Comments

3-comments

FOLLOW ME

LATEST

3-latest-65px

About

This just a demo text widget, you can use it to create an about text, for example.

Testimonials

3-tag:Testimonials-250px-testimonial

Popular Posts

Sections-BTLabels

Ads block

Banner 728x90px

About me

About Me


Aenean sollicitudin, lorem quis bibendum auctor, nisi elit consequat ipsum, nec sagittis sem nibh id elit. Duis sed odio sit amet nibh vulputate.

Section Background

Section Background

Follow Us Telegram & Facebook gage

Contact us-desc:Feel free to contact us at anytime about our service.

Name

Email *

Message *

SEARCH

በእንተ ስማ ለማርያም
Powered by Blogger.

Advertisement

3/recentposts

Comments

Ad Code

Responsive Advertisement

Facebook

Advertisement

Report Abuse

Featured Post

ሐምሌ ፳፯

††† ✝✝እንኳን ለአበው ቅዱሳን ሴት : ሕዝቅኤል ነቢይ እና ዮሐንስ ወንጌላዊ ዓመታዊ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፣ አደረሰን። †††✝✝ ††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††...

Post Top Ad

Archive

Sections

ዝክረ ቅዱሳን መዝሙር ስነ–ፅሁፍ

Blog Archive

SEARCH

Search This Blog

Recent in Sports

በእንተ ስማ ለማርያም

4-tag:Campus-500px-mosaic

Header Ads

Subscribe Us

Random Posts

Recent Posts

Header Ads

Header Background

Header Background
Header Background Image. Ideal width 1600px with.

Section Background

Section Background
Background image. Ideal width 1600px with.

Section Background

Section Background
Background image. Ideal width 1600px with.

Search This Blog

Categories

A Team Of Awesome People

We are a creative web design agency who makes beautiful websites for thousands of peoples.

Labels

Labels

Follow Us

Sponsor

Ads

Popular Posts

Pages

Blogger templates

3/recentposts

Blogroll

3-comments

Pages - Menu

Pages - Menu

About

Blogger templates

About

Popular Posts

LATEST POSTS

SEARCH

Skip to main content

የሐሙስ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ


የሐሙስ ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ
ይህ ዕለት ለምስጋና አራተኛ ለፍጥረት አምስተኛ ቀን ነው፡፡ በዚህም ቀን እመቤታችን ትመጣለች፤ የብርሃን ድባብ ይዘረጋል፤ የብርሃን ዙፋን ይነጸፋል፡፡ ከዚያ ላይ ኹናም ሊቁን ባርካው ምስጋናዉን ጀምሯል፡፡ ከወትሮ ይልቅም ነቢያትንና ሐዋርያትን አስከትላ መጥታለች፡፡

