✞✞✞ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✞✞✞
❖ ግንቦት 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
+"+ አባ መቃርስ ካልዕ +"+
+ይህ ቅዱስ "መቃርዮስ: መቃርስ: መቃሬም" ይባላል::
ትርጉሙ በ3ቱም መንገድ አይለወጥም:: ምክንያቱም
ሥርወ ቃሉ
በዮናኒ ልሳን "ብጹዕ: ንዑድ: ክቡር" ማለት ነውና::
+ከስሙ ቀጥሎ "ካልዕ-2ኛው": አንዳንዴ ደግሞ
"እስክንድርያዊ" እየተባለ ይጠራል:: "ካልዕ-2ኛው"
የሚባለው ከቀዳሚው
(ታላቁ መቃርስ) ለመለየት ሲሆን "እስክንድርያ" ደግሞ
ተወልዶ ያደገባት ሃገር ናት::
+አባ መቃርስ በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረ ገዳማዊ:
ጻድቅና ትሩፈ-ምግባር ነው:: በዓለም ለ40 ዓመት ሲኖር
እንደ ሕጉ
ፈጣሪውን ደስ ያሰኘ ሰው ነው:: ጻድቃን እንደ ከዋክብት
በበዙበት በዚያ ዘመን የታላቁ መቃርስን ዜና ሰምቷልና
ይህቺን
ክፉ ዓለም ከነግሳንግሷ ንቋት በርሃ ገብቷል::
+እንደሚገባ ሥርዓተ ገዳምን ጠብቆ: ለአበው ታዞ:
በጾም: በጸሎት: በትሕትናና በስግደት ተጠምዶ ቢያገኘው
ፈጣሪ አከበረው::
በዚያ ጊዜም ለታላቁ ገዳመ አስቄጥስ መናንያን አበ
ምኔት ሊሆን መረጡት::
+እርሱም እረኝነትን ያውቃልና በጐቹን (መነኮሳትን)
ከተኩላ (ሰይጣናት) ይጠብቅ ዘንድ ብዙ ተጋ:: ከብቃቱ
የተነሳም
ሳያስታጉል: ሳይበላ: ሳይጠጣና ሳይቀመጥ እስከ 40 ቀን
ይጸልይ ነበር:: ሲጸልይ ደግሞ በልቡ እየተቃጠለ በፍቅረ
ክርስቶስ ነበርና አጋንንት ይርዱለት ነበር::
+እርሱ ጸሎት ሲጀምርም በገዳሙ ዙሪያ ያሉ አጋንንት
እየጮሁ ይሸሹ ነበር:: ከተጋድሎው ጽናትና ከትሕትናው
ብዛት የተነሳ
ያዩት ትዕቢተኞች ሁሉ ይገሠጹ ነበር:: በዘመኑም ብዙ
ተአምራትን ሠርቷል::
+አንድ ቀን በበዓቱ ሳለ ጅብ መጥታ ተማጸነችው::
አብሯት ወደ ዋሻዋ ቢሔድ ልጆቿ በሙሉ ዓይነ ሥውራን
ሆነው አገኛቸው::
እርሱም ወደ መሬት ምራቁን እትፍ ብሎ በጭቃ ለውሶ
ቢቀባቸው የሁሉም ዐይናቸው በርቷል::
+ስለ ውለታውም ጅቢቱ የበግ ቆዳ እየጐተተች አምጥታ
ሰጥታዋለች:: (ከሰው ልጅ በቀር እንስሳት ውለታን
አይረሱምና) ቅዱስ
መቃርስም ለወትሮው ባዶው መሬት (አፈር) ላይ ይተኛ
የነበረው ከዚያ ቀን በኋላ በአጐዛው ላይ የሚተኛ ሁኗል::
+በሃገሩ እስክንድርያም ለ2 ዓመታት ዝናብ በመጥፋቱ
ሕዝቡ ተጨንቆ ነበርና "ናልን" ሲሉ መልዕክት ላኩበት::
እርሱ መጥቶ
ሲጸልይም መብረቅ የቀላቀለ ዝናብ ጣለ:: ዝናቡም ያለ
ማቆም ለ2 ቀናት በመዝነቡ ሕዝቡ ፈርተው "አባታችን ስለ
ኃጢአታችን
እንዳንጠፋ ለምንልን?" አሉት:: እርሱም በጸሎቱ
(በፈጣሪው ኃይል) እንደ ወደዱት ዝናቡን አቁሞላቸዋል::
+የአባ መቃርስን ዜና ሕይወትና ተአምራት ተናግሬ
አልፈጽመውም:: ግን አንዲት ብቻ ላክል:: ሁሌ ሳስበው
ስለሚገርመኝም
ነው::
+ብዙዎቻችን የጌታችን ሥጋና ደም አንቀበልም:: ለምን
ያከበርነውና የፈራነው አስመስለን ኃጢአትን ለመጥገብ
ቦታን (
አጋጣሚን) ስለምንፈልግ:: በተቃራኒው ደግሞ
አንዳንዶቻችን መለኮት የተዋሐደውን የጌታ ሥጋና ደም
