፨፨፨በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን በዚችም ዕለት የእናታችን የቅድስት ዜና ማርያም አመታዊ የበዓሏ መታሰቢያ ነው፨፨፨
✝✞✝ ቅድስት ዜና ማርያም ✝✞✝
፨ በ11መቶ ክፍለ ዘመን በቅዱስ ላሊበላ ዘመነ መንግሥት ግንቦት 30 ቀን በጎጃም ክፍለ ሀገር ተወለደች። የአባቷ ስም ገብረ ክርስቶስ የእናቷ ስም አመተ ማርያም ይባላሉ። እጅግ እግዚአብሔርን የሚፈሩ፡ ቅዲስ ጋብቻቸውን በንጽሕና የሚጠብቁ፡ ለሰው የሚራሩ ደጋግ ሰዎች ነበሩ። እንዲህ ባለ መልካም ግብር ከኖሩ በኀላ በፈቃደ እግዚአብሔር 3 ወንዶች ልጆች እናት አንዲት ሴት ልጅ ወለዱ። ይህችም ሴት ልጅ ተወዳጇ እናታችን ቅድስት ዜና ማርያም ናት።
፨ ቅድስት ዜና ማርያም እናት እና አባቷን እያገለገለች፡ ፈርሐ እግዚአብሔን፡ በጎ ምግባርን ከወለጆቿ እየተማረች አደገች። ለአቅመ ሔዋንም በደረሰች ጊዜ ወላጆቿ ለአንድ ወጣት አጯት። ታላቅ ግብዣ ተደረጎ በተክሊል ተዳረች። በዚያው ወራት ግን የዜና ማርያም እናት አመተ ማርያም አምስተኛ ልጅ ወልዳ ተኝታ ሳለች በአካባቢው ሕማመ ብድብድ (ተላላፊ በሽታ) በመነሳቱ የዜና ማርያም እናት ታማ ነበር፡ በመጨረሻም ከዚህ ኃላፊ ዓለም አረፈች።
፨ ከዚህ በኋላ የታመመውን ወንድሟንና ሌሎቹንም በመያዝ ከተላላፊው በሽታ ለመትረፍ ሲሉ አካባቢውን ለቀው ወደ በረሃ ወጡ። በዚያም ሌሊት የዱር አራዊት መጥተው ከበቧቸው ሁሉንም ሊበሏቸው ሞከሩ እናታችን ቅድስት ዜና ማርያም ስመ እግዚአብሔርን ስትጠራ አራዊቱ ወደኋላ በመሸሽ ከአካባቢው ራቁ። እርሷም ከክፉ ሁሉ የጠበቃቸውን፡ ከአራዊት መበላት የሰወራቸውን እግዚአብሔርን አመሰገነች። በነጋም ጊዜ የታመመውን ወንድሟን እና ሌሎችን በመያዝ መንገድን ቀጠሉ አንዲት ባዶ ቤት አግኝተው ከእርሷ ተጠጉ። በፀሐዩ ንዳድና ታናሽ ወንድሟን በማዘል እጅግ ስለደከመች ከባድ እንቅልፍ ጣላት። ጠዋት ስትነሳ ግን የታመመው ወንድሟ ከአጠገቧ አላገኘችውም ሌሊት የዱር አራዊት በልተውታልና። አጅም አዘነች የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው ብላ አራሷን አፅናናች የወንድሟን ተረፈ ሥጋ አጠራቅሟ ቀበረች። በመቀጠልም በአካባቢው ካለ ገዳም ሔዳ ምንኩስናን ተቀበለች።
፨ ከዚህ በኋላ ባሏ አባቷን ሚስቴን አምጣ እያለ ስለጨቀጨቀው ከብዙ ልፋት እና ድካም ፈልጎ አገኛት ወደ ሀገሯም ወሰዳት። በዚያም ወደ ጉባኤ ቀርባ ለምን ወደ ገዳመ እንደሄደች እና ባሏን አንደከዳች ተጠየቀች። እርሷም እግዚአብሔር ከብዙ መከራ አድኖኛል እና እራሴን ለእግዚአብሔር ሰጥቻለሁ አለች። የጉባኤው ተሰብሳቢ በሏ ሀብቷን ወርሶ እንዲያሰናብታት ፈረዱ። እርሷም በዚህ ነገር በመስማማት የነበራትን ላም እና በሮች አስረከበች።
፨ ከዚህ በኋላ በአባቷ ቤት ለአንድ ዓመት ያህል በመቀመጥ የእናቷን ተዝካር አውጥታ ወደ ገዳሙ ተመለሰች በዛም ለጥቂት አመታት የተለያዩ ገድላትን ስትፈጽም ከቆየች በኋሏ ከነፍስ አባቷ ባሕታዊ አባ ገብረ መስቀል ጋር ወደ ጎንደር ሀገረ ስብከት ልዩ ስሙ እንፍራንዝ (ጣራ ገዳም) አካባቢ ዋሻ እንድርያስ በተባለው ለ25 ዓመት በብሕትውና ኖረች። አሁንም ድረስ በዚያ ዋሻ እናታችን ዜና ማርያም በፀሎት ጊዜዋ እንቅልፍ እንዳይጥላት ስትጠቀምበት የነበረ ዘንግ ፣ የምተቆምበት ዙሪያውን በገመድ የታሰረ የተቦረቦረ ግንድ አሁንም ድረስ ተአምር እየሰሩ ይገኛሉ። ከዚህም በመቀጠል ዛሬ ዜና ማርያም ተብሎ ወደ ሚጠራው ዋሻ ሔደች በዚያም በጾምና በጸሎት በልዩ ልዩ ተጋድሎ እስከ እለተ እረፍቷ ድረስ በዚያ ኖራለች።
+++ የገድል ዓይነቶች +++
፨ በየሰዓቱ ከ 100-300 ትሰግድ ነበር
፨ ሁለት ቀን እየፆመች በሶስተኛ ቀን ጥቂት ጥሬ ቀምሳ ሳምንቱን ታሳልፈው ነበር
