†✝† በስመ አብ: ወወልድ: ወመንፈስ ቅዱስ: አሐዱ አምላክ †✝†
†✝† ግንቦት 16 †✝†
†✝† ቅዱስ ዮሐንስ ፍቁረ እግዚእ †✝†
=>አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌሉ እንደነገረን በመንግስተ ሰማያት ታላቁ ሰው ወንጌላዊው ዮሐንስ ነው:: ቅዱሱ ሐዋርያ ከዘብዴዎስና ከማርያም ባውፍልያ ተወልዶ: በገሊላ አካባቢ አድጐ: ገና በወጣትነቱ መድኃኔ ዓለምን ተከትሎታል::
+ቅዱስ ዮሐንስ ከሐዋርያት ቀድሞ ጌታን ከመከተሉ ባሻገር በምንም ምክንያት ከጐኑ አይጠፋም ነበር:: ስለ ንጽሕናውና በጐ የፍቅር ሕሊናው ሕጻን ሳለ በወንድሞቹ ሐዋርያት ዘንድ ሞገሱ ከፍ ያለ ነው:: ጌታችንን እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ በመከተሉ ድንግል እመቤታችንን ተቀብሏል::
+ከእርሷ ጋር ለ15 ዓመታት ቢቀመጥ መዝገበ ምሥጢር ሆነ:: ስንኩዋን ከሰው ልጆች ይቅርና ከልዑላኑ መላዕክትም ማዕረጉ ከፍ አለ:: ሰው ቢበቃ መላእክትን ሊያይ ይቻለዋል:: ቅዱስ ዮሐንስን ግን መላእክት ሊያዩት ይከብዳቸዋል:: ከፍጥረት ወገን ከእመ ብርሃን ቀጥሎ ክቡር እርሱ ነው::
+ቅዱስ ዮሐንስ በታናሽ እስያ ለ7ቱ አብያተ ክርስቲያናት መስበኩ ይታሰባል:: ቅዱሱ ከጌታችን ዕርገት በሁዋላ ለ70 ዓመታት በዚህ ምድር ሲኖር አብዛኛውን ጊዜውን ያሳለፈው በኤፌሶን አካባቢ ነው:: ሕዝቡን ወደ ክርስትና ለማምጣት በአፍም በመጽሐፍም ደክሟል::
+3 መልዕክታት: ራዕዩንና ወንጌልን ጽፎላቸዋል:: ሕይወትን ስለ ሰበከላቸው በፈንታው ብዙ አሰቃይተውታል:: ከእሳት እስከ ስለት: እስከ መጋዝም በስተእርጅና ደርሶበታል:: እርሱ ግን በትእግስቱ ገንዘብ አድርጉዋቸዋል::
††† ቅዱሱ በኤፌሶን †††
=>ይህቺ ኤፌሶን የሚሏት ሃገር መገኛዋ በቀድሞው ታናሽ እስያ (አሁን ቱርክ አካባቢ) ሲሆን ብዙ ሐዋርያት አስተምረውባታል:: ያም ሆኖ የሚፈለገውን ያህል ለውጥ ያመጣች አልነበረችምና ቅዱስ ዮሐንስ ሊሔድ ተነሳ::
+ከደቀ መዛሙርቱ መካከልም ቅዱስ አብሮኮሮስን (ከ72ቱ አርድእት አንዱ ነው) አስከትሎ እየጸለዩ በመርከብ ላይ ተሳፈሩ:: ሐዋርያት አበው መከረኞች ናቸውና ማዕበል ተነሳባቸው:: በጥቂት አፍታም መርከባቸው በማዕበሉ ተበታተነች::
+ቅዱስ አብሮኮሮስ በስባሪ ላይ ተሳፍሮ ወደ አንዲት ደሴት ደረሰ:: ከንጹሑ መምሕሩ ቅዱስ ዮሐንስ ተለይቷልና አለቀሰ:: ፍቁረ እግዚእ ግን ያለ ምግብና ውሃ ማዕበለ ባሕር እያማታው ለ40 ቀናት ቆየ::
+እርሱ በፈጣሪው ፍቅር የተመሰጠ ነበርና አለመመገቡ አልጐዳውም:: በ40ኛው ቀን ግን ደቀ መዝሙሩ ወዳለበት ደሴት ማዕበሉ አደረሰው:: 2ቱ ቅዱሳን ተፈላልገው ተገናኙ:: እጅግም ደስ ብሏቸው ፈጣሪን አመሰገኑ::
+አምላካቸው ወደዚህች ደሴት ያመጣቸው በጥበቡ ነውና ሲዘዋወሩ 2 ነገርን አስተዋሉ::
1ኛ የደሴቷ ሁሉም ነዋሪ የሚያመልኩት ጣዖትን ነው::
2ኛ አብዛኞቹ የቤተ መንግስት ውላጆች ናቸው:: ሮምና የሚሏት አንዲት ሴት ደግሞ እነዚህን ሁሉ እየመገበች ታስተዳድራለች::
+ቅዱሳኑ በቦታው በቀጥታ ትምሕርተ ወንጌልን ቢናገሩ እንደ ማይቀበሏቸው ስለ ተረዱ ሌላ ፈሊጥን አሰቡ:: እንዳሰቡትም ወደ እመቤት ሮምና ቤት ሒደው በባርነት ተቀጠሩ::
