✞✝✞ እንኩዋን ለታላቁ "የጌታ ጾም (ጾመ እግዚእ)" በሰላም አደረሳችሁ ✞✝✞
+*" ጾመ እግዚእ "*+
=>ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በአዋጅ ምዕመናን
እንዲጾሟቸው የሠራቻቸው 7 አጽዋማት አሏት:: "ጾም" ማለት "መከልከል" ነው:: የምንከለከለው ደግሞ ከኃጢአትና ከክፋት ሲሆን አንድም ሰውነትን ወደዚያ ከሚወስዱ አዝማደ መባልዕት (የምግብና የመጠጥ ዓይነቶች) መከልከልን ይመለከታል::
+"7ቱ" አጽዋማት:-
1.ዓቢይ ጾም
2.ጾመ ፍልሠታ
3.ጾመ ሐዋርያት
4.ጾመ ነቢያት
5.ጾመ ድኅነት
6.ጾመ ነነዌ እና
7.ጾመ ገሃድ ይሰኛሉ::
+በእነዚህ አጽዋማት ከዓቢይ ጾም በቀር እስከ 9 ሰዓት
ድረስ መጾም ይገባል:: ዓቢይ ጾም ግን የተለየ ሥርዓት
አለው:: ስለ ጾም ሲነሳ አስቀድሞ የሚመጣው ጥያቄ
አስፈላጊነቱ ነው:: "ጾም ለምን ያስፈልጋል?" ብሎ
ከመጠየቅ "ሃይማኖት ለምን ያስፈልጋል?" ብሎ
መጠየቁ ይቀላል::
+ምክንያቱም ከሃይማኖታዊ ትዕዛዛት ትልቁ በመሆኑ
እርሱን መቃወም ሃይማኖትንና አዛዡን እግዚአብሔርን
መቃወም ነውና:: እኛ ሃገር ላይ የተለመደች ክፉ ልማድ
አለች:: የከበደችንን ነገር "አያስፈልግም" በሚል
እንከራከራለን::
+ደግሞ ጾምን ለመሻር ጥቅስ የሚጠቅሱ ወገኖች
በጣም ይገርሙኛል:: ኃጢአትን ለመሥራት : ጾምንም
ለመሻር ጥቅስን መጥቀስ አያስፈልግም:: እኛ ግን
¤ከፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጀምሮ (ማቴ. 4:2)
¤አበው ቅዱሳን ጾመው (ዘዳ. 9:19, ነገ. 19:8, ሐዋ.
13:3, ቆሮ. 4:11) አሳይተውናልና እንደ አቅማችን
እንጾማለን::
+የጾሙ የመጀመሪያው ሳምንት (ዘወረደ) የሚጾመው
እስከ 12 ሰዓት ሲሆን ከቅድስት (ከ2ኛው ሳምንት) እስከ
ተጽኢኖ (የኒቆዲሞስ ዓርብ) ድረስ ደግሞ እስከ 11
ሰዓት ይጾማል::
በሰሙነ ሕማማት ግን የምንጾመው "እስከ ይሠርቅ
ኮከብ" (እስከ ምሽት 1 ሰዓት) ድረስ ይሆናል::
+ነገር ግን ሁሉም እንደ መጠኑ ነውና ከመምሕረ ንስሃ
ጋር ሊጨዋወቱት ይገባል:: በዓቢይ ጾም ለቻለ ቂጣ
በጨው እየበላ: ውሃ እየተጐነጨ ሊጾም ይገባል::
በእነዚህ 55 ቀናትም ከዕለተ ሆሳዕና በቀር ከበሮ
አይጐሰምም:: ጸናጽል አይጸነጸልም:: ተድላ ደስታም
አይደረግም::
+አብዝቶ መብላት : ሳቅ ማብዛትና ጌጥን ማብዛትም
እንዲሁ አይገባም:: ለቻለ ደግሞ በሌሊት ሰዓታቱን፡
በግህ ኪዳንና ስብሐተ ነግሁን : በመዓልት ቅዳሴውን :
በሰርክ (ምሽት) ደግሞ ምሕላውን ሊሳተፍ ይገባል::
+በእነዚህ 55 ቀናት ፈቃደ ሥጋ ሊደክም : ፈቃደ ነፍስ
ልትሰለጥን ግድ ነውና:: ከሌላው ጊዜ በተሻለ ወቅቱ
ምጽዋትና ጸሎት የሚደረግበት ነው:: በዚያውም ላይ
ነገሮችን እያመቻቹ በእነዚህ ዕለታት ቅዱስ ቃሉን
መስማት (ማንበብ) ይገባል:: በትዳር ውስጥ ላሉም
መኝታን መለየት ግድ ነው::
=>ከ7ቱ አጽዋማት አንዱ የሆነው ይህ ጾም=
1.ዐቢይ (ታላቁ) ጾም
2.የጌታ ጾም
3.ጾመ ሑዳድ
4.የድል ጾም
5.የካሳ ጾም
6.አርባ ጾም
7.የፍቅር ጾም . . .
በሚሉ መጠሪያዎችም ይታወቃል::
=>የጾሙ መግቢያ የመጀመሪያ ሳምንት ደግሞ=
1.ጾመ ሕርቃል
2.ጾመ በረከት ዘሐዋርያት
3.ሰሙነ ዘወረደም ይባላል::
=>ጾሙን የሰላም : የፍቅር : የምሕረት : የፀጋ :
የበረከት ያድርግልን:: ጾሞ ለማበርከትም ያብቃን፡፡
=>+"+ አሁንስ ይላል እግዚአብሔር በፍጹም ልባችሁ
በጾምም በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ:: ልባችሁን
እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ:: አምላካችሁም
እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ: ቁጣው የዘገየ: ምሕረቱም የበዛ: ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ:: +"+ (ትን. ኢዩኤል 2:12)
✞✝✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞✝✞
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
✝ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together
https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━⊱✿⊰━━
Comments
Post a Comment