፨ 150ን መዝሙረ ዳዊት እና ወንጌል በየቀኑ ትጸልይ ነበር
፨ በብሕትውና ወራት ማር፣ ቅቤን፣ ወተትን ፈጽሞ አትቀምስም ነበር
፨ የጌታችን መከራ መስቀል እና ስትየ ሐሞት በማሰብ በየሳምንቱ ዓርብ ዓርብ ኮሶ የሚባል ቅጠል እየበጠበጠች ከቅል ውስጥ ከሚገኘው መራራ ፍሬ ጋር በማዋሐድ ትጠጣ ነበር
፨ ከጸሎት እና ከስግደት በምታርፍበት ጊዜ አትክልት በመትከል እና በመኮትኮት ጊዜዋን ታሳልፍ ነበር
፨ የጌታችንን ግርፋቱን በማሰብ 100 ጊዜ ጀርባዋን ስለምትገረፍ እና ደም ስለሚፈሳት ጀርባዋ ይቆስል እና ይተላ ነበር።
+++ተአምራት+++
፨ ዓይናቸውን በተለያየ በሽታ የታመሙ ሰውዎች ሁሉ ከህመማቸው ተፈውሰዋል
፨ የራስ በሽታ ( የራስ ፍልጠት፣ ጭንቀት፣ ማዞር) የታመሙ ጸበሉን በመቀባት ድነዋል፡፡
፨ ጸበሉን በመጠመቅ፤ የጻድቋን ተአምር በማዘል፤ ስዕለት በመሳል መካኖች ወላድ ሆነዋል። ሌሎች በየቀኑ ብዙ ተአምራትን እናታችን ቅድስት ዜና ማርያም ታደርጋለች።
+++ቃል ኪዳን+++
ቅድስት ዜና ማርያም ከዚህ ዓለም የምታርፍበት ጊዜ እንደደረሰ በመንፈስ ቅዱስ በአወቀች ጊዜ ከታላቅ ዛፍ ወጥታ ስትፀልይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያምና ከእልፍ አእላፋት ቅዱሳን መላእክት ጋር፣ ከነቢያት፣ ከሐዋርያት፣ ከሰማዕታት፣ ከጻድቃን፣ ከደናግል መነኮሳት ጋር በመሆን ተገልጾ ከአረጋጋት በኋላ ቃል ኪዳንን ሰጧታል።
፨ በፀሎትሽ ያመነውን ኃጢአቱን ይቅር እለዋለሁ
፨ በስምሽ የተራበውን ያበላ በመንግስተ ሰማያት ኅብስተ ሕይወት አበላዋለሁ፤ የተጠማውን ያጠጣ ጽዋዓ ሕይወትን አጠጣዋለሁ
፨ መጽሐፈ ገድልሽን የጻፈውን፡ ያጻፈውን፡ የሰማውን፡ ያሰማውን ስሙን በዓምደ ወርቅ እጽፈዋለሁ
፨ ከሕፃንነትሽ እስከ አሁን ድረስ ስለ እኔ ብለሽ ብዙ መከራ ተቀብለሻል፦ ደጅሽን የረገጠ የሦስት ጭነት ጤፍ ያህል ነፍሳትን እንደሚምርላት፡ እንዲሁም ከሲዖል ነፍሳትን እንደሚያወጣላት ጌታችን በማይታበል ቃሉ ቃልኪዳን ገብቶላታል። እንዲሁም ከሲዖል ነፍሳትን እንደሚያወጣላት፡፡
+++ ገዳሟ እና መገኛው+++
፨ የቅድስት ዜና ማርያም መካነ መቃብሯ ( ጸበሏ) በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ከም ከም ወረዳ ይገኛል ቦታውም አዲስ ዘመን ከተማ 20 ኪ.ሜ ርቆ የሚገኝ ሲሆን ከከተማው በስተሰሜን በኩል "ደሪጣ" ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ይገኛል።
"ደሪጣ"
ሸክላ ማርያም ተብላ ትጠራ የነበረችው ቦታ ስያሜው ተቀይሮ ደሪጣ ዜና ማርያም ዋሻ (ገዳም) ተብሎ እስከ አሁን ድረስ እየተጠራ ይገኛል፡፡ ይህን ስያሜ ያገኘውም በቅድስት ዜና ማርያም ገድል ውስጥ " ወትሰቲ ሲካር (ኮሶ) ደሪፃ" የሚል ቃል ይገኛል። ይህም ማለት ኮሶ የተባለውን እንጨት (ቅጠል) ቀጥቅጣ (አልማ) ከቅል ውስጥ ከሚገኘው ፍሬ ጋር በማደባለቅ ትጠጣለች ማለት ነው። ስለዚህ ቦታው "ደሪፃ" ተብሎ ተሰየመ በማለት በአካባቢው የሚገኙ አባቶች ይናገራሉ። በመጨረሻም ተጋድሎዋን በመፈጸም በዚሁ በተቀደሰ ስፍራ ነሐሴ 30 ቀን ከዚህ አለም ድካም ዐርፋለች። የእናታችን የቅድስት ዜና ማርያም በረከቷ ቸርነቷ ይደርብን። አሜንን!!
+++ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ኪያነኒ ይምሐረነ በጸሎታ፡፡ ወበረከታ ለቅድስት ዜና ማርያም የሀሉ ምስሌነ ለዓለመ ዓለም አሜን!!! +++
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
✝ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together
https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━
Comments
Post a Comment