አመ ፭ ለወርኃ ጥቅምት በዛቲ ዕለት ኮነ ተዝካረ በዓሉ ለኢያሱ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ
"ወዴት ሂዶ ኖሯል ሰሞነኛ ቄሱ፣
ታቦት ተሸከመ ዘውዱን ጥሎ ኢያሱ፣
የተሸሸገውን የአባቱን ቅስና፣
ገለጠው ኢያሱ ታቦት አነሳና፣
አየነው ኢያሱን ደብረ ብርሃን ቆሞ፣
ልክ እንደ ኪሩቤል ሦስቱን ተሸክሞ፣
ሰውነቱን ትቶ መልአክ ሆነ ደግሞ፣
ሥላሴን ቢሸከም ኢያሱ ገነነ፣
ለአራቱ ኪሩቤል አምስተኛ ሆነ።"
(1674 - 1698) ዓ.ም ኢትዮጵያን የመሩት ታላቁ ንጉሥ አፄ ኢያሱ ቀዳማዊ ( አድያም ሰገድ) ሥላሴን በእጅጉ ከመውደዳቸው የተነሣ የአድባራት ኹሉ ንግሥት ብለው የሠየሙትን የሥላሴን ቤተ ክርስቲያን ለየት ባለ መልኩ ማሳነጽ ጀመሩ።
✝️ እጅግ ድንቅ ሆኖ እንዲታነጽ ካላቸው ታላቅ ፍላጎት በመነሳት አዋቂዎች የኾኑ በጊዜው አሉ የተባሉ ታላላቅ ባለሙያዎችን መረጡ ፤ ለረዥም ዘመናት ሊቆዩ የሚችሉ እንጨቶችን ከያሉበት በማስመጣት እጅግ ድንቅ የኾኑ በድንቅ መልክ የተጠረቡ ደንጊያዎችን አስመጥተው በዘመናቸው በጎንደር ከሚከገኙ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ተወዳዳሪ የሌለው ኾኖ እንዲታነጽ አደረጉ።
✝️ ንጉሥ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤት ካለው ታላቅ ፍቅር በመነሣት ቤተ መቅደሱን በወርቅ እንዳሣነጸው ፤ ንጉሥ አፄ ኢያሱም ለቤተክርስትያኑ የወርቅ ጉልላት በላዩ ላይ አሠርተው ከወርቅ የተሠራ መስቀል በላዩ ላይ እንዲደረግ አደረጉ ፤ ከወርቁ ጽርየት የተነሣ በቀን እንደ ፀሐይ በሌሊት እንደ ጨረቃ ያንጸባርቅ ነበር ይላሉ ፤ከማይነቅዝ እንጨት አሠርተው በዝኖን ጥርስ አስጊጠው እንዲያምር ተደረገ።
በዕውቅ ሠዓሊ አማካኝነት እጅግ አስደናቂው ቅዱሳት ሥዕላት ተሣሉ ፤ ጣራው በመላዕክት ሥዕል ተመላ ፤ ቅጽረ ኢያሪኮ ሰፊ እንደነበረ የቤተክርስትያኗኑ ግቢው እንዲ ሰፋ ተደርጎ ዙሪያው ረዥምና ሰፊ ኾኖ ታጠረ ፤ በፊት ለፊትም መውጫውና መግቢያ እንዲሆኑ ሁለት በሮች አእንዲሠሩ አደረጉ ፤ በበሮቹም ላይ የርእሰ አንበሳ ቅርጽ ያለው ባለ ግርማ ግንብ ተሠርቶ በዙሪያው አሥራ ሁለት ግንቦች ታነጹ።
✝️ ለሥላሴ መቅደስ የሚኾኑ ግዙፋን የኾኑ ሁለት ታላላቅ ደወሎች በጠንካራ ገመድ ታስረው እንዲንጠለጠሉ ኾኑ ።ከጽርየቱ የተነሣ በጊዜው ከእነዚህ ደወሎች የሚወጣው ድምጽ ከጎንደር እልፍ ወደሚሉ ግዞቶች ጭምር ይሰማ ነበር ። ከዚያም ለቅዳሴ ቤቱ ከንጹህ ወርቅ የተሠሩ ንዋያተ ቅድሳት እንዲዘጋጁ ተደረገው ካህናቱ ዲያቆናቱ ልብሰ ተክህኖ ለብሰው ፤ ማዕጠንተ ወርቁን ይዘው ዐጤ ኢያሱም ከመሳፍንቱ ከመኳንንቱ ጋር በታላቅ ደስታ ከቤተ መንግስት ወደ ቤተመቅደስ ጉዞ ተደረገ ።
✝️ ታበተ ጽዮን በታላቅ ግርማ ትታጀብ እንደነበር ፤ በተመሳሳይ መልኩ የመሰንቆ ፣ የእንቢልታ ፣ የነጋሪት፣ የእንዚራ ድምፅ እየተሰማ ፤ ካህናት ፣ ዲያቆናት ፣መዘምራን ከፍተኛ የምስጋና ድምፅን እያሰሙ ፤ንጉሥ ዐጤ ኢያሱም በሰራዊታቸው ታጅበው "ጉቤን " በሚባለው ፈረሳቸው ተቀምጠው ፤ እጨጌ አባ ጸጋ ክርስቶስ ታበተ #ሥላሴን ተሸክመው ጎንደር ደብረ ብርሃን ሥላሴ በር ላይ ሲደርሱ ፤ ንጉሥ ኢያሱም #ለሥላሴ ካላቸው እጅግ ጥልቅ ፍቅር ተነሥተው ታቦቱ ገና አልተባረከም ነበርና ጳጳሱን አስፈቅደወሸ ታቦቱን ከእጨጌው ተቀብለው እስከ ቅድስቱ አደረሱ ፤ ካህኑም ከቅድስት ተቀብሎ ወደ መቅደስ ካስገባ በኋላ #የሥላሴ ታቦትን ግብጻዊው ጳጳስ አቡነ ማርቆስ በቅብዐ ሜሮን ባርከው ቅዳሴ ቤቱ ተቀደሰና የታቦቱ አገባብ በታላቅ በዓል ጥር 7 ታስቧል ።
