✞✝ እንኩዋን "ለኖላዊ ሔር ክርስቶስ" : ለቅዱሳን "በርናባስ ሐዋርያ" እና "አባ ይስሐቅ" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✝✞✝
+*" ኖላዊ ሔር "*+
=>እግዚአብሔር አዳምን በ7 ሃብታት አክብሮ በገነት ቢያኖረው "አትብላ" የተባለውን ዕፀ በለስ በላ:: በዚህም ከፈጣሪው ተጣልቶ: በሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ: በርደተ መቃብር ርደተ ገሃነም ተፈረደበት:: በሁዋላ ግን ንስሃ ስለ ገባ "ከ5 ቀን ተኩል (5,500 ዘመን) በሁዋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ" የሚል ቃል ኪዳንን ሰጠው::
+ከዚህ በሁዋላ ለ5,500 ዘመናት ጊዜ ወደ ታች ይቆጠር ጀመር:: ስለ እግዚአብሔር ሰው መሆንና ዓለምን ማዳንም ትንቢት ይነገር: ሱባኤ ይቆጠር: ምሳሌም ይመሰል ገባ::
+ከአዳም እስከ ሙሴ (ዘመነ አበው) ምሳሌያት ይበዛሉ:: ከሙሴ እስከ ዳዊት (ዘመነ መሣፍንት) ምሳሌያቱ እየጐሉ መጥተዋል:: ከልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት እስከ ቅዱስ ሚልክያስ ድረስ (በዘመነ ነቢያት / ነገሥት) ግን ትንቢቶች ስለ ክርስቶስና ስለ ማደሪያ እናቱ እንደ ጐርፍ ፈሰዋል::
+ነቢያትም የመሲህን መምጣት እየጠበቁ በጾም: በጸሎትና በትሕርምት ኑረዋል:: እንባቸውንም አፍሰው ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶላቸዋል::
=>ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህችን ዕለት "ኖላዊ ሔር" ብላ ታከብራለች:: ይሕንንም ለሳምንት ያህል ታዘክራለች:: መሠረታዊ መነሻዋም (ዮሐ. 10:1) ነው:: "ኖላዊ" ማለት በቁሙ "እረኛ" ማለት ሲሆን "ሔር" ደግሞ "ቸር-ርሕሩሕ-አዛኝ" እንደ ማለት ነው::
+ገጥመን ብንተረጉመው ደግሞ "ቸር እረኛ" የሚል ትርጉምን ይሰጠናል:: ከአባታችን አዳም ስህተት በሁዋላ ተፈጥረው ከነበሩ ችግሮች አንዱ ቸር እረኛ ማጣት ነው:: እግዚአብሔር አዳምን ፈጥሮ: ቸር እረኛ ሆኖ በገነት አሰማርቶት ነበር::
+ኤዶም ገነት የለመለመች: ፈሳሾች የሞሉባት መልካም መስክ ናትና:: አባታችን ቅዱስ አዳም ደግሞ እንደ አቅሙ የጸጋ እረኝነት ተሰጥቶት ነበር:: ድቀት ካገኘው በሁዋላ ግን ከነፍስ እረኛው ጋር ተጣልቶ ከመልካሟ መስክ ገነት ወጣ::
+እርሷንና የነፍሱን እረኛ ሲሻም አለቀሰ:: ተስፋ ድኅነት ሲሰጠውም ለልጆቹ ነገራቸው:: ከዚያም በመንጋው ላይ በአዳም ሴት ተተካ:: ከሴት ኄኖስ: ከኄኖስ: ቃይናን . . . እያለ ከኖኅ ደረሰ::
