✝✞✝ እንኩዋን ለቅዱሳን "ሐዋርያት ቶማስ ወቲቶ" እና "አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✝✞✝
+*" ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ "*+
=>ከ12ቱ ቅዱሳን ሐዋርያት አንዱ የሆነው ቅዱስ ቶማስ ብዙ መከራን በማሳለፉና የጌታችንን ጐን በመዳሰሱ ይታወቃል::
+ቅዱስ ቶማስ እንደ ሌሎቹ ሐዋርያት በእሥራኤል ተወልዶ በዚያውም በሥርዓተ ኦሪት አድጐ ገና በወጣትነቱ የሰዱቃውያንን ማሕበር ተቀላቅሏል:: ሰዱቃውያን ሰው ከሞተ በሁዋላ አይነሳም (አልቦ ትንሳኤ ሙታን) የሚሉ ናቸው:: መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማስተማር ሲጀምር ግን ቅዱስ ቶማስ ከነበረበት ማሕበር ወጥቶ ጌታችንን ተከተለ:: ጌታችንም ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ ይሆን ዘንድ ሾመው:: የቀደመ ስሙ "ዲዲሞስ" ሲሆን ጌታችን "ቶማስ" ብሎታል::
+ቅዱስ ቶማስ ጌታ አልዓዛርን ለማስነሳት በሔደ ጊዜ ሌሎች ሐዋርያት ጌታን "አይሁድ ይገድሉሃል ቅር" ሲሉት እርሱ ግን "እንሒድና አብረን እንሙት" ሲል ፍቅሩን አሳይቷል:: (ዮሐ. 11:16)
+ጌታችን ትንሳኤውን ለደቀ መዛሙርቱ በገለጠ ጊዜ ያልነበረው ቶማስ ካላየሁ አላምንም አለ:: ምክንያቱም:-
1.ለጌታችን ከነበረው ፍቅር የተነሳ እውነት አልመስልህ ቢለው::
2.አንድም "ሌሎቹ ሐዋርያት ትንሳኤውን አየን እያሉ ሲያስተምሩ እኔ ግን ሰማሁ ብየ ማስተማሬ ነው" ብሎ በማሰቡ ነበር::
+ለጊዜው ጌታ ተገልጾ ቢገስጸው "እግዚእየ ወአምላኪየ (ጌታየና አምላኬ)" ብሎ ፍጹም ሃይማኖቱን ገልጿል:: ለፍጻሜው ግን የጌታችንን ጎን (መለኮትን) ይዳስስ ዘንድ ባለቤቱ እንዳደለው ያጠይቃል:: መለኮትን የዳሰሰች ይሕቺ ቅድስት እጁ ዛሬም ድረስ ሕያው ናት::
+ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ሐገረ ስብከት ሲከፋፈሉ ለቅዱስ ቶማስ ሕንድና በዙሪያዋ ያሉ ሃገራት ደረሱት::
+ከዚህ በሁዋላ ነው እንግዲህ ዘርዝረን የማንጨርሰውን ተጋድሎ የፈጸመው:: ቅዱሱ በነበረው ፍጹም ትጋት አባቶቻችን "ዘአሠርገዋ ለብሔረ ሕንደኬ (ሕንድን በወንጌል ያስጌጣት)" ሲሉ ያከብሩታል::
+ቅዱስ ቶማስ ንጉሥ ሉክዮስንና የሃገሩን ሕዝብ ለማሳመን በችንካር መሬት ላይ ወጥረው ቆዳውን ገፈውታል:: ቆዳውንም እንደ ገና ሰፍተው: አሸዋ ሞልተው አሸክመውታል:: በየመንገዱ የተገፈፈ ገላውን ጨው ቢቀቡት በጎች መጥተው ግጠው በልተውታል:: በዚሕ ምክንያት:-
"ኩሉ የአኪ እንዘ የአኪ ዘመኑ::
አባግዒሁ ለቶማስ እስመ አራዊተ ኮኑ::" ብለዋል ሊቃውንቱ::
+በሁዋላ ግን ከፎቅ ወድቃ የሞተችውን የንጉሡን ሚስት በተገፈፈ ቆዳው በማዳኑ ሁሉም አምነው ተጠምቀዋል::
