#የሰኞ_ውዳሴ_ማርያም_ትርጓሜ
ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም እመቤታችን ከባረከችው በኋላ ምስጋናውን የጀመረው “ፈቀደ እግዚእ…” ብሎ ነው፡፡
፩. በመቅድመ ወንጌል “ወአልቦቱ ካልእ ሕሊና ዘንበለ ብካይ ላዕለ ኃጢያቱ - በኃጢአቱ ከማዘን፣ ከማልቀስ በቀር ሌላ ግዳጅ አልነበረውም” እንዲል ጌታ ፭ ሺህ ከ፭፻ ዘመን በግብርናተ ዲያብሎስ ያዝን ይተክዝ የነበረ አዳምን ነጻ ያደርገው (ያድነው) ዘንድ ወደደ፡፡ ምድራዊ ንጉሥ የተጣላውን አሽከር “ሰናፊልህን (ልብስህን) አትታጠቅ፤ እንዲህ ካለ ቦታም አትውጣ” ብሎ ወስኖ ያግዘዋል፡፡ በታረቀው ጊዜ ግን ርስቱን፣ ጉልበቱን፣ ቤቱን፣ ንብረቱን እንደሚመልስለት ኹሉ ንጉሠ ሰማይ ወምድር እግዚአብሔርም “ጥንቱንም መሬት ነህና ወደ መሬት ተመለስ” /ዘፍ.፫፡፲፱/ ብሎ ፈርዶበት የነበረ አዳምን ይቅር ብሎ ወደ ቀደመ ቦታው ወደ ገነት፣ ወደ ቀደመ ክብሩ ወደ ልጅነት ይመልሰው ዘንድ ወደደ /ሉቃ.፳፫፡፵፫/፡፡
ሊቁ (ቅዱስ ኤፍሬም) በኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ ፫ ቁጥር ፱ ያለውን ኃይለ ቃል ሲተረጕምም እንዲህ ይላል፡- “ቸር ወዳጅ የኾነው እግዚአብሔር አዳምና ሔዋን ወዲያው እንደተሳሳቱ ፍርዱን አላስተላለፈባቸውም፤ ታገሣቸው እንጂ፡፡ ይኸውም ምኅረት ቸርነቱን ይለምኑት ዘንድ ነው፡፡ እነርሱ ግን አልለመኑትም፡፡ እግዚአብሔርም ምንም ሳይናገራቸው በገነት ውስጥ በእግር እንደሚመላለስ ሰው ኾኖ በድምፅ ብቻ መጥራቱን ቀጠለ፡፡ አዳምና ሔዋን ግን አሁንም አልመለስ አሉ፡፡ በመጨረሻም አምላክ ድምፁን ማሰማት ጀመር፡፡ ‘አዳምን ወዴት ነህ?’ ይላቸው ጀመር፡፡ አስቀድሞ በእግር እንደሚመላለስ ሰው ኾኖ በድምፅ ብቻ መጥራቱ መንገድ ጠራጊው ዮሐንስን እንደሚልክላቸው፣ ቀጥሎ ድምፅ አሰምቶ ወዴት ነህ ብሎ መፈለጉም ወልደ እግዚአብሔር ራሱ በተዋሕዶ ፍጹም ሰው ኾኖ ሊያድናቸው እንደ ፈቀደ ያጠይቃል” ይላል ፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም ኦሪት ዘልደትን በተረጐመበት በ፲፯ኛው ድርሳኑ ላይ፡- “በዚህ ንግግሩ የእግዚአብሔር ከአእምሮ የሚያልፈውን ፍቅሩን እንመለከታለን፡፡ አንድ አባት ልጁ የማይረባውን ነገር በማድረግ ከክብሩ ቢዋረድም አባቱ እጅግ እንዲወደውና ወደ ቀደመ ክብሩ ይመልሰው ዘንድ እንዲደክም፤ እግዚአብሔርም ከሰው ልጆች ጋር ይህን የመሰለ ፍቅር ሲያሳይ እናስተውላለን፡፡ አንድ ሐኪም ወደ ታማሚው አልጋ ጠጋ ብሎ በሽተኛውን እንዲጠይቀውና አስፈላጊውን ኹሉ እንደሚያደርግለት፣ ሰው ወዳጁ እግዚአብሔርም ወደ አዳም ጠጋ ብሎ ሲያነጋግረው እንመለከታለን” ይላል፡፡
ዳግመኛም በሌላ አንቀጽ “አዳም ሆይ ወዴት ነህ” ማለቱ፣ ለአቅርቦት መኾኑን ሲገልጥ፡- “አዳም ሆይ! ምን ኾንክብኝ? በመልካም ቦታ አስቀምጬህ ነበር፤ አሁን ግን ቦታህ ተለወጠብኝ፡፡ ብርሃን ተጐናጽፈህ ነበር፤ አሁን ግን ጨለማ ውስጥ አይሃለሁ፡፡ ልጄ! ወዴት ነህ? ይህ ኹሉ እንደምን ደረሰብህ? በአንተ ውስጥ ያኖርኩት መልኬ ማን አበላሸብኝ? በዚህ ያህል ፍጥነት የጸጋ ልብስህን ገፎ የጽልመት ልብስ ያከናነበህ ማን ነው? ውዴ! ባለጸጋ አድርጌ ፈጥሬህ አልነበረምን? ታድያ አሁን ድኽነት ውስጥ የከተተህ ማን ነው? ያን የግርማ ልብስህን ሰርቆ ዕራቆትህ ትኾን ዘንድ ያደረገህ ማን ነው? እኮ የጸጋ ልብስህን እንድታጣ ያደረገህ ማን ነው? ይህን የመሰለ ቅጽበታዊ መለወጥ ከወዴት መጣብህ? የከበረ ዕንቁህን እንድትጥል ያደረገህ ምን ቢገጥምህ ነው? አክብሮ በተወደደ ቦታ ካስቀመጠህና ኹል ጊዜ በስስት ዐይን ሲያነጋግርህ ከነበረው አምላክህ ተደብቀህ እንድትሸሸግ ያደረገህ ምንድነው? ማንም የወቀሰህ ሳይኖር፣ እንዲህ እንዲህ አድርገህ በድለሃል ብሎ የመሰከረብህ ሳይኖር ይህን ያህል በፍርሐት መናጥ ከወዴት አገኘህ?” ይላል፡፡
ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ሆይ! ፭ ሺሕ ከ፭፻ ዘመን በግብርናተ ዲያብሎስ የነበረ አዳምን ነፃ ካደረገው ልጅሽ ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኝልን፡፡ “ቅድስት” ማለቱ ንጽሕት፣ ጽንዕት፣ ክብርት ልዩ ሲል ነው፡፡ ይኸውም፡-
· ሌሎች ሴቶች ከነቢብ ከገቢር ቢነጹ ከሐልዮ አይነጹም፡፡ እሷ ግን የዕንቆራው ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ቴዎዶጦስ “ወኢረኩሰት በምንትኒ እምዘፈጠራ ድንግል በሕሊናሃ ወድንግል በሥጋሃ- ከፈጠራት ጀምሮ በምንም በምን (በሕሊናዋም በሥጋዋም) ከድንግልናዋ አልተለወጠችም” /ሃይ.አበ.፶፫፡፳፪/ እንዲል ከነቢብ፣ ከገቢር፣ ከሐልዮ ኃጢአት ንጽሕት ናትና፡፡
· ጽንዕትም አለ፡፡ ሌሎች ሴቶች ቢጸኑ ለጊዜው ነው፤ ኋላ ተፈትሖ አለባቸው፡፡ እሷ ግን ቅድመ ፀኒስ ጊዜ ፀኒስ፤ ቅድመ ወሊድ፣ ጊዜ ወሊድ፣ ድኅረ ወሊድ ጽንዕት (ወትረ ድንግል) ናትና፡፡
· ክብርትም አለ፡፡ ሌሎችን ሴቶች ብናከብቸው ጻድቃንን፣ ሰማዕታትን፣ ጳጳሳትን፣ ሊቃውንትን ወለዱ ብለን ነው፡፡ እሷን ግን ወላዲተ አምላክ ወልዳልናለች ብለን ነውና፡፡
· ልዩም አለ፡፡ እናትነትን ከድንግልና፣ አገልጋይነትን ከእናትነት፣ ወተትን ከድንግልና ጋር አስተባብራ የተገኘች፤ በድንግልናም እያለች ከጡቶቿ ወተት ተገኝተው በዝናም አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ የሚመግብ መጋቤ ፍጥረታት አምላክን የወለደች፤ እሳታውያን የሚኾኑ ኪሩቤል ሱራፌልም በፍርሐት በረዐድ ኹነው ዙፋኑን የሚሸከሙት እሳተ መለኮት ጌታን ፱ ወር ከ፭ ቀን በማሕፀኗ የተሸከመች፣ በክንዷ የታቀፈች፣ በዠርባዋ ያዘለች ከእመቤታችን በቀር ሌላ ሴት የለችምና፡፡
“ለምኚልን” ሲልም ልክ በዚህ ምድር እንደነበረው ዓይነት ልመና ከዚያ በኋላ ኖሮባት አይደለም፡፡ ስንኳን በሷና በሌሎችም የለባቸውም፡፡ በቀደመ ልመናዋ የምታስምር ስለ ኾነ እንዲህ አለ እንጂ፡፡ ይኸውም በቃል ኪዳኗ ማለት ነው፡፡ አንድም በቁሙ ይተረጐማል፡፡ ማዘከር (ማሳሰብ) አለና፡፡
“ሰአሊ ለነ ቅድስት” የሚለው ቅዱስ ኤፍሬም የተናገረው አይደለም፡፡ “ታድያ ይህን የጨመረው ማን ነው?” በሚለው ላይም ኹለት ዓይነት አመለካከለት አለ፡፡ “ቅዱስ ያሬድ ለዜማ መከፈያ ተናግሮታል” የሚሉ አሉ፤ “የኋላ ሊቃውንት ተናግረውታል” የሚሉም አሉ፡፡
