††† እንኳን ለታላቁ ሰማዕት ማር ገላውዴዎስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። †††
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††
††† ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት †††
††† ቅዱስ ገላውዴዎስ የተወለደው በ3ኛው መቶ ክ/ዘ በድሮው የሮም ግዛት በአንጾኪያ (አሁን ሶርያ ውስጥ) ነው:: አባቱ አብጥልዎስ የሮም ቄሣር የኑማርያኖስ ወንድም ነበር:: በዚህ ምክንያት ቅዱሱ ያደገው በቤተ መንግሥት ውስጥ ነው::
ወቅቱ መልካምም ክፉም ነገሮች ነበሩት:: መልካሙ ነገር በቤተ መንግሥት አካባቢ ይኖሩ የነበሩት ልዑላኑ አብዛኞቹ በፍቅረ ክርስቶስ የታሠሩ ነበሩ:: ከእነዚህ መካካከል "ቅዱስ ፋሲለደስ:
ቅዱሳኑ:- ፊቅጦር: ቴዎድሮስ: አባዲር: አውሳብዮስ: ዮስጦስ: አቦሊ: እስጢፋኖስ . . ." ነበሩ::
ቅዱሳቱ "ማርታ: ታውክልያ: ኢራኢ: ሶፍያ. . ." ነበሩ::
አስቸጋሪው ነገር ደግሞ ነጋ መሸ ኑሯቸው ጦርነት ነበር:: የዘመኑ የፋርስና የቁዝ መሪዎች ጦረኞች ነበሩና ዕለት ዕለት ፍልሚያ ነበር:: በዚህ ምክንያት ቅዱስ ገላውዴዎስ የተመሠከረለት አርበኛና የተባረከ ንጹሕ ክርስቲያን ሆኖ አድጓል:: ከልጅነቱ ጀምሮ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማጥናቱ ሕይወቱ በመንፈስ ቅዱስ ጨውነት ታሽቷል:: እርሱ የነገሥታቱ ቤተሰብ ነው:: ማዕዱ በየዓይነቱ ሞልቶ ካልመሸ እህል አይቀምስም::
ጸሎቱ ስሙር:
ስግደቱ ከምድር:
አኗኗሩ በፍቅር ሆነ:: በዚያውም ላይ በድንግልናው የጸና ኃያል ነበር::
በጊዜው የቅዱስ ገላውዴዎስን ያህል መልኩ ያማረ (ደመ ግቡ) በአካባቢው አልነበረም:: ይህ ግን ሊያታልለው አልቻለም:: ሁሉ በእጁ ቢሆንም ለእርሱ ግን ብቸኛ ምርጫው ሃይማኖተ ክርስቶስ ነበር::
ቅዱስ ገላውዴዎስ ለጦርነት ወጥቶ ሲመለስ ንጉሡ ዲዮቅልጢያኖስ ሃይማኖቱን ክዶ: ሕዝቡን ለጣዖት ሲያሰግድ: ክርስቲያኖችን ሲገድል ደረሰ::
††† ቅዱሱ ኃያል የጦር ሰው ነውና ንጉሡን መግደል ሲችል ተወው:: በዚያ ሰሞንም ለገላውዴዎስ ሁለት ምርጫዎች ቀረቡለት:-
1.ክርስቶስን ክዶ የንጉሡ ተከታይ መሆን:
2.በክርስትናው ደሙን ማፍሰስ::
የቅዱሳኑ ምርጫቸው የታወቀ ነውና ታስሮ ወደ ግብጽ ተጋዘ:: በዚያ ከመኮንኑ ጋር ስለ ሃይማኖት ተከራክረው መኮንኑ ስለተበሳጨ ቅዱሱን በረዥም ጦር ጐኑን ወጋው:: ዘለፍ ብሎ ነፍሱን ሰጠ:: ሕዝበ ክርስቲያኑ በድብቅ መጥተው የቅዱሱን ሥጋ ሽቱ ቀብተው: ከዝማሬ ጋር ገነዙት:: የጓደኛው እናት ቅድስት ሶፍያ መጥታ ወደ ሶርያ ወስዳዋለች::
††† ተወዳጅ: ኃያል: ቡሩክና መልካም ሰው ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት በሆነባት በዚሕች ዕለት በመላው ኦርቶዶክሳውያን ይከበራል::
††† አምላካችን የቅዱሱን መንኖ ጥሪት: ትዕግስት: ጸጋና በረከት ያሳድርብን:: አሜን::
††† ሰኔ 11 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት (ሕይወቱ መላእክትን የመሰለ)
2.አንድ ሺ ሰማንያ ስምንት ሰማዕታት (የቅዱስ ገላውዴዎስ ማኅበር)
3.አባ ክርዳኑ ሊቀ ጳጳሳት
4.እናታችን ቅድስት ክርስቶስ ክብራ ኢትዮጵያዊት (የአቡነ በጸሎተ ሚካኤል እህት)
5.የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዳሴ ቤቱ (ግብጽ)
††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ያሬድ ካህን
2.ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
3.ብፁዐን ኢያቄም እና ሐና
4.አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ
††† "የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ:: ደስ አያሰኙም የምትላቸውም ዓመታት ሳይደርሱ: ፀሐይ: ጨረቃና ከዋክብትም ሳይጨልሙ . . . አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ: ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ::
ሰባኪው:- "ከንቱ: ከንቱ: ሁሉ ከንቱ ነው" ይላል::" †††
(መክ. ፲፪፥፩-፱)
††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
✝ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together
https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━
Comments
Post a Comment