✞✝✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✝✞
✝ጥር 22 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
+✝+ አባ እንጦንስ +✝+
=>በቤተ ክርስቲያን አስተምሕሮ "ታላቁ / ዓቢይ / THE GREAT" የሚል ስም የሚሰጣቸው አባቶች የተለዩ ናቸው:: አንድም እጅግ ብዙ ትሩፋቶችን የሠሩ ናቸው:: በሌላ በኩል ደግሞ በተመሳሳይ ስም ከሚጠሩ ሌሎች ቅዱሳን እንለይበታለን::
+ገዳማዊ ሕይወት ጥንቱ ብሉይ ኪዳን ነው:: በቀዳሚነትም በደብር ቅዱስ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ደቂቀ ሴት እንደ ጀመሩት ይታመናል:: ሕይወቱ በጐላ: በተረዳ መንገድ የታየው ግን በታላቁ ጻድቅ ሄኖክ: ከዚያም በቅዱሱ ካህን መልከ ጼዴቅ አማካኝነት ነው::
+ቀጥሎም እነ ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ: እነ ኤልሳዕ ደቀ መዝሙሩ ኑረውበታል:: በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ሙሉ ሕይወቱን በገዳም (በበርሃ) ያሳለፈው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ቅድሚያውን ይይዛል::
+ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና መድኃኒታችን ክርስቶስ በገዳመ ቆረንቶስ ለ40 ቀናት በትሕርምት ኑሮ ገዳማዊ ሕይወትን ቀድሷል: አስተምሯል:: በዘመነ ስብከቱም ያድርባት የነበረችው የደብረ ዘይቷ በዓቱ (ኤሌዎን ዋሻ) በራሷ ለዚህ ሕይወት ትልቅ ማሳያ ናት::
+ከጌታ ዕርገት በኋላም ክርስቲያኖቹ የዓለም ሁካታ ሲሰለቻቸው: አንድም በንጹሕና በተሸከፈ ልቡና ለፈጣሪያቸው መገዛትን ሲሹ ከከተማ ወጣ እያሉ ይኖሩ እንደ ነበር የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ:: አኗኗራቸውም በቡድንም: በነጠላም ሊሆን ይችላል::
+ዋናው ነገር ግን በጾምና በጸሎት መትጋታቸው ነው:: ይሕም ሲያያዝ እስከ 3ኛው መቶ ክ/ዘመን ደረሰ:: በዚህ ዘመን ግን አባ ዻውሊ የሚባል አንድ ንጹሕ ክርስቲያን ይሕንን ሕይወት ወደ ሌላ ደረጃ ከፍ አደረገው:: ለ80 ዓመታት ሰው ሳያይ ተጋድሎ 'የባሕታውያን አባት' ተባለ:: ደንብ ያለው ተባሕትዎም ጀመረ::
+ይህ ከሆነ ከ20 ዓመታት በኋላ ደግሞ አባ እንጦንስ የሚባሉ ደግ ክርስቲያን ይህንን ገዳማዊ ሕይወት በሌላ መንገድ አጣፈጡት:: በቅዱስ ሚካኤል አመንኳሽነት ገዳማዊ ሕይወት በምንኩስና ተቃኘ:: ስለዚህም አባ እንጦንስ የመነኮሳት አባት ተባሉ::
+እርሳቸውም ሕይወቱን ለማስፋፋት ከተለያዩ አሕጉር ደቀ መዛሙርትን እየተቀበሉ አመንኩሰዋል:: ቅዱሳን የአባ እንጦንስ ልጆችም ወደየ ሃገራቸው ተመልሰው: ሕይወቱን በተግባር አሳይተው ገዳማዊነትን አስፋፍተዋል::
+"+ አባ እንጦንስ +"+
+አባ እንጦንስ የመነኮሳት ሁሉ አባታቸው: ለገዳማውያን ሁሉም ሞገሳቸው ናቸው:: እንዲያውም ብዙ ጊዜ "ኮከበ ገዳም: ማኅቶተ ገድል (የበርሃው ኮከብ: የተጋድሎ መብራት)" ተብለውም ይጠራሉ::
+ቤተ ክርስቲያን ለጀማሪዎች ትልቅ ትኩረት ትሰጣለች:: ለምሳሌ:- አባ ዻውሊን (የካቲት 2 የሚከበሩ) ለብሕትውና መሠረትን ስለ ጣሉ "አበ ባሕታውያን" ብላ ታከብራለች:: አባ እንጦንስን ደግሞ "አበ መነኮሳት (የመነኮሳት አባት): ቀዳሚሆሙ ለመነኮሳት (ለመነኮሳት ቀዳሚና ጀማሪ) ስትል ትጠራቸዋለች::
