#የካቲት4_5
የካቲት አራት በዚህች ቀን ሉቃስ የሣላት ከጒንጯ ደም የሚፈስሳት ተአምር አድራጊዋ #የእመቤታችን_ሥዕል የምትታሰብበት በዓሏ ነው፣ ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ ሐዋርያ የከበረ #ቅዱስ_አጋቦስ በሰማዕትነት ሞተ፣ በምግባር ፍጹም የሆነ ተጋድሎውም የበዛ #አባ_ዘካርያስ አረፈ።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#ተአምር_አድራጊዋ_የእመቤታችን_ሥዕል
በዚህች ዕለት ሉቃስ የሣላት ከጒንጯ ደም የሚፈስሳት ተአምር አድራጊዋ የእመቤታችን ሥዕል የምትታሰብበት በዓሏ ነው።
ይኸውም ከ829-842 ዓ.ም በቤዛንታይን የነገሠው ንጉሥ ቴዎፍሎስ በቅዱሳት ሥዕላት ላይ በክፋት ተነሳሥቶ ዐዋጅ በማወጁ ወታደሮቹ በርሱ ትእዛዝ በእያንዳንዱ ቤት እየዞሩ ቅዱሳት ሥዕላትን ለማጥፋት ፍተሻ ያደርጉ ነበር፤ በኒቅያ ከተማ አቅራቢያ አንዲት የተቀደሰች ሴት ነበረች፤ ቅዱስ ሉቃስ የሣላት የአምላክ እናት የቅድስት ድንግል ማርያም ውብ ሥዕሏን በቤቷ ውስጥ ደብቃ በማኖር በሥዕሏ ፊት መብራትን እያበራች ከልጇ እንድታማልዳት ትማፀን ነበር፡፡
የከሓዲው ንጉሥ ወታደሮቹም የአምላክ እናት ሥዕል በቤቷ እንዳለች በማወቃቸው ወደ ቤቷ በድንገት ዘልቀው ገቡ፤ ከመካላቸውም አንዱ ወታደር የእመቤታችንን ሥዕሏን በያዘው ጦር ጒንጯ ላይ ወጋት፡፡ ኾኖም ግን በእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ ይኽ ክፉ ሥራው በተአምር ተተክቶ፤ ከተወጋው ከአምላክ እናት ፊት ላይ ደም ይፈስስ ጀመር፡፡
ይኽን ግሩምና ድንቅ ተአምር ባዩ ጊዜ ወታደሮቹ ደንግጠው ሸሽተዋል፤ ሴቲቱም ይኽነን ድንቅ ተአምር ባየች ጊዜ ሌሊቱን ሙሉ በሥዕሏ ፊት መብራትን አብርታ በአምላክ እናት በቅድስት ድንግል ማርያም ሥዕል ፊት ስትጸልይ ዐደረች፤ በነጋታውም በእግዚአብሔር ፈቃድ ከጒንጮቿ ደም የፈሰሳትን የአምላክ እናት ሥዕሏን በባሕሩ ላይ እንድታስቀምጥ ታዘዘችና አስቀመጠቻት።
ሥዕሏም በባሕሩ ላይ በመንሳፈፍ በማዕበሉ እየተነዳች ያለምንም መስጠምና መርጠብ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ጉዞዋን አድርጋ ወደ አቶስ ደረሰች፡፡ ጊዜያቶች ካለፉ በኋላ ከዕለታት በአንዳቸው ምሽት በአቶስ ተራራ የአይቬሮን ገዳም መነኮሳት የብርሃን ምሰሶ በባሕሩ ላይ ተተክሎ እንደ ፀሓይ ሲያበራ ተመለከቱ፡፡
ይኽም ተአምር ለተካታታይ ቀናቶች በመቀጠላቸው በዚያ የተቀደሰ ተራራ በምናኔ ያሉ አባቶች ኹሉ በአንድ ላይ ተሰባስበው በማድነቅ የብርሃን ምሰሶ ወደተተከለበት የአምላክ እናት ሥዕል በላዩ ላይ ወደ ተንሳፈፈበት ወደ ባሕሩ በመውረድ ወደ ሥዕሏ ለመጠጋት ቢሞክሩም ሥዕሏ ወደ ኋላዋ እየተመለሰች ሊያነሷት አልተቻላቸውም፡፡
በዚያው የአይቮሪዮን ገዳም ረድእ (የጉልበት አገልጋይ) ኾኖ የሚኖር አባ ገብርኤል የተባለው መነኩሴ ብቻ ሥዕሏን ከባሕር ውስጥ ማንሣት የሚችል እንደኾነ የአምላክ እናት ለመነኮሳቱ ገለጠችላቸው፤ በተመሳሳይም ለአባ ገብርኤል እመቤታችን ተገልጣለት “ወደ ባሕሩ ኺድ፤ ማዕበሉንም ሳትፈራ በባሕሩ ውስጥ በእምነት ተጓዝ፤ እናም ኹሉም ለዚኽ አንተ ላለኽበት ገዳም ያለችን ፍቅርና ርኅራኄ ምስክር እንዲኾኑ፤ ሥዕሌን ከባሕር አውጣ” በማለት ነገረችው፡፡