፪. ወዶም አልቀረም ዘር ምክንያት ሳይኾነው ከድንግል በሥጋ ተወለደ፡፡ “አኮ ወልደ ማርያም በመለኮቱ አላ በከመ ሥርዓተ ትሥብእቱ- በመለኮቱ የማርያም ልጅ አይደለም፤ በተዋሐደው ሥጋ ነው እንጂ” እንዲል ድርሳነ ቄርሎስ በመለኮት ሳይኾን በሥጋ ተወልዶ አዳነን፡፡
ከእናንተ መካከል፡- “ልደቱ በዘርዕ ያላደረገው እንበለ ዘርዕ ያደረገው ስለ ምንድነው?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡-
· አንደኛ፡ “ልደት ቀዳማዊ ተዐውቀ በደኃራዊ” እንዲል ፭ ሺሕ ከ፭፻ ዘመን ሲፈጸም ከእመቤታችን ያለ አባት መወለዱ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት እንደ ተወለደ ለማጠየቅ፤
· ኹለተኛ ደግሞ ሊቃውንቱ እንደሚነግሩን በዘርዕ በሩካቤ ተወልዶ ቢኾን ኖሮ መናፍቃን “ዕሩቅ ብእሲ ነው” ባሉት ነበርና ነው፡፡ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘእንዚናዙ ይህን ሲያብራራው፡- “ሰውም በኾነ ጊዜ እንደ ዕሩቅ ብእሲ በዘር በሩካቤ አልተወለደም፤ አምላክ ሰው ኾነ እንጂ፡፡ እንደ ዕሩቅ ብእሲ በዘር በሩካቤ ተወልዶ ቢኾንስ ብዙ ሰዎች በተሳሳቱ ነበር፤ አምላክ ሰው መኾኑንም ሐሰት ባደረጉት ነበር” ይላል /ሃይ.አበው. ፷፡፲፱/፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም፡- “እንደ እኔስ በዘር በሩካቤ ተወልዶ ቢኾን ብዙ ሰዎች ዕሩቅ ብእሲ ባሉት ነበር፤ አምላክነቱንም በካዱት ነበር” ይላል /ሃይ.አበ. ፷፮፡፴፪/፡፡
አሁንም ከእናንተ መካከል፡- “ያውስ ቢሆን ተፈትሖ ካላት ያላደረገው፣ ተፈትሖ ከሌላት ያደረገው ስለ ምንድነው?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡-
· አንደኛ “እነሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች” ተብሎ የተነገረውን /ኢሳ.፯፡፲፬/ ለመፈጸም ሲኾን፤
· ኹለተኛው ደግሞ ምሳሌውን ለመፈጸም ነው፡፡ ይኸውም አዳም ከኅቱም ምድር ተገኝቷል /ዘፍ.፩፡፳፮/፤ ጌታም በኅቱም ማኅፀን ተወልዷል /ሕዝ.፵፬፡፩/፡፡ ሔዋን በኅቱም ገቦ (ጐን) ተገኝታለች /ዘፍ.፪፡፳፩/፤ ጌታም በኅቱም ማኅፀን ተወልዷል፡፡ ቤዛ ይሥሐቅ የሚኾን በግዕ ከኅቱም ጉንድ ተገኝቷል /ዘፍ.፳፪፡፲፫/፤ ቤዛ ዓለም ክርስቶስም በኅቱም ማኅፀን ተወልዷል፡፡ ጽምዐ እስራኤልን ያበረደ ውሃ ከኅቱም እብን (ዐለት) ተገኝቷል /ዘጸ.፲፯፡፮/፤ ጽምዐ ነፍሳትን ያበረደ ማየ ሕይወት ጌታም በኅቱም ማኅፀን ተገኝቷል፡፡ ጽምዐ ሶምሶንን ያበረደ ውሃ በኅቱም መንሰከ አድግ (የአህያ መንጋጋ) ተገኝቷል /መሳ.፲፭፡፲፱/፤ ጽምዐ ኃጥአንን ያበረደ ማየ ሕይወት ጌታም በኅቱም ማኅፀን ተገኝቷል፡፡ የዚህ ኹሉ ምሳሌ ፍጻሜው አንድ ነው፡፡ ይኸውም ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ‘ከመ ትኩን መራሒተ ለሃይማኖት ዐባይ - ለደገኛው ሃይማኖት መሪ ትኾን ዘንድ’ /ሃይ.አበ.፷፮፡፴፪/ እንዲላት እመቤታችን ጌታን ብትወልደው ማኅተመ ደንግልናዋ እንዳልተለወጠ ኹሉ እርሱም ሰው ሲኾን አምላክነቱ ላለመለመጡ ምሳሌ ነው፡፡ ዳግመኛም እርሷ “ድንግል ወእም” ስትባል መኖሯ እርሱም “አምላክ ወሰብእ” ሲባል ለመኖሩ ምሣሌ ነው፡፡
