✝✞✝ እንኩዋን ለአበው ቅዱሳን "አባ ዳንኤል" : "አባ ዸላድዮስ" : ወቅዱስ "ፊላታዎስ ሰማዕት" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✝✞✝
+*" ማር ዳንኤል "*+
=>"ዘዓምድ" በሚል ስም ከሚታወቁ የቤተ ክርስቲያን አበው መካከል 4ቱ ቅድሚያውን ይይዛሉ:: እነዚህም:-
1.ቅዱስ ስምዖን ዘዓምድ:
2.ቅዱስ አጋቶን ዘዓምድ:
3.ቅዱስ ዳንኤል ዘዓምድ እና
4.ቅዱስ ሉቃስ ዘዓምድ ናቸው::
+"ዘዓምድ" የሚለውን ቃል ምሥራቃውያን በልሳናቸው 'THE STYLITE' ይሉታል:: የእኛው ቃል ደግሞ ከግዕዝ የተወረሰ ነውና በቁሙ ቢተረጐም "የምሰሶው" የሚል ትርጉምን ይይዛል:: ይህም በ2 ምክንያቶች ነው::
+አንደኛው ቅዱሳኑ ተጋድሏቸውን የፈጸሙት ከረዥም ምሰሶ ላይ ወጥተው በመጸለይ ስለሆነ ነው:: ሌላኛው ምክንያት ደግሞ እነዚህ አባቶች በዘመኑ ለነበሩ ምዕመናንና መነኮሳት አጽናኝ: አስተማሪ: መሪና ፈዋሽ በመሆናቸውና እንደ ምሰሶ ተተክለው ሳይነቃነቁ በመጸለያቸው ነው::
+ልክ ከዓለም ሃገራት ብዙ ስውራንን እና ቅዱሳን ነገሥታትን በመያዝ ሃገራችን ቀዳሚ እንደ ሆነችው ሁሉ ምሰሶ ላይ ወጥተው የሚጋደሉ ቅዱሳንም ሶርያውያንና ምሥራቃውያን ናቸው:: በዚህ ዕለትም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የታላቁን ቅዱስ ማር ዳንኤልን በዓል ታከብራለችና ከዜና ሕይወቱ ለበረከት ጥቂት እንካፈል::
=>ይህ ቅዱስ ሰው (በስዕሉ የሚታየው) ሶርያዊ ሲሆን ተወልዶ ያደገባት አካባቢ በቀድሞው አጠራር "ሃገረ ዓምድ" ይሏታል:: "ማር" የሚለው ቃል በቤተ ክርስቲያን ቅድስናንና አለቅነትን የሚገልጽ ስም ነው:: በዚህ ስም ጥቂቶች ብቻ ሲጠሩበት ለሊቃውንትም: ለሰማዕታትም: ለጻድቃንም አገልግሏል::
+ቅዱሱ "ማር" ብቻ ሳይሆን "ዘዓምድ" ተብሎም ተጠርቷል:: ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ እርሱም በፊት እንደ ጠቀስናቸው አበው ምሰሶ ላይ ተጠግቶ (ቆሞ): ትኩል ከመ ዓምድ ሆኖ በመጸለዩ ነው::
+ማር ዳንኤል በምድረ ሶርያ ስመ ጥር ጻድቅ ነው:: በዘመነ ጻድቃን መጨረሻ አካባቢ ከክርስቲያን ወገኖቹ ተወልዶ: በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን አድጐ: ገና በልጅነቱ ለቤተ እግዚአብሔር ተሰጥቷል::
+የወቅቱ የሃገረ ዓምድ ዻዻስ (አባ ዼጥሮስ) ለማር ዳንኤል ፍኖተ ጽድቅን (የሕይወት - የእውነትን ጐዳና) በማሳየት ከፍ ያለውን አስተዋጽኦ አበርክቷል:: አስተምሮም ለመዓርገ ክህነት አብቅቶታል::
+ቅዱሱ በእድሜው እየበሰለ ሲሔድ ግን ምርጫው ምናኔ ሆኖ በመገኘቱ በፈቃዱ ወደ በርሃ ሔደ:: በዚያም መዓርገ ምንኩስናን ተቀብሎ በጾም: በጸሎትና በትሕርምት ይጋደል ገባ::
+ማር ዳንኤል በበዓቱ ተወስኖ ሲጾም: ሲጸልይና እግዚአብሔርን ሲያመልክ ከጸጋ (ከብቅዓት) ደረሰ:: ብዙ ተአምራትንም በመሥራቱ ስም አጠራሩ በአካባቢው ተሰማ:: እርሱ ግን ከሰው: ይልቁንም ከሴቶች ይርቅ: ላለማየትም ራሱን ይከለክል ነበር::
