✝✝✝ እንኳን ለእመቤታችን ንጽሕት ድንግል ወላዲተ አምላክ ማርያም ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። ✝✝✝
†✝† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †✝†
†✝† ዕረፍተ ድንግል †✝†
††† እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅድመ ዓለም በአምላክ ልቡና ታስባ ትኖር ነበር:: ከነገር ሁሉ በፊት እግዚአብሔር እናቱን ያውቃት ነበር::
*ዓለም ተፈጥሮ: አዳምና ሔዋን ስተው: መርገመ ሥጋና መርገመ ነፍስ አግኝቷቸው: በኃዘን ንስሃ ቢገቡ "እትወለድ እም ወለተ ወለትከ - ከ5 ቀን ተኩል (5500 ዘመናት) በሁዋላ ካንተ ባሕርይ ከምትገኝ ንጽሕት ዘር ተወልጄ አድንሃለሁ" ብሎ ተስፋ ድኅነት ሰጠው::
*ከአዳም አንስቶ ለ5500 ዓመታት አበው: ነቢያትና ካህናት ስለ ድንግል ማርያም ብዙ ሐረገ ትንቢቶችን ተናገሩ:: መዳኛቸውን ሱባኤ ቆጠሩላት:: ምሳሌም መሰሉላት:: ከሩቅ ዘመን ሁነውም ሊያገኟት እየተመኙ እጅ ነሷት::
"እምርሑቅሰ ርእይዋ: ወተአምኅዋ" እንዲል::
††† የድንግል ማርያም ሐረገ ትውልድ
*ከአዳም በሴት
*ከያሬድ በሔኖክ
*ከኖኅ በሴም
*ከአብርሃም በይስሐቅ
*ከያዕቆብ በይሁዳና በሌዊ
*ከይሁዳ በእሴይ: በዳዊት: በሰሎሞንና በሕዝቅያስ ወርዳ ከኢያቄም ትደርሳለች::
*ከሌዊ ደግሞ በአሮን: አልዓዛር: ፊንሐስ: ቴክታና በጥሪቃ አድርጋ ከሐና ትደርሳለች::
*አባታችን አዳም ከገነት በወጣ በ5,485 ዓመት ወላዲተ አምላክ ንጽሕና ሳይጐድልባት: ኃጢአት ሳያገኛት: ጥንተ አብሶ ሳይደርስባት ከደጋጉ ኢያቄም ወሐና ትወለዳለች:: (ኢሳ. 1:9, መኃ. 4:7) "ወኢረኩሰት በምንትኒ እምዘፈጠራ" እንዳለ:: (ቅዱስ ቴዎዶጦስ ዘዕንቆራ)
ከዚያም ከእናት ከአባቷ ቤት ለ3 ዓመታት ቆይታ ወደ ቤተ መቅደስ ትገባለች:: በቤተ መቅደስም ለ12 ዓመታት ፈጣሪዋን እግዚአብሔርን እያመሰገነችና እያገለገለች: እርሷን ደግሞ መላእክተ ብርሃን እያገለገሏት: ሕብስት ሰማያዊ ጽዋዕ ሰማያዊ እየመገቧት ኑራለች:: 15 ዓመት በሞላት ጊዜ አረጋዊ ዮሴፍ ያገለግላት ዘንድ ወደ ቤቱ ወሰዳት::
*በዚያም መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ዜና ድኅነትን ነግሯት አካላዊ ቃልን በማሕጸንዋ ጸነሰችው:: ነደ እሳትን ተሸከመችው: ቻለችው:: "ጾርኪ ዘኢይትጸወር: ወአግመርኪ ዘኢይትገመር" እንዳለ:: (ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ለብሐዊ)
*ወልደ እግዚአብሔርን ለ9 ወራት ከ5 ቀናት ጸንሳ: እንበለ ተፈትሆ (በድንግልና) ወለደችው:: (ኢሳ. 7:14) "ኢየሱስ" ብላ ስም አውጥታለት በገሊላ ለ2 ዓመታት ቆዩ::