እናም አዳምን ያድነው ዘንድ የፈቀደ አምላክ ከይሲ ዲያብሎስ ያሳታት ሔዋንን “ጻርሽን ጋርሽን ምጥሽን አበዛዋለሁ” ብሎ እግዚአብሔር ከፈረደባት በኋላ ሊቁ አባ ሕርያቆስ “ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኀያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከ ለሞት- የሰው ፍቅር ከዙፋኑ ስቦ ጐትቶ አወረደው፤ ከሞትም አደረሰው” እንዲል /ቅዳ.ማር. ቁ. ፻፳፭/ ሰውን ወደደና ሔዋንን ነጻ አደረጋት /ገላ.፭፡፩/፡፡ ሔዋንን ነጻ ካደረገ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፫. ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ አዳምን ነጻ ያደርገው (ያድነው) ዘንድ የፈቀደ፣ ሔዋንንም ወድዶ ነጻ ያደርጋት ዘንድ ሰው የኾነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው /ዮሐ.፩፡፲፬/፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚለው ስም የመለኮት ብቻ ወይም የትስብእት ስም ብቻ አይደለም፡፡ “ወእነግር አነሂ ከመ ኢመፍትው እስምዮ ለቃለ እግዚአብሔር ክርስቶስ ዘእንበለ ትስእብት ወኢ ለትስብእት ዘእንበለ መለኮት ክርስቶስሀ ይሰመይ ወእም ቅድመ ትሥጉት አልቦ ዘይሰምዮ በዝንቱ ስም ለቃለ እግዚአብሔር ክርስቶስ- ክርስቶስ ሲል ብትሰማ ብቻ አምላክ እንደኾነ ብቻ ሰውም እንደኾነ አታስብ፡፡ አንድ እንደ መኾኑ ሰው የኾነ አምላክ ነው እንጂ” /ሃይ.አበ.፷፰፡፵/ እንዲል ከኹለት አካል አንድ አካል ከኹለት ባሕርይ አንድ ባሕርይ ቢኾን የወጣለት ስም ነው እንጂ፡፡
አዳምን ነጻ ያደርገው ዘንድ ሰው የኾነው ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ ላይ አደረ /ዮሐ.፩፡፲፬/፡፡ ለአባቱ እንደ አንድ ልጅ ክብር የሚኾን ክብሩንም አየንለት፡፡ ልጅ ለአባቱ አንድ የኾነ እንደኾነ ደጃፍ የመለሰው ማጄት የጎረስው ኹሉ ገንዘቡ ነው፡፡ ለእርሱም “እስመ ኵሉ ዘቦ ለአቡየ ዚኣየ ውእቱ- ለአብ ያለው ኹሉ የእኔ ነው” /ዮሐ.፲፮፡፲፭/ እንዲል የአብ ገንዘብ ኹሉ ገንዘቡ ነውና ለአባቱ እንደ አንድ ልጅ የሚኾን ክብሩን አየንለት፡፡ “ወይሰገድ ከመዋሕድ- እንደ አባቱ ይመለካል” እንዲል ለአባቱ እንደ አንድ ልጅነቱ የሚኾን ክብሩን አየንለት፡፡ የአባቱን ጌትነት በደብረ ሲና እንዳየነ /ዘጸ.፲፱/ የእርሱንም ጌትነት በደብረ ታቦር አየንለት /ማቴ.፲፯፡፩-፰/፡፡ አባቱ በኤልያስ አድሮ አንድ ምዉት /፩ኛ ነገ.፲፯/፣ በኤልሳዕ አድሮ ኹለት ምዉት ሲያስነሣ እንዳየነው /፪ኛ ነገ. ፬/፤ እርሱም ሥጋን ተዋሕዶ የአራት ቀን ሬሳ አልዓዛርን ሲያስነሣ አየነው /ዮሐ.፲፩/፡፡ ይህን ጠቅለል አድርጐ ቅዱስ ባስልዮስ ሲናገረው፡- “ስለ አብ የተናገርነው ኹሉ ለወልድ ገንዘቡ ነው፡፡ በመልክ ይመስለዋል፤ በባሕርይ ይተካከለዋልና፡፡ ወንጌላዊው ዮሐንስ ለአባቱ አንድ እንደ ኾነ ልጅ ክብር ያለ ክብሩን አየን አለ” ይላል /ዮሐ.፩፡፲፬፣ ሃይ.አበ.፴፫፡፳፰/፡፡