ከዚያም በአቶስ ተራራ ያሉት መናንያን ኹሉ አባ ገብርኤልን ይዘው ልብሰ ተክህኖ ለብሰው፣ እያመሰገኑ፤ በማዕጠንታቸው ዕጣን እያጠኑ የብርሃን ምሰሶ ወደተተከለበት የአምላክ እናት ሥዕል ወዳለበት ወደ ባሕሩ ኼዱ፤ አባ ገብርኤልም በደረቅ መሬት እንደሚጓዝ ያለምንም ፍርሃት ወደ ባሕሩ ውስጥ በመግባት በናፍቆት ኾኖ የአምላክ እናት የቅድስት ድንግል ማርያምን ሥዕሏን በደረቱ ታቅፎ ተሳለማትና ወደ ባሕር ዳርቻ ይዟት ወጣ፤ እነርሱም በደስታ ኾነው እጅ ነሷት፡፡
ከዚያም ማግሰኞ በጠዋቱ ሥዕሏ ባረፈበት ቦታ ላይ በሚያመሰግኑበት ጊዜ ቀዝቃዛና ጣፋጭ ውሃ ከምድር ላይ ፈለቀላቸው፡፡ ከዚያም የእመቤታችንን ሥዕሏን በታላቅ ክብር በምስጋና ይዘው በመኼድ ወደ ቤተ መቅደስ አግብተው በመንበሩ ላይ አስቀመጧት፡፡
ነገር ግን በነጋታው መነኮሳቱ ወደ ቤተ መቅደስ ገብተው መብራት ሲያበሩ የእመቤታችን ሥዕሏን ባስቀመጡበት ቦታ አላገኟትም፤ ይልቁኑ በመግቢያው በር ባለው ግድግዳ ላይ ተሰቅላ አገኟት፤ እነርሱም መልሰው ቦታዋ ላይ ቢያኖሯትም ተመልሳ በገዳሙ መግቢያ ላይ ተሰቅላ ያገኟት ነበር፤ ከዚያም እመቤታችን ለአባ ገብርኤል ተገልጻለት “ለወንድሞች እንዲኽ ብለኽ ንገራቸው፤ ከዚኽ በኋላ ሥዕሌን ማግባት የለባቸውም፤ የእኔስ ፈቃድ በእናንተ ልጠበቅ ሳይኾን እኔን በምልጃዬ ጥላ በዚኽም ዓለም በወዲያኛውም ዓለም ልጋርዳችኊ እንጂ፤ ሥዕሌን በገዳሙ በምታዩበት ጊዜ ኹሉ የልጄ ምሕረትና ጸጋ ከእናንተ አይቋረጥም” አለችው፡፡
በዚህ ምክንያት ሥዕሏ በነገረ መለኮት ሊቃውንት "አቃቢተ ኆኅት" (ደጃፍን የምትጠብቅ) Panagia Portaitissa ("She who resides by the door" or "Keeper of the gate" ትባላለች።
መነኮሳቱም ይኽነን ሰምተው በእጅጉ በመደሰት ለአምላክ እናት ለእመቤታችን ክብር በገዳሙ በር አጠገብ አነስ ያለች ቤተ ክርስቲያን ሠርተው ገባሪተ ተአምራት ወመንክራት (ድንቅ ተአምር አድራጊዋን) የአምላክ እናት የቅድስት ድንግል ማርያምን ሥዕሏን ወደ ውስጥ አገቧት፤ የተቀደሰች የሥዕሏ መጠሪያም “የአይቬሮኗ የአምላክ እናት” (the Iviron Theotokos) ስትባል በግሪክ “ፓርታኢቲሳ” Παναγία Πορταΐτισσα; ትባላለች።
ከዚያም በአይቬሮን ገዳም ያለችው የእመቤታችን ሥዕል ድንቅ ተአምር በዓለም ኹሉ ላይ ከተሰማ በኋላ በረከቷን ለማግኘት ክርስቲያኖች ወደዚያች ገዳም መኼድን ጀመሩ፤ ይኽ የተቀደሰ ሥዕሏና ታሪኳም ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለሙ ኹሉ ላይ ተሰማ፤ ዛሬም ምእመናን ይማፀኑበታል፡፡
ለአባ ገብርኤል የተለመነች እና በረከቷን እንዳሳደረችበት ዛሬም የምልጃዋ ጥላ በዚኽም ዓለም በወዲያኛውም ዓለም አይለየን።
(#መጋቤ_ሐዲስ_ዶክተር_ሮዳስ_ታደሰ_እንደጻፈው)
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#ሐዋርያው_አጋቦስ