*አርዌ ሔሮድስ እገድላለሁ ብሎ በተነሳበት ወቅትም ልጇን አዝላ በረሃብ እና በጥም: በላበትና በድካም: በዕንባና በኃዘን ለ3 ዓመታት ከ6 ወራት ከገሊላ እስከ ኢትዮዽያ ተሰዳለች:: ልጇ ጌታችን 5 ዓመት ከ6 ወር ሲሆነው: ለድንግል ደግሞ 21 ዓመት ከ3 ወር ሲሆናት ወደ ናዝሬት ተመለሱ::
*በናዝሬትም ለ24 ዓመታት ከ6 ወራት ልጇን ክርስቶስን እያሳደገች: ነዳያንን እያሰበች ኑራለች:: እርሷ 45 ዓመት ልጇ 30 ዓመት ሲሆናቸው ጌታችን ተጠምቆ በጉባኤ ትምሕርት: ተአምራት ጀመረ:: ለ3 ዓመታት ከ3 ወራትም ከዋለበት እየዋለች: ካደረበትም እያደረች ትምሕርቱን ሰማች::
*የማዳን ቀኑ ደርሶ ልጇ ክርስቶስ ሲሰቀልም የመጨረሻውን ፍጹም ሐዘን አስተናገደች:: አንጀቷ በኃዘን ተቃጠለ:: በነፍሷም ሰይፍ አለፈ:: (ሉቃ. 2:35) ጌታ በተነሳ ጊዜም ከፍጥረት ሁሉ ቀድማ ትንሳኤውን አየች:: ለ40 ቀናትም ሳትለይ ከልጇ ጋር ቆየች::
*ከልጇ ዕርገት በሁዋላ በጽርሐ ጽዮን ሐዋርያትን ሰብስባ ለጸጋ መንፈስ ቅዱስ አበቃች:: በጽርሐ ጽዮንም ከአደራ ልጇ ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ለ15 ዓመታት ኖረች:: በእነዚህ ዓመታት ሥራ ሳትፈታ ስለ ኃጥአን ስትማልድ: ቃል ኪዳንን ከልጇ ስትቀበል: ሐዋርያትን ስታጽናና: ምሥጢርም ስትገልጽላቸው ኑራለች::
*ዕድሜዋ 64 በደረሰ ጊዜ ጥር 21 ቀን መድኃኒታችን አእላፍ ቅዱሳንን አስከትሎ መጣ:: ኢየሩሳሌምን ጨነቃት:: አካባቢውም በፈውስ ተሞላ:: በዓለም ላይም በጐ መዓዛ ወረደ:: እመ ብርሃን ለፍጡር ከዚያ በፊት ባልተደረገ: ለዘለዓለምም ለማንም በማይደረግ ሞገስ: ክብርና ተአምራት ዐረፈች:: ሞቷ ብዙዎችን አስደንቁአል::
"ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ::
ሞታ ለማርያም የአጽብ ለኩሉ::" እንዲል::
*ከዚህ በሁዋላ መላእክት እየዘመሩ: ሐዋርያቱም እያለቀሱ ወደ ጌቴሴማኒ: በአጐበር ሥጋዋን ጋርደው ወሰዱ:: ይሕንን ሊቃውንት:-
"ሐራ ሰማይ ብዙኃን እለ አልቦሙ ሐሳበ::
እንዘ ይዜምሩ ቅድሜኪ ወመንገለ ድኅሬኪ ካዕበ::
ማርያም ሞትኪ ይመስል ከብካበ" ሲሉ ይገልጡታል::
*በወቅቱ ግን አይሁድ በክፋት ሥጋዋን እናቃጥል ስላሉ ቅዱስ ገብርኤል (ጠባቂ መልአክ ነው) እነርሱን ቀጥቶ: እርሷን ከቅዱስ ዮሐንስ ጋር ወስዶ በዕጸ ሕይወት ሥር አኑሯታል:: በዚያም መላእክት እያመሰገኗት ለ205 ቀናት ቆይታለች::
*ቅዱስ ዮሐንስ መጥቶ ለሐዋርያቱ ክብረ ድንግልን ቢነግራቸው በጐ ቅንአት ቀንተው በነሐሴ 1 ሱባኤ ጀመሩ:: 2ኛው ሱባኤ ሲጠናቀቅም ጌታ የድንግል ማርያምን ንጹሕ ሥጋ ሰጣቸው:: እየዘመሩም በጌቴሴማኒ ቀብረዋታል::
