†✝† እንኳን ለታላቁ ነቢይ ቅዱስ ዘካርያስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †✝†
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††
††† ቅዱስ ዘካርያስ ነቢይ †††
††† ነቢይ ማለት በቁሙ ኃላፍያትን (አልፎ የተሠወረውን ምሥጢር): መጻዕያትን (ገና ለወደ ፊት የሚሆነውን) የሚያውቅ ሰው ማለት ነው:: ሃብተ ትንቢት የእግዚአብሔር የባሕርይ ገንዘቡ ሲሆን እርሱ ለወደደው ደግሞ በጸጋ ይሰጠዋል:: እነዚህም ከጌታ ሃብተ ትንቢት የተሰጣቸው አባቶችና እናቶች "ቅዱሳን ነቢያት" በመባል ይታወቃሉ::
ዘመነ ነቢያት ተብሎ የሚታወቀው ብሉይ ኪዳን ቢሆንም እስከ ምጽዓት ድረስ ጸጋውን እግዚአብሔር ለፈቀደላቸው አይነሳቸውም:: በሐዋርያት መካከልም ቅዱስ አጋቦስን የመሰሉ ነቢያት ነበሩ:: (ሐዋ. 11:27) ቅዱሳን ነቢያት ከእግዚአብሔር እየተላኩ ሰውን ከፈጣሪው እንዲታረቅ ይመክራሉ: ይገስጻሉ::
ከበጐ ሃይማኖታቸውና ንጽሕናቸው የተነሳም እግዚአብሔርን በተለያየ አርአያና አምሳል አይተውታል::
"እስመ በአንጽሖ መንፈስ ርዕይዎ ነቢያት ለእግዚአብሔር : ወተናጸሩ ገጸ በገጽ::" እንዳለ አባ ሕርያቆስ:: (ቅዳሴ ማርያም)
የብዙ ነቢያት ፍጻሜአቸው መከራን መቀበል ነው:: እውነትን ስለ ተናገሩ: አንዳንዶቹም በእሳት: አንዳንዶቹም በሰይፍ: አንዳንዶቹም በመጋዝ ተፈትነዋል:: ሌሎቹ ለአናብስት ሲጣሉ ቀሪዎቹ ደግሞ በድንጋይ ተወግረዋል::
ስለዚህም መከራቸው ለቤተ ክርስቲያን መሠረት ተብለዋል:: ጌታም ለደቀ መዛሙርቱ "ሌሎች ደከሙ:: እናንተ በድካማቸው ገባችሁ::" ብሎ የነቢያቱን መከራ ተናግሯል:: (ዮሐ. 4:36)
ነቢያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እና ድንግል እናቱን ለማየት ብዙ ጥረዋል:: ሽተዋልም:: "ብዙ ነቢያትና ጻድቃን እናንተ የምታዩትን ሊያዩ ሹ" እንዳለ ጌታ በወንጌል:: (ማቴ. 13:16, 1ጴጥ. 1:10) ዛሬ ግን በሰማያት ጸጋ በዝቶላቸው: ክብር ተሰጥቷቸው ሐሴትን ያደርጋሉ::
ቅዱሳን ነቢያት በዋነኝነት "አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት" : "አራቱ ዐበይት ነቢያት" : "አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት" እና "ካልአን ነቢያት" ተብለው በ4 ይከፈላሉ::
††† "አሥራ አምስቱ አበው ነቢያት" ማለት:-
1.ቅዱስ አዳም አባታችን
2.ሴት
3.ሔኖስ
4.ቃይናን
5.መላልኤል
6.ያሬድ
7.ኄኖክ
8.ማቱሳላ
9.ላሜሕ
10.ኖኅ
11.አብርሃም
12.ይስሐቅ
13.ያዕቆብ
14.ሙሴ እና
15.ሳሙኤል ናቸው::
††† "አራቱ ዐበይት ነቢያት"
1.ቅዱስ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል
2.ቅዱስ ኤርምያስ
3.ቅዱስ ሕዝቅኤል እና
4.ቅዱስ ዳንኤል ናቸው::
††† "አሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት"
1.ቅዱስ ሆሴዕ
2.አሞጽ
3.ሚክያስ
4.ዮናስ
5.ናሆም
6.አብድዩ
7.ሶፎንያስ
8.ሐጌ
9.ኢዩኤል
10.ዕንባቆም
