✝✞✝ እንኩዋን ለጻድቃን ቅዱሳን አቡነ ዘርዓ ቡሩክ እና 7ቱ ደቂቅ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✝✞✝
✝ አቡነ ዘርዓ ቡሩክ ✝
=>ሃገራችን ኢትዮዽያ:-
*ብሉይ ከሐዲስ ያልጐደለባት
*በክርስቶስና በድንግል እናቱ ኪደተ እግር የተቀደሰች
*የቅዱሳን መጠጊያ እና
*ብዙ ቅዱሳንን ከእቅፏ ያፈራች ስለ ሆነች የተባረከች ሃገር ትባላለች::
+ሁሉም የሃገራችን ክፍሎች ቅዱሳንን አፍርተዋል:: በምሥራቅም: በምዕራብም: በሰሜንም: በደቡብም ያሉ አካባቢዎች ሁሉ የቅዱሳን ቤቶች ናቸው:: ቅዱሳንን በብዛት ካፈሩ አካባቢዎች አንዱ ደግሞ ምድረ ጐጃም ነው::
+በጐጃም አካባቢ ከተነሱ ቅዱሳን ደግሞ አንዱና ስመ ጥሩ ጻድቅ አቡነ ዘርዓ ቡሩክ ናቸው:: አቡነ ዘርዓ ቡሩክ በብዙ ጐዳና የተለዩ አባት ናቸው:: ለመጥቀስ ያህል እንኩዋ:-
1.በታሪክ ዓለምን ከበው የያዙ 2ቱ ግሩማን አራዊት (ብሔሞትና ሌዋታንን) ጥርስ ቆጥረው: ብዙ ምሥጢራትንም ተመልክተው ተመልሰዋል:: (በነገራችሁ ላይ ይህ ጉዳይ ዛሬም ድረስ ሳይንሱ በብዙ ድካም ያልደረሰበት ነው)
2.ጻድቁ በልደታቸው ጊዜ ዓይነ ስውራንን አብርተዋል:: ለራሳቸው ግን ይህን የግፍ ዓለም ላለማየት ጸልየው ዓይናቸው እንዲጠፋ አድርገዋል::
3.መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚል ቅዱስ ኢያሱ በገባኦን ፀሐይን አቁሟል:: ዘርዓ ቡሩክ ግን በጥበበ እግዚአብሔር ፀሐይን ለ5 ዓመት አቁመዋል::
4.ጻድቁ ከንጽሕናቸው ብዛት 12 ክንፍ (መንፈሳዊ ክንፍ) ተሰጥቷቸው ነበር:: ከዚህ በተረፈም በጾም: በጸሎት: በትርምትና በስብከተ ወንጌል ፍጹም ጽሙድ ነበሩ::
+ጻድቁ የተወለዱት በ16ኛው መቶ ክ/ዘመን እዚያው ጐጃም ውስጥ ሲሆን አባታቸው ደመ ክርስቶስ: እናታቸው ደግሞ ማርያም ሞገሳ ይባላሉ:: ወላጆች በልጅ እጦት ተማለው ይህን የተቀደሰ ፍሬ አገኙ:: "ጸጋ ኢየሱስ" ብለውታል:: ከኢየሱስ ክርስቶስ ተሰጥቷቸዋልና::
+ቀጥሎ የወለዱትንም "ተስፋ ኢየሱስ" ብለውታል:: ይህም የጻድቁ ታናሽ ወንድም ነው:: በሒደት ግን የጸጋ ኢየሱስ ስም በፈቃደ እግዚአብሔር ወደ ዘርዓ ቡሩክነት ተቀይሯል:: ጻድቁን ስመ ጥር ካደረጉዋቸው ሥራዎቻቸው መካከል በአፄ ሱስንዮስ ዘመን የሠሩት ቅድሚያውን ይወስዳል::
+ነገሩ እንዲህ ነው:: በ1598 ዓ/ም በኢትዮዽያ ላይ የነገሡት አፄ ሱስንዮስ ዼጥሮስ ፓኤዝ (ፔድሮ ፓኤዝ) ከሚባል ፈረንጅ መናፍቅ ጋር በፈጠሩት ወዳጅነት ሃይማኖታቸውን ለወጡ:: ካቶሊክ (ሮማዊ)ም ሆኑ::
