✝✞✝ በስመ አብ : ወወልድ : ወመንፈስ ቅዱስ : አሐዱ አምላክ . . . አሜን:: ✝✞✝
✝✝✝ ግብረ-ሰላም ✝✝✝
(ከአንድ ወንድም በደረሰኝ ጥያቄ መሠረት ለጊዜው እነዚህን ጉዳዮች ብቻ እንመልከት)
"ገብረ ሰላመ በመስቀሉ::
ትንሳኤሁ አግሃደ::"
1." ትርጉም "
=>"ግብረ-ሰላም" ማለት "የሰላም : የፍቅር : የአንድነት ተግባር" እንደ ማለት በጥሬው ሊተረጐም ይችላል::
2." ምንነት "
=>ግብረ-ሰላም የጌታን ትንሳኤ ተከትለው በሚመጡ 50 ቀናት የሚከናወን ተግባር ሲሆን መንፈሳዊና ሥጋዊ ድግሶች የሞሉበት ትውፊታዊ ክዋኔ ነው::
3." መነሻ "
=>ቤተ ክርስቲያናችን የሁሉ ነገሯ መሠረት መድኃኔ ዓለምና ትዕዛዛቱ ናቸው:: የግብረ ሰላምም መሠረቱ ቅዱስ መጽሐፍ ነው:: በብሉይ ኪዳን አገልጋይ ካህናትና ነቢያትን መመገብ በጐና የተለመደ ተግባር ነበር::
+ኦሪት ላይ እንደተጻፈው ቅዱስ ኢያሱ ርስትን ሲያካፍል ለካህናት አልሰጣቸውም:: ምክንያቱም የካህናቱ ርስት ሕዝቡ ነበርና:: (ኢያ. 21) በመጽሐፈ ነገሥት 2ኛ ያቺ ደግ ሱነማይት ሴት ለቅዱስ ኤልሳዕን ትመግበው : ታሳድረውም እንደ ነበርም ተጽፏል:: እንዲያውም ቤት ሁሉ ሠርታለታለች:: (2ነገ. 4:8)
+በሐዲስ ኪዳን ደግሞ የክብር ባለቤት : አማናዊው ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰዎች ቤት ገብቶ ግብር ሲያገቡለት (ሲጋበዝ) እንደ ነበር ቅዱስ ወንጌል ይናገራል:: እንደ ማሳያም ቤተ ማርታን (ሉቃ. 10:38) : ቤተ ስምዖን ዘለምጽን (ማቴ. 26:6) : ቤተ አልዓዛር ወኒቆዲሞስን (ዮሐ. 12:1) መጥቀስ እንችላለን::
<< ስለዚህ ካህናትን ወደ ቤት ጠርቶ መጋበዙ (ግብረ ሰላም ማድረጉ) መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው:: >>
+በተአምረ ኢየሱስ ላይ እንደተጠቀሰው ደግሞ በበዓለ ሃምሳ ካህናትን እንደ አቅሙ (ከ1 ጀምሮ) ያበላ በፍርድ ቀን ከመከራ እንደሚያመልጥ ጌታ መናገሩ ተዘግቧል::
+በተለይ ግን አበው ሐዋርያትን ጌታ እንዲህ ብሏቸዋል ሲል ቅዱስ ማቴዎስ ነግሮናል::
"በምትገቡባትም በማናቸውም ከተማ ወይም መንደር : በዚያ የሚገባው ማን እንደሆነ በጥንቃቄ መርምሩ:: እስክትወጡም ድረስ በዚያ ተቀመጡ:: ወደ ቤትም ስትገቡ ሰላምታ ስጡ:: ቤቱም የሚገባው ቢሆን ሰላማችሁ ይድረስለት:: (ይደርበት) ባይገባው ግን ሰላማችሁ ይመለስላችሁ:: ከማይቀበላችሁም : ቃላችሁንም ከማይሰሙ ሁሉ ከዚያ ቤት ወይም ከዚያች ከተማ ስትወጡ የእግራችሁን ትቢያ አራግፉ:: እውነት እላቹሃለሁ:: በፍርድ ቀን ከዚያች ከተማ ይልቅ ለሰዶምና ለገሞራ አገር ፍርድ ይቀልላቸዋል::" (ማቴ. 10:11)