+ለእርሷም "ድሮ የአባትሽ ባሮች የነበርን ሰዎች ነን" ስላሏት 2ቱን ቅዱሳን እሳት አንዳጅና ገንዳ አጣቢ አደረገቻቸው:: ለሰማይ ለምድሩ የከበዱ እነዚህ ቅዱሳን የካዱትን ይመልሱ ዘንድ በባርነት ግፍን ተቀበሉ:: የመከር (የማሳመኛ) ጊዜ ሲደርስም አንዳች አጋጣሚ ተፈጠረ::
+ቅዱሳኑ ዮሐንስና አብሮኮሮስ ወደ መታጠቢያ ቤቱ ሲገቡ ሰይጣን በውስጥ ኖሮ ደንግጧልና እወጣለሁ ብሎ ሲሮጥ የንጉሡን ልጅ ረግጦ ገደለው:: ሮምናና የአካባቢው ሰዎች ከበው ሲላቀሱ ቅዱሳኑ ቀረቡ::
+ሮምና ግን በቁጣ "ልትሣለቁ ነው የመጣችሁ?" በሚል ቅዱስ ዮሐንስን በጥፊ መታችው:: መላእክት እንኩዋ ቀና ብለው ሊያዩት የሚከብዳቸው ሐዋርያ ይህንን ታገሰ:: በጥፊ ወደ መታችው ሴት ቀረብ ብሎም "አትዘኚ! ልጁ ይነሳል" አላትና ጸለየ::
+ወደ ሞተውም ቀረብ ብሎ በጌታችን ስም አስነሳው:: በዚህ ጊዜም ሮምናን ጨምሮ በሥፍራው የነበሩ ሰዎች ለቅዱስ ዮሐንስ ሰገዱ:: እርሱ ግን ሁሉንም አስነስቶ ትምሕርተ ሃይማኖትን: ፍቅረ ክርስቶስን ሰበከላቸው::
+በስመ ሥላሴ አጥምቆ: ካህናትን ሹሞ: ቤተ ክርስቲያንም አንጾላቸው ወጥቷል:: በሁዋላም ለሮምናና ለደሴቷ ሰዎች ክታብ (መልዕክትን) ጽፎላቸዋል:: ይህች መልዕክት ዛሬ 2ኛዋ የዮሐንስ መልዕክት ተብላ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትታወቃለች::
+ቅዱስ ዮሐንስ ቀጥሎ የተጉዋዘው ወደ ኤፌሶን ነው:: በዚህች ከተማ የምትመለክ አርጤምስ (አርጢሞስ) የሚሏት ጣዖት ነበረች:: አርጤምስ ማለት መልክ የነበራት ትዕቢተኛ ሴት ስትሆን አስማተኛ ባሏ ነው እንድትመለክ ያደረጋት::
+ቅዱስ ዻውሎስ ብዙ ምዕመናን ከእርሷ እንዲርቁ ማድረግ ችሏል:: ጨርሶ ያጠፋት ግን ቅዱስ ዮሐንስ ነው:: በቦታውም ብዙ ግፍ ደርሶበት: በርካታ ተአምራትን አድርጉዋል:: ቤተ ጣዖቱንም በተአምራት አፍርሶታል::
††† የፍቅር ሐዋርያ †††
=>ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ዮሐንስን 'የፍቅር ሐዋርያ' ትለዋለች:: ለ70 ዘመናት በቆየ ስብከቱ ስለ ፍቅር ብዙ አስተምሯል:: ፍቅርንም በተግባር አስተምሯል:: በየደቂቃውም "ደቂቅየ ተፋቀሩ በበይናቲክሙ - ልጆቼ ሆይ! እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ" እያለ ይሰብክ ነበር::
+በተለይ ደግሞ ከፈጣሪው ክርስቶስ ጋር የነበረው ፍቅር ፍጹም የተለየ ነበር:: በዚህ ምክንያትም ጌታ ባረገ ጊዜ እንዲህ ብሎታል:- "ለፍጡር ከሚገለጥ ምሥጢር ከአንተ የምሠውረው የለኝም" ብሎታል::
+ቀጥሎም በንጹሕ አፉ ስሞታል:: ሊቁ:-
"ሰላም ለአፉከ ለዮሐንስ ዘሰዓሞ:
ንጽሐ ኅሊናሁ ወልቡ ለዐይነ ፍትወትከ ሶበ አደሞ" እንዳለው:: (መልክዐ ኢየሱስ)
=>ቅዱስ ዮሐንስ ከእመቤታችንም ጋር ልዩ ፍቅር ነበረው:: እርሷ እንደ ልጇ ስትወደው: እርሱ ደግሞ እንደ እናቱ ልቡ እስኪነድ ድረስ ይወዳት ነበር:: እስከ እግረ መስቀሉ ድረስ ተከትሎ ያገኛት እመቤቱ ናትና::
+ከዚያ ሁሉ ጸጋና ማዕረግ የመድረሱ ምሥጢርም ድንግል ናት:: ለ15 ዓመታት በጽላሎተ ረድኤቷ (በረዳትነቷ ጥላ) ተደግፎ አብሯት ሲኖር ብዙ ተምሯል:: ከመላእክትም በላይ ከብሯል:: ከንጽሕናዋ በረከትም ተካፍሏል::
+ስለ ድንግል ማርያምም "ነገረ ማርያም" የሚል ድርሰት ሲኖረው "የሰኔ ጐልጐታንም" የጻፈው እርሱ ነው::