፩. ነደ እሳት ሰፍሮባት፣ በነደ እሳት ተከባ፣ ጫፎቿ ሳይቃጠሉ ሙሴ በደብረሲና ያያት ዕፅ ድንግል ማርያምን ትመስላለች /ዘጸ.፫፡፩-፫/፡፡ አካላዊ ቃል ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ሰው ኹኗልና፤ ባሕርየ (እሳተ) መለኮቱም አልለወጣትምና (አላቃጠላትምና) ሐመልማላዊቱ ዕፅ እመቤታችንን ትመስላለች፡፡ዳግመኛም እርሱን ከወለደችው በኋላ ማኀተመ ድንግልናዋ አልተለወጠምና ሐመልማላዊቱ ዕፅ እመቤታችንን ትመስላለች፡፡ እርሱም ምንም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷም ነፍስ ነስቶ ፍጹም ሰው ቢኾንም ባሕርየ መለኮቱ አልተለወጠምና እሳቱን ይመስላል፡፡ ሰውም ቢኾን ባሕርየ መለኮቱ አልተለወጠምና ሰው ኾኖ ያዳነን የባሕርይ አምላክ ነው፡፡ ሰው ኾኖ ካዳነን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋዉን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፪. ይቅርታሽ (ምልጃሽ) ለኹላችን ይኾን ዘንድ አምላክን የወለድሽ እመቤታችንሆይ! ኹላችን እናከብርሻለን፤ እናገንሻለን፡፡ ሔዋን ባደረገችው ዐመፅ በባሕርያችን ጸንቶ የነበረ መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ በእርሷ ምክንያት የጠፋልን አምላክን የወለደች ድንግል ማርያም የኹላችን መመኪያ ናት፡፡ “ሔዋን ምን አደረገች?” ትለኝ እንደኾነም ዕፀ በለስን በልታለች እልሃለሁ፡፡ “ወአዘዞሙ ለኪሩቤልወሱራፌል ዘውስተ እደዊሆሙ ሰይፈ እሳት እንተ ትትመያየጥ ከመ ይዕቀቡ ፍኖተ ዕፀ ሕይወት - ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውንም መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና የምትገለባበጥ የነበልባል ሰይፍን በዔድን ገነት ምሥራቅ አስቀመጠ”እንዲል /ዘፍ.፫፡፳፬/ በሔዋን ምክንያት የገነት ደጅ ተዘጋ፡፡ “ወአግኃሦ ለሱራፊዘየዐቅብ ፍና ዕፀ ሕይወት፤ ወአእተተ እምእዴሁ ኵናተ እሳት - ” እንዲልም በድንግል ማርያም ምክንያት ዳግመኛ ተከፈተልን፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ ዘስሩግም፡- “አዳምን እንዲሞት ያደረገች ያቺ ቀን ተለወጠች፡፡ እርሱም ከሞት የሚድንባት ሌላ ቀን መጣች፡፡ እባቧ ሳትኾን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ይናገር ዘንድ ተነሣ፡፡ ሔዋን ሳትኾን ድንግል ማርያምም ቃሉን ትቀበል ዘንድ ተዘጋጀች፡፡ በተንኰል የሚያስተው ሳይኾን ሕይወትን የሚያውጀው ቃል ወጣ፡፡ በሞት ዛፍ መካከል የሞት ዕዳዋን በጻፈችው ሔዋን ፈንታ ልጇ (ማርያም) የአባቷን ዕዳ ኹሉ ከፈለች፡፡ ሔዋንና እባቡ በቅድስት ድንግል ማርያምና በቅዱስ ገብርኤል ተተኩ፡፡ ያ ከመጀመርያው የተበላሸው ነገር አሁን ተስተካከለ፡፡ የሔዋን ጀሮና ቀልብ አታላዩ በሚናገርበት ጊዜ እንደምን እንዳዘነበለ አስተውሉ፤ ያ በገነት ሲመለከታቸው የነበረው መልአክ አሁን በድንግል ማርያም ጀሮ የድኅነትን ተስፋ ሲያሰርጽና የእባቡን ከፉና መርዛማ ቃል ሲያጠፋ ደግሞ አስተውሉ፡፡ ሔዋን ያፈረሰችው ሕንፃ ገብርኤል ገነባው፡፡ በዔደን ገነት ውስጥ ኹና ሔዋን ያፈረሰችውን መሠረት ዳግሚት ሔዋን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ምድር ኹና ገነባችው፡፡ ከኹለት መልእክተኞች መልእክት የተቀበሉ ኹለት ደናግላን ኹለት ትውልድን ቀጠሉ፡፡ አንዱም የአንዱ ተቃራኒ ኾነ፡፡ በእባብ ምክንያት ሰይጣን ምሥጢርን ለሔዋን ላከ፡፡ በሌላ ቅዱስ መልአክ አማካኝነት ደግሞ ጌታ የምሥራቹን ወደ ቅድስት ድንግል ማርያም ላከ፡፡ እባብ ለሔዋን የሐሰትን ቃል ለሔዋን ስትናገር ቅዱስ ገብርኤል ግን የእውነትን ቃል ለቅድስት ድንግል ማርያም ተናገረ፡፡ እውነትን በሚናገር አንደበቱ የቀደመውን የእባብ ቃል አደሰው፡፡ እውነትን ተናገረና ሐሰቱን አስወገደው፡፡ አስቀድሞ ሐሰትን ከራሱ አንቅቶ ሰይጣን ሔዋንን በዔደን ገነት አታለላት፡፡ ይህንንም ታላቅ ስሕተት በጀሮዋ አልፎ እንዲሰማት ፈቀደች፡፡ አሁን ግን በመጀመርያዋ ድንግል ፈንታ ሌላ ድንግል ተመረጠች፡፡ በዚህች ድንግል ጀሮም ከአርያም የተላከ የእውነት ቃል ገባ፡፡ ሞት በገባበት በዚያ በር (ጀሮ) ሕይወት ገባ፡፡ ክፉው (ዲያብሎስ) ያጠበቀው ጽኑ የሞት ማሰርያም ተፈታ፡፡ ኀጢአትና ሞት ሠልጥነውበት በነበረ ቦታ ጸጋ ከመጠን ይልቅ በዝቶ ታየ፡፡ … እባብ የስሕተትን ዜማ ለሔዋን ዘመረላት፤ ሐሰትንም ረጨባት፡፡ በተፈጥሮዋ ገና ድንግል በምትኾን በሔዋን ላይ ክፉ ምክርና ስሕተት አፈሰሰባት፡፡ በመርዝ የተለወሰና ደምን የተጠማ ክፉ ምክር በአዳም ቤት ውስጥ አስገባ፡፡ ኃይለ ልዑል የላከው መልአክ ግን እነዚህን የክፋት ሰይፎች ለመቆራረጥ ክንፉን እያማታ እየበረረ መጣ፡፡ ለሰው ኹሉ የሚኾን የድኅነት ሰነድ ይዞ መጥቶም ለድንግሊቱ (ለማርያም) አበሠራት፡፡ ሰገደላት፡፡ ሕይወትን በውስጧ አሰረጸ፡፡ ሰላም ዐወጀ፡፡ በፍቅር ቀረባት፡፡ የቀድሞውን የሞት ዳባ በጣጠሰው፡፡ እባብ የገነባውን የማታለል ግንብ ዳግም ላይገነባ በወልደ እግዚአብሔር እንደሚናድ ነገራት፡፡ በእባብ የታጠረው የሞት ቅጽር በወልድ መውረድ እንደሚሰባበር ቀጠሮው እንደደረሰ ነግሮ የምሥራች አላት” በማለት ከማር የጣፈጠ ትምህርቱን እያነጻጸረ አስተምሯል፡፡
ከዕፀ ሕይወትም እንበላ ዘንድ አደለን፡፡ ይኸውም እኛን ስለ መውደድ ሰውኾኖ ያዳነን የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ነው፡፡
ወዮ! ሰውን የሚወድ ሰውም የሚወደው እግዚአብሔር፣ ማኅደርም ኀዳሪምያይደለ አካላዊ ቃል፣ ሳይለወጥ ቅድመ ዓለም የነበረ እግዚአብሔር ወልድ፣ ከአብ አንድነት ሳይለይ መጥቶ ንዕድ ክብርት ከምትኾን ከእመቤታችን ሰው ኾኗልና፤ እርሱንም ከወለደችው በኋላ እንደ ቀድሞ ማኅተመ ድንግልናዋ ሳይለወጥ ኑራለችና፤ ስለዚህም ነገር አምላክን የወለደች እንደኾነች በጎላ በተረዳ ነገር ታውቃለችና ለርሷ ድንቅ ኾኖ የሚነገረውን ነገር መናገር የሚቻለው ምን አንደበት ነው? መስማትስ የሚቻለው ምን ጆሮ ነው? ማወቅስ የሚቻለው ምን አእምሮ ነው? የእግዚአብሔር የጥበቡ ምላት ስፋትስ ምን ይረቅ? ምን ይጠልቅ? አንድም ለእግዚአብሔር ለጥበቡ ምላት ስፋት አንክሮ ይገባል፡፡ “በፀነስሽጊዜ ጭንቅሽን እጅግ አበዛለሁ፤ በጭንቅ ትወልጃለሽ፤ ፈቃድሽም ወደ ባልሽይሆናል፥ እርሱም ገዥሽ ይሆናል” /ዘፍ.