††† እንኳን ለታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። †††
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††
††† ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ †††
††† በቤተ ክርስቲያን ታሪክ በደራሲነታቸው : በወንጌል አገልግሎታቸውና በቅድስናቸው ከተመሠከረላቸው ዐበይት ሊቃውንት አንዱ ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ነው::
ሊቁ የተወለደው መጋቢት 27 ቀን በ433 ዓ/ም ሲሆን ሃገሩ ሶርያ ነው:: ወላጆቹ ክርስቲያኖች ለዚያውም አባቱ ሊቀ ካህናት ነበር:: ቅዱስ ያዕቆብ ገና በልጅነቱ ጀምሮ ጸጋ እግዚአብሔር የጠራው ነውና በብዙ ነገሩ የተለየ ነበር::
አንድ ቀን በዕለተ ሰንበት : ገና በ3 ዓመቱ : እናቱ አቅፋ ወደ ቤተ መቅደስ ወሰደችው:: ምዕመናን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ሲቀበሉ ሕጻኑ ያዕቆብም ይቆርብ ዘንድ ቀረበ:: ሊቀ ዻዻሱ ደሙን በዕርፈ መስቀል ሊያቀብለው ሲል መልአኩ መጥቶ "በጽዋው ጋተው" አለው:: የጌታን ደም በጽዋ ቢጠጣ ምስጢር ተገለጸለትና "አንሰ እፈርሕ ሠለስተ ግብራተ - እኔስ 3 ነገሮች ያስፈሩኛል" ሲል አሰምቶ ተናገረ::
††† ዻዻሱና ሕዝቡ ወደ ሕጻኑ ያዕቆብ ቀርበው "ምን ምን?" አሉት:: እርሱም:-
1.ነፍሴ ከሥጋየ ስትለይ::
2.ቅድመ እግዚአብሔር ለፍርድ ስቀርብ::
3.ከፈጣሪየ የፍርድ ቃል ሲወጣ" አላቸው::
ያን ጊዜ ሕዝቡና ሊቀ ዻዻሳቱ "እግዚአብሔር በዚሕ ሕጻን አድሮ ዘለፈን" እያሉ ለንስሃ በቅተዋል::
ቅዱስ ያዕቆብ 7 ዓመት ሲሞላው ይማር ብለው ወደ ጉባዔ አስገቡት:: በ5 ዓመታት ብሉይ ከሐዲስ ጠንቅቆ በ12 ዓመቱ ሊቅ ሆኗል:: በዚህ ወቅት የነበሩ ታላላቅ ሊቃነ ዻዻሳት ወደ እርሱ ተሰበብስበው "እንግዳ ድርሰት ድረስልን:: አዲስ ምሥጢር ንገረን" አሉት:: እርሱ ግን ሲቻለው ስለ ትሕትና "አልችልም" አላቸው::
"እንግዲያውስ ትንቢተ ሕዝቅኤልን ተርጉምልን" ቢሉት ባጭር ታጥቆ አመሥጥሮላቸው ተደስተዋል:: ፈጣሪንም አመስግነዋል::
ቅዱስ ያዕቆብ ከዚህ በኋላ ወደ ገዳም ገብቶ ትሕርምተ አበውን : ዕጸበ ገዳምን : ሕይወተ ቅዱሳንን በተግባር ተምሯል:: በድንግልናው ጸንቶ : ጾምና ጸሎትን እያዘወተረ ኑሯል:: በፈቃደ እግዚአብሔር የሥሩግ (በኤፍራጥስና ጤግሮስ ወንዞች መካከል የምትገኝ የሶርያ ግዛት ናት) ኤዺስ ቆዾስ ሆኖ ተሹሟል::
††† በዘመኑም:-
1.የ451ን የኬልቄዶን ጉባኤ አውግዟል::
2.ብዙ መናፍቃንን ተከራክሮ ምላሽ አሳጥቷል::
3.በወንጌል አገልግሎት መልካም እረኝነቱን አሳይቷል::
4.ዛሬ የምንገለገልበትን መጽሐፈ ቅዳሴውን ጨምሮ በርካታ መንፈሳዊ ድርሰቶችን ደርሷል::
በመጨረሻም ከብዙ የተጋድሎና የቅድስና ዓመታት በኋላ በተወለደ በ72 ዓመቱ በ505 ዓ/ም በዚሕች ቀን አርፏል:: አንዳንድ ምንጮች ደግሞ ሰኔ 27 ቀን እንዳረፈ ይናገራሉ:: ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ ለቤተ ክርስቲያን የቁርጥ ቀን ተወዳጅ ልጇ ነውና በእጅጉ ታከብረዋለች::
††† አምላከ ቅዱሳን ከታላቁ ሊቅ በረከት ይክፈለን::
††† ሰኔ 7 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ
2.ቅዱስ : ቡሩክና አሸናፊ አባ አበስኪሮን (ታላቅ ሰማዕትና ባለ ብዙ ተአምራት ነው)
3."16,000" ሰማዕታት (በአንድ ቀን የተገደሉ)
4.የእመቤታችን ቤተ ክርስቲያን የተከፈተበት በዓል (ከ1ሺ ዓመታት በፊት ምስር (CAIRO) ውስጥ)
††† ወርሐዊ በዓላት
1.ሥሉስ ቅዱስ (አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ)
2.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ
3.አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን አለቃ)
4.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት
5.አባ ባውላ ገዳማዊ
6.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ
7.ቅዱስ አግናጥዮስ (ለአንበሳ የተሰጠ)
††† "ይሕንን እዘዝና አስተምር :: በቃልና በኑሮ : በፍቅርም : በእምነትም : በንጽህናም ለሚያምኑቱ ምሳሌ ሁን እንጂ ማንም ታናሽነትህን አይናቀው:: እስክመጣ ድረስ ለማንበብና ለመምከር : ለማስተማርም ተጠንቀቅ::" †††
(1ጢሞ. 4:11)
††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
✝ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together
https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━
Comments
Post a Comment