"" ✝በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ::አሜን:: ""✝
+*✝" ቅዱስ ያዕቆብ ዘእልበረዲ (እል-በረዳይ) ✝"*+
(St. Jacob baradaeus)
(በተለይ በሃገራችን የተዘነጋ የሚመስለው የምሥራቅ ኮከብ -ኮከበ ጽባሕ)
=>"ያዕቆብ" ለሚል ስም ትርጉምን የሰጡ አበው በ2 መንገድያትቱታል::
1.አኃዜ ሰኮና:: ነገሩ ከወልደ ይስሐቅ ወርብቃው ርዕሰ አበው ያዕቆብ ጋር የተያያዘ ቢሆንም አበው ግን ለትህትና ይተረጉሙታል::
2.አእቃጺ / አሰናካይ:: ነገሩ ስድብ (አሉታዊ) ይምሰል እንጂ በዚህ ስም የተጠሩ አበው ሁሉ ለአጋንንትና ለመናፍቃን ትልቅ መሰናክል ሆነውባቸው ኑረዋልና አባባሉ ምስጋና እንጂ ነቀፋን አይወክልም::
+የ6ኛው መቶ ክ/ዘመን ምሥራቃዊ ኮከብ ቅዱስ ያዕቆብም ለመለካዊ መናፍቃንና ለተዋሕዶ ተገዳዳሪዎች ትልቅ መሰናክል ሆኖባቸዋል:: የቀናችውን ቀርነ ሃይማኖትንም አጽንቷል::
+ብዙ ጊዜ "ዘ"-እልበረዲ መባሉን ይዘው በ"ዘ" ምክንያት እልበረዲን እንደ ሃገር የቆጠሯት አልጠፉም:: በረከታቸው ይድረሰንና ትጉሑ ዻዻስ አቡነ ጐርጐርዮስ ካልዕ ግን ለዚሁ መላምት "የለም!" ባይ ናቸው::
+'የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ' በተሰኝ ተወዳጅ መጽሐፋቸው "እል-በረዲ" ማለትን በዓረብኛ ከሠጋር በቅሎ : ከሥሙር ሠረገላ ጋር አነጻጽረው አስቀምጠውታል:: ለምን ቢባል
- እንደ ሠረገላ በተፋጠነ አገልግሎቱ ወዳጅንም ጠላትንም አስደምሟልና::
+ቅዱስ ያዕቆብ የተወለደው በ6ኛው መቶ ክ/ዘመን መጀመሪያ (በ500 አካባቢ) ሲሆን ያረፈው ደግሞ በ578 ዓ/ም እንደሆነ ይታመናል:: ነገሩን ልብ ስንለው ቅዱስ ማኅሌታይ ያሬድን - ወዲህ በዘመን : ወዲያ ደግሞ በአገልግሎት ይመስለዋል:: እርግጥ ነው ለውለታው የሶርያ ቤተ ክርስቲያን "ያዕቆባዊት"
ስትባል የእኛዋስ ምናለ "ያሬዳዊት" ብትባል የሚል ቁጭትን ያመጣል::
+ጊዜው (5ኛውና 6ኛው መቶ ክ/ዘመን) ወዲህ ወርቃማ : ወዲያ ደግሞ ጨለማ ተብሎ ሊጠራ የሚችል ዘመን ነበር::
¤በብርሃንነቱ በተለይ በምሥራቁ ዓለም ያበሩ አበው እነ ያዕቆብ ዘስሩግ : ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ : ያዕቆብ ዘእልበረዲን የመሰሉ አበው ተገኝተውበታል:: ሲያልፍ ደግሞ ዘይኑንና አንስጣስዮስን የመሰሉ ደጋግ ነገሥታት በዘመኑ መነሳታቸውን እናስባለን::
+በተቃራኒው ግን ዘመኑ ቤተ ክርስቲያን ለ2 የተከፈለችበት : መለካውያን የነገሥታቱ ደጀን አላቸውና ተዋሕዶ ሃይማኖትን ከሥሯ ነቅሎ ለማጥፋት ብዙ የሞከሩበት ዘመን ነውና ጨለማነቱ ይጐላብናል::
+በእርግጥም ከመርቅያን እስከ ዮስጢኖስ ዳግማዊ ዘመን ድረስ ለ100 ዓመታት መለካውያኑ የልዮን ልጆች 2 ባሕርይ ማለትን ሊያሰፉ : ተዋሕዶንም ሊያጠፉ የከፈቱት ዘመቻ ሊሳካ ጫፍ የደረሰ ይመስል ነበር::
+ግን አማናዊት ቤቱን የማይተው አማናዊው ጌታ መድኃኔ ዓለም አርመኖቹን ስቦ በ490ዎቹ ወደ መንጋው ቀላቀለ:: በግብጽ አባ ቴዎዶስዮስን : በሶርያ ደግሞ ታላቁን ሊቅ ቅዱስ ሳዊሮስን አስነስቷል:: ከቤተ መንግስትም ስም አጠራሯ ያማረ ንግሥት ታኦድራን ማርኯል:: በእነዚህ ቅዱሳን ትጋት የለመለመችው ተዋሕዶ እንደ ቅዱስ ያዕቆብ ዘእልበረዲ ያለ
አርበኛን ግን ያገኘችው በጭንቅ ቀን ነበር::
+ሰው መሆን ሰው በጠፋባቸው ቀናት ነውና : በግብጽና በቁስጥንጥንያ በትምህርትና ምናኔ ላይ የነበረው ቅዱሱ ታጥቆ ለአገልግሎት የተሰለፈው በ530ዎቹ አካባቢ ነበር::