፫፡፲፮/ ብሎ የፈረደባት ማኀፀን የሕይወት፣ የድኅነት መገኛ ኾነች፡፡ ዕንቆ ጳዝዮን የተባለ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም፡- “እስመ ቀዳሚኒ ሔዋን ኮነት ድንግል ወአስሐታ ዲያብሎስ ለማርያምሂ ድንግል አብሠራ ገብርኤል ወባሕቱ ለሔዋንሰ አስሐታ ዲያብሎስ ወወለደት ቃየልሀ ዘውእቱ ምክንያተ ሞት ወማርያምሰ ሶበ አብሠራ መልአክ ወለደት ቃለ በሥጋ ዘውእቱ መራሔ ኵሉ ኀበ ሕይወት ዘለዓለም - ቀድሞም ሔዋን ድንግል ነበረችና ዲያብሎስ አሳታት እንጂ፤ ድንግል ማርያም ግን ገብርኤል አበሠራት፡፡ ነገር ግን ሔዋንን አሳታት፤ የሞት ምክንያት የሚኾን ቃየልን ወለደች፤ ማርያም ግን መልአክ ባበሠራት ጊዜ ኹሉን ወደ ዘለዓለም ሕይወት የሚመራ አካላዊ ቃልን በሥጋ ወለደች፡፡ የሔዋንን ልብላ ልብላ ማለቷ ዕፀ በለስ የሞት ምክንያት እንደኾነ አስረዳ፡፡ በዚያም አዳም ተድላ ደስታ ካለበት ከገነት ወጣ፡፡ ከድንግል የተወለደ አካላዊ ቃል ግን ዕፀ መስቀል የድኅነት ምክንያት እንደኾነ ገለጠ፡፡ በዚያም መስቀል ቀማኛ ወንበዴ የነበረው ሰው ከአባቱ ከአዳምና ከቀደሙ አባቶች ኹሉ ጋር ተድላ ደስታ ወዳለበት ገነት ገባ” ብሏል /ሃይ.አበ.፷፯፡፫-፭/፡፡
ከባሕርያችን መርገመ ሥጋን መርገመ ነፍስን የሚያጠፋልንን ጌታን ዘር ምክንያት ሳይኾናት ወለደችው፡፡ ስለዚህ ነገር “ሰውን የምትወድ ሰው የሚወድህ አቤቱ ክብር ላንተ ይገባል” እያልን እናመስግነው፡፡ “ኄር ዘበህላዌሁ ዘልማዱ ኂሩት - በባሕርይው ቸር የኾነ፤ ቸርነትን ማድረግም ልማዱ የኾነ” እያልን እናመስግነው፡፡ ኄር ዘበህላዌሁ ዘልማዱ ኂሩት ከሚባል ልጅሽ ጸንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፫. ዘር ምክንያት ሳይኾናት አምላክን የወለደች ድንግል፣ የማኅፀንዋ ሥራ ምንይረቅ? ምን ይጠልቅ? አንድም ለድንግል ለማኅፀኗ ሥራ አንክሮ ይገባል፡፡ ለዮሴፍ የነገረው መልአክ ሳይለወጥ ሰው የኾነ አካላዊ ቃል ከርሷ የሚወለድ በግብረ መንፈስ ቅደስ እንደኾነ መስክሯልና /ማቴ.፩፡፳/፡፡ ማርያም የዚህ ደስታ ዕፅፍ ድርብ የሚኾን ጌታን ወለደችው፡፡ ሴቶች ልጅ ትወልዳላችሁ ሲባሉ ደስ ይላቸዋል፤ ይልቁንም ወንድ ትወልዳላችሁ ሲሏቸው ደስ ይላቸዋል፡፡ እመቤታችን ግን ከዚሁ ኹሉ ያለፈ አምላክን ወልዷለችና ደስታዋ ዕፅፍ ድርብ ኾነላት፡፡ መልአኩ፡- “ልጅ ትወልጃለሽ፤ ስሙም አማኑኤል ይባላል” አላት፡፡ አማኑኤልም ማለት እግዚአብሔር ከሥጋችን ሥጋ ከነፍሳችን ነፍስ ነሥቶ ከኛ ጋራ አንድ ባሕርይ ኾነ ማለት ነው፡፡ ዳግመኛም ወገኖቹን ከኃጢአታቸው ፍዳ የሚያድናቸው መድኃኒት ይባላል አላት /ማቴ.፩፡፳፩/፡፡ በመኾኑም በክሂሎቱ (በከሃሊነቱ) ያድነን ዘንድ፣ ኃጢአታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ (እስከ ዕለተ ምፅአትድረስ ክብር ይግባውና) ሰው የኾነ እርሱ አምላክ እንደኾነ በተረዳ ነገር አወቅነው፡፡ አምላክ ብቻ ቢኾን ባልታመመ ነበርና፤ ሰውም ብቻ ቢኾን ባላደነን ነበርና፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም ከዚህ ጋር አያይዞ ፡- “ፍቁራን ሆይ! ምንም እንኳን ለዚህ ክብር የተገባን ኾነን ባንገኝም አባታችን በከኀሊነቱ እንዲሁ ከኀጢአታችን አድኖናልና ይህን ክብር፣ ይህን ጸጋ በፍጹም ልናክፋፋው (ልናቆሽሸው) አይገባንም፡፡ ልጅነት እንዲሁ ሳይሰጠን ለምረረ ገሃነም የተገባን የቁጣ ልጆች ከነበርን፤ ይህ ከኅሊናት በላይ የኾነ ጸጋ ከተቀበልን በኋላማ ፍዳችን እንደምን የበዛ አይኾን? ልጆቼ! ይህን የምለው እንዲሁ ለመናገር ያህል አይደለም፡፡ ዳግም ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ከተወለዱ በኋላ ብዙ ክርስቲያኖች በኀጢአት፣ በስንፍና፣ ለምግባርና ለትሩፋት ሳይሽቀዳደሙ ታክተው ስለምመለከት ነው እንጂ” ሲል ይመክረናል ፡፡