✝️ እንደ አዛዥ ሐዋርያ ክርስቶስ ያሉ ሊቃውንት ዐጼ ኢያሱን በቅኔ ያወደሷቸው ሲኾን ፤ #ሥላሴ በተባለው የቅኔ ዐይነት :-
" አምላክ ዘኢፈቀድከ ደቂቀ ቆሬ ወዖዝያን ሶበ ማዕጠንተ ወርቅ ነሥኡ ከመ ይኩኑ ካህናተ
ነሥኡ ተቀሥፎ ወለብሱ እሳተ
እለ ይፈርሁከ ሰብአ ባሕቱ እምኀበ ረከብከ አንተ
በዘወሀብኮሙ ትእምርተ
አመ ርኅበ በልዐ ዳዊት መሥዋዕተ
ወኢያሱ አንሥአ ጽላተ "
(የዖዝያንና የቆሬ ልጆች ካህናት ለመኾን አስበው አምላክ ያልፈቀድከውን የወርቅ ማዕጠንት በወሰዱ ጊዜ ተቀሥፈው እሳት በላቸው ፤ አንተን የማፈሩኽ ሰዎች ግን በሰጠኻቸው ምልክት ተመርተው ፤ ዳዊት ቢራብ መሥዋዕትን በላ ፤ ኢያሱሜ ጽላትን አነሣ) እያሉ ተቀኙላቸው ።
✝️ የአማርኛ ገጣሚውም በጊዜያቸው በአንክሮ ኾኖ :-
"ወዴት ሂዶ ኖሯል ሰሞነኛ ቄሱ፣
ታቦት ተሸከመ ዘውዱን ጥሎ ኢያሱ፣
የተሸሸገውን የአባቱን ቅስና፣
ገለጠው ኢያሱ ታቦት አነሳና፣
አየነው ኢያሱን ደብረ ብርሃን ቆሞ፣
ልክ እንደ ኪሩቤል ሦስቱን ተሸክሞ፣
ሰውነቱን ትቶ መልአክ ሆነ ደግሞ፣
ሥላሴን ቢሸከም ኢያሱ ገነነ፣
ለአራቱ ኪሩቤል አምስተኛ ሆነ።" በማለት ገጠሙላቸው ።
✝️ካህናቱም ሕዝቡም :- የልዑል እግዚአብሔር ወዳጆች ደጋግ ነገሥታት የነበሩ የእነ ቆስጠንጢኖስን ፣ የእነ አኖሬዎስን ፣ የእነ አርቃዴዎስን ....የክቡራን ነገሥታት ኹሉ በረከት ያሳድርብዎ " እያሉ ንጉሡ ዐጼ ኢያሱን አመሰገኗቸው ።
✝️ቅዳሱ ቤቱ ጥር 7 ተደርጎ ከዚያም ዐጤ ኢያሱ ለሦስት ቀናት በቤተመንግሥታቸው እጅግ ታላቅ ግብዣ አደረጉ ፤ የጥር ወር በገባ በ ሰባተኛው ቀን ሁሌም በዓሉ እኝዲከበር አዘዙ ፤ #ለሥላሴ መቅደስም 170 ካህናት እንዲያገለግሉ አድርገው እጅግ ብዙ ርስት ሰጥተዋልና የመልከዐ ሥላሴ ደራሲ አባ ስብሐት ለአብም ይኽንን የዐጤ ኢያሱ አድያም ሰገድን ውለታ ባለመዘንጋት በመልከዐ ሥላሴ መጽሐፉ ላይ ይኸንን ታሪክ እንደ ወርቅ አንከብልሎ እንደ ሸማ ጠቅልሎ ታሩኩን :-
"ሰላም ለርእስክሙ ዘአስተዋደደ ርእስ
አጋዕዝተ ሥጋ ሥላሴ እንዘ ኢትሌልዩ ነፍሰ
በርእሰ ኢያሱ አንብሩ አክሊለክሙ ሞገሰ
በስምክሙ አሐዱ እስመ ያመልክ ሥሉስ
ወበስምክሙ ሐነጸ መቅደሰ "
( #አብ_ወልድ_መንፈስ_ቅዱስ_ሆይ የነፍስና የሥጋ ገዥ እንደ መሆናችሁ አመቻችቶና አቀናብሮ አስተናብሮ ርእሰ ፍጡራንን ለፈጠረ መለኮተታዊ ርእሳችሁ ሰላምታ ይገባል #ሥሉስ_ቅዱስ_ሆይ የባለሟልነታችሁ ዘውድ በእያሱ ራስ ላይ አቀዳጁ ። በስም ሦስት በባሕርይ አንድ #አምላክ ብሎ በማመን በስማችሁ ቤተ መቅደስን አሳንጿልና ።) በማለት ይገልጣል ።
የፃድቁ ንጉሥ ኢያሱ በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን።
፨ ከመጋቢ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰ
ወስብሀት ለእግዚያብሔር
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ::" /ማቴ ፫:፫/
ዝክረ ቅዱሳንን ተማሩ ብለን እንለምናችኋለን!!።
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
✝ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Togethellettps://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━━━
Comments
Post a Comment