=>+"+ እንኩዋን ለቅዱስ "እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት": ለቅዱስ "ፊልያስ" እና ለቅድስት "ሐና ነቢይት" ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ +"+
+*" ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት "*+
=>በሕገ ወንጌል (ክርስትና) የመጀመሪያው ሊቀ ዲያቆናትና ቀዳሚው ሰማዕት ይህ ቅዱስ ነው:: ቅዱሱ በመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን አስገራሚ ማንነት ከነበራቸው እሥራኤላውያን አንዱ ነበር:: ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-
+የቅዱስ እስጢፋኖስ ወላጆቹ ስምዖንና ማርያም ይባላሉ:: (ሌሎች ናቸው የሚሉም አሉ) ገና ከልጅነቱ ቁም ነገር ወዳድ የነበረው ቅዱስ በሥርዓተ ኦሪት አድጐ እድሜው ሲደርስ ወደ ት/ቤት ገባ:: የወቅቱ ታላቅ መምሕር ገማልያል ይባል ነበር:: ይህ ሰው በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 5:33 ላይ ተጠቅሷል::
+በትውፊት ትምሕርት ደግሞ ይህ ደግ (ትልቅ) ሰው በርካታ ቅዱሳንን (እስጢፋኖስን: ዻውሎስን: ናትናኤልን: ኒቆዲሞስን . . .) አስተምሯል:: በጌታችን መዋዕለ ስብከት ጊዜም ከፈጣሪያችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ እየቀረበ ይጨዋወት ነበር:: በፍጻሜውም አምኗል::
+ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና ቅዱስ እስጢፋኖስ ከዚህ ምሑር ዘንድ ተምሮ: ኦሪቱን ነቢያቱን ጠንቅቆ ወጣ:: ወቅቱ አስቸጋሪና ለኃጢአት ሕይወት የተመቸ ቢሆንም ቅዱሱ ግን የመሲህን መምጣት በጸሎትና በተስፋ ይጠባበቅ ነበር::
+በወቅቱ ደግሞ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ የንስሃ ጥምቀትን እየሰበከ መምጣቱን የተመለከተ ቅዱስ እስጢፋኖስ ነገሩን መረመረ:: ከእግዚአብሔር ሆኖ ቢያገኘው የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ሆነ:: ለ6 ወራትም በትጋት ቅዱስ ዮሐንስን አገለገለ::
+ለ6 ወራት ከቅዱስ ዮሐንስ ዘንድ ከተማረ በሁዋላ ለስም አጠራሩ ስግደት ይድረሰውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተጠመቀ::
በወቅቱ የተደረገውን ታላቅ ተአምር ልብ ያለው ቅዱስ እስጢፋኖስ መምሕሩን ቅዱስ ዮሐንስን እንዲያስረዳው ጠየቀው::
+"ከእኔ ይልቅ ከፈጣሪው አንደበት ይስማው" በሚል ላከው:: ቅዱሱም ከጌታ ዘንድ ሔዶ: እጅ ነስቶ ተማረ:: (ሉቃ. 7:18) በዚያውም የጌታ ደቀ መዝሙር ሆኖ ቀረ:: ጌታም ከ72ቱ አርድእት አንዱ አድርጐት ለአገልግሎት ላከው:: አጋንንትም ተገዙለት:: (ሉቃ. 10:17)
+ቅዱስ እስጢፋኖስ ጌታችን መድኃኔ ዓለም ከዋለበት እየዋለ: ካደረበት እያደረ ወንጌልን ተማረ:: ምሥጢር አስተረጐመ:: ጌታ በፈቃዱ ስለ እኛ ሙቶ ከተነሳ በሁዋላ ሲያርግ ደቀ መዛሙርቱን በአንብሮ እድ ባርኩዋል::
+በዚህ ጊዜም ቅዱሱ እንደ ወንድሞቹ ሐዋርያት ቅስናን (ዽዽስናን) ተሹሟል:: በበዓለ ሃምሳም መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ ከ72ቱ አርድእት የእርሱን ያህል ልሳን የበዛለት: ምሥጢርም የተገለጠለት የለም:: በፍጹም ድፍረትም ወንጌልን ይሰብክ ገባ::
