††† እንኳን ለጌታችንና አምላካችን መድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ዓመታዊ የስቅለት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††
††† መድኃኔ ዓለም †††
††† ጌታችን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ለእኛ ሲል በፈጸመው የማዳን ሥራ በዚሕ ዕለት ክፉዎች አይሁድ ከምሽቱ 3:00 ጌቴሴማኒ ውስጥ ያዙት::
ሙሉውን ሌሊት ከቀያፋ ወደ ሐና: ከሐና ወደ ቀያፋ ሲያመላልሱት: አስረው ሲደበድቡት አድረዋል::
*ዝም ቢላቸው ዓይኑን ሸፍነው በጥፊ መቱት:: ምራቃቸውን ተፉበት:: ዘበቱበት:: ራሱንም በዘንግ መቱት:: እርሱ ግን ሁሉን ታገሰ::
*በጧት ከገዢው ዘንድ ሞት እንዲፈረድበት አቀረቡት:: በሠለስት (ሦስት ሰዓት ላይ) አካሉ እስኪያልቅ እየተዘባበቱ 6,666 ገረፉት:: ሊቶስጥሮስ አደባባይ ላይ እርጥብ መስቀል አሸክመው ወደ ቀራንዮ ወሰዱት::
*ስድስት ሰዓት ላይ በረዣዥም ብረቶች አምስት ቦታ ላይ ቸንክረው ሰቀሉት:: ሰባት ታላላቅ ተአምራት በምድርና በሰማይ ታዩ::
ዓለም በጨለማ ሳለች ጌታ በመስቀል ላይ ሰባት ቃላትን ተናገረ::
*ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በባሕርይ ሥልጣኑ ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው ለየ:: በዚያች ሰዓትም ወደ ሲዖል ወርዶ የታሠሩትን ሁሉ ፈታ:: አሥራ አንድ ሰዓት ላይ ደጋጉ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከታላቅ ክብርና ሐዘን ጋር በአዲስ መቃብር ቀበሩት::
*በዚያች ቀን ድንግል ማርያም ልቧ በሐዘን ተቃጠለ:: ወዳጁ ቅዱስ ዮሐንስም ፍፁም ለቅሶን አለቀሰ:: ቅዱሳት አንስት በዋይታ ዋሉ:: (ማቴ. 27:1, ማር. 15:1, ሉቃ. 23:1, ዮሐ. 19:1)
††† ለእኛ ለኀጥአን ፍጡሮቹ ሲል ይህንን ሁሉ መከራ የታገሰ አምላክ ስለ አሥራ ሦስቱ ኅማማቱ: አምስቱ ቅንዋቱ: ስለ ቅዱስ መስቀሉ: ስለ ድንግል እናቱ ለቅሶና ስለ ወዳጁ ቅዱስ ዮሐንስ ብሎ ይማረን::
††† ከቅዱሳኑ በዚሕች ዕለት:-
††† ከ80 ዓመታት በላይ በገዳም የኖረ: የገዳማውያን ሞገሳቸው: የመነኮሳትም ሁሉ አለቃ ታላቁ ቅዱስ መቃርስ አርፏል::
††† ዳግመኛ በዚህ ቀን ንግሥናን ከሊቅነት: ጽድቅን ከሰማዕትነት ጋር የደረበው ሰማዕቱ ቅዱስ ገላውዴዎስ አንገቱን ተከልሏል:: ቅዱስ ገላውዴዎስ የጻድቁ ዐፄ ልብነ ድንግል ልጅ ነው::
††† መድኃኔ ዓለም ከወዳጆቹ ጸጋ ክብርን ያድለን::
††† መጋቢት 27 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ (ፍቁረ እግዚእ)
2.ቅዱሳት አንስት (ከእግረ መስቀሉ ያልተለዩ)
3.ቅዱሳን ባልንጀሮች (በጌታ ስቅለት ጊዜ ከሞት የተነሱ)
4.ቅዱሳን ዮሴፍና ኒቆዲሞስ
5.ታላቁ ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት አለቃ)
6.ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት (የኢትዮዽያ ንጉሥ)
7.ቅዱስ ዕፀ መስቀል
††† ወርኀዊ በዓላት
1.አቡነ መብዐ ፅዮን ጻድቅ
2.ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት
3.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ
4.ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት
††† "የተጠራችሁለት ለዚህ ነው:: ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሏልና:: እርሱም ኃጢአት አላደረገም:: ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም:: ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም:: መከራንም ሲቀበል አልዛተም . . . እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ::" †††
(፩ጴጥ. ፪፥፳፩-፳፭)