+ለአንድ መናኝ በሰዎች መካከል: ይልቁንም በተቃራኒ ጾታ ጐን መኖር ያልተፈቀደ: ፈታኝም ድርጊት ነውና ከፈጣሪው ጋር እንዲህ የሚል ቃልን ገባ:: "ከዚህ በሁዋላ ሴት ልጅን አላይምም" አለ:: በእንዲህ ያለ የቅድስና ሕይወት ሳለ ወላጅ እናቱ ልታየው ተመኘች::
+ወደ ገዳሙ መጥታም "ልጄ! ላይህ ሽቻለውና ልግባ : ወይ ብቅ በል" ስትል ላከከችበት:: ቅዱሱ ግን "እናቴ! ሴትን አላይም ብየ ቃል ስለ ገባሁ አልችልም" ሲል መለሰላት:: በጣም አዝና "እኔ ወልጄ: አዝዬ: አጥብቼ: አሳድጌ እንደ ሌሎች ሴቶች አስመሰልከኝ? በል ፈጣሪ 2 ሴቶች በአንድ ልብስ ሆነው ይዩህ!" ብላ ረግማው ወደ ቤቷ ተመለሰች::
+የሚገርመው ማር ዳንኤል በበርሃ የበቃውን ያህል እናቱ በዓለም ሳለች በጐ ሰርታለችና እርሷም ጸጋውን አብዝቶላታል:: በምን ይታወቃል ቢሉ:- ያቺ የተናገረቻት ነገር ሁሉ ደርሶበታልና::
+አንድ ቀን ለገንዘብ ሲል አንድ ሰው የገደለውን አምጥቶ በቅዱሱ በር ላይ ጣለው:: ቅዱሱም ያለ አበሳው ታሥሮ ወደ ከተማ ሲወሰድ መታጠቢያ (shower) ቤት ውስጥ የነበሩ ሴቶች ሊያዩት ቸኩለው: አንድ ልብስ ለብሰው ወጥተዋል:: ማር ዳንኤል ይህንን ሲያይ የእናቱ ነገር ትዝ ብሎት ሳቅ ብሏል::
+በታሠረበት ቦታ ግን የሞተውን ሰው በጸሎቱ በማስነሳቱ በክብር ወደ በዓቱ ተመልሷል:: የከተማዋ ንጉሥም ገዳምን አንጾለታል:: በተረፈ ዘመኑም ለብዙ ቅዱሳን አባት ሆኖ እስከ እርጅናው አገልግሏል:: በዚህች ቀንም በክብር ዐርፏል::
+*" አባ ዸላድዮስ "*+
=>አባ ዸላድዮስም በተመሳሳይ የዘመነ ጻድቃን ፍሬ ነው:: በርሃ ከገባባት ቀን ጀምሮ ጾምን: ጸሎትን አዘውትሮ ክርስትናውን አጽንቷል:: ሙሉ እድሜውን በጐ በመሥራት በማሳለፉ ፈጣሪውን ሲያስደስት ለብዙዎች አንባ: መጠጊያ መሆን ችሏል::
+በጸሎቱ አካባቢውን በደህንነት ይጠብቅ ነበር:: ምዕመናን እንኩዋን ወደ እርሱ መጥተው ተባርከው ባሉበት ቦታ ሁነው ተማጽነው እንኩዋ መሻታቸውን አያጡም ነበር:: ምንም ያህል ኃጢአተኞች ይሁኑ እግዚአብሔር ስለ አባ ዸላድዮስ ሲል ይለመናቸው ነበር::
+አንድ ቀን አንድ ነጋዴ ሰው በባሕር ላይ ሲሔድ ድንገት ማዕበል ይነሳበታል:: ብቻውን ነበርና ጨነቀው:: እሱ ያለባት ጀልባም ትንሽ በመሆኗ ልትሠበር ደረሰች:: መዳን እንደ ማይችል ሲያውቅ ተስፋ ቆረጠ::
+ድንገት ግን አባ ዸላድዮስ ትዝ ብሎት ቀና ብሎ "ጌታየ! ስለ ቅዱሱ አባት ብለህ ብትምረኝ ለወዳጅህ መቶ ዲናር ወርቅ እሰጣለሁ" ሲል ተሳለ:: ቃሉን ተናግሮ ሳይጨርስ አባ ዸላድዮስ በጀልባው ላይ ቁጭ ብሎ ታየው:: ማዕበሉም ጸጥ እንዲል አድርጐ ከወደብ አድርሶ ተለየው::
+ነጋዴውም ፈጣሪውን ስለ ድኅነቱ እያመሰገነ 100 ዲናር ወርቁን ይዞ አባ ዸላድዮስን ፍለጋ ወጣ:: የሚያውቀው በዝና ብቻ ነበርና:: መንገድ ላይም ሞሪት የሚባል መሪ አግኝቶ ከአባ ዸላድዮስ በዓት ደረሰ::
+ከቅዱሱ ተባርኮ ወርቁን ቢያቀርብለት "ልጄ! እኔ ይህን አልፈልገውም:: ለነዳያን በትነው" አለው:: ነጋዴው ሲወጣ ግን ሞሪት (መሪው) ገንዘቡን ፈልጐ ገደለውና ከጻድቁ በር ላይ ጣለው:: ሃገረ ገዢውም ሲሰማ አባ ዸላድዮስን አሠረው::
