱን
ሲያለቅሱና ሲጸልዩ አደሩ:: መንፈቀ ሌሊት በሆነ ጊዜም
ታላቁ መቃርስ በግርማ ወርዶ መኮንኑን "ለምን ወደ ልጆቼ
እንዳልሔድ ትከለክለኛለህ?" ሲል በራዕይ ተቆጣው::
በዚህ ምክንያትም መነኮሳቱ የቅዱሱን ሥጋ ተቀበሉ::
+ሕዝቡም በዝማሬና በማሕኅሌት: ከብዙ እንባ ጋር
ሸኟቸው:: ታላቁ መቃሬ ወደ ገዳሙ ሲደርስም ታላቅ ደስታ
ተደረገ:: ቅዱሳን ልጆቹ ከመንፈሳዊ አባታቸው ተባርከው
በክብር አኑረውታል::
=>አምላከ ቅዱሳን የታላቁ ቅዱስ መቃርስን ትሕትናውን:
ትእግስቱንና ቅንነቱን ያድለን:: በበረከቱም ይባርከን::
=>+"+ እግዚአብሔር ፍርድን ይወድዳልና::
ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና::
ለዘለዓለምም ይጠብቃቸዋል . . .
ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ::
በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ::
የጻድቅ አፍ ጥበብን ያስተምራል::
አንደበቱም ፍርድን ይናገራል::
የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው::
በእርምጃውም አይሰናከልም:: +"+ (መዝ. 36:28-31)
<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
✝ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together
https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━⊱✿⊰━━
Comments
Post a Comment