*በ3ኛው ቀን (ነሐሴ 16) እንደ ልጇ ባለ ትንሳኤ ተነስታ ዐርጋለች:: ትንሳኤዋንና ዕርገቷንም ደጉ ሐዋርያ ቅዱስ ቶማስ አይቶ: መግነዟን ተቀብሏል:: ሐዋርያቱም መግነዟን ለበረከት ተካፍለው: እንደ ገና በዓመቱ ነሐሴ 1 ቀን ሱባኤ ገቡ::
*ለ2 ሳምንታት ቆይተው: ሁሉንም ወደ ሰማይ አወጣቸው:: በፍጡር አንደበት ተከናውኖ የማይነገር ተድላ: ደስታና ምሥጢርንም አዩ:: ጌታ ራሱ ቀድሶ ሁሉንም አቆረባቸው:: የበዓሉን ቃል ኪዳን ሰምተው: ከድንግል ተባርከው ወደ ደብረ ዘይት ተመልሰዋል::
††† ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን: ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሳን ለምኚልን:: አእምሮውን: ለብዎውን: ጥበቡን በልቡናችን ሳይብን አሳድሪብን:: †††
††† ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሊቅ †††
††† ለዚህ ቅዱስ አባት ብጹዕ መባል ተገብቷል:: ክቡር: ምስጉን: ንዑድ ሰው ነውና:: በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን በቂሣርያ ቀዸዶቅያ የተወለደው ቅዱሱ ሰው ለደሴተ ኑሲስ ብርሃኗ ነው:: አባቱ ኤስድሮስ: እናቱ ኤሚሊያ: ወንድሞቹ ቅዱሳን "ባስልዮስ: ዼጥሮስ: መክርዮስና መካርዮስ" ይባላሉ::
የተቀደሰች እህቱም ማቅሪና ትባላለች:: ከዚህ የተባረከ ቤተሰብ ለቅድስና ያልበቃ አንድም ሰው የለም:: ሊቁ ቅዱስ ጐርጐርዮስም ከማር በጣፈጠ ዜና ሕይወቱ እንደ ተጻፈው:-
*በልጅነቱ ቅዱሳት መጻሕፍትን ተምሯል::
*ሥጋውያን ጠቢባንን ያሳፍር ዘንድም የግሪክን ፍልሥፍና በልኩ ተምሯል::
*በታላቅ ወንድሙ ቅዱስ ባስልዮስ መሪነት ገዳማዊ ሕይወትን ተምሯል::
*በመንኖ ጥሪት ተመስግኗል::
*ተገብቶትም በኑሲስ ደሴት ላይ ዻዻስ ሆኗል::
*እርሱ ሲሔድ በከተማው የነበሩ ክርስቲያኖች 11 ብቻ የነበሩ ሲሆን እርሱ ሲያርፍ ክርስቶስን የማያመልኩ ሰዎች ቁጥር 11 ብቻ ነበር::
*ቅዱስ ጐርጐርዮስ ፍጹም ሊቅ ነበርና ከቁጥር የበዙ ድርሳናትን ደርሷል::
*ታላቁን ጉባኤ ቁስጥንጥንያን (በ381 ዓ/ም) መርቷል:: ብዙ መናፍቃንንም አሳፍሯል::
ከንጽሕናው የተነሳ መላእክት ያቅፉት: እመ ብርሃንም ትገለጥለት ነበር:: ለ33 ዓመታት እንደ ሐዋርያት ኑሮ በዚህ ቀን ድንግል ጠራችው:: ቀድሶ አቁርቦ: ሕዝቡን አሰናብቶ: የቤተ መቅደሱን ምሰሶ እንደ ተደገፈ ዐርፎ ተገኝቷል:: በዝማሬና በፍቅር ቀብረውታል::
††† ቅድስት ኢላርያ †††
††† "ኢላርያ" ማለት "ፍሥሕት (ደስ የተሰኘች)" እንደ ማለት ነው:: ከተባረኩ ቅዱሳት አንስት ትልቁን ሥፍራ ትይዛለች:: ማን እንደ እርሷ!
