#የእሑድ_ውዳሴ_ማርያም_ትርጓሜ ፠
በዚህ ዕለት እመቤታችን ከወትሮው ይልቅ ቀደም ብላ
መጥታለች፡፡ “ዛቲ ዕለት ተዓቢ እምኩሎን ዕለታት፤
ወውዳሲያቲሃኒ የዓብያ እምኵሉ ውዳሴያት - ከዕለታት ኹሉ ይህቺ ዕለት ታላቅ ናት፤ ከውዳሲያቱም ኹሉ የዚች ዕለት ውዳሴ ታላቅ ነው” አለችውና ባረከችው፡፡ እርሱም በቤተ መቅደስ ባሉ ንዋያት ማለትም፡- በመሶበ ወርቅ፣ በተቅዋመ ወርቅ፣ በማዕጠንተ ወርቅ፣ በበትረ አሮን እየመሰለ ሲያመሰግናት አድሯል፡፡
፩. ንዕድ ክብርት ሆይ! ከሴቶች ተለይተሽ የሥላሴ ባለሟል ተባልሽ፡፡ ከተለዩ የተለየሽ፣ ከከበሩ የከበርሽ፣ ቅዱሳን ኪሩቤል የተሣሉብሽ፣ ቅዱሳን ካህናት የሚያመሰግኑሽ ኹለተኛ ክፍል አንቺ ነሽ /ዘጸ.፳፮፡፩-፴/፡፡ ሕግ የተጻፈባት ጽላት ያለብሽ የምትባዪ አንቺ ነሽ /ዘጸ.፴፪፡፲፭-፲፱/፡፡ ኪዳንም ያልኹት በእግዚአብሔር ጣቶች የተጻፉ (በግብር አምላካዊ የተገኙ) ዐሥሩ ቃላት ናቸው፡፡ ዐሥርቱ ቃላትን በጽላቱ ጽፎ እንዳኖረ ኹሉ ዋሕድ ቃለ እግዚአብሔርም በአፃብዐ መንፈስ ቅዱስ (ያለ ወንድ ዘር፣ በግብረ መንፈስ ቅዱስ) በማኅፀንሽ እንዲቀረጽ ኾኗልና የሙሴ ጽላት አንቺ ነሽ /ቅዳ.ማር. ቁ.፴፫/፡፡ ዐጤ ዘርዐ ያዕቆብም በነገረ ማርያም መጽሐፉ፡- “… ወማኅፀናሰ ለማርያም ድንግል በክልኤ ይትሜሰል በጽላት ዘተጽሕፈ ውስቴታ ዐሠርተ ቃላት፡፡ ወዐሠርተ ቃላት ቀዳሜ ስሙ ለወልዳ ውእቱ ዘውእቱ የውጣ ዘተሰምየ በኈልቄ ዐሠርተ ቃላት - … በኹለት ወገን ድንግል የምትኾን የማርያም ማኅፀንስ ዐሥሩ ቃላት በውስጧ በተጻፈ ጽላት ይመሰላል፡፡
ዐሥሩ ቃላትም የልጇ የኢየሱስ ክርስቶስ የመዠመርያ ስሙ ነው፤ ያውም የውጣ በዐሥሩ ቃላት የተጠራ ነው” ብሏል / ነገረ ማርያም በብሉይ ኪዳን፣ ክፍል ፩፣ ገጽ ፻፳፰፣ በመጋቤ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ/፡፡ከአንቺ ሳይለወጥ ሰው ኾነን፡፡ ለኦሪት ሳይኾን ለወንጌል ሊቀ
ካህናት ኾነን፡፡ ለምድረ ርስት ሳይኾን ለመንግሥተ ሰማያት አስታራቂ ኾነን፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “በውድ ልጁም፥ እንደ ጸጋው ባለ ጠግነት መጠን፥ በደሙ የተደረገ ቤዛነታችንን አገኘን፤ እርሱም የበደላችን ስርየት ነው” እንዲል በከበረ ደሙ ፈሳሽነት በዓለመ ሥጋ በዓለመ ነፍስ ያሉትን አዳናቸው /ኤፌ.፩፡፯/፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም የኤፌሶንን መልእት በተረጐመበት በአንደኛው ድርሳኑ ላይ፡- “ከእግዚአብሔር ዘንድ ያገኘነው ሥርየተ ኃጢአት በርግጥ ታላቅ ነው፡፡ ተቀዳሚ ተከታይ በሌለው በልጁ ደም መኾኑ ግን ከምንም በላይ ታላቅ ነው” በማለት የእግዚአብሔር ከኅሊናት የሚያልፈውን የማዳን ምሥጢር (ፍቅር) በመደነቅ ተናግሯል፡፡