ወዮ! ንዕድ ክብርት ከምትኾን ከእመቤታችን ይህ የአምላክ መወለድ ምን ይረቅ? ምን ይጠልቅ? ቃልን ወሰነችው፡፡ ለልደቱም ዘርዕ ምክንያት አልኾነውም፡፡ በመወለዱም ማኅተመ ድንግልናዋን አልለወጠውም፡፡ ከአብ አካል ዘእምአካል ባሕርይ ዘእም ባሕርይ ድካም ሳይሰማው የተወለደ እርሱ ፭ ሺሕ ከአምስት መቶ ዘመን ሲፈጸምም ከድንግል ሕማም ሴቶች የሚሰማቸውን ሕማም ሳይሰማት እርሱን ሕፃናትን የሚሰማቸው ሕማም ሳይሰማው ተወለደ እንጂ፡፡
ሰብአ ሰገል ሰገዱለት፡፡
አምላክ ነውና አምላክ እንደኾነ ለማጠየቅ ዕጣን አመጡለት፡፡ ንጉሥ ነውና ንጉሥ እንደ ኾነ ለማጠየቅ ወርቅ አመጡለት፡፡ ማኀየዊ የሚኾን የሞቱ ምሳሌ ከርቤንም አመጡለት፡፡
አንድም “ይኸን ወርቅ እንገብርላቸው የነበሩ ነገሥታት ቀድሞም ፍጡራን ኋላምኀላፍያን ናቸው፤ አንተ ግን ቀድሞም ያልተፈጠርህ ኋላም የማታልፍ ነህ” ሲሉወርቅ አመጡለት፡፡ “ይኽን ዕጣን እናጥናቸው የነበሩ ጣዖታት ቀድሞም ፍጡራን ኋላም ኃላፊያን ናቸው፤ አንተ ግን ቀድሞም ያልተፈጠርህ ኋላም የማታልፍ ነህ” ሲሉ ዕጣን አመጡለት፡፡ “ምንም ቀድሞ ያልተፈጠርህ ኋላም የማታልፍ ብትኾን በሰውነትህ መራራ ሞትን ትቀምሳለህ” ሲሉ ከርቤ አመጡለት፡፡
አንድም ወርቅ ጽሩይ ነውና “ጽሩየ ባሕርይ ነህ” ሲሉ ወርቅ አመጡለት፡፡ ዕጣን ምዑዝ ነውና “አንተም ምዑዘ ባሕርይ ነህ” ሲሉ ዕጣን አመጡለት፡፡ ዳግመኛም “ከርቤ የተሰበረውን ይጠግናል፤ የተለያየውን አንድ ደርጋል፡፡ አንተም ከማኀበረ መላእክት የተለየ አዳምን አንድ ታደርገዋለህ፤ ጽንዓ ነፍስ ሰጥተህ ታጸናዋለህ” ሲሉ ከርቤ አመጡለት፡፡
አንድም ወርቅ ጽሩይ ነውና “ባንተ ያመኑ ምዕመናን ጽሩያነ ምግባር ወሃይማኖት ናቸው” ሲሉ ወርቅ አመጡለት፡፡ ዕጣን ምዑዝ ነውና “ባንተ ያመኑ ምእመናንም ምዑዛነ ምግባር ወሃይማኖት ናቸው” ሲሉ ዕጣን አመጡለት፡፡ ዳግመኛም በዕለተ ሞቱ ያቀምሱታልና ከርቤ አመጡለት፡፡ ቸርና ሰው ወዳጅ የኾነ አንድ እርሱ ብቻ ነው፡፡ ቸርና ሰው ወዳጅ ከኾነ ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፬. ከአዳም ጎን አንድ ዐፅም መንሣቱ ምን ይረቅ? ምን ይጠልቅ? “በእምነት ዓይን