የመጽሐፍ ልማድ ኾኖ የብሉዩን ለአብ የሐዲሱንም ለወልድ ሰጥቶ ተናገረ እንጂ ኹሉም በኹሉ አሉ፡፡ ከእናንተ መካከል፡- “ያውስ ቢኾን (ቅዱስ ኤፍሬም) ወዴት ነበርና ነው አየንለት የሚለው?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡- አየንለት የሚለው የብሉዩን የእነ ሙሴን ዐይን ዐይን አድርጎ፤ የሐዲሱን ደግሞ የእነ ጴጥሮስን ዐይን ዐይን አድርጎ መናገሩ ነው፡፡ ይኸውም አባ ሕርያቆስ የሓዋርያትን መብል መብል አደርጎ፡- “በላዕነ ወሰተይነ ምስሌሁ - ከእርሱ ጋር በላን ጠጣን” እንዳለው ማለት ነው /ቅ.ማር. ቁ.፹፮/፡፡
ይህ ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የኾነው ክብሩን ያየንለት ወዳጅ ይቅር ይለን ዘንድ ወደደ፡፡ ይቅር ይለን ዘንድ ከወደደ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና፤ እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፬. ነቢዩ ኢሳይያስ ትንቢት በሚገልጽ መንፈስ ቅዱስ የአማኑኤልን ምሥጢር አየና አሰምቶ ተናገረ፡፡ አማኑኤል ማለት ሰው የኾነ አምላክ ማለት ነውና “ሕፃን ተወለደልን፤ ወልድ ለሕማም ለሞት ተሰጠልን፡፡ አንድም ወልድ ለኩነተ ሥጋ ተሰጠልን ፤ ሕጻንም ኾኖ ተወለደልን” ብሎም ጮኸ /ኢሳ.፱፡፮/፡፡ አትናቴዎስ ሐዋርያዊም “ስለ ድኅነተ ሰብእ የአዳምን ባሕርይ ገንዘብ አደረገ፤ ካሣ ይከፍልልን ዘንድ ቃል ሥጋ ኾነ” ይላል /Ep. 61:3./፡፡ ወልድ ዘበላዕሉ ሕፃን ዘበታሕቱ ከሚባል ልጅሽ እመቤታችን ጽንዕት በድንግልና ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፭. ባሕርየ ዕጓለ እመሕያው (ሰው) ሆይ! እግዚአብሔር ሰውን ወዶታልና በውሰጥ በአፍአ፣ በነፍስ በሥጋ ደስ ይበልህ፡፡ “ወዶ ምን አደረገለት?” ትለኝ እንደኾነም “በእርሱ የሚያምን ኹሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” ተብሎ እንደተጻፈ /ዮሐ.፫፡፲፮/ ልጁን ለሕማም ለሞት እስከ መስጠት ደርሶ ለቤዛ ሰጥቶለታል ብዬ እመልስልሃለሁ፡፡ ልዑል እግዚአብሔር ረቂቅ ክንዱን ሰደደልን /ኢሳ.፶፩፡፱፣ ፶፫፡፩/፡፡ ነገር ግን ቅ.ዮሐንስ አፈወርቅ የዕብራውያንን መልእክት በተረጐመበተ በ፫ኛው ድርሳኑ “ወልድ ዋሕድ እንደ መላእክት በተላከ ጊዜ ቦታውን የለቀቀ አይደለም፤ በአንድ ፈቃድ ከአባቱ ጋር እያለ ነው እንጂ” ብሎ እንደተናገረው በለቢሠ ሥጋ ነው እንጂ በመለኮት የተላከ አይደለም፡፡ ክንድ ከአካል ሳይለይ የወደቀውን ዕቃ አንሥተው ይመልሱበታል፤ የራቀውንም ያቀርቡበታል፡፡ የአብ ኃይል፣ ክንድ የሚባለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የወደቀውን አዳምን ያዳነው ከባሕርይ አባቱ፣ ከአባቱ አንድነት ሳይለይ ነው፡፡
እዱ መዝራዕቱ ከሚባለው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኝልን፡፡