+በሁዋላም አልፎንሱ ሜንዴዝ የሚሉት እሾህ መጥቶ ሁሉም የኢትዮዽያ ሕዝብ መናፍቅ እንዲሆን ከንጉሡ ጋር መከረ:: ለጊዜው በቤተ መንግስቱ አካባቢ የነበሩ መሣፍንት ተቀላቀሉ:: እየቆየ ግን ዜናው በመላ ሃገሪቱ ተሰማ::
+በተለይ በ1611 በተዋሕዶ አማኞችና በመናፍቁ ንጉሥ መካከል ነገሩ ተካሮ ዻዻሱ አቡነ ስምዖን ጠዳ ላይ መገደላቸው ተሰማ:: በዚህ ጊዜ ገበሬው ከእርሻው: ሴቷ ከማዕድ ቤት: ካህኑ ከመቅደሱ: ነጋዴው ከገበያው እየወጡ ስለ ቀናችው ሃይማኖት ደማቸውን አፈሰሱ::
+በበዓት የተወሰኑ በሺህ የሚቆጠሩ ቅዱሳንም ወጥተው ተሰየፉ:: በዚህ ጊዜም የግሺው አቡነ ዘርዓ ቡሩክ ዳዊታቸውን አንግበው ለሰማዕትነት ሔዱ:: ዓባይ ወንዝ ላይ ሲደርሱ ዳዊታቸውን ወደ ወንዙ ውስጥ ጣሉት::
+ተሻግረውም ከንጉሡ አደባባይ ደንቀዝ ደረሱ:: በጊዜውም ልክ እንደነ ፍቅርተ ክርስቶስና ወለተ ዼጥሮስ እርሳቸውም መከራ ደረሰባቸው:: ንጉሡም ሳይገደሉ እንዲታሠሩ አደረገ:: በጨለማ እስር ቤትም 5 ዓመታትን ሲያሳልፉ ትኩስ ምግብን ያመጡላቸው ነበር::
+እርሳቸው ግን ምግባቸው ሰማያዊ ነበርና አልነኩትም:: ከ5 ዓመት በሁዋላም ያ ሁሉ ምግብ በተአምራት በትኩስነቱ እየጨሰ ተገኝቷል:: ዘርዓ ቡሩክም ከእሥር ተፈትተዋል::
+እግዚአብሔርም በከሐዲው ንጉሥ ላይ ፈርዶ ፋሲል ነግሷል: ሃይማኖት ተመልሷል:: ጻድቁም በዓባይ ወንዝ ላይ የጣሉት ዳዊታቸውን ሳይርስ አግኝተውታል::
+ጐጃም ሲደርሱም ሰይጣን እርሳቸውን መስሎ ሲያስት ስላገኙት ወደ ጥልቁ አስጥመውታል:: በተረፈ ዘመናቸው አቡነ ዘርዓ ቡሩክ ብዙ ተጋድለው ጥር 13 ቀን ዐርፈዋል:: ታኅሳስ 13 ቀን ልደታቸው ነው::
<< ድንቅ ሠሪ አባት ናቸውና ዛሬም በግሺ ብዙ ተአምራት ይደረጋሉ >>
+" ቅዱሳን 7ቱ ደቂቅ "+
=>እነዚህ 7 ቅዱሳን ከዘመነ ሰማዕታት እስከ ዘመነ ጻድቃን የተዘረጋ ታሪክ አላቸው:: 7ቱም ባልንጀሮች ሲሆኑ በ2ኛው መቶ ክ/ዘመን በኤፌሶን ተወልደው አድገዋል:: ክርስትናን ተምረውም በወጣትነታቸው የንጉሥ ጭፍሮች ሁነዋል:: የተቀጠሩትም የቤተ መንግስቱን ግምጃ ቤት ለመጠበቅ ነው::
+በሥራቸውም ሆነ በጠባያቸው ደጐች ነበሩና ንጉሡ ዳኬዎስም: ሕዝቡም ይወዷቸው ነበር:: እነርሱ ግን በጉብዝና ወራት ፈጣሪን ማሰብን መርጠው በፍቅር: በጸሎትና በምጽዋት ይተጉ ነበር:: ከጥቂት ዓመታት በሁዋላ ግን ጭንቅ መከራ መጣ::
+ንጉሡ ዳኬዎስ ክርስትናውን ትቶ ጣዖት አምላኪ ሆነ:: አዋጅም አስነገረ:: አዋጁም "ክርስቶስን ያልካደ: ለጣዖትም ያልሰገደ: ሃብት ንብረቱ ለዘረፋ: እጅ እግሩ ለእስር: ደረቱ ለጦር: አንገቱ ለሰይፍ: ቤቱም ለእሳት ይሰጣል" የሚል ነበር:: በዚህ ምክንያት ብዙ ክርስቲያኖች ተሰደዱ::