✞✞✞ እንኩዋን ለታላቁ "ቅዱስ መቃርስ" ዓመታዊ
የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✞✞✞
+*"+ ታላቁ ቅዱስ መቃርስ +"*+
=>ታላቁ ቅዱስ መቃርስ (ቅዱስ መቃሬ) 'ጽድቅ እንደ መቃርስ' የተባለለት: የመነኮሳት ሁሉ አለቃ: ከ80 ዓመታት በላይ በበርሃ የኖረ: በግብፅ ትልቁን ገዳም (አስቄጥስን) የመሠረተ: ከ50,000 በላይ መነኮሳትን ይመራና ይመግብ የነበረ ፍፁም ጻድቅ ነው::
+በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን አርዮሳውያን ደጉን ታላቅ አባት በሰንሰለት አስረው ከግብፅ ወደ እስያ በርሃ ከጉዋደኛው ቅዱስ መቃርዮስ እስክንድርያዊ ጋር አሰድደውታል:: በዚያ ለ2 ዓመታት ስቃይን ከተቀበሉ በሁዋላ በአረማውያን ፊት ድንቅ ተአምር አድርገው አረማውያንን ከነንጉሳቸው አጥምቀዋል::
+በተሰደዱባት ሃገርም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ (ስም አጠራሩ ይክበርና) እመቤታችንን: ቅዱሳን ሐዋርያትን:
አዕላፍ መላእክትን: በተለይ ደግሞ ቅዱሳኑን ዳዊትን:
ዮሐንስ መጥምቁንና ወንጌላዊውን: ማርቆስን: ዼጥሮስን:
ዻውሎስን አስከትሎ ወርዶ ተገልጦላቸዋል:: በቅዱስ
አንደበቱም የምሕረት ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል::
+ታላቁ ቅዱስ መቃርስና ባልንጀራው መቃርዮስ ከ2
ዓመታት ስደትና መከራ በሁዋላ ስደት በወጡባት ዕለት
መልዐኩ ኪሩብ በክንፉ ተሽክሞ ወደ ግብፅ
መልሷቸዋል:: በወቅቱም ጻድቁን ለመቀበል ከ50,000
በላይ የሚሆኑ ልጆቻቸው መነኮሳት በዝማሬ ወጥተዋል::
+ስለ ታላቁ ቅዱስ መቃርዮስ ቅድስና ለመጻፍ መነሳት
በረከቱ ብዙ ነው:: ግን 'ዓባይን በጭልፋ' እንዲሉ አበው
ከብዛቱ የተነሳ የሚዘለቅ አይሆንም::
+ቅዱስ መቃርስ ከዘመናት በላይ በቆየበት የበርሃ
ሕይወቱ:-
1.አባ ብሶይ: አባ ባይሞይ: አባ ሳሙኤል: አባ በብኑዳን
ጨምሮ እርሱን የመሰሉ (ያከሉ) ቅዱሳንን ወልዷል::
2.ለሕይወታችን መንገድ የሚሆኑንን ብዙ ቃላትን
ተናግሯል::
3.ከገዳማት እየወጣ በብዙ ቦታዎች ቅዱስ ወንጌልን
ሰብኩዋል::
4.አጋንንትን ድል ከመንሳት አልፎ እንደ ባሪያ ገዝቷቸዋል::
5.ለዓይንና ጀሮ ድንቅ የሆኑ ብዙ ተአምራትን ሰርቷል:: . .
.
+በእነዚህና ሌሎች ምክንያቶችም ቤተ ክርስቲያን "ርዕሰ
መነኮሳት (የመነኮሳት ሁሉ አለቃ)" ስትል ትጠራዋለች::
በ97 ዓመቱ መጋቢት 27 ቀን ሲያርፍ መላእክት ብቻ
ሳይሆን አጋንንትም ስለ ድል አድራጊነቱ ዘምረውለታል::
=>ታላቁ ቅዱስ መቃርስ ካረፈ በሁዋላ ከክቡር ሥጋው
ብዙ ተአምራት ይታዩ ነበርና የሃገሩ (የሳስዊር) ሰዎች
ሊወስዱት ፈለጉ:: ሳስዊር ማለት ቅዱሱ ተወልዶ
ያደገባት: ወላጆቹ (አብርሃምና ሣራ ይባላሉ) የኖሩባት ቦታ
ናት:: የምትገኘውም ግብጽ ውስጥ ነው::
+በምድረ ግብጽ: በተለይም በገዳመ አስቄጥስ የአባ
መቃርስን ያህል ክቡርና ተወዳጅ የለምና የሃገሩ ሰዎች
የነበራቸው አማራጭ መስረቅ ነበር:: መሥረቅ ኃጢአት
ቢሆንም እነሱ ግን ስለ ፍቅር: አንድም ለበረከት (በረከትን
ሲሹ) አደረጉት::
+ወደ ሳስዊርም ወስደው: ቤተ ክርስቲያን በቅዱሱ ስም
አንጸው በክብር አኖሩት:: በዚያም ለ160 ዓመታት
ተቀመጠ:: በ7ኛው መቶ ክ/ዘመን ግን ተንባላት
(እስላሞች) መጥተው ቤተ ክርስቲያኑን አጠቁ:: በዚህ
ጊዜም ሕዝቡ የጻድቁን አጽም ይዘው ሸሹ:: በሌላ ቦታም
እንደ ገና በስሙ ቤተ ክርስቲያን አንጸው በዚያ አኖሩት::
+በእነዚህ ሁሉ ዓመታት የመንፈሳዊ አባታቸውን ሥጋ
ያጡት የገዳመ አስቄጥስ ቅዱሳን ያዝኑ ይጸልዩ ነበርና
ልመናቸውን ፈጣሪ ሰማ:: አባ ሚካኤል ሊቀ ዻዻሳት
በነበረበት ዘመን: ከገዳሙ ለሌላ ተግባር ወደ ሳስዊር
የተላኩ አበው ከታላቁ አባት ቤተ ክርስቲያን ሲደርሱ
ሰውነታቸው ታወከ::
+ይዘው ለመውሰድ ሙከራ ቢያደርጉ ሊሳካላቸው
አልቻለም:: ምክንያቱም የቤተ ክርስቲያኑ ጠባቂ ደወል
ደውሎ ሕዝቡን ሁሉ ጠርቶ ነበርና:: ሕዝቡና ሃገረ ገዢው
የሆነውን ሲሰሙ "የቅዱሱን ሥጋ ብትነኩ እንገላቹሃለን"
ብለው ሰይፍ: ዱላ: ጐመድና ጦር ይዘው መጡባቸው::
Comments
Post a Comment