+አባ እንጦንስ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ለሚነሱ ቅዱሳን መነኮሳት ሁሉ መንገድን ይጠርጉ ዘንድ ብዙ መከራን በትዕግስትና በአኮቴት ተቀብለዋል:: ላለፉት 1,700 ዓመታት እንደ ሻማ እየቀለጡ ያበሩ አበው ቅዱሳን ሁሉ የአባ እንጦንስ ልጆች ናቸው::
+ከምጥ የከፋ የዲያብሎስ ፈተናን ተቀብለው ከመንፈሳዊ አብራካቸው ቅዱሳኑን ወልደዋል:: የመነኮሳት አለቃ የሆኑትን ታላቁን መቃርዮስን ጨምሮ በርካቶችን አመንኩሰው ለቅድስና አብቅተዋል::
+አባ እንጦንስ ግብጻዊ ሲሆኑ የተወለዱት አቅማን በምትባል ቦታ አካባቢ ነው:: ጊዜውም በ252 ዓ/ም ነው:: የተባረኩ ወላጆች ለቅዱሱ እንጦንስና አስከትለው ለወለዷት ሴት ልጃቸው አስቀድመው ፍቅረ ክርስቶስን: አስከትለውም ሃብት ንብረታቸውን አውርሰው ዐርፈዋል::
+በዚህ ጊዜ የአባ እንጦንስ እድሜ አፍላ ወጣትነት ላይ ነበር:: በልጅነት ጊዜአቸውም አባ እንጦንስን ሲስቁ: ሲጫወቱ: አልያም ሲቀልዱ አየሁ የሚል ሰው አልነበረም:: ፍጹም ቁም ነገረኛና ታዛዥ: በዚያ ላይም አስተዋይ ነበሩና ሙሉ ጊዜአቸውንም ከቅዱስ ቃሉ በመመገብ: በትምሕርትና በማስቀደስ ያሳልፉ ነበር::
+ዘወትርም ዜና ሐዋርያትን እያነበቡ በመንፈሳዊ ቅናት ይቃጠሉ ነበር:: በጊዜው የምናኔ ሕይወት ጐልቶ ባለ መገለጡ አባ እንጦንስ የሚያደርጉት ይጨንቃቸው ነበር:: ሲጸልዩም "አበው ሐዋርያት ይሕንን ክፉ ዓለም ንቃችሁ ጌታችሁን የተከተላችሁበት ጥበብ እንደ ምን ያለ ነው!" እያሉ ይደነቁ ነበር:: መሻታቸውን ያወቀ ጌታም ምሥጢርን ገለጠላቸው::
+አንድ ቀን በቅዳሴ ላይ ወንጌል ሲነበብ ካህኑ ስለ ምናኔ የሚጠቅሰውን ክፍል አነበበ:: ለአንድ ባለ ጠጋ ሕግጋትን ከነገረው በኋላ "ፍጹም ልትሆን ከወደድክስ ያለህን ሁሉ ሸጠህ ተከተለኝ" (ማር. 10:17) የሚለውን ጥቅስ ሲሰሙ ተገርመው "ጌታ ሆይ! ይህንን የተናገርኸው ለእኔ ነው" ሲሉ አሰቡ:: በቀጥታም ሃብታቸውን ለአካባቢው ሰው አካፍለው: እህታቸውን ከደናግል ማኅበር ደምረው እርሳቸው ወደ ዱር ሔዱ::
+ከዚህች ቀን ጀምረው አባ እንጦንስ ከ80 እስከ መቶ ለሚገመቱ ዓመታት ከአጋንንት ጋር በጦርነት ነበር የኖሩት::
በንጹሕ አምልኮታቸውና በቅድስናቸው የቀና ጠላት ሰይጣን በብዙ ጐዳና ፈተናቸው:: አቅም ቢያጥረው አራዊትን መስሎ ታገላቸው::
+በዚህ አልሳካ ቢለው የእሳት ሰንሰለትን አምጥቶ ገረፋቸው:: በሞትና በሕይወት መካከል ጥሏቸው ሔደ:: ወድቀው ያገነኟቸው ሰዎች ለዘመዶቻቸው ሰጥተዋቸው አገገሙ:: ልክ ሲነቁ ግን ፈጥነው ወደ በርሃ ተመለሱ::
+ሰይጣን በርሃው የቅዱሳን ማደሪያ እንዳይሆን ሰግቷልና ጨክኖ ታገላቸው:: ግን አልቻላቸውምና ተረታ:: አምላከ ኃያላን ክርስቶስ ከቅዱሱ ጋር ነበርና:: ከዚህ በኋላ ግን ጸጋው በዝቶላቸው ድውያንን የሚፈውሱና ሰይጣን የማይቀርባቸው ሰውሆኑ::
+በረዥም ዘመነ ቅድስናቸውም:-
1.ብዙ አርድእትን ከመላው ዓለም ሰብስበው: አስተምረው: ምናኔ ከግብጽ ማዶ በመላው ዓለም አስፋፉ::
2.በደመና እየተጫኑ ብዙ አሕጉራትንም እየዞሩ ሰበኩ:: በዚህም አሕዛብን ወደ እምነት: ኃጥአንን ወደ ንስሃ መለሱ::
3.ጊዜው ዘመነ ሰማዕታት ነበርና ወደ አደባባይ ሒደው ከሃዲዎችን ገሠጹ:: ማንም ደፍሮ ግን አልገደላቸውም::