በከበረ ደሙ ፈሳሽነት በዓለመ ሥጋ በዓለመ ነፍስ ያሉትን ካዳነ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፪. ኹል ጊዜ ንጽሕት የምትኾኚ አምላክን የወለድሽ
እመቤታችን ሆይ! ስለዚህ ነገር ኹላችን እናከብርሻለን፤
እናገንሻለንም፡፡ ሰውን ከሚወድ ሰው ከሚወደው ከርሱ
ይቅርታን እናገኝ ዘንድ ኹል ጊዜ ዓይነ ልቦናችንን ወዳንቺ እንሰቅላለን፡፡ ሸምሸር ሰጢን ከሚባል ከማይነቅዝ (በአምልኮተ ጣዖት ከማይለወጥ) እንጨት የተቀረጸ በአፍአ በውስጥ በወርቅ የተለበጠ ታቦት አካላዊ ቃልን ይመስልልናል /ዘጸ.፳፭፡፱-፳/፡፡
ይህ ንጹሕ የሚኾን፣ መለወጥ የሌለበት እርሱ ባለመለወጡ አለመለወጧን ነገራት፤ ከአብ ዕሪና ባለመለየቱም አለማለየቷን ነገራት (አምላክ ወሰብእ ኾኖ እርሷም እም ወድንግል መኾኗን ነገራት)፡፡ ከጥበብ በሚበልጥ ጥበብም ዘር ምክንያት ሳይኾነው እንደ እኛ ሰው ኾነ፡፡ አበው፡- “ዓለሙን ከፈጠረበት ጥበብ ይልቅ ሰው ኾኖ ዓለሙን ያዳነበት ጥበብ ይበልጣል” የሚሉትም ስለዚሁ ነው፡፡ አደፍ ጉድፍ ሳያገኝሽ መለኮቱን አዋሕዶ ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ
ነፍስ ነሥቶ ሰው ኾነ፡፡ መለኮቱን አዋሕዶ ሰው ከኾነ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኝልን፡፡
፫. እግዚአብሔር በፈጠራቸው በኪሩቤል አምሳል፤ ሙሴ የሣላቸው ኪሩቤል የሚጋርዱሽ መቅደሰ ሙሴ አንቺ ነሽ፡፡ አንድም እግዚአብሔር በፈጠራቸው በኪሩቤል አምሳል፣ ሰሎሞን የሣላቸው ኪሩቤል የሚጋርዱሽ መቅደሰ ሰሎሞን
አንቺ ነሽ፡፡ ጌታ በማኅፀንሽ ያደረብሽ አማናዊቷ መቅደስ አንቺ ነሽ፡፡ ሳይለወጥ ካንቺ ሰው የኾነው አካላዊ ቃል በውስጥ በአፍአ በነፍስ በሥጋ ኃጢአታችንን የሚያስተሠርይልን ኾነ፡፡
ኃጢአታችንን ከሚያስተሠርይልን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኝልን፡፡
፬. መና ያለብሽ መሶበ ወርቅ አንቺ ነሽ /ዘጸ.፲፮፡፴፫-፴፬/፡፡
ይኸውም መና የተባለው ከሰማይ የወረደና ፱ ወር ከ፭ ቀን በማኅፀንሽ የተሸከምሽው ነው፡፡ እርሱም “አበዊክሙሰ መና በልዑ በገዳም ወሞቱ - አባቶቻችሁ በምድረ በዳ መና በሉ፤ ሞቱም” እንዳለው ያይደለ፤ ይልቁንም ለሰው ኹሉ ሕይወት የሚያድል ኅብስት ነው /ዮሐ.፮፡፶/፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድም በአንቀጸ ብርሃን ላይ፡- “አስተማሰልናኪ ቅድስት ወብፅዕት ስብሕት ወቡርክት ክብርት ወልዕልት በመሶበ ወርቅ ዘውስቴታ ኅብስተ ሕይወት ዘወረደ እምሰማያት ወሃቤ ሕይወት ለኵሉ ዘየአምን ኪያሁ ወይበልዕ እምኔሁ በአሚን