፮. ሊቁ ምስጋናውን ሲቀጥል “እምቅድመ ዓለም የነበረው፣ ዓለምን አሳልፎ የሚኖረው፣ ለኩነት ሥጋ የመጣው፣ ዳግመኛም ዓለሙን ለማሳለፍ የሚመጣው አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርሰቶስ ካንቺ ሳይለወጥ ፍጹም ሰው ኾነ” ይላል፡፡ ይኸውም በሌላ አንቀጽ “ባሕርዩን ከፍሎ አልተዋሐደም፤ ባሕርዩንም ሕፁፅ በማድረግ ኹለተኛ እንስሳ አልኾነም፡፡ አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመኾን ምሉ ፍጹም ሰው ነው እንጂ፡፡ የአምላክነትን የሰውነትንም ሥራ ይሠራል፤ ይህስ ባይኾን አንዱ ተለይቶ በቀረ ነበር” ካለው ጋር ተመሳሳይ ነው /ዮሐ.፩፡፩-፲፬፣ ሃይ.አበ.ዘኤፍሬም ፵፯፡፴፪/፡፡
“ተቀዳሙ ተካታይ የሌለው ወልድ ዋሕድ በሥራው ኹሉ ከነሣው ሥጋ አልተለየም፡፡” ይህም በኹለት መልኩ ይተረጐማል፡-
፩ኛ፡- “አካላዊ ቃል አንድ ግብር፣ አንድ ባሕርይ፣ አንድ አካል ነው እንጂ” ማለት ሲኾን፤
፪ኛ፡- ደግሞ “ተቀዳሙ ተካታይ የሌለው ወልድ ዋሕድ ሰውም ቢኾን ከአብ ከባሕርይ አባቱ፣ ከመንፈስ ቅዱስ ከባሕርይ ሕይወቱ አልተለየም፡፡ አካላዊ ቃል አንድ ኅብረ መልክዕ፣ አንድ ባሕርይ፣ አንድ አገዛዝ ነው እንጂ” ማለት ነው፡፡
ሰውም ቢኾን ከአብ ከባሕርይ አባቱ፣ ከመንፈስ ቅዱስ ከባሕርይ ሕይወቱ ካልተለየ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳነሣን ለምኝል፡፡
፯. ዳግማይ አዳም (ክርስቶስ) ካንቺ ባንቺ ባሕርይ ተወልዷልና የነቢያት ሀገረ ትንቢታቸው ቤተ ኀብስት እመቤታችን ሆይ! ደስ ይበልሽ፡፡ የቀደመ ሰው አዳምን ከሲዖል ወደ ገነት ከኀሣር ወደ ክብር ይመልሰው ዘንድ ካንቺ ባንቺ ባሕርይ ተወልዷልና የነቢያት ሀገረ ትንቢታቸው ቤተ ኀብስት እመቤታችን ሆይ! ደስ ይበልሽ፡፡ ከእናንተ መካከል፡- “ሊቁ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ዳግማይ አዳም ማለቱ ከቀዳማዊ አዳም ጋር የሚያመሳስለው ምን ስላለው ነው?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡- በቀዳማዊ አዳም ምክንያት የሰው ልጅ በሙሉ በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ገሃነም ተፈርዶበት ነበር፤ በዳግማይ አዳም በክርስቶስ ግን የጽድቅ በር ለኹሉም ተከፍቷል፡፡ ከቀዳማዊ አዳም ጋር አብረው ዕፀ በለስን ያልበሉት ስንኳ ሞት ነግሦባቸው ይኖር ነበር፤ በዳግማይ አዳም በክርስቶስ ትሩፋት ግን የሰው ልጅ በሙሉ የድኅነት መንገድ ተሰጥቶታል፡፡ ስለዚህ ክርስቶስ ዳግማይ አዳም ሲባል በአዳም የመጣው በደል ክርስቶስ ከሰጠው ጸጋ ጋር ወይም ደግሞ በአዳም ምክንያት የመጣው ሞትና በክርስቶስ የተሰጠው ሕይወት ለማስተካከል ሳይኾን አዳም ለሚሞቱት ኹሉ አባት እንደኾነ ኹሉ ክርስቶስ ደግሞ ትንሣኤ ሕይወት ላላቸው ኹሉ አባታቸው መኾኑን ለመግለጥ ነው /፡፡ አንድም በጥንተ ተፈጥሮ ይመስሏልና፡፡
በዕፅ ምክንያት የወደቀ (ከገነት የወጣ፣ ከክብሩ የተዋረደ) አዳም ንስሐ ቢገባም፣ ጩኸቱን ሰምተው ነቢያት ካህናት ቢነሡም እንደ እርሱ ንጽሐ ጠባይዕ አድፎባቸዋልና በግዝረታቸው በመሥዋዕታቸው አዳምን ማዳን አልቻሉም /ኢሳ.፷፬፡፮/፡፡ ነገር ግን “አንሥእ ኃይለከ፤ ፈኑ እዴከ” /ኢሳ.፶፩፡፱/ ያሉትን ልመናቸውን ሰምቶ ካንቺ ባንቺ ባሕርይ ተወለደ (ሰው ኾነ)፡፡ የአዳምን ባሕርይ ባሕርይ አድርጐ “አዳም ጥንቱንም መሬት ነህ ወደ መሬትነትህ ተመለስ” ብሎ በአዳም የፈረደበትንም የሞት ፍርድ (መከራ) ተቀብሎ ያድነው ዘንድ ካንቺ ባንቺ ባሕርይ ተወልዷልና፣ የነቢያት ሀገረ ትንቢታቸው ቤተ ኀብስት እመቤታችን ሆይ! ደስ ይበልሽ፡፡ ብዙ ኃጢአት ካለች ዘንድ ጸጋ እግዚአብሔር ትበዛለች /ሮሜ.