እንደ ተርታ ነገር (ያለ
ጥንቃቄ) ስንቀበል ይታያል:: 2ቱም ግን ስሕተት ነው::
+ፈርተን (ፍርሃቱ ጤነኛ ባይሆንም) ስለ ራቅን በፍርድ ቀን
ማምለጥ አንችልም:: "ሥጋየን ያልበላ: ደሜንም ያልጠጣ
የዘለዓለም ሕይወት የለውም" ይለናልና:: (ዮሐ. 6:52)
+በድፍረት ለምንቀበልም ሥጋው እሳት ሁኖ እንዳይበላን:
ደሙም ባሕር ሆኖ እንዳያሰጥመን ልናከብረው ይገባናል::
"ሳይገባው
ከጌታ ሥጋና ደም የተቀበለ የጌታ ሥጋ ዕዳ አለበት"
ይለናልና:: (1ቆሮ. 11:27)
<< ታዲያ የሚሻለው ለሁላችንም ንስሃ ገብቶ: በፍርሃት
ሆኖ መቅረቡ ነው:: >>
+ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና አባ መቃርስ ወደ በርሃ
እንደ ገባ ሥጋ ወደሙን ተቀብሎ ነበር:: ቅዱሱ ይህንን
እያሰበ
ለ60 ዓመታት ምራቁን ሳይተፋ ኑሯል:: ለዚያ አይደል
አበው "ብታከብሩት ያከብራቹሃል" ያሉት::
+ሊቃውንቱም ይህንን ሲያደንቁ:-
"ኢታስተማስልዎ ለቁርባን ከመ ሕብስት ዕራቆ::
አኮኑ ሥጋ መለኮት ዘይትላጸቆ::
መቃርዮስ አብ ዕበየ ቁርባን ለአጠይቆ::
ድኅረ ተወክፈ በአሚን እንበለ ያብዕ ናፍቆ::
መጠነ ዓመታት ስሳ ኢተፍአ ምራቆ::" ብለዋል::
+ቅዱስ መቃርስም በ100 ዓመቱ በ5ኛው ክ/ዘመን
መጀመሪያ አካባቢ በዚህች ቀን ዐርፏል::
❖ጌታችን ከክብሩ: ከበረከቱ አይለየን::
=>ግንቦት 6 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ አባ መቃርስ ገዳማዊ
2.እናታችን ቅድስት ሰሎሜ ኢትዮዽያዊት
3.አባ ይስሐቅ ጻድቅ
4.ቅድስት ዲላጊና 4 ሴት ልጆቿ (ሰማዕታት)
5.ቅዱስ ዳናስዮስ ሰማዕት
6.ቅዱስ በንደላዖስ ሰማዕት (የታላቁ ኤስድሮስ አባት)
7.አባ አሞን ጻድቅ (ዽዽስናን አልፈልግም ብሎ የሸሸ አባት)
=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅድስት ደብረ ቁስቁዋም
2.አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን
3.አባታችን ኖኅና እናታችን ሐይከል
4.ቅዱስ ኤልያስ ነቢይ
5.ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ
6.ቅዱስ ዮሴፍ አረጋዊ
7.ቅድስት ሰሎሜ
8.አባ አርከ ሥሉስ
9.አባ ጽጌ ድንግል
10.ቅድስት አርሴማ ድንግል
=>+"+ ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘለዓለም ሕይወት አለው:: እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሳዋለሁ:: ሥጋዬ እውነተኛ መብል: ደሜም እውነተኛ መጠጥ ነውና:: ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል:: እኔም በርሱ እኖራለሁ:: +"+ (ዮሐ. 6:53-56)
<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
✝ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together
https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━
Comments
Post a Comment