+ድንግል ባረፈችበት ቀንም ልክ እንደ ልጇ ክርስቶስ እርሷም ስማው: ታቅፋው ዐርፋለች:: ሊቃውንቱ ለዚህ አይደል በንጹሕ ከንፈሮቿ መሳምን (መባረክን) ሲሹ:-
"በከመ ሰዓምኪ ርዕሰ ዮሐንስ ቀዳሚ:
ስዒሞትየ ማርያም ድግሚ" ያሉት::
+ታላቁ ቅዱስ ሐዋርያ ዕድሜው 90 ዓመት በሆነው ጊዜ ተሰውሯል:: ከዚያ አስቀድሞም የዓለምን ፍጻሜ ተመልክቷል:: ዛሬ ያለበትን የየሚያውቅ ቸር ፈጣሪው ነው::
††† ይሕች ዕለት ለሐዋርያው ቅዳሴ ቤቱ ናት:: †††
=>እናት ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ዮሐንስን ስትጠራው እንዲሕ ነው:-
*ወንጌላዊ
*ሐዋርያ
*ሰማዕት ዘእንበለ ደም
*አቡቀለምሲስ (ምሥጢራትን ያየ)
*ታኦሎጐስ (ነባቤ መለኮት)
*ወልደ ነጐድጉዋድ
*ደቀ መለኮት ወምሥጢር
*ፍቁረ እግዚእ
*ርዕሰ ደናግል (የደናግል አለቃ)
*ቁጹረ ገጽ
*ዘረፈቀ ውስተ ሕጽኑ ለኢየሱስ (ከጌታ ጎን የሚቀመጥ)
*ንስር ሠራሪ
*ልዑለ ስብከት
*ምድራዊው መልዐክ
*ዓምደ ብርሐን
*ሐዋርያ ትንቢት
*ቀርነ ቤተ ክርስቲያን
*ኮከበ ከዋክብት
=>በቅዱስ ዮሐንስ ላይ ያደረ የእመቤታችን ድንግል ማርያምና የአንድ ልጇ ፍቅር በእኛም ላይ ይደር::
=>ቅዱስ ዮሐንስን የወደደ ጌታ በፍቅሩ ይጠግነን:: ከእናቱ ፍቅር አድርሶ በሐዋርያው በረከት ያስጊጠን::
=>ግንቦት 16 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ (ስብከቱና ቅዳሴ ቤቱ)
2.ቅዱስ ኢያሱ ሲራክ ነቢይና ጠቢብ (መጽሐፈ ሲራክን የጻፈ)
3.ቅድስት እናታችን ዐስበ ሚካኤል (ኢትዮዽያዊት)
=>ወርኀዊ በዓላት
1.ኪዳነ ምሕረት (የሰባቱ ኪዳናት ማሕተም)
2.ቅድስት ኤልሳቤጥ (የመጥምቁ ዮሐንስ እናት)
3.ቅዱስ ገብረ ማርያም ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮዽያ (የቅ/ላሊበላ ወንድም)
4.ቅዱስ አኖሬዎስ ንጉሥ ጻድቅ
5.አባ አቡናፍር ገዳማዊ
6.አባ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ
7.አባ ዳንኤል ጻድቅ
=>+"+ በጌታ ኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ: የእናቱም እህት: የቀለዮዻም ሚስት ማርያም: መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር:: ጌታ ኢየሱስም እናቱን: ይወደው የነበረውንም ደቀ መዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን 'አንቺ ሆይ! እነሆ ልጅሽ' አላት:: ከዚህ በሁዋላ ደቀ መዝሙሩን 'እናትህ እነሁዋት' አለው:: ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት:: +"+ (ዮሐ. 19:25)
✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞
✞ ወለወላዲቱ ድንግል ✞
✞ ወለመስቀሉ ክቡር አሜን ✞
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ::" /ማቴ
ዝክረ ቅዱሳንን ተማሩ ብለን እንለምናችኋለን!!።
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together.https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━━━
Comments
Post a Comment