ወበልብ ሥሙር ምስለ እለ በየማኑ - የተለየሽና ደግ የኾንሽ የተመሰገንሽና የተባረክሽ የከበርሽና ከፍ ከፍ ያልሽ ሆይ! የሕይወት ኅብስት ባለበት በወርቅ መሶብ መሰልንሽ፡፡ የሕይወት ኅብስትም በቀኙ ካሉ ጻድቃን ጋር እርሱን ለሚያምን በሃይማኖትና ፈቃደኛ በኾነ ልብ ከእርሱ ለሚበላም ኹሉ ሕይወትን የሚሰጥ ከሰማይ የወረደ ነው” ብሏል /ቁ.፯/፡፡ ዳግመኛም አባ ጊዮርጊሥ ዘጋሥጫ፡- ኦ መሶብ ቤተ ልሔማዊት ዘወለደቶ ለኅብስተ ሰማይ ዘኢያብቌልዎ ዝናማት ወዘኢሐፀንዎ አየራት - ዝናማት ያላበቀሉትን አየራት ያላሳደጉትን የሰማዩን እንጀራ የወለድሽው ቤተ ልሔማዊት መሶብ ሆይ” በማለት መስክሯል /አርጋኖን ዘረቡዕ/፡፡ ከአባቶች አንዱም፡- “ድንግል ሆይ! በእውነቱ አንቺ ከታላላቅ ይልቅ ታላቅ ነሽ፡፡ ማኅደረ ቃለ አብ ሆይ! አንቺን ሊተካከል የሚችል ታላቅ ማን ነው? ድንግል ሆይ! ከየትኛው ፍጥረት ጋር አወዳድርሻለሁ? አንቺ ቀድሞ በወርቅ ካጌጠችው የሕጉ ታቦት ይልቅ በንጽሕና ያጌጥሽ ታላቅ ነሽ! እውነተኛውን መና የተሸከምሽ መሶበ ወርቅ አንቺ ነሽ፡፡ መና የተባለውም መለኮት የተዋሐደው ሥጋው ነው” ብሏል፡፡ ኅብስተ ሕይወት ከሚባል ልጅሽ ጸንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፭. ብርሃንነት ያለውን ፋና የተሸከምሽ የወርቅ ተቅዋም
(መቅረዝ) አንቺ ነሽ /ዘጸ.፳፭፡፴፩-፵/፡፡ ይኸውም ፋና ለሰው ኹሉ ዕውቀትን የሚገልጽ ብርሃን ነው፡፡ ጥንት ከሌለው ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ነው፡፡ ከባሕርይ አምላክ የተገኘ የባሕርይ አምላክ ነው፡፡ ሳይለወጥ ካንቺ ሰው የኾነው ነው፡፡ ሰውም በመኾኑም በድንቁርና በቀቢጸ ተስፋ ለምንኖር ለኛ አበራልን (ዕውቀትን ገልጸልን)፡፡ በጥበቡ ባደረገው ሥጋዌ እግረ ልቡናችንን ወደ ሕገ ወንጌል ጎዳና አቀናልን /ኢሳ.፱፡፩- ፪፣ ማቴ.፬፡፲፬-፲፮/፡፡ ታላቁ የዜማ አባት ሊቁ ቅዱስ ያሬድም፡-
“አንቲ ውእቱ ተቅዋም ዘወርቅ ዘኢገብራ እደ ኬንያ ዘሰብእ… - የብልሐተኛ እጅ ያልሠራት በውስጧም መብራት የሚያበሩባት የወርቅ መቅረዝ አንቺ ነሽ፤ ራሱ የአብ ብርሃን ያበራባታል እንጂ፡፡ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ወደ አንቺ መጥቶ አደረ፡፡ አምላክነቱም በዓለም ኹሉ አበራ፡፡ ጨለማን ከሰዎች ላይ አራቀ፡፡ እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ በብርሃኔ እመኑ፤ ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ ብሎ በሚያድን ቃሉ አዳነን” ብሏል /
ቁ.፰፣ ዮሐ.፲፪፡፴፭፣ ፩ኛ ዮሐ.፩፡፭/፡፡ በጥበቡ ባደረገው