የካቲት አራት በዚህች ቀን ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ ሐዋርያ የከበረ አጋቦስ በሰማዕትነት ሞተ። ይህም ቅዱስ ጌታችን ከመረጣቸውና ይሰብኩ ዘንድ ከመከራው በፊት ከላካቸው ከሰባ ሁለቱ አርድእት ውስጥ ነው።
በጽርሐ ጽዮንም አጽናኝ መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ ከሐዋርያት ጋር ስጦታውን ተቀብሏል። እግዚአብሔርም የትንቢትን ሀብት ሰጠው ስለርሱ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እንደ ተናገረ የቅዱስ ጳውሎስን መታጠቂያ አንሥቶ ራሱ እግሮቹን አሠረባትና የዚችን መታጠቂያ ባለቤት በኢየሩሳሌም አይሁድ እንዲህ ያሠሩታል አለ መንፈስ ቅዱስ ብሎ ትንቢት ተናገረ ትንቢቱም ተፈጸመች።
ከዚህም በኋላ ሕይወት በሆነ በወንጌል ትምህርት ሊአስተምር ከሐዋርያት ጋር ወጣ እያስተማረና ቀና የሆነ የእግዚአብሔርን መንገድ እየመራ ብዙ አገሮችን ዞረ ከአይሁድና ከዮናናውያንም ብዙዎችን የክብር ባለቤት ወደሆነ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅን ሃይማኖት አስገባቸው በከበረች በክርስትና ጥምቀትም አነፃቸው።
ቅናትን የተመሉ አይሁድም ብቻውን በኢየሩሳሌም በድንገት ያዙትና ታላቅ ግርፋትንም ገረፉት ከዚህም በኋላ በአንገቱ ገመድ አስገብተው እስከ ከተማ ውጭ ጐትተው በዚያም ነፍሱን እስከአሳለፈ ድረስ በደንጊያ ወገሩት። በዚያንም ጊዜ ከሰማይ ብርሃን ወርዶ በሥጋው ላይ እንደ ምሰሶ ተተከለ ወደ ሰማይም ደርሶ አሕዛብ ሁሉ ወደርሱ ሲመለከቱ ነበር።
እግዚአብሔርም የአንዲት አይሁዳዊት ሴት ልቡናዋን ገለጠላት እርሷም በውስጥዋ ሽንገላና ቅናት ጠብ የሌለባት ናት የኦሪትንም ሕግ የምትጠብቅ ነበረች እርሷም ይህን ብርሃን አይታ ይህ ሰው እውነተኛ ነው አለች። ያን ጊዜም በላይዋ ብርሃን ወረደ እንዲህ ብላ ጮኸች እኔ በቅዱስ አጋቦስ ፈጣሪ የእግዚአብሔር ልጅ በሆነ በጌታ ኢየሱስ የማምን ክርስቲያን ነኝ እግዚአብሔርንም ከፍ ከፍ እያደረገች ስታመሰግነው በደንጊያ ወገሩዋት ነፍሷንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጠች።
✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞✞
#አባ_ዘካርያስ
በዚህችም ቀን በምግባር ፍጹም የሆነ ተጋድሎውም የበዛ አባ ዘካርያስ አረፈ፡፡ እርሱንም ነፍሱ ከሥጋው በምትለይ ጊዜ አባ ሙሴ ወንድሜ ሆይ ምን ታያለህ አለው እርሱም ለእኔስ ዝምታ ይሻለኛል አለ ነፍሱም ስትወጣ አባ ኤስድሮስ ሰማይ ተከፍቶ አየ ልጄ ዘካርያስ ሆይ የመንግሥተ ሰማያት በር ተከፍቶልሃልና ደስ ይበልህ አለው በእንዲህም ያለ ሁኔታ አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳኑ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
(#ስንክሳር_ዘወርኀ_የካቲት እና #መጋቤ_ሐዲስ_ሮዳስ)
Comments
Post a Comment