††† እንኩዋን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የመገለጥ በዓል (ደብረ ምጥማቅ) በሰላም አደረሳችሁ †††
††† ደብረ ምጥማቅ †††
=>የአርያም ንግሥት: የሰማይና የምድር እመቤት: የሰውነታችንም መመኪያ ቅድስት ድንግል ማርያም በዚሕች ዕለት በምድረ ግብፅ ለተከታታይ ቀናት ተገልጻለች::
+ጥንተ ነገሩስ እንደ ምን ነው ቢሉ:
+ለስም አጠራሩ ስግደት ይሁንና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድረ ግብፅና ኢትዮዽያ በተሰደደ ጊዜ ከድንግል እናቱ: ከዮሴፍና ሰሎሜ ጋር ዛሬ ደብረ ምጥማቅ በሚባለው ቦታ ላይ አርፎ ነበር:: ቦታውን ባርኮ ለዘለዓለም ያንቺ መገለጫ ይሁን ብሎም ቃል ኪዳን ገብቶላት ነበር::
+ጊዜው በደረሰ ሰዓት ደብረ ምጥማቅ ተገድሞ የበርካታ መነኮሳት ቤት ሆነ:: እመቤታችንም በልጇ ፈቃድ ግንቦት 21 ቀን አእላፍ መላእክትን: ጻድቃን ሰማዕታትን አስከትላት መጣች::
+በዚያ ሕዝበ ክርስቲያንም: አሕዛብም ተሰብስበው ለ5 ቀናት ከእመ ብርሃን ጋር ይሰነብታሉ:: እንግዲህ ልብ በሉት:-
እንኩዋን የአርያም ንግስት: የአምላክ እናቱ እመቤታችንን ይቅርና በዚሕ ዓለም ሰይጣን ቤቱ ያደረጋቸውን: የመዝናኛው ኢንዳስትሪ ዝነኛ ሰዎችን ለማየት የዘመናችን ሰው እንዴት እንደሚቸኩል::
+እመቤታችንን በአካል መመልከት አይደለም ስሟን መጥራት ነፍስን ከሥጋ መለየት የሚችል ጣዕምና ደስታ አለው:: ባይሆን ይሔ ለሚገባውና ላደለው ብቻ ነው::
+የደብረ ምጥማቅና የአካባቢዋ ሰዎች ከእመቤታችን ጋር የሚቆዩባቸው ቀናት የዘለዓለም የሕይወት ስንቅ የሚይዙባቸው ናቸው:: ፈልገው የሚያጡት: ጠይቀው የማይፈጸምላቸው ምንም ነገር አልነበረም:: ነቢያት: ሐዋርያት: ጻድቃን: ሰማዕታት: ደናግል: መነኮሳት: መላዕክትና ሊቃነ መላእክት ለድንግል ማርያም ሲሰግዱ ይታዩ ነበርና:: እመ ብርሃንም እየመላለሰች ትባርካቸው ነበር::
+እነዚያ እርሷን ያዩ ዐይኖች: በፊቷ የቆሙ እግሮች ክብር ይገባቸዋል:: 5ቱ ዕለታት ሲፈጸሙ ሕዝቡ እመቤታችንን በዕንባ ይሰናበቷታል:: እመ ብርሃንም በብርሃን መስቀል ባርካቸው ከቅዱሳኑ ጋር ታርጋለች::
††† አባ መርትያኖስ †††
=>አባ መርትያኖስ በበርሃ ከ68 ዓመታት በላይ በቅድስና የኖሩ አባት ናቸው:: ሰይጣን እርሳቸውን ፊት ለፊት ተዋግቶ መጣል ቢያቅተው በዝሙት በተለከፉ ሴቶች ያስቸግራቸው ነበር::
+አንድ ቀን አንዷ ሽቶ አርከፍክፋ በዝሙት ልትጥላቸው ብትል እግራቸውን እሳት ውስጥ ጨምረው እግራቸው እየተቃጠለ በሚወጣው ጠረን አጋንንትን አርቀዋል:: እሷንም በንስሃ መልሰው ለቅድስና አብቅተዋታል:: ጻድቁ ከፈተና ለመራቅ በ108 ሃገራት 108 በዓቶች የነበሯቸው ብቸኛ አባት ናቸው::
††† ለአባት እናቶቻችን የተገለጠች እመቤታችን ለእኛም በረድኤት ትገለጽልን:: ጣዕመ ስሟ በአንደበታችን: ጣዕመ ፍቅሯ በልባችን ይደርብን:: †††
=>ግንቦት 21 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅድስት ደብረ ምጥማቅ (የእመቤታችን መገለጥ)
2.አባ መርትያኖስ ጻድቅ (በዝሙት ላለመሰናከል እግራቸውን በእሳት ያቃጠሉ አባት)
3.ቅዱስ አሮን ሶርያዊ
4.ቅዱስ አሞጽ ነቢይ
=>ወርኀዊ በዓላት
1.አበው ጎርጎርዮሳት
2.አቡነ ምዕመነ ድንግል
3.አቡነ አምደ ሥላሴ
=>+"+ የምድር ባለጠጐች አሕዛብ በፊትሽ ይማለላሉ::
ለሐሴቦን ንጉሥ ልጅ ሁሉ ክብሯ ነው::
ልብሷ የወርቅ መጐናጸፊያ ነው::
በሁዋላዋ ደናግሉን ለንጉሥ ይወስዳሉ . . .
በአባቶችሽ ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ::
በምድርም ሁሉ ላይ ገዥዎች አድርገሽ ትሾሚያቸዋለሽ::
ለልጅ ልጅ ሁሉ ስምሽን ያሳስባሉ:: +"+ (መዝ. 44:12-17)
††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
✝ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together
https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━
Comments
Post a Comment