፭፡፳/፡፡ “በአንድ ሰው (አዳም) ምክንያት የገባች ኃጢአት ሕግ በተሰጣቸውና ባልተሰጣቸው ኹሉ እንዲህ ከነገሠች፣ በዳግማይ አዳም በአካላዊ ቃል በኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጠች ጸጋማ እንዴት አብልጣ አትበዛ?” /St. John Chrysostom, Ibid/፡፡ ዳግማይ አዳም ከሚባል ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳነሣን ለምኚልን፡፡
፰. የሰው ኹሉ አእምሮ በአፍአ በውስጥ በሥጋ በነፍስ ደስ ይላታል፡፡ “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ- አምላክ ለኾነ ለሥጋ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ በአንድነት ምስጋና ይገባዋል፡፡ በምድርም ዕርቅ ተወጠነ፡፡ የሰው ግዕዛኑ ይሰጠው ዘንድ” እያሉ ከመላእክት ጋራ (እንደ መላእክት) ንጉሥ ክርስቶስን ያመሰግኑታል /ሉቃ.፪፡፲፬/፡፡ አንድም “ዮም አሐደ መርዔተ ኮኑ መላእክት ወሰብእ ከመ ይሰብሕዎ ለክርስቶስ በቃለ አሚን- ” እንዲል የሰው ፍቅር አገብሮት አምላክ ሰው ቢኾን ሰውም አምላክ ቢኾን በመላእክት ዘንድ ምስጋና ተደረገ፡፡ በምድርም አንድነት ተደረገ፤ ኖሎት (እረኞች) ከመላእክት ጋራ አንድ ኾነው አመሰገኑ /ሉቃ.፪፡፳/፡፡ “ኃጢአትን አጠፋ፤ በመስቀልም ተሰቅሎ ፍዳን አጠፋ፡፡ በመቃብርም ፈርሶ በስብሶ መቅረትን አጠፋ፡፡ በሲዖልም ሞተ ነፍስን አጠፋ፡፡ ሥራ በሠራበት ኹሉ ድኅነትን አደረገልን” እንዲል የቀደመ መርገመ ሥጋ መረገመ ነፍስን አጥፍቷልና ኖሎት ከመላእክት ጋራ አንድ ኾነው አመሰገኑ /ሃይ.አበ.፹፱፡፳፬/፡፡ የጸላኢ የዲያብሎስ ምክሩን አፍርሶበታልና ኖሎት ከመላእክት ጋራ አንድ ኾነው አመሰገኑ፡፡ በመቅድመ ወንጌል “ወበከመ ኮነ በጉህለት ተኀብአ ሰይጣን ውስተ ሥጋ ከይሲ ከማሁ ኮነ ድኅነትነ በተሰውሮ ቃለ እግዚአብሔር ዘመድነ- ሰይጣን በተንኰል በሥጋ ከይሲ እንደተሠወረ እኛም ከፍዳ መዳናችን ቃለ እግዚአብሔር በባሕርያችን በመሠወሩ ኾነ” እንዲል በሥጋ ከይሲ ተሰውሮ ቢያስትበት በሥጋ ተሰውሮ አድኖበታልና ኖሎት ከመላእክት ጋራ አንድ ኾነው አመሰገኑ፡፡ ዲያብሎስ “ሥጋን በመቃብር ነፍስን በሲኦል ተቆራኝቼ እኖራለሁ” ብሎ ነበርና የመከረባቸውን ሥጋንና ነፍስን ተዋሕዶ አድኖበታልና ኖሎት ከመላእክት ጋራ አንድ ኾነው ንጉሥ ክርስቶስን አመሰገኑ፡፡ ይኸውም ጥበበኛው ሰሎሞን “ጠቢብ የኃያላንን ከተማ ይገባባታል፥ የሚታመኑበትንም ኃይል ያፈርሳል” እንዳለው ነው /ምሳ.፳፩፡፳፪/፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፤ የአዳምንና የሔዋንን የዕዳ ደብዳቤቸውን አጥፍቶላቸዋልና /ቈላ.፪፡፲፬/ “አምላክ ለኾነ ለሥጋ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ በአንድነት ምስጋና ይገባዋል፡፡ በምድርም ዕርቅ ተወጠነ፡፡ የሰው ግዕዛኑ ይሰጠው ዘንድ” እያሉ መላእክት አመሰገኑት /ሉቃ.