+ቅዱሱ ሐዋርያ ልክ እንደ ቅዱስ ዻውሎስ አንዳንዴ በፈሊጥ: ሌላ ጊዜም በመከራ ለወንጌልና ለቤተ ክርስቲያን ተጋድሏል:: ያለ ማቁዋረጥም ከሕንድ እስከ ሃገራችን ኢትዮዽያ ድረስ ለ38 ዓመታት ወንጌልን ሰብኩዋል:: በመጨረሻም በ72 ዓ/ም በሰማዕትነት አርፏል:: መቃብሩና ቅድስት እጁ ዛሬ ድረስ ሕንድ ውስጥ አሉ:: ከኘሮቴስታንቶች በቀር መላው ዓለም ያከብረዋል:: ዛሬ የቅዱሱ ሐዋርያ በዓለ ፍልሠቱ ነው::
+*" ቅዱስ ቲቶ ሐዋርያ "*+
=>የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ቅዱስ ቲቶ ከ72ቱ አርድእት አንዱ ሲሆን በተወሰነ መንገድም ቢሆን የተዘነጋ ሐዋርያ አይደለም:: በተለይ ደግሞ ቅዱስ ዻውሎስ ከጻፋቸው 14 መልእክታት መካከል አንዷ የተላከችው ለዚህ ቅዱስ በመሆኗ ታሪኩ እንኩዋ ባይነገር ስሙ አይረሳም:: ቅዱስ ዻውሎስም በመልዕእክታቱ በጐ ስሙን እየደጋገመ ያነሳዋል::
=>ለመሆኑ ሐዋርያው ቅዱስ ቲቶ ማን ነው?
+ቅዱስ #ቲቶ የተወለደው በ1ኛው መቶ ክ/ዘ እስያ ውስጥ ቀርጤስ በምትባል ከተማ ነው::
+መዳን በእውቀት ይመስላቸው ስለ ነበር የአካባቢው ሰዎች የግሪክን ፍልስፍና ጠንክረው ይማሩ ነበር:: ቅዱስ ቲቶም በወጣትነቱ ወደ ት/ቤት ገብቶ የግሪክን ፍልሥፍናና የዮናናውያንን ጥበበ ሥጋ ተማረ:: በጥቂት ጊዜም የሁሉ የበላይ ሆነ::
+ቅዱሱ ምክንያቱን ሳያውቀው ለእኔ ቢጤዎች ያበላ: ያጠጣ: ይንከባከባቸውም ነበር:: እግዚአብሔር ግን የዚህ ቅን ሰው በጐነቱ እንዲሁ እንዲቀር አልወደደምና አንድ ቀን በራዕይ ተገለጠለት::
+በራዕይም አንድ ምንነቱን ያልተረዳው ነገር "ቲቶ ሆይ! ስለ ነፍስህ ድኅነት ተጋደል:: ይህ ዓለም ኃላፊ ነው" ሲለው ሰማ:: ከእንቅልፉ ነቅቶ በእጅጉ ደነገጠ:: የሚያደርገውንም አጣ:: ያናገራቸው ሁሉ ምንም ሊገባቸው አልቻለም::
+ድንገት ግን በዚያ ሰሞን ከወደ ኢየሩሳሌም አዲስ ዜና ተሰማ:: "ክርስቶስ የሚሉት ኢየሱስ: እርሱም የባሕርይ አምላክ የሆነ ወደ ምድር ወርዶ: ስለ እግዚአብሔር መንግስትም እየሰበከ ነው" ሲሉ ለቲቶ ነገሩት::
+"ሌላስ ምን አያችሁ?" አላቸው:: "በእጆቹ ድውያን ይፈወሳሉ: ሙታን ይነሳሉ: እውራን ያያሉ: ለምጻሞች ይነጻሉ: ሌሎች ብዙ ተአምራትም እየተደረጉ ነው" አሉት:: የወቅቱ የሃገረ አክራጥስ መኮንን ፈላስፋ ነበርና ስለ ክርስቶስ ሲሰማ ሊመራመር ወደደ::
+"ብልህ ጥበበኛ ሰው ፈልጉልኝ" ብሎ ተከታዮችን ቢልካቸው ከቲቶ የተሻለ በአካባቢው አልነበረምና እርሱኑ አመጡት:: መኮንኑ ቲቶን "ነገሩ ትክክል ወይም ስሕተት መሆኑን በጥልቅ መርምረህ ምላሽ አምጣልኝ" ብሎ ላከው::
+ቅዱስ ቲቶም ፈጥኖ ተነስቶ ወደ ኢየሩሳሌም ገሰገሰ:: ወደ ከተማዋ እንደገባም ጌታችንን አፈላልጐ አገኘው::