+በተጨማሪም "የሚያበራየውን በሬ አፉን አትሠር" ያለውን የኦሪት ትዕዛዝ "ይደልዎ አስቦ ለዘይትቀነይ-ለሠራተኛ ደሞዙ ይገባዋል" ሲል ጌታ ተናግሮታል:: የአነጋገሩ ምሥጢር ብዙ ቢሆንም በጥሬው ግን የካህናት ደሞዝ ከምዕመናን መሆኑን ያሳያል:: (ዘዳ.25:4, 1ቆሮ.9:9, ማቴ.10:10
4." አፈጻጸም "
=>ግብረ-ሰላም በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ (በቤተ ምርፋቅ) ሊከወን ቢችልም ብዙ ጊዜ የሚፈጸመው በምዕመናን ቤት ነው:: ለምን? . . . ቤታቸው በአበው ካህናት ይባረክ ዘንድ ይገባልና::
+ከትንሳኤ ማግስት ጀምሮ ምዕመናን እንደ አቅማቸው:-
1.መምህረ ንስሃ (የነፍስ አባታቸውን)
2.ከደብሩ ካህናት በቁጥር
3.የደብሩን ሁሉ አገልጋዮች
4.የአድባራትን ሊቃውንት . . . ሊጠሩ ይችላሉ:: ባለጠጐች ከሆኑ ብዙ ሊጠሩ ይችላሉ:: የኔ ብጤ የሆነ ደግሞ እንደ አቅሙ ማለት ነው::
+የተጠሩ ካህናት (ሊቃውንት) ወደ ቤት ሲደርሱ የቤቱ አባወራ አደግድጐ : እማወራዋ አገልድመው ከበር ላይ ይጠብቃሉ:: "እንኩዋን ደህና መጣችሁ" እያሉ አስገብተው በየማዕረጋቸው እንዲቀመጡ ይደረጋል::
+ከሁሉ የሚቀድም ጸሎት ነውና ማዕዱ ቀርቦ ጸሎት በርዕሰ ደብሩ ወይም በመምህሩ ይደረጋል:: ሲበላም በመስሪያ (6 ሆነው) ሲሆን ይህም ከ6ቱ ቃላተ ወንጌል ብዙዎቹ የሚከወኑበት መሆኑን ያጠይቃል:: በየመሥሪያው አበው እየቆረሱ "በእንተ ማርያም" ሰጥተው በሥርዓት ይበላል::
+መጠጥም (ወይን : ጠላ : ጠጅ ወይም ሌላ ሊሆን ይችላል) ጐን ለጐን ይቀርባል:: አጥንት ካለ እንደየ ማዕርጋቸው ለመምህራንና ለአበው ፍሪምባ : ቅልጥም ለምክትል መምህራን ወዘተ. ተሰጥቶ በቃለ ማኅዘኒ "ስብሐት ለአብ" ተብሎ እግዚአብሔር ይመሰገናል::
+መምህሩ አፉን አጥርቶ ትምህርት ከሰጠ በሁዋላ አበው እየተነሱ ይመርቃሉ:: የዜማ መምህራን በበኩላቸው የክርስቶስን ትንሳኤና የማዳን ሥራ የሚያዘክሩ ወረቦችን እየቃኙ ይወርባሉ:: ይቸበችባሉ:: በመጨረሻም ኑዛዜ ተሰጥቶ ስንብት ይሆናል::
+አበውና ካህናት "ስብሐት" ብለው ያተረፉትንም የቤቱ ባለቤቶች : ሕጻናትና ጐረቤት ሁሉ በደስታ ተካፍሎ ይበላዋል:: እጅግ ታላቅ በረከት ነውና::
5." ግብረ-ሰላም በትውፊት "
=>ይህ መንፈሳዊ ተግባር ምንም እንኩዋ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቢሆንም በቤተ ክርስቲያንና በሃገራችን ታሪክም ተዘግቦ የሚገኝ : ለባለጠጐች : ለመሣፍንቱና ለነገሥታቱ ከነ ስሙም "ግብር ማግባት" የሚባል ነበር::
+በዘመነ ሐዋርያትና ሰማዕታት አገልጋይ ካህናትን ሰብስቦ መጋበዙ የሚታሰብ አልነበረም:: ምክንያቱም ጊዜው የመከራና ክርስቲያኖች መብታቸው የተነፈገበት ነበርና::
