✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞
✞✞✞ እንኳን ለአባቶቻችን ቅዱሳን 12ቱ ደቂቀ ነቢያት ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞
✞✞✞ 12ቱ ቅዱሳን ደቂቀ ነቢያት ✞✞✞
=>ነቢይ ማለት ከእግዚብሔር ተመርጦ ኃላፍያትን (አልፎ የተሠወረውን): መጻዕያትን (ለወደፊቱ የሚደረገውን) የሚያውቁ ሰዎች ሲሆኑ ሕዝቡን እንዲመሩ: እንዲገስጹም ይላካሉ:: ሕይወታቸውም በቅድስና የተለበጠ ነው:: ነቢያትን በቁጥር መግለጽ ከባድ ቢሆንም ቤተ ክርስቲያን እንድንረዳቸው እንዲህ ትከፍላቸዋለች::
=>በኩረ ነቢያት_አዳም
=>ሊቀ ነቢያት_ሙሴ
=>ርዕሰ ነቢያት_ኤልያስ
=>ልበ አምላክ_ዳዊት
=>15ቱ ነቢያት (ከአዳም ጀምሮ እስከ ሳሙኤል)
=>4ቱ ዐበይት ነቢያት (ኢሳይያስ: ኤርምያስ: ሕዝቅኤልና ዳንኤል)
=>12ቱ ደቂቀ ነቢያት ደግሞ ከሆሴዕ እስከ ሚልክያስ ያሉት ናቸው::
+በዚህች ቀን ታዲያ 12ቱ ቅዱሳን ደቂቀ ነቢያት በአንድነት ይታሠባሉ:: እነዚህም:-
1.ቅዱስ ሆሴዕ (ኦዝያ)
2.ቅዱስ አሞጽ
3.ቅዱስ ሚክያስ
4.ቅዱስ ኢዩኤል
5.ቅዱስ አብድዩ
6.ቅዱስ ዮናስ
7.ቅዱስ ናሆም
8.ቅዱስ እንባቆም
9.ቅዱስ ሶፎንያስ
10.ቅዱስ ሐጌ
11.ቅዱስ ዘካርያስ እና
12.ቅዱስ ሚልክያስ ናቸው::
+ቅዱሳኑ ደቂቀ ነቢያት የተባሉት
1.የነቢያት ልጆች በመሆናቸው
2.የጻፏቸው ሐረገ ትንቢቶች በንጽጽር ከዐበይቱ (ከነኢሳይያስ) ስለሚያንስ ነው::
+በምግባር: በትሩፋት: በአገልግሎት ግን ያው ናቸው:: ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እሊህን ነቢያት "እለ አውኀዙ ተነብዮ በእንተ ስመ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ" ይሏቸዋል:: ( ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መውረድ: መወለድና የማዳን ሥራ የትንቢት ጐርፍን ያፈሰሱ እንደ ማለት ነው :: )
+ቅዱሳኑ ከክርስቶስ የማዳን ሥራ ባሻገር ዓለማችን ላይ ከነበሩበት ዘመን እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሊደረጉ ያላቸውን ነገሮችም ተናግረዋል:: የነበሩበት ዘመን በአማካኝ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ከ900 እስከ 500 ነው:: በትንቢት ደረጃም እንደነ ሆሴዕና ዘካርያስ 14 ምዕራፎችን: እንደነ አብድዩም አንዲት ምዕራፍ ብቻም የጻፉ አሉ::
+በሕይወታቸው ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ያሻቸው ናቸውና በየጊዜው ከእግዚአብሔር ጋር እየተነጋገሩ የእርሱን ድምጽ ለእሥራኤል (አንዳንዴም ለአሕዛብ) ያደርሱ ነበር:: ፊት አይተው የማያዳሉ ናቸውና ሕዝቡንም ሆነ ነገሥታቱን ስለ ኃጢአታቸው ይገሰጹ ነበር:: በዚህም ምክንያት ከነገሥታቱና ከሕዝቡ አለቆች መከራ ደርሶባቸዋል:: አልፎም ያለ አበሳቸው ሕዝቡ በኃጢአቱ ሲማረክ አብረውት ወርደዋል::
+በመጨረሻ ሕይወታቸውም አንዳንዶቹን ክፉዎች ሲገድሏቸው አንዳንዶቹ ደግሞ በመልካም ሽምግልና ዐርፈዋል:: ዛሬ ነቢያት ከእነርሱ ባሕርይ በተገኘችና ብዙ ትንቢትን በተናገሩላት በእመቤታችን ምክንያት ክርስቶስ ድኅነትን ፈጽሞላቸው በተድላ ገነት ይኖራሉ:: ስለ እኛም ይማልዳሉ::
=>" ናጥሪ እንከ ትሕትና ዘምስለ ንጽሕና"
(እንግዲህ እንደ ነቢያት ትሕትናን ከንጽሕና ጋር ገንዘብ እናድርግ)
"እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር: ወተናጸሩ ገጸ በገጽ"
(ነቢያት መንፈስን ንጹሕ በማድረግ እግዚአብሔርን አይተውታልና: ፊት ለፊትም ተያይተዋልና)
/ቅዳሴ ማርያም/
=>ከአባቶቻችን ቅዱሳን ነቢያት በረከት ይክፈለን::
=>ሐምሌ 4 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1."12ቱ" ቅዱሳን ደቂቀ ነቢያት
2.ቅዱስ ሶፎንያስ ነቢይ (ዕረፍቱ)
3.ቅዱሳን ሰማዕታት አቡቂርና ዮሐንስ (ቅዳሴ ቤታቸው)
=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጉዋድ /ወንጌላዊው/
2.ቅዱስ እንድርያስ ሐዋርያ
3.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
4.ቅዱስ ዮሐንስ ዘሐራቅሊ /ሰማዕት/
=>+"+ ለእናንተም ስለሚሰጠው ጸጋ ትንቢት የተናገሩት ነቢያት ስለዚህ መዳን ተግተው እየፈለጉ መረመሩት:: በእነርሱም የነበረ የክርስቶስ መንፈስ ስለ ክርስቶስ መከራ ከእርሱም በሁዋላ ስለሚመጣው ክብር አስቀድሞ እየመሠከረ በምን ወይም እንዴት ባለ ዘመን እንዳመለከተ ይመረምሩ ነበር:: +"+ (1ዼጥ. 1:10)
<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ::" /ማቴ ፫:፫/
ዝክረ ቅዱሳንን ተማሩ ብለን እንለምናችኋለን!!
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
✝ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together
https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━
Comments
Post a Comment