+የበርካቶቹም ደማቸው ፈሰሰ:: ኤፌሶን የግፍና የአመጻ ከተማ ሆነች:: የመከራ ጽዋው ጊዜውን ጠብቆ ወደ 7ቱ ወጣቶች ዘንድ ደረሰ:: ንጉሡ እነሱንም አስጠርቶ "ለጣዖት ስገዱ" አላቸው:: እነርሱ ግን የአምላካቸውን ፍቅር በዋዛ የሚቀይሩ አልነበሩምና "እንቢ" አሉት::
+ንጉሡ ምንም ክፉና አውሬ ቢሆንም ይወዳቸዋል:: ሊገድላቸው አልፈለገምና አሳሰራቸው:: ከቀናት በሁዋላ አስጠርቶ ሊያታልላቸው ሞከረ:: ግን አልተሳካለትም:: በዚያ ወራት ጦርነት ይበዛ ነበርና ግዛት ለማስፋትም ቢሉ ለማስገበር ዳኬዎስ ወጣ::
+ከመውጣቱ በፊት ግን 7ቱን አስጠርቶ "አሁን ከእስር ፈትቻቹሃለሁ:: ከጦርነት እስክመለስ ከልባችሁ ጋር ምከሩ:: ካልሆነ ሞት ይጠብቃቹሃል" ብሏቸው ነበር የወጣው:: ቅዱሳኑ ንጉሡ እንደ ወጣ ተቀምጠው መከሩ:: ውሳኔንም አስተላለፉ::
+ዓለምን ንቀው: ሃብት ንብረታቸውን መጽውተው: ትንሽ ሳንቲም ብቻም ይዘው በድብቅ ወጡ:: አንድ ወታደር (በጐች አሉት) ይከተላቸው ነበርና የት እንደ ገቡ ተመለከተ:: ቅዱሳኑ ዘወትር በመዓልትና በሌሊት በበዓታቸው ውስጥ ይተጉ ነበር:: ከእነሱም አንዱ በተራ እየወጣ ቂጣ ይገዛ ነበር::
+አንድ ቀን ግን ከእነሱ አንዱ ራት ሊገዛ ሲወጣ ንጉሡ መመለሱን ሰማ:: ወደ በዓቱ ተመልሶ ለወንድሞቹ ነገራቸው:: ከዚያች ቀን በሁዋላ 7ቱም አልወጡም:: በዓታቸውን ዘግተው ሲጸልዩ ደክሟቸው ተኙ:: ከዚያች ቀን በሁዋላ ግን አልነቁም::
+ያ የበጐች ባለቤት (ወታደር) ለብዙ ቀናት አለመውጣታቸውን ሲመለከት "ሙተዋል" ብሎ አዘነ:: በድብቅ ክርስቶስን ያመልከው ነበርና:: እርሱ የቅዱሳኑን ተጋድሎ በድንጋይ ሰሌዳ ላይ ጽፎ ወደ በዓታቸው ውስጥ ጣለው::
+ትልቅ ድንጋይም አምጥቶ ገጠመው:: እነዚህ ቅዱሳን ተኝተዋልና አልነቁም:: ቀናት: ወራት: ዓመታት ተዋልደው ለ372 ዓመት ተኙ:: አንድ ቀን አንድ እረኛ ለሥራ ፈልጐት ድንጋዩን ፈነቀለው:: በዚህ ጊዜ ቅዱሳኑ ነቁ::
+በወቅቱ መልካቸው የወጣት ነው:: እድሜአቸው ግን 400 ሊሞላ ትንሽ ቀርቶት ነበር:: ልክ እንደ አቤሜሌክ ብዙ መተኛታቸው አልታወቃቸውምና ከመካከላቸው አንዱ የራት ዳቦ ሊገዛ ቢወጣ ግራ ተጋባ:: ኤፌሶን የማያውቃት ሌላ ሃገር ሆነችበት:: ከተማዋ ዘምናለች::+በየቦታው አብያተ ክርስቲያናት: ቅዱስ መስቀልም በየአደባባዩ ተተክለዋል:: ነገሩ ግር ቢለው አንዱን ከመንገድ ጠርቶ "ወንድሜ! ይህቺ ከተማ ኤፌሶን አይደለችምን?" አለው:: እርሱም "አዎ ናት" ብሎት አለፈ::
