††† ✝እንኳን ለታላቁ ነቢይ ቅዱስ ኢያሱ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። ✝†††
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††
††† ✝ቅዱስ ኢያሱ ነቢይ ወመስፍን ✝†††
††† ቅዱሱ የተወለደው በምድረ ግብፅ በባርነት ከነበሩ እሥራኤላውያን ሲሆን የቀደመ ስሙ "አውሴ" ይባላል:: ዘመኑ እግዚአብሔር ሕዝቡን ከ215 ዓመታት ባርነት ሊያወጣ የተቃረበበት ነውና ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከምድያም ሲመለስ ከመረጣቸው ተከታዮቹ ዋነኛው ኢያሱ ነበር:: እሥራኤል ከባርነት ሲወጡ ሙሴ 80 ዓመቱ : ኢያሱ ደግሞ 40 ዓመቱ ነበር::
ሕዝቡ አንገተ ደንዳና ነበርና ለ40 ቀን የታሠበላቸውን መንገድ 40 ዓመት እንዲሆን አደረጉት:: በዚህ ጊዜ ኢያሱ ከመምሕሩ ከሙሴና ከሕዝቡ አልተለየም::
አውሴን "ኢያሱ" ብሎ ስም የቀየረለት ሙሴ ሲሆን ይሔውም በፈቃደ እግዚአብሔር ነው:: ኢያሱ ማለት "መድኃኒት" ማለት ነው::
ለዚሕም ምክንያቶች አሉት:- ለጊዜው አማሌቃውያንን ድል ነስቶ ሕዝቡን አድኗል:: ምድረ ርስትን አውርሷል::
ለፍጻሜው ግን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ (ጥላ) እንዲሆን ነው::
ቅዱስ ኢያሱ በበርሃ ለ40 ዘመናት እግዚአብሔርን አምልኮታል:: ሊቀ ነቢያትን ታዝዞታል (አገልግሎታል):: እሥራኤልንም የጦር አለቃ ሆኖ ከአሕዛብ እጅ አድኗቸዋል::
በዚህም በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ዘንድ ሞገስን አግኝቷል:: ቅዱስ ሙሴ ደብረ ናባው ላይ ባረፈ ጊዜ ሕዝቡን : ካሕናቱንና ታቦተ ጽዮንን ተረከበ:: ይህን ጊዜ ዕድሜው 80 እየሆነ ነበር::
††† እግዚአብሔርም ኢያሱን "ከአንተ ጋር ነኝ" ብሎ በሕዝቡ ላይ ነቢይና መስፍን (አስተዳዳሪ) እንዲሆን ሾመው:: ቅዱሱም ሰላዮችን ልኮ አስገምግሞ:
¤ባሕረ ዮርዳኖስን ከፍሎ
¤ሕዝቡን አሻግሮ
¤የኢያሪኮን ቅጥር 7 ጊዜ ዙሮ
¤በኃይለ እግዚአብሔር አፍርሶ
¤የኢያሪኮን ነገሥታት አጥፍቶ ለሕዝቡ ምድረ ርስትን አወረሰ::
የገባዖን ሰዎች "አድነን" ብለው በላኩበት ጊዜ ነገሥተ አሞሬዎንን ይወጋ ዘንድ ኢያሱ ወጣ:: እነዚያን ግሩማን ነገሥታት በፈጣሪው ኃይል : በጦርና በተአምራት ድል ነስቶ የእግዚአብሔር ስሙ ከፍ ከፍ አለ:: በዚያች ዕለትም ለ12ቱ ነገደ እሥራኤል ርስትን ሲያካፍል ፀሐይን በገባዖን: ጨረቃን ደግሞ በቆላተ ኤሎም (በኤሎም ሸለቆ) አቆመ::
ሰባት አሕጉራተ ምስካይ (የመማጸኛ ከተሞችን) ለየ:: ነቢይና መስፍን ሆኖ ሕዝቡን ለ40 ዓመታት አገለገለ:: በመጨረሻም ለሕዝቡ አላቸው:-
"እኔና ቤቴ እግዚአብሔርን እናመልካለን:: (ኢያ. 24) እናንተስ?" አላቸው:: እነርሱም "እኛም እንዳንተ ነን" አሉት:: ለዚህም ምልክት ይሆን ዘንድ 3 ገጽ ያላት ሐውልትን በመካከላቸው አቆመ::
ይህችውም የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት:: ሐውልቷ 3 ገጽ እንዳላት እመቤታችንም በ3 ወገን (በነፍስ: በሥጋ: በልቡና) ድንግል ናት:: አንድም በ3 ወገን (ከኃልዮ: ከነቢብ: ከገቢር ኃጢአት) ንጽሕት ናት:: ለዚህም ነው አባ ሕርያቆስ
"ሐውልተ ስምዕ ዘኢያሱ" (የኢያሱ የምስክር ሐውልት አንቺ ነሽ) ሲል ያመሰገናት::
ታላቁ ነቢይ ኢያሱ ግን ከግብጽ በወጡ በ80 ዓመት: በተወለደ በ120 ዓመቱ (ጥሬው መጽሐፍ ቅዱስ በ110 ዓመቱ ይላል) በወገኖቹ መካከል ዐርፎ በያዕቆብ መቃብር ተቀበረ:: እሥራኤልም ለ30 ቀናት አለቀሱለት::
††† በወዳጁ በኢያሱ እጅ የአሕዛብን ቅጥር ያፈረሰ እግዚአብሔር የእኛንም የኃጢአታችንን ግንብ በወዳጆቹ ምልጃ ያፍርስልን:: ከቅዱሱ ነቢይም በረከትን ያሳትፈን::
††† ሰኔ 26 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ኢያሱ ነቢይ ወመስፍን
2.ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት (ቅዳሴ ቤቱ)
††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ
2.አቡነ ሐብተ ማርያም ጻድቅ
3.አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
4.ቅዱሳን ሰማዕታተ ናግራን
5.አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን
††† "አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩ:: በእውነተኛም ልብ አምልኩት . . . እግዚአብሔርን ማምለክ ክፉ መስሎ ቢታያችሁ . . . የአሞራውያንን አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ: የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ:: እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን::" †††
(ኢያሱ. 24:14)
††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ::" /ማቴ ፫:፫/
ዝክረ ቅዱሳንን ተማሩ ብለን እንለምናችኋለን!!
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
✝ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together
https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━
Comments
Post a Comment