#የካቲት_12
አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም
የካቲት ዐሥራ ሁለት በዚች ቀን የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ #ቅዱስ_ሚካኤል ወደ ረዓይታዊ ወደ ሶምሶን ተልኮ ኃይልን ሰጥቶት ጠላቶቹን ድል እንዲያደርግ የተራዳበት መታሰቢያ ነው፣ ተጋዳይ የሆነ የከበረ አባት #አባ_ገላስዮስ አረፈ፣ ታላቁ አባት #አቡነ_ሠርጸ_ጴጥሮስ አረፉ፡፡
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#የመላእክት_አለቃ_ቅዱስ_ሚካኤል
የካቲት ዐሥራ ሁለት በዚች ቀን የመላእክት አለቃ የከበረ መልአክ ሚካኤል ወደ ረዓይታዊ ወደ ሶምሶን ተልኮ ኃይልን ሰጥቶት ጠላቶቹን ድል እንዲያደርግ የተራዳበት መታሰቢያ ነው።
በዚች ዕለት የከበረ ሚካኤልን እግዚአብሔር ወደ ረዓይታዊ ወደ ሶምሶን ላከው የፍልስዔም ሰዎች ሊገድሉት በጠላትነት በተነሡበት ጊዜ ድል እስከ አደረጋቸውና እስከ ገደላቸው ድረስ ረዳው ኃይልንም ሰጥቶ በአህያ መንጋጋ ከእርሳቸው አንድ ሺህ ሰዎችን ገደለ። ተጠምቶም ለሞት በተቃረበ ጊዜ የመላእክት አለቃ ሚካኤል ተገለጠለትና አጸናው እግዚአብሔር ከአህያ መንጋጋ አጥንት ውኃን አፈለቀለትና ጠጥቶ ዳነ።
ዳግመኛም ከሚስቱ ጋር ተስማምተው ዐይኖቹን አሳወሩ የራሱንም ጠጉር ላጩ አሠሩትም ከዚህም በኋላ ለጣዖቶቻቸው በዓልን በአዘጋጁ ጊዜ ሶምሶንን ወደ ጣዖቶቻቸው ቤት ወሰዱት በዚያም ሦስት ሽህ ያህል ሰዎች ተሰብስበው ነበር የከበረ ሚካኤልም ተገለጠለትና ኃይልን መላው የዚያንም ቤት ምሰሶዎች ነቀላቸው ቤቱም በላያቸው ወድቆ ከእርሱ ጋር ሁሉንም ገደላቸው።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#ቅዱስ_አባ_ገላስዮስ_ገዳማዊ
በዚህችም ቀን ተጋዳይ የሆነ የከበረ አባት አባ ገላስዮስ አረፈ። የዚህ ቅዱስ ወላጆቹ አግዚአብሔርን የሚፈሩ ምእመናን ናቸው ጥበብንና የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት አስተማሩትና ዲቁና ተሾመ።
ከታናሽነቱም ጀምሮ ይህን ዓለም ንቆ ተወ የክብር ባለቤት የሆነ የክርስቶስንም ቀንበር በመሸከም በምንኵስና ሆኖ በትጋት እየጾመ እየጸለየና እየሰገደ ታላቅ ተጋድሎን ተጋደለ እግዚአብሔርም መርጦት በአስቄጥስ ገዳም ባሉ መነኰሳት ላይ ቅስና ተሾመ።
ተጋድሎውንና አገልግሎቱን እየፈጸመ ሳለ ለአባ ጳኵሚስ እንደ ተገለጠ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለትና መነኰሳትን ሰብስቦ ፈሪሀ እግዚአብሔርን የምንኵስናንም ሕግ ያስተምራቸው ዘንድ አዘዘው በዚያንም ጊዜ ብዙዎች መነኰሳትን ሰበሰበ መንፈሳዊ የሆነ የአንድነት ማኅበራዊ ኑሮንም ሠራላቸው እርሱ በመካከላቸው እንደ መምህር አልሆነም ከእርሳቸው እንደሚያንስ አገልጋይ እንጂ።
ይህም አባት የዚህን ዓለም ጥሪት ሁሉ ንቆ የተወ ሆነ እጅግም የዋህና ቸር ሆነ ከብሉይና ከሐዲስ መጻሕፍቶችም የተሰበሰበ አንድ ታላቅ መጽሐፍን አጻፈ ለማጻፊያውም ዋጋ ዐሥራ ስምንት የወርቅ ዲናር አወጣ ከርሱ ሊጠቀሙ በሚፈልጉ ጊዜ መነኰሳቱ እንዲያነቡት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአትሮንስ ላይ አኖረው።