1.ጌታችን ክርስቶስ በሥልጣነ ቃሉ ደዌያትን ሲያርቅ: አጋንንትን ሲያሳድዳቸው ተመልክቶ ይህ ሥራ የፍጡር እንዳልሆነ ተረዳ::
2.ጌታችን የሚያስተምረው ትምሕርት ከግሪክ ፍልሥፍና እጅግ ርቆና መጥቆ አገኘው:: ጌታ በጣዕመ ቃሉ የሚያስተምረው ሰማያዊ: በዚያ ላይ ዘለዓለማዊ የሆነ ትምሕርት ነው:: በራዕይ "ስለ ነፍስህ ተጋደል" ያለው ምሥጢር አሁን ተተረጐመለት::
+በዚህ ምክንያትም ጊዜ አላጠፋም:: ወዲያውኑ አምኖ ተከታዩ ሆነ:: ጌታም ከ72ቱ አርድእት ደመረው:: የአክራጥስ መኮንን "ምነው ዘገየህ?" ቢለው ያየውን ሁሉ ጽፎ: እንደማይመለስም አክሎ ደብዳቤ ላከለት::
+ከዚህ በሁዋላ ቅዱስ ቲቶ ከጌታችን እግር ለ3 ዓመታት ተምሮ: በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስን ተቀብሎ: በመላው እስያ ወንጌልን ሰብኩዋል:: ቅዱስ ዻውሎስ ባመነ ጊዜ ደግሞ የእርሱ ደቀ መዝሙር ሆኖ ለ25 ዓመታት አስተምሯል::
+ቅዱስ ዻውሎስ ሰማዕት ከሆነ በሁዋላ ደግሞ ወደ አክራጥስ ተመልሶ: ሕዝቡን አሳምኖና አጥምቆ: ቤተ ክርስቲያንን አንጿል:: ዕድሜው በደረሰ ጊዜም መምሕራንን: ካህናትን ሹሞላቸው: ባርኩዋቸውም ዐርፏል:: ዛሬ የቅዱሱ ሐዋርያ በዓለ ፍልሠቱ ነው::
+*" አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን "*+
=>ቅዱሱ በትውልዳቸው ግሪካዊ ቢሆኑም ሶርያ አካባቢ እንዳደጉ ይታመናል:: በቀደመ ስማቸው ፍሬምናጦስ የሚባሉት አቡነ ሰላማ ወደ ኢትዮዽያ የመጡት በአደጋ ምክንያት ቢመስልም ውስጡ ግን ፈቃደ እግዚአብሔር ነበረበት::
+በድንበር ጠባቂዎች ከባልንጀራቸው ኤዴስዮስ ጋር ተይዘው ወደ አክሱም የመጡት በንጉሥ ታዜር (አይዛና) እና በሚስቱ ሶፍያ (አሕየዋ) ዘመን ነው:: ጊዜው በውል ባይታወቅም በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ነው::
+ፍሬምናጦስ ምንም የመጡበት ዓላማ ስብከተ ወንጌል ባይሆንም በአክሱም ቤተ መንግስት አካባቢ ይሰብኩ ነበር:: ያን ጊዜ በጃንደረባው ቅዱስ ባኮስ የተቀጣጠለው የክርስትና ችቦ ውስጥ ውስጡን በሃገሪቱ ነበረና ፍሬምናጦስ አልተቸገሩም:: በተለይ ኢዛናና ሳይዛናን ከልጅነት ስላስተማሯቸው ነገሮች የተሳኩ ሆኑ::+ንጉሥ ታዜር እንደ ሞተ2ቱ ሕጻናት በመንበሩ ተቀመጡ:: ፍሬምናጦስንም ወደ ግብፅ ዻዻስና ጥምቀት ከመጻሕፍት ጋር እንዲያመጣላቸው ላኩ:: ሐዋርያዊ ቅዱስ አትናቴዎስም ፍሬምናጦስን "ሰላማ" ብሎ ሰይሞ: በዽዽስና: በንዋየ ቅድሳትና በመጻሕፍት ሸልሞ መለሳቸው::
+አቡነ ሰላማ ወደ ኢትዮዽያ እንደተመለሱ ከነገሥታቱ ጀምረው ለሕዝቡ ጥምቀትን አደሉ:: ኢዛናና ሳይዛናም አብርሃ እና አጽብሃ ተብለው ስማቸው ተደነገለ:: ከዚያ በሁዋላ ድንቅ በሚሆን አገልግሎት ነገሥታቱ: ዻዻሱ ሰላማና ሊቀ ካህናቱ እንበረም ለክርስትና መስፋፋት በጋራ ሠርተዋል::