+ጻድቁ ግን የሞተውን ባርኮ አስነሳውና "ማን ገደለህ" ቢለው "ሞሪት" ሲል መልሷል:: መኮንኑ ሞሪትን ሊገድለው ቢልም "የለም" ብሎ ነጋዴውን በደስታ: ሞሪትን ደግሞ በንስሃ ሸኝቷቸዋል:: አባ ዸላድዮስ ግን ተረፈ ዘመኑን በቅድስና ሲጋደል ኑሮ በክብር ዐርፏል::
+*" ቅዱስ ፊላታዎስ ሰማዕት "*+
=>"ፊላታዎስ" ማለት "መፍቀሬ እግዚአብሔር - እግዚአብሔርን የሚወድ: እርሱም የሚወደው" ማለት ነው:: ቅዱሱ የዘመነ ሰማዕታት (3ኛው መቶ ክ/ዘመን) ፍሬ ሲሆን ለየት ያለ ታሪክ ያለው ቡሩክ ወጣት ነው::
+እርሱ የባለ ጸጐች ልጅ: ስለ ክርስትና ምንም ሰምቶ የማያውቅ ሕጻን ነበር:: ወላጆቹ የሚያመልኩት ላምን ሲሆን የአካባቢው ሰው ደግሞ ለጸሐይ ይንበረከክ ነበር:: ቤተሰቦቹ ስለ አምልኮ ሲጠይቁት "እናንተ የምታመልኯቸው ፍጡራን ስለ ሆኑ አልፈልግም" አላቸው::
+ሕጻን ቢሆንም ስለ ፈጣሪው ተመራመረ:: በመጨረሻውም ፀሐይን "አንተ ምንድነህ?" ቢለው "እኔ ፍጡር ነኝ" ሲል መልሶለታል:: በዚያች ዕለት ግን ቅዱስ መልአክ ወርዶ: ሁሉን ነገር አስተምሮ የክርስቶስ ወታደር አድርጐታል::
+ወደ ቤቱ ተመልሶም የወላጆቹን ላም "እውነትን ተናገር" ብሎ ገስጾታል:: ላሙም ሰይጣን እንዳደረበት በሰው ልሳን ተናግሮ: የቅዱሱን ወላጆች ወግቶ ገድሏቸዋል:: ቅዱስ ፊላታዎስ ግን ላሙን አስገድሎ: ወላጆቹን ከሞት አስነስቶ ከአካባቢው ሰው ጋር በስመ ሥላሴ አስጠምቁዋቸዋል::
+በድንግልና ኑሮም ዘመነ ሰማዕታት ሲጀምር በርጉም ዲዮቅልጥያኖስ እጅ ብዙ ተሰቃይቷል:: በጸሎቱም ጣዖታቱን (እነ አዽሎንን) ከነ አገልጋዮቻቸው ወደ ጥልቁ አስጥሟቸዋል:: እርሱም በዚህች ቀን በሰይፍ ተከልሎ ለክብር በቅቷል:: ለእኛ ለኃጥአን የሚሆን ቃል ኪዳንንም ከጌታው ተቀብሏል::
=>የቅዱሳን አባቶቻችን አማናዊት ርስት ድንግል ማርያም አትለየን::
=>ጥር 16 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ፊላታዎስ ሰማዕት
2.አባ ዸላድዮስ ገዳማዊ
3.ማር ዳንኤል ሶርያዊ
4.አባ ዮሐንስ መሐሪ (ሊቀ ዻዻሳት)
5.11,004 ሰማዕታት (የቅ/ቂርቆስ ማሕበር)
6.11,503 (የቅ/ፊላታዎስ ማሕበር)
7.አባ ጽሕማ (ከተስዓቱ ቅዱሳን አንዱ)
=>ወርሐዊ በዓላት
1.በዓለ ኪዳና ለድንግል
2.ቅዱስ አኖሬዎስ ንጉሥ
3.ቅዱስ ገብረ ማርያም (ንጉሠ ኢትዮዽያ)
4.ቅድስት ኤልሳቤጥ
5.አባ ዳንኤል
6.አባ አቡናፍር ገዳማዊ
7.አባ ዮሐንስ ወንጌሉ ዘወርቅ
=>+"+ ጻድቅ እንደ ዘንባባ ያፈራል::
እንደ ሊባኖስ ዝግባም ያድጋል::
በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ተተክለዋል::
በአምላካችንም አደባባይ ውስጥ ይበቅላሉ::
ያን ጊዜ በለመለመ ሽምግልና ያፈራሉ::
ደስተኞችም ሆነው ይኖራሉ:: +"+ (መዝ. 91:12)
<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
Comments
Post a Comment