+ጊዜው ወዲህ አንበሳው ቅዱስ ሳዊሮስ ከሶርያ ወደ ግብጽ እንደተሰደደ ያረፈበት ነበር:: ወዲያ ደግሞ ሊቁ አባ ቴዎዶስዮስ የግብጹ ለግዞት የተዳረገበት ነበርና የተዋሕዶ ምዕመናን ያለ እረኛ ተቅበዘበዙ:: የቤተ
መንግስቱ ተጽዕኖ ደግሞ 2 ባሕርይ በማይሉት ላይ እሥራትና ግድያን ወደ ማወጅ ተሸጋግሯልና የምእመናን ቁጥር እጅጉን መመንመኑ ቀጠለ::
+ይህ ዕረፍት የነሳው ቅዱስ ያዕቆብ በበኩሉ ነገሩን በዝምታ ሊያልፈው አልወደደምና አገልግሎቱን አሰፋ:: ሌሊቱን በጸሎት ያድራል:: ቀን በቤተ ክርስቲያን አካባቢ ማስተማር ባይችል በየቦታው እየዞረ ያስተምር ነበር::
+ከትምህርቱ ጣዕምና ከመልእክቱ ሥምረት የተነሳም ምእመናን እንደገና ተነቃቁ:: እርሱም ከግብጽ እስከ ሶርያ : አልፎም እስከ ቁስጥንጥንያ ድረስ ያለ ዕረፍት ሲሰብክ 40 ዘመናትን አሳለፈ:: በተለይ አዲስ አማኞችን ያጠምቅ ዘንድ በእሥረኛው ቅዱስ
ቴዎዳስዮስ ኤዺስ ቆዾስነትን ተቀብሏል::
+የሶርያ (አንጾኪያ) የፕትርክና መንበሩ ክፍት ሆኖ እርሱን ቢጠብቀውም እርሱ ግን የዚህ (የስልጣን) ፈላጊ አልነበረምና ሌሎች እንዲሾሙበት አድርጉዋል::
+ቅዱስ ያዕቆብ በስብከት አገልግሎት ምሥራቁን ዓለም ሲያበራ የተባበሩት ደቀ መዛሙርት ቢኖሩም ያሳለፈው ድካምና መከራ ግን ተወዳዳሪ አልነበረውም:: በተለይ የወቅቱ የአንጾኪያ ኃያላን
መኩዋንንትና ሹመኛ መናፍቃን ብዙ አሳደውታል::
+እርሱ ግን በጥበብና በፈሊጥ እዚያው ደጃቸው ላይ የነበሩ ምዕመናንን በእረኝነት ጠብቁአል:: ለዚህ ሲባልም ራሱን እየቀያየረ የመሣፍንቱን አጥሮችና ቅጥሮች አልፏል:: ለቤተ ክርስቲያን ክብርም እንደ እብድ : እንደ ሴትም መስሎ የወንጌልን ዘር ዘርቷል::
¤ከብዙ ፈተናና አገልግሎት በሁዋላም በተወለደ በ78 ዓመቱ (በ578 ዓ/ም) ዐርፎ በክብር ተቀብሯል::
¤ትልቁ መታሰቢያው የሶርያ ቤተ ክርስቲያን "ያዕቆባዊት" : ምዕመኑ "ያዕቆባውያን" መባላቸው ሲሆን እኛ ደግሞ በአንገታችን ላይ እንድናስራት ባስተማረን ማዕተብ (ማኅተም) ዘወትር እናስበዋለን:: ለመጀመሪያ ጊዜ ማዕተብን በአንገት ላይ ስለ ማሰር ያስተማረ እርሱ ነውና::
¤የምሥራቁን ኮከብ እል-በረዲ ያዕቆብን በየዓመቱ ሰኔ 28 ቀን በነገረ ቅዱሳን መደበኛ ጉባኤ (ጐንደር) እናከብራለን:: ሶርያውያን ደግሞ July 31 (ሐምሌ 24 ቀን) ያከብሩታል::
=>+"+ እናንተ የምድር ጨው ናችሁ . . . እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ:: በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትም:: መብራትንም አብርተው በዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያናሩታል:: በቤት ላሉት ሁሉም ያበራል::
መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ:: +"+
(ማቴ. 5:13-16)
=>አምላከ ቅዱስ ያዕቆብ ተዋሕዶ ሃይማኖታችን ይጠብቅልን:: ከቅዱሱ በረከትም አይለየን::
<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር:: አሜን:: >>>
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ::" /ማቴ ፫:፫/
ዝክረ ቅዱሳንን ተማሩ ብለን እንለምናችኋለን!!
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
✝ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together
https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━
Comments
Post a Comment