†✝† እንኩዋን ለጥንተ በዓለ ዸራቅሊጦስ (መንፈስ ቅዱስ) እና ለጻድቁ አባ ገዐርጊ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ †✝†
†✝† በዓለ ዸራቅሊጦስ †✝†
✝✞✝ ከዚሕ በፊት እንደተመለከትነው የጌታችን ዓበይት በዓላቱ 2 ጊዜ (ማለትም ጥንተ በዓልና የቀመር በዓል ተብለው) ይከበራሉ:: ዛሬም ከ1,978 ዓመታት
በፊት አምላካችን መንፈስ ቅዱስ በቅዱሳን ሐዋርያት ላይ መውረዱን እናስባለን::
††† ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
+ቸር አምላክ ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ሲል
*ከልዑል ማዕርጉ ወርዶ:
*በማሕጸነ ድንግል ተጸንሶ:
*በኅቱም ድንግልና ተወልዶ:
*ከኃጢአት በቀር በግዕዘ ሕጻናት አድጐ:
*በ30 ዘመኑ ተጠምቆ:
*ቅድስት ሕግ ወንጌልን አስተምሮ:
*በፈቃዱ ሙቶ:
*በባሕርይ ስልጣኑ ተነስቶ:
*በአርባኛው ቀን ያርጋል::
+ታዲያ ደቀ መዛሙርቱን የቅዱስ መንፈሱን ጸጋ ተስፋ እንዲያደርጉ ነግሯቸው
ነበርና በተነሳ በ50ኛው ቀን: በዐረገ በ10 ቀን ተስፋውን ፈጸመላቸው::
+እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ እንድትይዝ
በአንድ ላይ ሰብስባ ለክብረ መንፈስ ቅዱስ አብቅታቸዋለች:: 120ው ቤተሰብ
ከጌታችን እናት ጋር ሲጸልዩ መንፈስ ቅዱስ በአውሎ ንፋስ አርአያ ወርዶ
በአምሳለ እሳት አደረባቸው::
+ቅዱሳን ሐዋርያት ፈሪዎች የነበሩ ደፋሮች: አሮጌ ሕሊና የነበራቸው
ሐዲሶች ሆኑ:: በአዕምሮ ጐለመሱ: ቁዋንቁዋ ተናገሩ: ምሥጢርም
ተረጐሙ:: በቅጽበትም ብሉይ ከሐዲስ በልቡናቸው ውስጥ ተሞላ::
+ሐዋርያቱ ቅዱስ መንፈስን ተቀብለው ዓለምን በወንጌል ዕርፈ መስቀል
አርሰዋል:: አልጫውን ዓለም ጨው ሆነው አጣፍጠዋል:: ሳይሳሱም
አንገታቸውን ለሰይፍ ሰጥተዋል::
"ኪያሁ መንፈሰ ነሢኦሙ ለለአሐዱ:
ሐዋርያት ለሰቢክ አሕጉራተ ዓለም ዖዱ:
ሰማዕትኒ ለሕማም ነገዱ::" እንዳለ ደራሲ::
+በዚህ ቀን 2 ነገሮች በትኩረት ይነገራሉ:-
1."የመንፈስ ቅዱስ የባሕርይ አምላክነት:-"
*እርሱ ከአብ የሠረጸ: ቅድመ ዓለም የነበረ: በባሕርይ ስልጣኑ ከአብና
ከወልድ ጋር እኩል የሆነ: የራሱ ፍጹም አካል ያለው ፍጹም አምላካችን
ነውና::
2."ቅድስት ቤተ ክርስቲያን:-"
*አብ ያሰባት: ወልድ በደሙ የቀደሳት: መንፈስ ቅዱስ በጸጋው ያጸናት
የክርስቲያኖች አማናዊት አንድነት: አንድም ቤት ናትና:: ዛሬ በጉባዔ
ተመስርታለች::
††† አባ ገዐርጊ †††
=>በዚችም ዕለት የአባ አብርሃም ጓደኛ የከበረ አባ ገዐርጊ አረፈ።ይህም ቅዱስ የክርስቲያን ወገን ነው ወላጆቹ ደጎች ጻድቃን ናቸው።በአደገም ጊዜ የወላጆቹን ከብቶች የሚጠብቅ እረኛ ሆነ።ሁል ጊዜም የምንኵስና ልብስ ይለብስ ዘንድ በልቡ ይመኝ ነበር።
ዐሥራ አራት ዓመትም በሆነው ጊዜ የእግዚአብሔር ጸጋ አነሣሳችው በጎቹንም ትቶ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ።እየተጓዘም ሳለ ከሩቅ የብርሃን ምሰሶ አየ ወደ ወንዝ እስከ ደረሰ ድረስ ወደ ርሱ ሔደ ከዚህም በኃላ ያ የብርሃን ምሰሶ ከእርሱ ተሰወረ።
ያንንም ወንዝ በተሻገረ ጊዜ በሽማግሌ አምሳል ሰይጣን ተገለጠለትና ልጄ ሆይ ዕወቅ ስለ አንተ ልብሱን ቀዶ አባትህን አየሁት እርሱም ያዝናል ያለቅሳል ተመልሰህ የአባትህን ልብ ልትአጽናና ይገባሃል።የዱር አውሬ ነጥቆ የበላህ መስሎታልና አለው።
አባ ገዐርጊም ደንግጦ አንድ ሰዓት ያህል ቆመ ከዚህም በኃላ የከበረ ወንጌል ከእኔ ሊሆን አይገባውም ደቀ መዝሙሬም ሊሆን አይችልም ብሏል ብሎ አሰበ።ይህንንም በአለ ጊዜ ሰይጣን እንደ ጢስ ሆኖ ተበተነ።አባ ገዐርጊም ሰይጣን እንደ ሆነ አወቀ በዚያን ጊዜም ያ የብርሃን ምሰሶ ደግሞ ተገለጠለት የእግዚአብሔርም መልአክ በመነኵሴ አምሳል አብሮት ተጓዘ ቅዱሱም መልአኩን ተከተለው እርሱም ከአባ አርዮን ገዳም አደረሰው።አባ ገዐርጊም ከአንድ ጻድቅ ሰው መነኵሴ ጋራ በዚያ ዐሥራ አራት ዓመት ወጥሳይቀምስ ወይን ሳይጠጣ የአትክልት ፍሬም ቢሆን በዚህ በዐሥራ አራት ዓመት ያህል ከሚቀመጥ በቀር አልተኛም።