=>የአቡነ ሰላማ ትሩፋቶች:-
1.ዽዽስናና ክህነትን ከእውነተኛ ምንጭ አምተዋል::
2.ክርስትናና ጥምቀትን በሃገራችን አስፋፍተዋል::
3.ቅዱሳት መጻሕፍትን ከውጭ ልሳኖች ተርጉመዋል::
4.ገዳማዊ ሕይወትን ጀምረዋል::
5.አብያተ ክርስቲያናትን አንጸዋል::
6.ግዕዝ ቁዋንቁዋን አሻሽለዋል::
ሀ.ከግራ ወደ ቀኝ እንዲፃፍ
ለ.እርባታ እንዲኖረው
ሐ.ከ"አበገደ" ወደ "ሀለሐመ" ቀይረዋል::
+ባላቸው ንጹሕ የቅድስና ሕይወት ለሕዝቡ ምሳሌ ሆነዋ:: "ወበእንተዝ ተሰይመ ከሳቴ ብርሃን" እንዲል በነዚህ ምክንያቶች "ከሣቴ ብርሃን" (ብርሃንን የገለጠ) ሲባሉ ይኖራሉ:: በመጨረሻም ከመልካሙ ገድል በሁዋላ በ352 ዓ/ም ዐርፈው ተቀብረዋል:: ቅዱሱ ለሃገራችን ዻዻስ ሆነው የተሾሙት በዚህች ዕለት ነው::
=>አምላከ አበው ቅዱሳን በመጽናታቸው ያጽናን:: ከበረከታቸውም ያድለንና።
=>ታሕሳስ 18 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ (ፍልሠቱ)
2.ቅዱስ ቲቶ ሐዋርያ (ፍልሠቱ)
3.አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን
4.ቅዱስ ፊልሞና ባሕታዊ
5.ቅዱስ ኢርቅላ
=>ወርሐዊ በዓላት
1.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ረባን
2.አቡነ አኖሬዎስ ዓቢይ
3.ማር ያዕቆብ ግብጻዊ
4.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ከ72ቱ)
5.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ (ከ12ቱ)
=>+"+ የእግዚአብሔር ባሪያና የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ዻውሎስ . . . መድኃኒታችን እግዚአብሔር እንዳዘዘ: ለእኔ አደራ በተሰጠኝ ስብከት ቃሉን ገለጠ: በሃይማኖት ኅብረት እውነተኛ ለሚሆን ልጄ ቲቶ::
ከእግዚአብሔርም አብ: ከመድኃኒታችንም ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ምሕረት: ሰላምም ይሁን:: +"+ (ቲቶ. 1:1)
✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞
✞ ወለወላዲቱ ድንግል ✞
✞ ወለመስቀሉ ክቡር አሜን ✞
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ::" /ማቴ ፫:፫/
ዝክረ ቅዱሳንን ተማሩ ብለን እንለምናችኋለን!!።
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together.https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━━━
Comments
Post a Comment