አንድ መጻተኛ ሰውም አረጋዊ አባ ገላስዮስን ሊጎበኝ በገባ ጊዜ ያንን መጽሐፍ አየውና አማረው በጭልታም ከዚያ ሰርቆት ወጣ ወደ ከተማ ውስጥም በገባ ጊዜ ሊሸጠው ወደደ አንድ ሰውም ዋጋው ምን ያህል ነው አለው እርሱም ዐሥራ ሰባት የወርቅ ዲናር ስጠኝ አለው። ያ የሚገዛውም ሰው ያልከውን እሰጥሃለሁ ነገር ግን ለወዳጄ እስካሳየው ታገሠኝ አለው ያሳየውም ዘንድ ሰጠው የሚገዛው ሰው ግን ወደ አባ ገላስዮስ ወሰደውና ተመልከትልኝ መልካም ከሆነ እገዛዋለሁ አለው አባ ገላስዮስም ያመጣውን ሰው ከአንተ ምን ያህል ፈለገ አለው ዐሥራ ሰባት የወርቅ ዲናር አለው ቅዱስ ገላስዮስም መጽሐፉ መልካም ነው ዋጋውም ቀላል ነው ግዛው ብሎ መለሰለት።
ወደ ሌባውም በተመለሰ ጊዜ አባ ገላስዮስ የነገረውን ሠውሮ ለአባ ገላስዮስ አሳየሁት እርሱም ዋጋው በዝቷል አለኝ አለው ሌባውም ያ ሽማግሌ ሌላ የተናገረህ ነገር የለምን አለው አዎን የለም አለው። ሌባውም እንግዲህ እኔ አልሸጠውም ብሎ ወደ አባ ገላስዮስ ሒዶ ከእግሩ በታች ወድቆ ለመነው ሰይጣን አስቶኛልና ይቅር በለኝ መጽሐፍህንም ውሰድ አለው የከበረ ገላስዮስም እኔ መጽሐፉን መውሰድ አልሻም አለው። ሌባውም በፊቱ እያለቀሰና እየሰገደ ብዙ ለመነው በብዙ ድካምም መጽሐፉን ተቀበለው ማንም ያወቀ የለም። እግዚአብሔርም ትንቢት የመናገርን ሀብት ሰጥቶት ድንቆች ተአምራቶችን አደረገ።
በአንዲትም ዕለት ለገዳሙ መነኰሳት ዓሣ አመጡ ባለ ወጡ ዓሣውን አብስሎ በቤት ውስጥ አኑሮ አንዱን ብላቴና ጠባቂ አድርጎ ወደ ሥራው ሔደ ብላቴናውም ከዚያ ዓሣ በላ። ባለ ወጡ በመጣ ጊዜ ተበልቶ አገኘውና በብላቴናው ላይ ተቆጥቶ አረጋውያን አባቶች ሳይባርኩት እንዴት ደፍረህ በላህ አለው የቊጣ መንፈስም በልቡ አደረና ብላቴናውን ረገጠው ወዲያውኑ ሞተ እንደሞተም አይቶ ደነገጠ ታላቅ ፍርሀትንም ፈራ ሒዶ ለአባ ገላስዮስ የሆነውን ሁሉ ነገረው እርሱም ወስደህ ከቤተ መቅደሱ ፊት አስተኛው አለው ሰውየውም እንዳዘዘው አደረገ።
ወደ ማታ ጊዜም አረጋውያን መነኰሳት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተሰብስበው የማታውን ጸሎት አድርሰው ወጡ አረጋዊ አባ ገላስዮስም በወጣ ጊዜ የሞተው ብላቴና ተነሥቶ በኋላው ተከተለው ከመነኰሳትም ማንም አላወቀም እርሱም የገደለውን ባለ ወጥ ለማንም እንዳይናገር አዘዘው።
የተመሰገነ አባ ገላስዮስም ያማረ ትሩፋቱንና ተጋድሎውን ፈጽሞ አድርሶ እግዚአብሔርንም አገልግሎ ይህንንም በጎ መታሰቢያ ትቶ ከዚህ ከኃላፊው ዓለም የሚለይበት ሲደርስ በሰላም አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#አቡነ_ሠርጸ_ጴጥሮስ
ዳግመኛም በዚህች እለት ታላቁ አባት አቡነ ሠርጸ ጴጥሮስ አረፉ፡፡ የትውልድ አገራቸው ሸዋ ደብረ ጽላልሽ ሲሆን በሕፃንነታቸው ወደ ወሎ ሄደው ሐይቅ እስጢፋኖስ ገብተው ብዙ ተጋድለዋል፡፡ከተጋድሎአቸውም በኋላ በአቡነ ኢየሱስ ሞዐ እጅ መነኰሱ፡፡ በገዳሙ ብዙ ካገለገሉ በኋላ በመልአክ ትእዛዝ ወደ ጎጃም ሲሄዱ ዓባይን የተሻገሩት አጽፋቸውን አንጥፈው እርሱን እንደ ጀልባ ተጠቅመው ነው፡፡
ጻድቁ ታላቋን ተድባበ ማርያምን ለ41ዓመት አጥነዋል፡፡ የንጉሡ ልጅ ሞቶ ሊቀብሩት ሲወስዱት የአቡነ ሠርጸ፡ጴጥሮስ ጥላቸው ቢያርፍበት ከሞት አፈፍ ብሎ ተነሥቶ ድኖ "አምላከ አቡነ ሠርጸ ጴጥሮስ" ብሎ ፈጣሪውን አመስግኗል፡፡ ጻድቁ ሲያርፉም መቋሚያቸው አፍ አውጥታ ተናግራለች፤ ርዕደተ መቃብራቸው ሲፈጸምም እንባ አፍስሳ አልቅሳላቸዋልች፡፡ ይህቺ ተአምረኛ መቋሚያቸው ዛሬም ጎጃም ውስጥ መካነ መቃብራቸው ባለበት በደብረ ወርቅ ገዳም ትገኛለች፡፡ ጻድቁ ደብረ ወርቅ ገዳምን እንደ መሶብ አንሥተው አስባርከዋታል፡፡ አቡነ ሠርፀ ጴጥሮስ የካቲት12 ቀን ያረፉ ሲሆን ዐፅማቸውም በታላቋ ደብረ ወርቅ ይገኛል፡፡ ከሰማይ የወረደላቸው የወርቅ መስቀላቸውም በዚያው ይገኛል፡፡