ሥጋዌ እግረ ልቡናችንን ወደ ሕገ ወንጌል ጎዳና ከአቀናልን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩንእንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፮. ቡሩክ አሮን ከቤተ መቅደስ ይዞሽ የወጣ እሳትነት ያለውን ፍሕም የተሸከምሽ ማዕጠንተ ወርቅ አንቺ ነሽ /ዘጸ.፴፡፩-፰/፡፡ ፍሕም የተባለውም በአፍኣ በውስጥ በሥጋ በነፍስ ኃጢአትን የሚያስተሠርይ ነው፡፡ ይኸውም ከአንቺ ሰው የኾነውና “ወአንከረ አብ እምዝንቱ መሥዋዕት - ከዚህ መሥዋዕት የተነሣ አብ አደነቀ” እንዲል /ሃይ.አበ.፷፰፡፳፫/ ለአባቱ ራሱን ያማረ የተወደደ መሥዋዕት አድረጎ ያቀረበ አካላዊ ቃል ነው /ኤፌ.፭፡፪/፡፡ ራሱን ያማረ የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ካቀረበ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፯. አካላዊ ቃልን የወልድሽልን መልካም ርግብ ማርያም ሆይ! ደስ ይበልሽ፡፡ ከእሴይ ሥር የወጣሽ መዓዛ ሠናይ አበባ አንቺ ነሽ፡፡ መዐዛ ሰናይ የተባለውም የቅዱሳን መዐዛ የሚኾን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው /መጽሐፈ ድጓ፣ ገጽ.፻፺፱/፡፡ መዐዛ ሠናይ ከተባለ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፰. ሳይተክሏት የበቀለች፣ ውሃ ሳያጠጧትም የለመለመች ያበበች ፲፪ በኵረ ሎሚ ያፈራች የአሮን በትር ነበረች /ዘኁ.፲፯፡፩-፲/፡፡ ከቤተ መቅደስ ፲፪ ዓመት ኑረሽ፣ ዘር ምክንያት ሳይኾነው ሰው ኾኖ ያዳነን እውነተኛ አምላካችንን ክርስቶስን የወለድሽልን አንቺም እንደርሷ ነሽ /ኢሳ.፯፡፲፬/፡፡ አባ ጊዮርጊሥ ዘጋሥጫም በአርጋኖን ዘሰኑይ ላይ፡- “ዕፀ ከርካዕ እንከ እሰምየኪ እስመ ከርካዕ ሠናየ ይጸጊ፤ ወሠናየ ይፈሪ፤ ወሠናየ ይጼኑ፤ ወከመ በትር ይቡስ ዘቦ ላዕሌሁ ወፅአ ዑፃዌ
ክህነት አሥረጸ አዕጹቀ ወአቊጸለ ከርካዕ ምዑዘ፤ ወከማሁ አንቲኒ ነበርኪ ውስተ ቤተ መቅደስ ዐሠርተ ወክልኤተ ክራማተ ወፀነስኪዮ ለኢሱስ ዘእንበለ ዘርዐ ብእሲ - እንግዲህ የሎሚ ዕንጨት ብዬ እጠራሻለሁ፡፡ ሎሚ መልካሙን ያብባል፤ መልካሙን ፍሬ ያፈራል፡፡ በጐ በጐ ይሸታልና ዕጣ እንደ ወጣበት ደረቅ በትር ሳይተከል በቤተ መቅደስ ለምልሞ፣ ቅንጣት አውጥቶ፣ አብቦ ተገኘ፡፡ ሽታው ያማረ የተወደደውን ሎሚ አፈራ፡፡ እንዲሁም አንቺ በቤተ መቅደስ ዐሥራ ኹለት ዓመት ተቀምጠሸ ያለ ወንድ ዘር መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ፀነስሺው” በማለት አብራርቶታል፡፡ ዳግመኛም ሊቁ ቅዱስ ያሬድ፡- “ሳይተክሏትና