11.ዘካርያስ እና
12.ሚልክያስ ናቸው::
††† "ካልአን ነቢያት" ደግሞ:-
*እነ ኢያሱ
*ሶምሶን
*ዮፍታሔ
*ጌዴዎን
*ዳዊት
*ሰሎሞን
*ኤልያስ እና
*ኤልሳዕ . . . ሌሎችም ናቸው::
††† ነቢያት በከተማም ይከፈላሉ::
*የይሁዳ (ኢየሩሳሌም):
*የሰማርያ (እሥራኤል) እና
*የባቢሎን (በምርኮ ጊዜ) ተብለው ይጠራሉ::
††† በዘመን አከፋፈል ደግሞ:-
*ከአዳም እስከ ዮሴፍ (የዘመነ አበው ነቢያት):
*ከሊቀ ነቢያት ሙሴ እስከ ነቢዩ ሳሙኤል (የዘመነ መሳፍንት ነቢያት)
*ከቅዱስ ዳዊት እስከ ዘሩባቤል ያሉት (የዘመነ ነገሥት ነቢያት):
*ከዘሩባቤል ዕረፍት እስከ መጥምቁ ዮሐንስ ያሉት ደግሞ (የዘመነ ካህናት ነቢያት) ይባላሉ::
††† ስለ ቅዱሳን ነቢያት በጥቂቱ ይህንን ካልን ወደ ዕለቱ በዓል እንመለስ::
††† ቅዱስ ዘካርያስ ቁጥሩ ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት ሲሆን ዘመነ ትንቢቱም ቅ/ል/ክርስቶስ በ450 ዓ/ዓ አካባቢ ነው:: "ደቂቀ ነቢያት" ማለት በጥሬው "የነቢያት ልጆች" ማለት ነው:: አንድም የጻፏቸው ትንቢቶች ሲበዙ 14 ምዕራፍ: ሲያንስ አንድ ምዕራፍ ያላቸው ናቸውና ደቂቅ ይላቸዋል::
††† ነቢዩ ቅዱስ ዘካርያስ:-
*ከክርስቶስ ልደት 450 ዓመታት በፊት የነበረ::
*በጻድቅነቱ የተመሰከረለት::
*14 ምዕራፎች ያሉት ሐረገ - ትንቢት የተናገረ::
*ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራ በስፋት የተነበየ ነቢይ ሲሆን ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያትም አንዱ ነው::
††† የአባታችን በረከት ይደርብን::
††† የካቲት 15 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ዘካርያስ ነቢይ (ከአሥራ ሁለቱ ደቂቀ ነቢያት አንዱ)
2.ቅዱስ አባ በፍኑትዮስ ገዳማዊ (ከጻድቅነቱ ባሻገር በግብጽ በርሃ የሚኖሩ የብዙ ቅዱሳንን ዜና ሕይወት የጻፈ አባት ነው::)
3.ቅዱሳን አርብዐ ሐራ ሰማይ (40 የሰማይ ጭፍሮች) ለ40 ቀናት ሰብስጥያ በምትባል ሃገር መከራ ተቀብለው በሰማዕትነት ያለፉ ክርስቲያን ጓደኛሞች::
††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ኢየሉጣ
2.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት)
3.ቅዱስ ሚናስ ግብጻዊ
4.ቅድስት እንባ መሪና
5.ቅድስት ክርስጢና
††† ". . . የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:: 'ወደ እኔ ተመለሱ . . . እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ::' " †††
(ዘካርያስ ፩፥፫)
††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
✝ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together
https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━⊱✿⊰━━
Comments
Post a Comment