፪፡፲፬/፡፡ ዲያብሎስ በአዳምና በሔዋን የጨለማ መጋረጃ ጋርዶ ሥቃይ አጽንቶ “ስመ ግብርናት ጽፋችሁ ብትሰጡኝ አቀልላችኋለሁ” ብሏቸው አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋንም አመቱ በዲያብሎስ ብለው ጽፈው ሰጥተውት ነበር፡፡ ዲያብሎስም ያንን በእብነ ሩካም ጽፎ አንዱን በዮርዳኖስ አንዱን በሲኦል ጥሎት ነበር፡፡ አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ኾኖ ሲመጣ ግን ዲያብሎስ በዮርዳኖስ የጣለውን ሲጠመቅ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ እንደ ሰውነቱ ተረግጦ አጥፍቶታል፤ በሲኦል የጣለውንም በዕለተ ዐርብ በአካለ ነፍስ ወርዶ አጥፍቶላቸውና መላእክት አመሰገኑት /ቈላ.፪፡፲፬/፡፡ በዳዊት ሀገር ከዳዊት ባሕርይ የተወለደ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምና ሔዋንን ነጻ አድርጓቸዋልና አመሰገኑት /መዝ.፻፴፪፡፲፩/፡፡ አዳምንና ሔዋንን ነጻ ካደረጋቸው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
፱. በዚህ ዓለም ለሚኖሩ ሰዎች ኹሉ የምታበራ (ዕውቀትን የምትገልጥ)፣ ጠፈር ደፈር የማይከለክልህ፣ መዓልትና ሌሊትም የማይፈራረቅብህ ብርሃን ዘበአማን (እውነተኛ ብርሃን) ክርስቶስ ሆይ! ስለ ሰው ፍቅር ልሙት ልሰቀል ብለህ ወደ ዓለም በመምጣትህ ፍጥረት ኹሉ ደስ አለው፡፡ አዳምን ከስሕተት፣ ሔዋንንም ከሞት ፃዕረኝነት (ከመጣባቸው ፍዳ) ነፃ አድረገኻቸዋልና ለእኛ በተደረገው ክብር መላእክት ከእኛ ጋር ደስ አላቸው /ሃይ.አበ.፷፰፡፴፪/፡፡ የሰው ፍቅር አገብሮህ ባጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስነህ ሲያዩህ “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር” ብለው መላእክት አመሰገኑ፡፡ ከዚህም የተነሣ በጣዕም ላይ ጣዕም በጸጋ ላይ ጸጋ ተጨምሮላቸው ደስ ብሏቸዋል፡፡ እኛም ቅብዐ ትፍስሕት የሚኾን መንፈስ ቅዱስን አንድም ሀብተ ልደትን ተቀብለን ከመላእክት ጋር ደስ አለን፤ አመሰገንንህም፡፡ እንስሳት፣ አራዊት ስንኳ ሳይቀሩ ሰው ከፈጣሪው ጋር በመታረቁ ደስ ብሏቸዋል፡፡
ጽንዕት በድንግልና ቅድስት እመቤታችን ሆይ! ብርሃን ከሚባል ልጅሽ ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡
ይህንን ሲጨርስ በያዘችው መስቀለ ብርሃን ባርካው ዐረገች፤ እርሱም እጅ ነሥቶ ቀርቷል፡፡
አነሣሥቶ ላስጀመረን አስጀምሮም ላስፈጸመን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባው አሜን፡፡
[ገ/እግዚአብሔር ኪደ]
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ::" /ማቴ ፫:፫/
ዝክረ ቅዱሳንን ተማሩ ብለን እንለምናችኋለን!!
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
✝ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together
https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━━━
Comments
Post a Comment