ውሃ ሳያጠጧት የለመለመች የአሮን በትር በቤተ መቅደስ ነበረች፡፡ ለካህናት ዝግጁ ያደረጋት ነበረች፡፡ አንቺም በቅድስናና በንጽሕና ጸንተሸ እንደ እርሷ በቤተ መቅደስ ኖርሽ፡፡ ከቤተ መቅደስም በክብር በታላቅ ደስታ ወጣሽ፡፡ በእውነት የሕይወት ፍሬ የኾነ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከአንቺ ተገኘ፡፡ ቅድስት ሆይ! ከመልአኩ እንደተረዳሽው ከወንድ ያለመገናኘት ልጅን አገኘሽ፡፡ መልአኩ መንፈስ ቅዱስ መጥቶ ያድርብሻል፤ የልዑል ኀይልም ይጸልልሻል ብሎ ነግሮሽ ነበርና” በማለት አማናዊቷ የአሮን በትር እርሷ መኾኗን አስተምሯል /ቁ.፲፩/፡፡ ሰው ኾኖ ካዳነን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን
እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፱. ምልዕተ ክብር ሆይ! ከቅዱሳን ኹሉ ይልቅ ትለምኚልን ዘንድ ላንቺ ይጋባል፡፡ ከሊቃነ ጳጳሳት አንቺ ትበልጫለሽ፡፡ ከመምህራን፣ ከሐዋርያት፣ ከ፸ አርድእትም አንቺ ትበልጫለሽ፡፡ ከሱራፌልና ከኪሩቤል ይልቅ የሚበልጥ የመወደድ የመፈራት ግርማ አለሽ፡፡ ሊቁ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴው፡- “ኦ ሙኃዘ ፍስሐ! ፈድፋደ ብኪ ግርማ ራዕይ ዘየዐቢ እም ኪሩቤል እለ ብዙኃት አዕይንቲሆሙ ወሱራፌል ፮ ክነፊሆሙ - የደስታ (የጌታ) መገኛ የምትኾኚ እምቤታችን
ሆይ! ዐይናቸው ብዙ ከሚኾን ከኪሩቤል፣ ክንፋቸው ስድስት ከሚኾን ከሱራፌል ይልቅ በምእመናን ዘንድ የመወደድ፣ በአጋንንት በአይሁድ በመናፍቃን ዘንድ የመፈራት፣ በሥላሴ ዘንድም የባለሟልነት መልክ አለሽ” ይላል /ቁ.፳፪/፡፡ በእውነት የባሕርያችን መመኪያ አንቺ ነሽ፡፡ ለሰውነታችን ሕይወትን የምታማልጅን አንቺ ነሽ፡፡ አንድነቱን ሦስተነቱን በማመን አጽንቶ ሥጋዌውን በማመን ያፀናን ዘንድ፣ “ጸጋሰ ሥርየተ ኃጢአት ይእቲ” እንዲል በቸርነቱ ብዛት ኃጢአታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ አማልጅን፡፡
ኃጢአታችንን ከሚያስተሠርይልን ልጅሽ ፅንዕት በድንግልና እመቤታችን
ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ::" /ማቴ ፫:፫/
ዝክረ ቅዱሳንን ተማሩ ብለን እንለምናችኋለን!!
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
✝ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together
https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━━━
Comments
Post a Comment