+ከዘመነ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ወዲህ ግን ተመሳሳይ ግብር የማግባት (የግብረ ሰላም) ተግባራት እንደ ነበሩ ይታመናል:: እንደ ምሳሌም በ4ኛውና 5ኛው መቶ ክ/ዘ የነበሩ ደጋግ ነገሥታት (እነ ቴዎዶስዮስ 1ኛና 2ኛ : አርቃድዮስ : አኖሬዎስ : ዘይኑን እና አንስጣስዮስ) እንዲሁ ያደርጉ እንደ ነበር ገድላተ ቅዱሳን ያሳያሉ::
+በሃገራችን ኢትዮዽያም ከብሉይ ኪዳን ሲያያዝ የመጣው ተግባር በክርስትና ጸንቶ መቀጠሉን በነገሥታቱ ዜና መዋዕሎች ላይ መመልከት ይቻላል:: ሁሉም ነገሥታት ይህንን ያደርጉ ነበር ብሎ መናገር የሚቻልም ይመስለኛል:: በሕዝቡ ደረጃም አበው እና እማት ይህንን ሲከውኑ እዚህ ደርሰናል::
6." ዛሬስ "
=>ግብረ-ሰላም ዛሬም በትውፊታዊ ሥርዓቱ ቀጥሎ በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች ይከወናል:: በተለይ ደግሞ በሰሜኑ አካባቢ:: ነገር ግን አፈጻጸሙ ላይ ከሚታዩ ስሕተቶች የተነሳ ለጊዜውም ቢሆን እያስነቀፈን ይገኛል::
1.የተግባሩን መንፈሳዊነት ያልተረዱ አንዳንድ ምዕመናን . . . ሲጀመር "እንካ ብላ : አፈር ብላ" ዓይነት ግብዣ እያደረጉ አበው ካህናትን ሲያቀሉ ተመልክተናል::
2.በአንድ ጊዜ ጠጅ : ጠላ : አረቄ እና ውስኪን ቀላቅለው የሚጋብዙ እንዳሉም ሰምቻለሁ::
3.በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ "ማኅሌተ ገንቦ" በሚል ኃጢአት የሆነውን ዘፈን የሚሞክሩም አይጠፉምና "ቢታሰብበት!" ባይ ነኝ::
+ይህንን የመሰለ መጽሐፋዊ : ትውፊታዊና ታሪካዊ የበረከት ሃብታችንን በሥርዓቱ ማስቀጠል ብንችል . . . ወዲህ እንጠቀማለን:: ወዲያ ደግሞ ለትውልድ እናስተላልፋለን::
‹‹የእግዚአብሔር ሙላቱ በእርሱ እንዲኖር በእርሱ በኩል በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ያሉት ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዷልና ›› (ቆላ. 1:19-20)
=>የሰላም አምላክ የእርሱን ሰላም (ዮሐ. 14:27) : የድንግል እናቱን ሰላም (ሉቃ. 1:41) : የቅዱሳኑን ሰላም (ማቴ. 10:13) በእኛ ላይ ያሳድርብን::
<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር:: አሜን:: >>>
Re =>(2012)። Dn Yordanos Abebe
=>በድጋሚ (2014)
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
✝ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together
https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━
Comments
Post a Comment