✝††† እንኳን ለአባታችን ቅዱስ ብስንድዮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን✝። †††
††† ✝በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!✝ †††
††† ✝ቅዱስ ብስንድዮስ ጻድቅ✝ †††
††† ቅዱስ ብስንድዮስ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ድንቅ ሥራ ከሠሩት እንደ አንዱ ሆኖ ይዘከራል:: ቅዱሱ ግብጻዊ ሲሆን በልጅነቱ ወደ ትምሕርት ቤት ገብቶ ቅዱሳት መጻሕፍትን ተምሯል:: የሚገርመው የብሉይም ሆነ የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍትን በሙሉ ያጠናቸው በቃሉ ነበር::
በእርግጥ ይሕንን ማድረግ የቻሉ በርካታ የሃገራችን ሊቃውንት ዘንድሮም አሉ:: ልዩነቱ ግን ወዲህ ነው:: ቅዱስ ብስንድዮስ መጻሕፍቱን ያጠናቸው ለሕይወት እንጂ ለእውቀት አልነበረምና ሁሌም ነግቶ እስከ ሚመሽ እያንዳንዱን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እያጣጣመ ይጸልይ ነበር:: ይሕንን ሲያደርግ ደግሞባጭር ታጥቆ
ጫማውን አውልቆ:በባዶ ሆዱ ቁሞ ነው::
ታዲያ እያንዳንዱን የመጽሐፍ ክፍል ሲጸልይ ነቢይ ቢሆን ሐዋርያ ወደ እርሱ ይወርድለት ነበር:: ለምሳሌ ዘፍጥረትን ሲጸልይ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ይመጣና ከፊቱ ተቀምጦ ይሰማዋል:: ትንቢተ ኢሳይያስ ላይ ሲደርስ ኢሳይያስ: ወንጌለ ማቴዎስ ላይ ሲደርስ ቅዱስ ማቴዎስ ይመጡና ደስ እያላቸው ያደምጡት ነበር::
አንዱ ነቢይ: ወይ ሐዋርያ ሲወጣ ቅዱስ ብስንድዮስን ባርኮ ሌላኛውን ተክቶ ነው:: በዚህ ምክንያት የቅዱሱ ሕይወት በምድር እያለ ሰማያዊ ሆነ: ሰማንያ አንዱን አሥራው መጻሕፍት የጻፉ ቅዱሳንን ለማየት በቃ:
በእጆቻቸውም ተባረከ::
የቅዱስ ብስንድዮስ ቀጣይ የሕይወቱ ተግባር ብሕትውና ሆነ:: ዓለምንና ግሳንግሷን ትቶም ወደ በርሃ መነነ:: በአጽንዖ በዓት: ጾምና በጸሎት: በትሕርምትም ተጋደለ:: በየደረሰበት ቦታ ሁሉ እግዚአብሔር በእጆቹ ድንቅ ተአምር ይሠራ ነበር:: ብዙ ድውያንን ፈወሰ: አጋንንትንም ከአካባቢው አሳደደ::
በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት ግን ስዕለት ስላለበት ሴቶችን ላለማየት ይጠነቀቅ ነበር:: በሆድ ሕመም ትሰቃይ የነበረችና ጥሪቷን በመድኃኒት የጨረሰች አንዲት ሴት ስለ ቅዱሱ ዝና ትሰማለች:: ችግሩ ግን እርሱ ከውዳሴ ከንቱና ከሴት የሚርቅ ነውና እንዴት ብላ ታግኘው? አንድ ቀን ከበዓቱ አካባቢ ተደብቃ ውላ ሲመጣ የልብሶቹን ዘርፍ ለመንካት በእምነት አሰበች::
ልክ ከበዓቱ ሲዘልቅ ስሉጥ(ፈጣን) ነበርና ገና እንዳያት ሩጦ አመለጣት:: እንዳትከተለው ድውይ ናትና አልቻለችም:: አዝና ዝቅ ስትል ግን የረገጠውን ኮቲ ተመለከተች:: በፍጹም ልቧ: በእምነት "የጻድቁ አምላክ ማረኝ" ብላ ከአፈሩ ቆንጥራ በላች:: ደቂቃ አልቆየችም:: ፈጥና ከደዌዋ ዳነች:: እንደ እንቦሳ እየዘለለች ወደ ከተማ ሔዳ ተአምሩን ተናገረች::
ከእነዚህ ዘመናት በኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድ ቅፍጥ(Qift) በምትባል ሃገር ጵጵስናን (እረኝነትን) ተሹሟል:: ወደ ከተማ ሲገባ የቀደመ ተጋድሎውን ቸል አላለም:: ይልቁኑ ይተጋ ነበር እንጂ:: ከብቃት መዓርግ ደርሷልና ሲቀድስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በገሃድ ያየው: ሠራዊተ መላእክትም ይከቡት ነበር::
ሕዝቡ ሊቆርቡ ሲመጡ የእያንዳንዱ ኃጢአት በግንባራቸው ተጽፎ ይታየው ነበር:: የበቁትን እያቀበለ: ያልበቁትን እየመከረና ንስሐ እየሰጠ ይመልሳቸዋል:: እንዲሕ በጽድቅ: በሐዋርያዊ አገልግሎትና በንጽሕና ተመላልሶ ቅዱስ ብስንድዮስ በዚህች ቀን ዐርፏል::
ቅዱስ ብስንድዮስ ካረፈ በኋላ ደቀ መዝሙሩ ከመግነዙ ጥቂት ቆርጦ አስቀርቶ ብዙ ድውያንን ፈውሶበታል::
††† ቸር አምላክ ለአባቶቻችን የሰጠውን ጸጋ ለእኛ ለባሮቹም አይንሳን:: ከቅዱሱ በረከትም ያድለን::
††† ሐምሌ 13 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ብስንድዮስ ሊቅ ወጻድቅ
2.ቅዱስ አሞን ሰማዕት (ዘሃገረ ጡህ)
††† ወርኀዊ በዓላት
1.እግዚአብሔር አብ
2.ቅዱስ ሩፋኤል ሊቀ መላእክት
3.ዘጠና ዘጠኙ ነገደ መላእክት
4.ቅዱስ አስከናፍር
5.አሥራ ሦስቱ ግኁሳን አባቶች
6.ቅዱስ አርሳንዮስ ጠቢብ ገዳማዊ
7.አቡነ ዘርዐ ቡሩክ
††† "አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት ነገር ጸንተህ ኑር:: ከማን እንደተማርኸው ታውቃለህና:: ከሕፃንነትህም ጀምረህ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ሊሰጡህ የሚችሉትን ቅዱሳት መጻሕፍትን አውቀሃል:: የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጐ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምሕርትና ለተግሣጽ: ልብንም ለማቅናት: በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል::" †††
(፪ጢሞ. ፫፥፲፬)
††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ::" /ማቴ ፫:፫/
ዝክረ ቅዱሳንን ተማሩ ብለን እንለምናችኋለን!!
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
✝ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together
https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━
Comments
Post a Comment