+በመጀመሪያይቱ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ከማዕድ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ፈተና ሲመጣ በመንፈስ ቅዱስ ምርጫ 7 ዲያቆናት ሲመረጡ አንዱ እርሱ ነበር:: አልፎም የ6ቱ ዲያቆናት አለቃ እና የ8ሺው ማሕበር መሪ (አስተዳዳሪ) ሆኗል::
+8ሺ ሰውን ከአጋንንት ፈተና መጠበቅ ምን ያህል ከባድ እንደ ሆነ ለማወቅ አባቶቻችንን መጠየቅ ነው:: አንድን ሰው ተቆጣጥሮ ለድኅነት ማብቃት እንኩዋ እጅግ ፈተና ነው:: መጽሐፍ እንደሚል ግን "መንፈስ ቅዱስ የሞላበት: ማሕደረ እግዚአብሔር" ነውና ለእርሱ ተቻለው:: (ሐዋ. 6:5)
+አንዳንዶቻችን ቅዱስ እስጢፋኖስ "ሊቀ ዲያቆናት" ሲባል እንደ ዘመኑ ይመስለን ይሆናል:: እርሱ በመጀመሪያ ሐዋርያና ካህን ነው:: ዲቁናው ለእርሱ "በራት ላይ ዳረጐት" ነው እንጂ እንዲሁ ዲያቆን ብቻ አይደለም::
+ቅዱስ እስጢፋኖስ ከጌታ ዕርገት በሁዋላ ለ 1 ዓመት ያህል 8ሺውን ማሕበር እየመራ: ወንጌልን እየሰበከ ቢጋደል ኦሪት "እጠፋ እጠፋ": ወንጌል ደግሞ "እሰፋ እሰፋ" አለች:: በዚህ ጊዜ "ክርስትናን ለማጥፋት መፍትሔው ቅዱስ እስጢፋኖስን መግደል ነው" ብለው አይሁድ በማመናቸው ሊገልድሉት አስበውም አልቀሩ ገደሉት::
+እርሱ ግን ፊቱ እንደ እግዚአብሔር መልአክ እያበራ ፈጣሪውን በብዙ ነገር መሰለው:: በመጨረሻውም ስለ እነሱ ምሕረትን እየለመነ በድንጋይ ወገሩት:: ደቀ መዛሙርቱም ታላቅ ለቅሶን እያለቀሱ ቀበሩት::
+ይህች ዕለት ለቅዱስ እስጢፋኖስ በዓለ ሲመቱ ናት:: ቅዱሱ መጽሐፍ እንደሚል "ምሉዓ ጸጋ ወሞገስ-ሞገስና ጸጋ የሞላለት" (ሐዋ. 6:5, ቅዳሴ ማርያም) ነውና የ6ቱ ዲያቆናት አለቃና የ8ሺው ማሕበር መሪ ሆኖ ተመርጦ እንደሚገባ አገልግሏል:: በሰማይ ባለችው መቅደስም የሚያገለግለው በዚሁ ማዕረጉ ነው::
+"+ ቅዱስ ፊልያስ ሰማዕት +"+
=>ሰማዕቱ የነበረበት ዘመን 3ኛው መቶ ክ/ዘ (ዘመነ ሰማዕታት) ሲሆን ቀምስ ለምትባል የግብጽ አውራጃም ዻዻስ ነበር:: ቅዱሱ እጅግ ጻድቅ በዚያውም ላይ ክቡርና ተወዳጅ ሰው ነበር:: የመከራው ዘመን ሲመጣ በቃሉ ያስተማራቸውን እንደ በጐ እረኝነቱ በተግባር ይገልጠው ዘንድ ወደ መኮንኑ ሔደ::
+ሕዝቡ በአንድነት ተሰብስበው ሳለ መኮንኑ ቁልቁልያኖስ ቅዱስ ፊልያስን 4 ጥያቄዎችን ጠየቀው:: ምላሾቹ ለእኛ ሕይወትነት ያላቸው ናቸውና እንመልከታቸው::
1."የእናንተ እግዚአብሔር ምን ዓይነት መስዋዕትን ይሻል?" ቢለው "ልበ ትሑተ: ወመንፈሰ የዋሃ: ወነገረ ሕልወ: ወኩነኔ ጽድቅ: ዘከመዝ መስዋዕት ያሠምሮ ለእግዚአብሔር-እግዚአብሔርን ትሑት ልቦና: የዋህ ሰብእና: የቀና ፍርድና ቁም ነገር ደስ ያሰኘዋል" ሲል መለሰለት::
2."የምትወዳቸው ሚስትና ልጆች የሉህም?" ሲለው ደግሞ "እምኩሉ የአቢ ፍቅረ እግዚአብሔር - ከሁሉ የእግዚአብሔር ፍቅር ይበልጣል" አለው::
3."ለነፍስህ ትጋደላለህ ወይስ ለሥጋህ?" ቢለው "ለ2ቱም እጋደላለሁ:: አምላክ በአንድነት ፈጥሯቸዋልና:: በትንሳኤ ዘጉባኤም ይዋሐዳሉና" ብሎታል::
4."አምላካችሁ የሠራው ምን በጐ ነገር አለ?" ብሎትም ነበር:: ቅዱስ ፊልያስ መልሶ: "አስቀድሞ ፍጥረታትን በጥንተ ተፈጥሮ ፈጠረ:: በሁዋላም በሐዲስ ተፈጥሮ ያከብረን ዘንድ ወርዶ ሞተልን: ተነሣ: ዐረገ" ቢለው መኮንኑ "እንዴት አምላክ ሞተ ትላለህ!" ብሎ ተቆጣ:: ቅዱሱም "አዎ! በለበሰው ሥጋ ስለ እኛ ሙቷል" ብሎ እቅጩን ነገረው::
