††† እንኳን አምላካችን እግዚአብሔር ከሥራው ሁሉ ላረፈባት የመጀመሪያዋ ዕለተ ሰንበትና ለቅዱስ ሕዝቅኤል ነቢይ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††
††† አምላካችን እግዚአብሔር በ6ቱ ቀናት 22ቱን ሥነ ፍጥረት ፈጥሮ በ7ኛዋ ዕለት ደክሞት ያይደለ ለእኛ ያስተምረንና ሰንበትን ይቀድስልን ዘንድ አረፈ::
ዕለተ ሰንበት ማለት አንዳንድ ልባቸውን ያሳወሩ ሰዎች እንደሚያወሩት የሥራ መፍቻ ቀን ሳትሆን:-
1.ከሥጋዊ ተግባራችን ታቅበን መንፈሳዊ ተግባራትን (6ቱ ቃላተ ወንጌልን) የምንፈጽምባት:
2.ለጊዜውም ቢሆን ጥቂት እርፍ ብለን አማናዊቷን ዕረፍተ መንግስተ ሰማያት የምናስብባት ዕለት ናት::
እንደ ቤተ ክርስቲያን ስርዓትም ለሰንበተ ክርስቲያን ቀዳሚውን ቦታ ሰጥተን ቀዳሚት ሰንበትንም እንደሚገባ ልንጠቀምባት ይገባል::
††† የሰንበት ጌታዋ: የምሕረትም አባቷ ጌታችን እግዚአብሔር ለዕረፍተ መንግስቱ የተዘጋጀን ያድርገን::
††† ቅዱስ ሕዝቅኤል ነቢይ †††
††† ነቢዩ ቅዱስ ሕዝቅኤል የነበረው ቅ/ል/ክርስቶስ በ500 ዓመት አካባቢ ሲሆን የጼዋዌ (ምርኮ) አባልም ነበር:: እሥራኤልና ይሁዳ ወደ ባቢሎን በምርኮ ሲወርዱ አብሮ ወርዷል:: ቅዱሱ ከ4ቱ ዐበይት ነቢያት አንዱ ሲሆን ሐረገ ትንቢቱም በ48 ምዕራፎች የተዋቀረ ነው::
በዘመኑ ሁሉ ቅድስናን ያዘወተረው ቅዱሱ ከደግነቱ የተነሳ በጸጋማይ (ግራ) ጐኑ ተኝቶ ቢጸልይ 600 ሙታንን አስነስቷል:: ወገኖቹ እሥራኤልንም ያለ መታከት አስተምሯል:: ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዚህች ዕለት ታላቁን ራዕይ እንዳየ ታስተምራለች:: ነቢዩ በፈለገ ኮቦር ካያቸው ምሥጢራት እነዚህን ያነሷል:-
1.እግዚአብሔርን በዘባነ ኪሩብ ተቀምጦ ሲሠለስና ሲቀደስ አይቶታል:: የኪሩቤልንም ገጸ መልክእ በጉልህ ተመልክቷል:: (ሕዝ. 1:1)
2.በመጨረሻው ቀን ትንሳኤ ሙታን : ትንሳኤ ዘጉባኤ እንደሚደረግም ተመልክቷል:: (ሕዝ. 31:1)
3.እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ኆኅት ኅትምት/ኆኅተ ምሥራቅ (የምሥራቅ ደጅ) ሁና አይቷታል::
ይሕ የምሥራቅ ደጅ (በር) ለዘለዓለም እንደታተመ ይኖራል:: የኃያላን ጌታ ሳይከፍት ገብቶ: ሳይከፍት ወጥቷልና:: (ሕዝ. 44:1)
በመጨረሻ ሕይወቱ እሥራኤል ለክፋት አይቦዝኑምና ነቢዩን አሰቃይተው ገድለውታል::
††† ከነቢዩ በረከት አምላኩ ያድለን::
††† ሚያዝያ 5 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት
1.እግዚአብሔር ሰንበትን ቀደሰ
2.ቅዱስ ሕዝቅኤል ነቢይ
3.ቅዱስ ዲዮስቆሮስ (ክፉ ላለመናገር ድንጋይ ጐርሶ የኖረ አባት)
4.ቅድስት ታኦድራ
5.ቅዱስ አርሳኒ
6.ቅዱስ ያሬድ ካህን (ልደቱ)
††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዼጥሮስ ሊቀ ሐዋርያት
2.ቅዱስ ዻውሎስ ሐዋርያ
3.አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጻድቅ (አባ ገብረ ሕይወት)
4.ቅዱስ ዮሐኒ ኢትዮዽያዊ
5.ቅዱስ አሞኒ ዘናሒሶ
††† "እግዚአብሔር ሰንበቴን ስለሚጠብቁ: ደስ የሚያሰኘኝንም ነገር ስለሚመርጡ: ቃል ኪዳኔንም ስለሚይዙ ጃንደረቦች እንዲህ ይላልና:- በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ:: የማይጠፋም የዘለዓለም ስም እሰጣቸዋለሁ::" †††
(ኢሳ. 56:4-5)
††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
✝ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together
https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━⊱✿⊰━━
Comments
Post a Comment