ቅድስት ኢላርያ ማለት:-
*የታላቁ ንጉሠ ነገሠት: የደጉ ዘይኑን (Emperor Zenon) የበክር ልጅ
*በ6ኛው መቶ ክ/ዘመን የተወለደች
*ትምሕርተ ሃይማኖትን: ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የተማረች
*ምድራዊ ንግሥናን ንቃ ፍቅረ ክርስቶስን የመረጠች
*የአባቷን ቤተ መንግስት ትታ ከሮም ግዛት ወደ ግብጽ (ገዳመ አስቄጥስ) የወረደች:
*ስሟን ከኢላርያ ወደ ኢላርዮን ቀይራ በወንዶች ገዳም የመነኮሰች
*ራሷን በፍጹም ገድል ቀጥቅጣ ከወንዶቹ በላይ በሞገስ ከፍ ከፍ ያለች
*ትንሽ እህቷን ጨምሮ በርካቶችን የፈወሰች
*በእርሷ ምክንያት ለግብጽና በመላው ዓለም ለሚገኙ ገዳማት ብዙ ቸርነት በዘይኑን የተደረገላት ታላቅ እናት ናት::
ቅድስት ኢላርያ ማንም ሴት መሆኗን ሳያውቅባት: አባ ኢላርዮን እንደ ተባለች በዚህች ቀን ዐርፋለች:: ቤተ ክርስቲያንም እነሆ ላለፉት 1,400 ዓመታት: ቅድስቲቱንና የተባረከ አባቷን ዘይኑንን: ስለ በጐነታቸውና ውለታቸው ታስባቸዋለች::
††† የእመቤታችን ድንግል ማርያም ጣዕሟ: ፍቅሯ: ጸጋዋና በረከቷ ይደርብን:: †††
††† ጥር 21 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ በዓላት
1.በዓለ አስተርዕዮ ማርያም (እመቤታችን ከእረፍቱዋ በሁዋላ ለደቀ መዛሙርት በዚሁ ቀን ተገልጣ ነበር)
2.ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ (ታላቅ ሊቅና ጻድቅ)
3.ቅድስት ኢላርያ እናታችን (የዘይኑን ንጉሥ ልጅ)
4.ቅዱስ ኤርምያስ ነቢይ
5.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ
6.ቅዱስ ኒቆላዎስ ሰማዕት
7.አባ ፊቅጦር
††† ወርሐዊ በዓላት
1.አባ ምዕመነ ድንግል
2.አባ አምደ ሥላሴ
3.አባ አሮን ሶርያዊ
4.አባ መርትያኖስ
5.አበው ጎርጎርዮሳት
††† "ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን:: እግሮቹ በሚቆሙበት ሥፍራ እንሰግዳለን::
አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነስ::
አንተና የመቅደስህ ታቦት::
ካህናቶችህ ጽድቅን ይልበሱ::
ቅዱሳንህም ደስ ይበላቸው::
ስለ ባሪያህ ስለ ዳዊት. . ."
(መዝ. 131:7)
††† "ወዳጄ ሆይ! ተነሺ::
ውበቴ ሆይ! ነዪ::
በዓለት: በንቃቃትና በገደል መሸሸጊያ ያለሽ ርግብ ሆይ!
ቃልሽ መልካም: ውበትሽም ያማረ ነውና:
መልክሽን አሳዪኝ::
ድምጽሽንም አሰሚኝ::"
(መኃ. 2:13)
✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞
✞ ወለወላዲቱ ድንግል ✞
✞ ወለመስቀሉ ክቡር አሜን ✞
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ::" /ማቴ ፫:፫/
ዝክረ ቅዱሳንን ተማሩ ብለን እንለምናችኋለን!!።
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together.https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━━━
Comments
Post a Comment