+ችግሩ ግን "ራት ልግዛ" ብሎ ወደ ገበያ ሲሔድ: እርሱ የያዘው ገንዘብ የዳኬዎስ ስም የተጻፈበት መሆኑ የፈጠረው ነበር:: በነጋዴዎቹ "የተደበቀ የጥንት ገንዘብ አግኝተሃል" በሚል ተከሶም ወደ ንጉሡ ቴዎዶስዮስ ዘንድ ቀረበ:: (ትንሹ ቴዎዶስዮስ ነው:: የነገሠውም በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው)
+በክርክሩ መካከል ቅዱሱ የእሱንና የወንድሞቹን ነገር ሲናገር ንጉሡም: ሊቀ ዻዻሱም (አባ ቴዎድሮስ ይባላል) ተገረሙ:: አብረው ከከተማ ወጥተው ሔደው: 7ቱንም ሲጸልዩ አገኟቸው:: ፊታቸውም እንደ እግረ ፀሐይ ያበራ ነበር:: 7ቱም ለ7 ቀናት በኤፌሶን ድውያንን እየፈወሱ: ሰውን ሁሉ እየባረኩ ቆዩ::
+ይህ ሁሉ የተደረገው በወቅቱ "ትንሳኤ ሙታን የለም" የሚሉ መናፍቃን ተነስተው ብዙ ሰው ክዶ ነበርና ለእነሱ ምሥክር ሊሆንባቸው ነው:: በርካቶችም በዚህ ድንቅ ተስበው ወደ ሃየማኖት ተመልሰዋል:: 7ቱ ቅዱሳን ግን በ7ኛው ቀን በክብር ዐርፈዋል:: ንጉሡ 7 የወርቅ ሣጥኖች ቀብሯቸዋል::
=>አምላከ አበው ቅዱሳን በመጽናታቸው ያጽናን:: ከበረከታቸውም ያድለን::
ጥር 13 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.አቡነ ዘርዓ ቡሩክ ኢትዮዽያዊ (እረፍታቸው)
2.ሰባቱ ደቂቅ ቅዱሳን (ከኤፌሶን)
3.ቅዱስ አባ ነካሮ
4.ቅዱስ ቃሮስ
=>ወርሐዊ በዓላት
1.እግዚአብሔር አብ
2.ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላእክት
3.ቅዱስ አስከናፍር
4."13 ግኁሳን ጻድቃን"
5.ቅዱስ አርሳንዮስ ጠቢብ
6.ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት
=>+"+ በተቀደሰ አሳሳም እርስ በርሳችሁ ሰላምታ ተሰጣጡ:: ቅዱሳን ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላቹሃል:: የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ: የእግዚአብሔርም ፍቅር: የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን:: አሜን:: +"+ (2ቆሮ. 13:12)
✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞
✞ ወለወላዲቱ ድንግል ✞
✞ ወለመስቀሉ ክቡር አሜን ✞
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ::" /ማቴ ፫:፫/
ዝክረ ቅዱሳንን ተማሩ ብለን እንለምናችኋለን!!።
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together.https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━━━
Comments
Post a Comment