††† እንኳን ለጻድቁ አባታችን ቅዱስ ጐርጐርዮስ ረዓዬ ኅቡዓት ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††
††† ቅዱስ ጐርጐርዮስ ረዓዬ ኅቡዓት †††
††† ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሃገሩ ሮሃ (ሶርያ አካባቢ) ሲሆን ረዓዬ ኅቡዓት (ምሥጢራትን የተመለከተ) ይባላል::
ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
ቅዱሱ ተወልዶ ባደገባት ሃገር ይህ ቀረው የማይባል ኃጢአተኛ ሰው ነበር:: ታዲያ ምንም ኃጢአተኛ ሰው ቢሆን እመቤታችን ድንግል ማርያምን በፍፁም ልቡ ይወዳት ነበርና በመዳን ቀን ጥሪ ለንስሐ አበቃችው::
ከዚያች ዕለት ጀምሮም ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰው : ንጹሕ የቤተ ክርስቲያን መስዋዕት : ጽኑዕ የበርሃ ምሰሶ ሆነ:: ድንግል እመቤታችንም ከነሥጋው ወደ ሰማያት ወስዳ ገነትና ሲዖልን አሳይታ : ከአዳም : ኖኅ : አብርሃም : ሙሴ : ዳዊትን ከመሰሉ ቅዱሳን ጋር አስተዋውቃ : ከዚህም በላይ የሆነና በሰብአዊ አንደበት የማይነገር ብዙ ምሥጢር አሳይታ ወደ ምድር መልሳዋለች::
ቅዱስ ጐርጐርዮስ በሰማይ (በገነት) በነበረው ቆይታ ክብረ ቅዱሳንን ተመልክቶ አድንቋል:: በተለይ በፍጹምነት ድንግልናቸውን የጠበቁ ቅዱሳንና ቅዱሳት ደናግል አኗኗራቸው ከአምላክ እናት : ከሰማይ ንግሥት : ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም ጋር መሆኑን አይቷል::
"የለበሱት ልብስም በፍጡር አንደበት ተከናውኖ ሊነገር የሚቻል አይደለም" ይላል:: የደናግል ፊታቸው ከፀሐይ 7 እጅ ያበራልና ግርማቸው ያስፈራል::
ቅዱሱ ሰው በዚያው በሰማይ ሳለ ደግሞ ይህንን ተመለከተ:: አንድ አረጋዊ : ጽሕሙ ተንዠርግጐ : የብርሃን ካባ ላንቃ ለብሶ ይመጣል:: ቅዱሳን መላእክት በፊት በኋላ : በቀኝ በግራ ከበውት ሳለ እግዚአብሔርን ሊያመሰግን ጀመረ::
"እግዚኦ እግዚእነ : ጥቀ ተሰብሐ ስምከ በዲበ ምድር (አቤቱ ጌታችን : በምድር ሁሉ ስምህ የተመሰገነ ሆነ)" ሲል . . . መላእክቱ በዝማሬ አጀቡት:: በዚህ ጊዜም ታላቅ መናወጥ ሆነ:: ደናግሉም የቅዱሱን ሽማግሌ በረከቱን ተሳተፉ::
ይህ አመስጋኝ ሽማግሌ ልበ-አምላክ : ጻድቅ : የዋህና የእሥራኤል ንጉሥ የሆነው ዳዊት ነበር:: በምን ታወቀ ቢሉ :- በበገናው:: አንድም እመቤታችን "አባቴ ዳዊት!" ብላ ስትጠራው ጐርጐርዮስ ሰምቷልና::
በመጨረሻም እመቤታችንን በፍጹም ክብርና ግርማ ተመልክቷት ሐሴትን አድርጓል:: እመ-ብርሃንም "ተወዳጅና ንጹሕ ሰው ነህ" ስትል ቅዱስ ጐርጐርዮስን አመስግናዋለች:: ስለዚህ ዓለምም እንዲህ የሚል መልእክትን ልካለች::
"ልጆቼ ሆይ! ከብርሃን ጨለማን : ከደግነት ክፋትን : ከጽድቅ ይልቅ ኃጢአትን . . . ምነው መምረጣችሁ? እኔ ስለ እናንተ በየቀኑ እየለመንሁ እነሆ አለሁ:: ወደ ጨለማ ገሃነም እንዳትወርዱ እባካችሁ ንስሐ ግቡ!"
ቅድስት ድንግል ማርያም ይህንን ለቅዱሱ ሰው ነግራው : ቅዱስ ዳዊትን አስከትላ : በግሩማን መላእክት ታጅባ ወደ ውሳጤ መንጦላዕት (የእሳት መጋረጃዎች ወደ ተተከሉበት ድንኳን) ገባች:: በዚያም ተመሰገነች::
ለዛም አይደል ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ:-
"ይዌድስዋ መላእክት ለማርያም በውስተ ውሳጤ መንጦላዕት : ወይብልዋ : በሐኪ ማርያም ሐዳስዩ ጣዕዋ::" ሲል ያመሰገናት::
ቅዱስ ጐርጐርዮስም ከሰማይ ቆይታ መልስ ያየውን ሁሉ ጽፎ ለአበው ሰጥቷል:: ስለዚህም ረዓዬ ኅቡዓት (ምሥጢራትን ያየ) ይሰኛል:: ቅዱሱ ተረፈ ዘመኑን በተጋድሎ ፈጽሞ በዚህች ቀን አርፏል::
††† የቅዱሱ እመቤት ድንግል እመ ብርሃን መዓዛ ፍቅሯን ታብዛልን::
††† መጋቢት 2 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ረዓዬ ኅቡዓት (ዘሃገረ ሮሃ)
2.አቡነ መክፈልተ ማርያም ጻድቅ (ኢትዮጵያዊ)
3.አባ መከራዊ ዘሃገረ ኒቅዮስ (አረጋዊ: ጻድቅ: ጳጳስና ሰማዕት)
††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
2.ቅዱስ ታዴዎስ ሐዋርያ
3.ቅዱስ ኢዮብ ጻድቅ ተአጋሲ
4.ቅዱስ አቤል ጻድቅ
5.ቅዱስ አባ ጳውሊ ገዳማዊ (ታላቁ)
6.ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ
7.አባ ሕርያቆስ ዘሃገረ ብሕንሳ
††† "ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው:: ከኃጢአተኞችም ዋና እኔ ነኝ:: ስለዚህ ግን የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት በእርሱ ያምኑ ዘንድ ላላቸው ሰዎች ምሳሌ እንድሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ዋና በምሆን በእኔ ላይ ትዕግስቱን ሁሉ ያሳይ ዘንድ ምሕረትን አገኘሁ::" †††
(፩ጢሞ. ፩፥፲፭)
††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
✝ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together
https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━⊱✿⊰━━
Comments
Post a Comment