ተጋድሎውንም በጨመረ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለትና እንዲህ አለው ሥጋህ እንዳይደክም በመካከለኛ ገድል ተጋደል ብሎሃል ጌታ።ከዚህም በኃላ ሊሠራው የሚገባውን ሥርዓት ሠራለት ።ሁል ጊዜም እስከሚመሽ እንዲጾም ትንሽም እንጀራን እንዲበላ ከአራት ሰዓት እስከ መንፈቀ ሌሊት ስለ ሥጋው ዕረፍት እንዲተኛ በቀረው ሌሊት እስቲነጋ ተግቶ እንዲጸልይ።
በዚህም ተጋድሎ ብዙ ዘመናት እየተጋደለ በኖረ ጊዜ በበረሀ ውስጥ ብቻውን ሊኖር ወዶ በጫካ ውስጥ እየተመላለሰ ሁለት ዓመት ኖረ።ከዚህም በኃላ ጌታ ተገለጾለት ወደ ቦታው እንዲመለስ አዘዘው።ያን ጊዜም አምላካዊት ኃይል ከከበሩ መክሲሞስና ደማቴዎስ ገዳም አደረሰችው እርሷም ለደብሩ አቅራቢያ ናት።
ወደ ደብሩም በተመለሰ ጊዜ በዚያን ወቅት አብርሃም ከዓለም ወደዚያ ገዳም መጥቶ ሁለቱም ተገናኙና በአንድነት ተስማምተው የአስቄጥስ ገዳም አበ ምኔት ወደ ሆነ ወደ አባ ዮሐንስ ደረሱ።እርሱም ቦታ ሰጥቷቸው በውስጡ ኖሩ ያ ቦታም እስከ ዛሬ ታውቆ ይኖራል ።
ያቺም ዋሻ በግቢግ ትባላለች የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዐለት የሆነ ጣሪያዋን ሠንጥቆ ወደ እነርሱ የወረዳበት ናት ።እነርሱም ሰገዱለት ሰላምታም ሰጥቷቸው አጽናንቷቸው ከእርሳቸው ዘንድ ዐረገ።በዚያችም ጌታችን በወረደበት መስኮት ብርሃንን አዩ እስከ ዛሬም የተከፈተች ሁና ትኖራለች።
እሊህ ቅድሳንም ለመነኰሰኘሳት የሚሆን ብዙ ድርሳናትንና ብዙ ተግሣጻትን ደረሱ።ለአባቶቹ የሚታዘዘውንና የሚገዛውን አመሰገኑት።ከዚህም በኃላ አባ አብርሃም ጥር ሁለት ቀን አረፈ።ከእርሱ በኃላም የከበረ አባ ገዐርጊ በዚች በግንቦት ወር በዐሥራ ስምንት ቀን አረፈ።መላ ዕድሜውም ሰባ ሁለት ዓመት ሆነ።በዓለም ዐሥራ አራት ዓመት በምንኩስና ኃምሳ ስምንት ዓመት ነው።ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትሁን አሜን።
=>በዚችም ዕለት የሰማዕት ሲኖዳ መታሰቢያው ነው በረከቱ ከእኛ ጋራ ለዘላለም ትኑር አሜን።
=>አምላከ ገዐርጊ ከቅዱስ መንፈሱ ጸጋ ለኃጥአን ባሮቹ ያድለን::
=>ግንቦት 18 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱሳን ሐዋርያት ወአርድእት
2.አባ ገዐርጊ ገዳማዊ
3.ቅዱስ ሲኖዳ ሰማዕት
=>ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ
2.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ሰባኬ ሃይማኖት (ረባን)
3.አቡነ አኖሬዎስ ዘደብረ ጽጋጋ
4.ማር ያዕቆብ ግብፃዊ
=>+"+ በዓለ ሃምሳም የተባለው ቀን በደረሰ ጊዜ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው
አብረው ሳሉ ድንገት እንደሚነጥቅ አውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምጽ መጣ::
ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው:: እንደ እሳትም የተከፋፈሉ
ልሳኖች ታዩአቸው:: በእያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው:: በሁሉም
መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው:: መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደሰጣቸው በሌላ
ልሳኖች ይናገሩ ጀመር:: +"+ (ሐዋ. 2:1-4)
<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
✝ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together
https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━
Comments
Post a Comment