††† እንኳን ለታላቁ የቤተ ክርስቲያን ጠበቃ ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††
††† ቅዱስ ኤዺፋንዮስ †††
††† ሊቁ ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ጽድቅ ከቅድስና : ድርሰት ከጥብቅና የተሳካለት አባት ነው:: "ኤዺፋንያ" ማለት የመለኮት መገለጥ ሲሆን "ኤዺፋንዮስ" ማለት ደግሞ ምሥጢረ መለኮት የተገለጠለት ማለት ነው::
ቅዱስ ኤዺፋንዮስ የተወለደው ክርስቶስን ከሚጠሉ አይሁዳውያን ቤተሰቦች ቤተ ገብርኤል ውስጥ ነው:: ቤተሰቦቹ ከአንድ አህያ በቀር ምንም የሌላቸው ድሆች ነበሩ:: በዚያ ላይ በልጅነቱ አባቱ በመሞቱ ከእናቱና ከአንዲት እህቱ ጋር በረሃብ ሊያልቁ ሆነ:: ሕጻኑ ኤዺፋንዮስ በአህያው እንዳይሠራ አህያው ክፉ ነበርና ሊሸጠው ገበያ አወጣው::
ፊላታዎስ ከሚባል ክርስቲያን ጋር ለግዢ ሲደራደሩ አህያው የኤዺፋንዮስን ኩላሊቱን ረግጦት ለሞት አደረሰው:: በዚህ ጊዜ አብሮት ያለው ክርስቲያኑ በትእምርተ መስቀል አማትቦ አዳነው:: በፈንታው ግን አህያው ሞተ:: ሕጻኑ ኤዺፋንዮስ እያደነቀ ሔደ::
ከቆይታ በኋላ ሀብታም አጎቱ ገንዘቡን አውርሶት በመሞቱ ገና በ16 ዓመቱ ባለጠጋ ሆነ:: ያቺ ገበያ ላይ ያያት ተአምር ግን በልቡ ውስጥ ትመላለስ ነበር::
አንድ ቀን ደግሞ ሉክያኖስ ከሚባል ክርስቲያን ጋር ሲሔዱ ነዳይ አገኙ:: ባለጠጋው ኤዺፋንዮስ አለፈው:: ያ ድሃ ክርስቲያን ግን የለበሳትን አውልቆ መጸወተው:: በዚሕ ጊዜ መልዐኩ መጥቶ የብርሃን ልብስ ሲያለብሰው ኤዺፋንዮስ ተመለከተ::
ኤዺፋንዮስ ጊዜ አላጠፋም:: ከእህቱ ጋር በክርስቶስ አምኖ ተጠመቀ:: ሃብት ንበረቱን ግማሹን መጸወተ:: በተረፈው ደግሞ መጻሕፍትን ገዝቶ ወደ አባ ኢላርዮን ገዳም ገባ:: በዚያም መናንያኑ እስኪያደንቁት ድረስ በፍጹም ትጋትና ቅድስና ተጋደለ::
በጸሎቱ ዝናም አዘነመ : ድውያንን ፈወሰ : ብዙ ተአምራትንም አደረገ::
እግዚአብሔር ደግሞ ለሌላ አገልግሎት ሽቶታልና በቆዽሮስ ደሴት ላይ ዻዻስ ሆኖ ተሾመ:: ብሉይ ከሐዲስ የወሰነ ሊቅ ነውና ብዙ መጻሕፍትን ተረጎመ:: በሺሕ የሚቆጠሩ ድርሳናትን ደረሰ:: በአፍም በመጽሐፍም ብሎ መናፍቃንንና አይሁድን ምላሽ በማሳጣቱ ቤተ ክርስቲያን "ጠበቃየ" ትለዋለች::
ከደረሳቸው መጻሕፍት መካከል "ሃይማኖተ አበው ዘኤዺፋንዮስ : መጽሐፈ ቅዳሴውና አክሲማሮስ (ስነ ፍጥረት)" ዛሬም በቅርብ ይገኛሉ:: ሊቁ ቅዱስ ኤዺፋንዮስ በመልካም እረኝነትና በሚደነቅ ቅድስና ተመላልሶ በ406 ዓ/ም ዐርፏል:: እድሜውም 96 ዓመት ያህል ነበር::
††† አምላካችን ከቅዱሱ ሊቅ በረከት ያድለን::
††† ግንቦት 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ሊቅ (ዘደሴተ ቆዽሮስ)
2.ቅዱስ ኢላርዮን ገዳማዊ
3.አባ ሉክያኖስ ጻድቅ
4.ቅዱስ ፊላታዎስ ክርስቲያናዊ
††† ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት (ቀዳሜ ሰማዕት)
2.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ ዘብዴዎስ)
3.ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
4.አባ ገሪማ ዘመደራ
5.አባ ዸላሞን ፈላሢ
6.አባ ለትጹን የዋህ
††† "የሚታገልም ሁሉ በነገር ሁሉ ሰውነቱን ይገዛል:: እነዚያም የሚጠፋውን አክሊል ሊያገኙ ነው:: እኛ ግን የማይጠፋውን:: ስለዚህ እኔ ያለ አሳብ እንደሚሮጥ ሁሉ እንዲሁ አልሮጥም:: ነፋስን እንደሚጐስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም:: ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጐሰምሁ አስገዛዋለሁ::" †††
(1ቆሮ. 9:25)
††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
✝ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together
https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━
Comments
Post a Comment