ጸበላቸው እጅግ ፈዋሽና ኃይለኛ ከመሆኑም በላይ በሰውነት ውስጥ የሚገኝ በሽታንና አጋንንትን የሚያስወጣበት መንገድ ለየት ያለው፡፡
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በከበሩ ቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
(#ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት እና #ከገድላት_አንደበት)
††† የካቲት 12 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1."30,000" ሰማዕታተ ኢትዮዽያ (ሮማዊው ፋሽስት የገደላቸው)
2.ቅዱስ ሶምሶን ረዓይታዊ (የእስራኤል መስፍን)
3.ቅዱስ አባ ገላስዮስ ገዳማዊ
4.ቅድስት ዶርቃስ
††† ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላዕክት
2.ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
3.ቅዱስ ድሜጥሮስ
4.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
5.ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ (ሰማዕት)
6.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
7.አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ
8.ቅዱስ ላሊበላ ጻድቅ
††† አምላከ አበው ቅዱሳን መዓዛ ቅድስናቸውን ያሳድርብን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::
††† "ሶምሶንም:- 'ስለ ሁለቱ ዓይኖቼ ፍልስጥኤማውያንን አሁን እንድበቀል : እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! እባክህ አስበኝ? አምላክ ሆይ! . . . እባክህ አበርታኝ?' ብሎ እግዚአብሔርን ጠራ:: . . . ሶምሶንም:- 'ከፍልስጤማውያን ጋር ልሙት' አለ:: ተጐንብሶም ምሰሶዎችን በሙሉ ኃይሉ ገፋ:: . . . በሞቱም የገደላቸው ሙታን በሕይወት ሳለ ከገደላቸው በዙ::"
(መሣ. 16:28)
††† "እንግዲህ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎንና ስለ ባርቅ: ስለ ሶምሶንም: ስለ ዮፍታሔም: ስለ ዳዊትና ስለ ሳሙኤልም: ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛልና:: እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ:: ጽድቅንም አደረጉ . . ." †††
(ዕብ. 11:32)
††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
✝ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together
https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━⊱✿⊰━━
Comments
Post a Comment