+ከኖኅም በሴም ከአብርሃም: ከአብርሃምም በይስሐቅና በያዕቆብ ወርዶ ከሙሴ ደረሰ:: ከሙሴም በኢያሱ አልፎ ከነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ደረሰ:: እነዚህ ሁሉ እረኞች ምንም እንኩዋ ለእግዚአብሔር ሕዝብ በትጋት ቢሠሩም ሕዝቡን ከሲዖል ማዳን አልቻሉም::
+ከሲዖል የሚያድን የነፍስ እረኛ ነውና ያን ጊዜ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት የራሱን: የአባቶቹንና የልጆቹን ጩኸት ባንድ አድርጐ ጮኸላቸው:: "ኖላዊሆሙ ለእሥራኤል አጽምዕ - የእሥራኤል እረኛ ሆይ ስማን!" አለ:: (መዝ. 79:1)
+ጩኸቱም ቅድመ እግዚአብሔር ደረሰ:: ይህንን የሰማ ጌታም በጊዜው ከድንግል ማርያም ተወለደ:: በየጥቂቱ አድጐ ቸር እረኝነቱን ገለጠ:: መድኃኒታችን እንዳስተማረን እርሱ ቸር እረኛ ነው::
+ከእርሱ በፊት የተነሱት ቴዎዳስ ዘግብጽና ይሁዳ ዘገሊላ (ሐዋ. 5:36, ዮሐ. 10:8) ሐሰተኛ እረኞች ነበሩ:: እርሱ ግን እውነተኛው የበጐች በር ነውና (ዮሐ. 10:7) በእርሱ የሚገቡ ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን ያገኛሉ::
+እርሱ እውነተኛ እረኛ ነውና (ዮሐ. 10:11) ለመንጋው ራሱን አሳልፎ ይሰጣል:: በእሥራኤል ባሕል እረኞች ከፊት: መንጋው (በጐቹ) ከሁዋላ ሆነው ይሔዳሉና ገዳይ ቢመጣ መጀመሪያ የሚገድለው እረኛውን ነው::
+መድኃኒታችን ክርስቶስ በሞቱ ሕይወትን: በመራቆቱ የጸጋ ልብስን: በውርደቱ ክብርን: በድካሙ ኃይልን ይሰጠን ዘንድ ስለ እኛ ራሱን አሳልፎ ሰጠ:: የማይሞት ንጉሥ ስለ መንጋው ሞተ:: ሰማይን ከነግሡ ምድርንም ከነልብሱ የፈጠረ ጌታ (ዘፍ. 1:1, ዮሐ. 1:2) ስለ በጐቹ ይህንን ሁሉ ታግሦ ከሲዖል አዳነን::
+በሚያርግ ጊዜም በእርሱ ፈንታ ባለ ሙሉ ስልጣን እረኞችን: ሐዋርያትን (ዮሐ. 21:15) ሊቃነ ዻዻሳትን (ሐዋ. 20:28) ካህናትን (ማቴ. 18:18) ሾመልን:: እነርሱን እረኞች አሰኝቶ እርሱ "ሊቀ ኖሎት-የእረኞች አለቃ" ተባለ:: እነርሱም እስከ ዓለም ፍጻም የክርስቶስን መንጋ ሊጠብቁ ስልጣኑም: ኃላፊነቱም አለባቸው:: (ማቴ. 28:19)
+*" ቅዱስ በርናባስ ሐዋርያ "*+
=>ቅዱሱ ሐዋርያ ስሙ ሲጠራ ሞገስ አለው:: የቅዱሱ ሰው የመጀመሪያ ስሙ ዮሴፍ ሲሆን በርናባስ ያለው መድኃኒታችን ክርስቶስ ነው:: ትርጉሙም "ወልደ ኑዛዜ-የመጽናናት ልጅ" እንደ ማለት ነው::
+በምሥጢሩ ግን "ማሕደረ መንፈስ ቅዱስ-የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ" እንደ ማለት ያስተረጉማል:: ቅዱስ በርናባስ ምንም በትውልዱ እሥራኤላዊ ቢሆን ተወልዶ ያደገው በቆዽሮስ ነው:: እስከ ወጣትነት ጊዜውም የቆየው እዚያው ነው::
+የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የመሆኑ ዜና ሲሰማ ግን ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ መድኅን ክርስቶስን ተመለከተ:: ጌታውንም ሊከተል በልቡ ቆረጠ:: የፈጠረን ክርስቶስም እንዲረባ (እንዲጠቅም) አውቆ: ስሙን ቀይሮ አስከተለው:: ከ72ቱ አርድእትም ደመረው::
+ቅዱስ በርናባስ እንደ ወንድሞቹ ሐዋርያት ለ3 ዓመት ከ3 ወር ከጌታ እግር ቁጭ ብሎ ተማረ:: ተአምራቱንም ሁሉ ተመለከተ:: ከጌታ ዕርገት በሁዋላ 120ው ቤተሰብ በጽርሐ ጽዮን ሲጸልዩም አብሮ ይተጋ ነበር::
+በጊዜውም አበው ሐዋርያት በይሁዳ ፈንታ ከ12ቱ የሚቆጠረውን ሰው ለመምረጥ 2 ሰዎችን አቅርበው ነበርና አንዱ ይኸው ቅዱስ ነው:: እዚያውም ላይ ጌታችንን ከመጀመሪያው ጀምሮ ማገልገሉ ተመስክሮለታል:: (ሐዋ. 1:22)
+ስሙንም ኢዮስጦስ ብለውታል:: ባለ 3 ስም ነበርና:: በወቅቱም ዕጣ በቅዱስ ማትያስ ላይ ስለ ወደቀ በርናባስ ከ72ቱ አርድእት: ማትያስ ከ12ቱ ሐዋርያት ሆነው ቀጠሉ::
+ከዚህ በሁዋላ ቅዱስ በርናባስ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ በኃይል ያገለግል ጀመር:: የሐዋርያትን ዜና በሚናገር መጽሐፍ ላይ የተጻፉና ስለ ቅዱሱ ማንነት የሚናገሩ ክፍሎችን እንመልከት::
1.ቅዱሳን ሐዋርያት የእኔ የሚሉት ንብረት ሳይኖራቸው: ያላቸውን በጋራ እየተጠቀሙ በፍቅር ይኖሩ ዘንድ የመንፈስ ቅዱስ ትዕዛዝ ነበር:: ያለውን ሁሉ ሸጦ በሐዋርያት እግር ላይ በማኖር ደግሞ ቀዳሚውን ሥፍራ ቅዱስ በርናባስ ይይዛል:: (ሐዋ. 4:36) በዚህም የዘመነ ሐዋርያት የመጀመሪያው መናኝ ተብሏል::
2.ልሳነ እፍረት (ብርሃነ ዓለም) ቅዱስ ዻውሎስ ባመነ ጊዜ ሐዋርያት ለማመን ተቸግረው ነበር:: የሆነውን ሁሉ አስረድቶ ቅዱስ ዻውሎስን ከሐዋርያት ጋር የቀላቀለው ይህ ቅዱስ ነው:: (ሐዋ. 9:26)
3.አንድ ቀን መንፈስ ቅዱስ "ፍልጥዎሙ ሊተ ለሳውል ወለበርናባስ - በርናባስና ሳውልን (ዻውሎስን) ለዩልኝ" በማለቱ ሐዋርያት ጾመው: ጸልየው: እጃቸው ከጫኑባቸው በሁዋላ ላአኩአቸው:: (ሐዋ. 13:1)
+እነርሱም ወንጌልን እየሰበኩ በየሃገሩ ዞሩ:: በሃገረ ልስጥራን መጻጉዕን ስለ ፈወሱ ሕዝቡ "እናምልካችሁ" ብለው የአማልክትን ስም አወጡላቸው:: 2ቱ ቅዱሳን ግን ይህንን ሲሰሙ ልብሳቸውን ቀደው በጭንቅ አስተዋቸው:: መመለክ የብቻው የፈጣሪ ገንዘብ ነውና:: (ሐዋ. 14:8-18, ዘጸ. 20:1)
4.በአንጾኪያ የነበሩ አሕዛብ ክርስትናን በተቀበሉ ጊዜ ከሐዋርያት ተልኮ ሒዶ በጐ ጐዳናን መራቸው:: (ሐዋ. 11:22)
+ቅዱስ በርናባስ በአገልግሎት ዘመኑ መጀመሪያ ከቅዱስ ዻውሎስጋር: ቀጥሎ ደግሞ ቅዱስ ማርቆስን አስከትሎ ብዙ አሕጉራትን አስተምሯል:: ቆዽሮስም ሃገረ ስብከቱ ናት::