+ወዲያውም "እስከ አሁን የታገስኩህ በዘመድ የከበርክ ስለሆንክ ነው" ቢለው ቅዱሱ መልሶ "ክብሬ ክርስቶስ ነው:: መልካምን ካሰብክልኝ ቶሎ ግደለኝ" አለው:: በዚያን ጊዜ የሃገሩ ሰዎች "አትሙትብን! እባክህን ለመኮንኑ ታዘዘው?" ሲሉ ለመኑት::
+ቅዱስ ፊልያስ "እናንተ የነፍሴ ጠላቶች ዘወር በሉ ከፊቴ! እኔ ወደ ክርስቶስ ልሔድ እናፍቃለሁና" ብሎ ገሰጻቸው:: መኮንኑም ወስዶ ከብዙ ስቃይ ጋር ገድሎታል::
+"+ ቅድስት ሐና ነቢይት +"+
=>"ሐና" ማለት "የእግዚአብሔር ስጦታ" ማለት ነው:: እጅግ ከሚታወቁ ሴት ነቢያት አንዷ የሆነችው ቅድስት ሐና ከክርስቶስ ልደት 1,100 ዓመታት በፊት በዚህች ቀን እንደ ተወለደች ይታመናል:: ቅድስቲቱ ልጅ በማጣት ተቸግራ: ከጐረቤት እስከ ሊቀ ካህናቱ ኤሊ ድረስ ሽሙጥና ስድብን ታግሣ ታላቁን ነቢይ ቅዱስ ሳሙኤልን ወልዳለች::
+በሐረገ ትንቢቷም:-
"ኢይጻእ ዐቢይ ነገር እምአፉክሙ: እስመ እግዚአብሔር አምላክ ማዕምር ውዕቱ - እግዚአብሔር ሁሉን አዋቂ አምላክ ነውና ከአንደበታችሁ (ጽኑዕ) ነገርን አታውጡ" ስትል ተናግራለች:: (ሳሙ. 2:3)
=>አምላከ ቅዱሳን የእስጢፋኖስን ጸጋ: የፊልያስን ማስተዋልና የሐናን በጐነት ያሳድርብን:: ከበረከታቸውም ይክፈለን::
=>ጥቅምት 17 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ እስጢፋኖስ ሊቀ ዲያቆናት (ወቀዳሜ ሰማዕት)
2.ቅዱስ ፊልያስ ሰማዕት
3.ቅድስት ሐና ነቢይት
4.ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ጐርጐርዮስ ዘኑሲስ
5.የደብረ ሊባኖስ ሰማዕታት (ካቶሊካውያን የገደሏቸው)
6.ቅዱሳን ሔራን ሰማዕታት
7.አባ ዲዮስቆሮስ ካልዕ
=>ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ያዕቆብ ሐዋርያ (ወልደ ዘብዴዎስ)
2.ቅዱሳን አበው መክሲሞስና ዱማቴዎስ
3.አባ ገሪማ ዘመደራ
4.አባ ዸላሞን ፈላሢ
5.አባ ለትጹን የዋህ
6.ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ሊቅ (ዘደሴተ ቆዽሮስ)
=>+"+ እስጢፋኖስም ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር . . . አንዳንዶቹ ተነስተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር:: ይናገርበት የነበረውንም ጥበብና መንፈስ ይቃወሙ ዘንድ አልቻሉም:: በዚያን ጊዜ በሙሴ ላይ: በእግዚአብሔርም ላይ የስድብን ነገር ሲናገር ሰምተነዋል የሚሉ ሰዎችን አስነሱ . . . በሸንጐም የተቀመጡት ሁሉ ትኩር ብለው ሲመለከቱት እንደ መልአክ ፊት ሆኖ ፊቱን አዩት:: +"+ (ሐዋ. 6:8-15)
✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ::" /ማቴ ፫:፫/
ዝክረ ቅዱሳንን ተማሩ ብለን እንለምናችኋለን!!።
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
✝ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Togethellettps://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━━━
Comments
Post a Comment