+እነዚህንና ሌሎች ተግባራትን እየሠሩ በቅዱስ ሚካኤል እጅ መነኮሱ:: እርሳቸውም ብዙዎችን አመነኮሱ:: አርጅተው እንኳ ከተጋድሎ ያላረፉት አባታችን የጣመ ነገር ቀምሰው: ገላቸውን ታጥበው አያውቁም:: በ372 ዓ/ም በዚህች ቀን ሲያርፉም ዕድሜአቸው 120 ደርሶ ነበር::
+የአባ እንጦንስን በዓል ለማክበር የምትሹ ቤተ ክርስቲያናቸው ጎንደር ከተማ ከቀሃ ኢየሱስ በላይ ይገኛል::
<< ለአባታችን እንጦንዮስ / እንጦንስ / እንጦኒ ክብር
ይገባል:: >>
+" ቅዱስ ዑራኤል "+
+በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት ከ7ቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ የሆነው ቅዱስ ዑራኤል:-
1.ድንግል ማርያም በአካለ ሥጋ እያለች ወደ ሰማይ አሳርጉዋታል:: በሠረገላ ብርሃን ጭኖ: በክንፎቹም ተሸክሞ: አስቅድሞ ገነትን ቀጥሎም ሲዖልን አስጐብኝቷታል:: በዚህም ምክንያት እመ ብርሃን ስለ ኃጥአን የምታለቅስ: የምትለምንና የምትማልድ ሆናለች:: ለምናም አልቀረች የምሕረት ቃል ኪዳን ተቀብላለች::
2.ቅዱሱ መልአክ እመ ብርሃንን በስደቷ ጊዜ ወደ ኢትዮዽያ መርቶ አምጥቷታል:: በክንፉ ተሸክሞ: በ4 አቅጣጫ አዙሮ አሳይቶ አሥራት እንድትቀበል አድርጉዋል::
3.ጌታችን በተሰቀለ ጊዜ ደሙን በጽዋዕ አድርጐ በኢትዮዽያ ወንዞች ላይ አፍስሷል::
4.ለብዙ ቅዱሳን (አባ ጊዮርጊስን ጨምሮ) ጽዋዐ ልቡናን አጠጥቷል::
✞አምላከ ቅዱሳን ስለ ወዳጆቹ በጐ ምኞታችንን
ይፈጽምልን:: ከበረከታቸውም ያድለን::
✞ጥር 22 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አባ እንጦንስ (የመነኮሳት አባት-የበርሐው
ኮከብ /ልደቱና ዕረፍቱ)
2.ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላዕክት (ለተጠሙ ጽዋዓ
ልቡናን የሚያጠጣ: ምሥጢር ገላጭ መልዐክ)
3.ቅዱስ ሚናስ ኤዺስ ቆዾስ
✝ወርኀዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ዑራኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ
3.ቅዱስ ደቅስዮስ (የእመቤታችን ወዳጅ)
4.አባ እንጦንስ አበ መነኮሳት
5.አባ ዻውሊ የዋህ
++"+ እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ:: መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ:: ነፍሱን ሊያድን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል:: ስለ እኔ ግን ነፍሱን የሚያጠፋ ሁሉ ያገኛታል:: +"+ (ማቴ. 16:24)
✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞
✞ ወለወላዲቱ ድንግል ✞
✞ ወለመስቀሉ ክቡር አሜን ✞
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ::" /ማቴ ፫:፫/
ዝክረ ቅዱሳንን ተማሩ ብለን እንለምናችኋለን!!።
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together.https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━━━
Comments
Post a Comment