+ቅዱሱ ከብዙ ትጋት በሁዋላ በዚህች ቀን አረማውያንና አይሁድ ገድለውታል:: ቅዱስ ማርቆስም ገንዞ ቀብሮታል::
<< ስለርሱ መጽሐፍ "ደግ: መንፈስ ቅዱስ የሞላበት ነው" ይላልና ክብር ይገባዋል !! >> (ሐዋ. 11:24)
+"+ አባ ይስሐቅ ጻድቅ +"+
=>ይህ ቅዱስ በመካከለኛው ዘመን በምድረ ግብጽ የነበረ ገዳማዊ ነው:: መንኖ ለብዙ ዘመናት በገዳም ሲኖር ምኞቱ አንዲት ብቻ ነበረች:: እመቤታችንን በአካል መመልከትን ይፈልግ ነበር::
+የገዳሙ ጠባቂ በመሆኑ መነኮሳት ሲተኙ መቅደሱን ከፍቶ በድንግል ማርያም ስዕል ፊት ይጸልይ: ይሰግድ: ያነባ ነበር:: እንዲህ ለ7 ዓመታት ስለ ተጋ ድንግል እመ ብርሃን ልመናውን ሰማች::
+በዚህ ዕለትም ከፀሐይ 7 እጅ ደምቃ ወደ እርሱ መጣች:: ደንግጦ ሲወድቅ አነሳችው:: "ከ3 ቀናት በሁዋላ እመለሳለሁ" ብላም ተሠወረችው:: በ23ም ዐረፈ::
"በዛቲ ዕለት ሶበ ጸለየ ጥቡዐ::
ለይስሐቅ አስተርዓየቶ እም አይቆናሃ ወጺአ::
እምጸዳለ መብረቅ ጥቀ እንዘ ትጸድል ስብአ::" እንዳለ ደራሲ:: (አርኬ)
=>የእሥራኤል እረኛ ሥጋችንን ከመቅሰፍት: ነፍሳችንን ከገሃነመ እሳት ይጠብቅልን:: ከበረከተ ቅዱሳንም ይክፈለን::
=>ታሕሳስ 21 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ኖላዊ ሔር
2.ቅዱስ በርናባስ ሐዋርያ
3.አባ ይስሐቅ ጻድቅ
=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅድስት ድንግል እግዝእትነ ማርያም
2.አበው ጎርጎርዮሳት
3.አቡነ ምዕመነ ድንግል
4.አቡነ አምደ ሥላሴ
5.አባ አሮን ሶርያዊ
6.አባ መርትያኖስ ጻድቅ
=>+"+ መልካም እረኛ እኔ ነኝ:: አብም እንደሚያውቀኝ: እኔም አብን እንደማውቀው የራሴን በጐች አውቃለሁ:: የራሴም በጐች ያውቁኛል:: ነፍሴንም ስለ በጐች አኖራለሁ:: ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጐች አሉኝ:: እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል:: ድምጼን ይሰማሉ:: አንድም መንጋ ይሆናሉ:: +"+ (ዮሐ. 10:14)
✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞
✞ ወለወላዲቱ ድንግል ✞
✞ ወለመስቀሉ ክቡር አሜን ✞
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ::" /ማቴ ፫:፫/
ዝክረ ቅዱሳንን ተማሩ ብለን እንለምናችኋለን!!።
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together.https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━━━
Comments
Post a Comment