ከማየት በቀር ይህ ከኅሊናት በላይ የኾነውን ድንቅ ነገር በቋንቋ መናገር አይቻለንም” /St. John Chrysostom, Homily 15 on Genesis/፡፡ ከእርሱ (ከአዳም) ሔዋንን ፈጠረ፡፡ ፍጥረትንም ኹሉ ከአዳምና ከሔዋን ፈጠረ፡፡ እንዲህምአድርጎ የአብ አካላዊ ቃል ለኵነተ ሥጋ (ለሕማም ለሞት) ተሰጠ፡፡ ከልዩ ድንግልም ሰው ኾነና አማኑኤልም ተባለ፡፡ “ኦ ለዝንቱ መንክር ልዑል ላዕለ ኵሉ ሕሊናት ብእሲት ምድራዊት ወለደቶ ለእግዚአብሔር ቃል ዘኮነ ሰብአ… - ከኅሊናት ኹሉ ለራቀ ለዚህ ድንቅ ምሥጢር አንክሮ ይገባል፤ ምድራዊት ሴት ሰው የኾነ እግዚአብሔር ቃልን ወለደችው፡፡ ድንግል ፈጣሪዋን ወለደችው፤ እርሱም እናቱን ፈጠረ፡፡ ከእርሷም እርሱ የፈጠረውን ሥጋ ተዋሐደ” /ሃይ.አበ.፵፯፡፪/፡፡
ስለዚህ ነገር ከልጅዋ ከወዳጅዋ ታማልደን ዘንድ ኹል ጊዜ እርስዋን እንለምን፡፡ በቅዱሳን ዘንድ ቸር ናትና እርሷን እንለምን፡፡ ለሊቃነ ጳጳሳት አስበ ጵጵስናችን (የጵጵስናችን ዋጋ) ይሰጠናል ብለው ደጅ የሚጠኑትን ወልዳላቸዋለችና ከልጅዋ ከወዳጅዋ ታማልደን ዘንድ ኹል ጊዜ እርስዋን እንለምን፡፡ ነቢያት አስበትንቢታችንን ይሰጠናል ብለው “ይወርዳል፤ ይወለዳል” ብለው ትንቢት የተናገሩለትን ወልዳላቸዋለችና ከልጅዋ ከወዳጅዋ ታማልደን ዘንድ ኹል ጊዜ እርስዋን እንለምን፡፡ ሐዋርያት አስበ ሰብከታችንን ይሰጠናል ብለው “ውስተ ኵሉምድር ወፅአ ነገሮሙ ወእስከ አጽናፈ ዓለም በጽሐ ነቢቦሙ - መምህራነ ሐዲስ ሐዋርያት ለምእመናነ ሐዲስ ወረደ ተወለደ ብለው አስተማሩ” እንዲል /መዝ.፲፰፡፬/ ጽንፍ እስከ ጽንፍ ዙረው ወረደ ተወለደ ብለው ያስተማሩለትንወልዳላቸዋለችና ከልጅዋ ከወዳጅዋ ታማልደን ዘንድ ኹል ጊዜ እርስዋን እንለምን፡፡ ሰማዕታ ከዓላውያን ነገሥታት፣ ከዓላውያን መኳንንት ገብተው አስበ ትዕግሥታችንን ይሰጠናል ብለው መከራውን ታግሠው የተቀበሉለትን፣ ምዕመናን አስበ ተጋድሏቸውን ይሰጠናል ብለው ከፍትወታት ከእኩያት ኃጣውእ የተዋጉለት ኢየሱስ ክርስቶስን ወልዳቸዋችና ከልጅዋ ከወዳጅዋ ታማልደን ዘንድ ኹል ጊዜ እርስዋን እንለምን፡፡ ሰው ኹኖ አድኖናልና በጥበቡ እየሰፈረ የሚሰጠው፣ ዳግመኛም የጸጋው ብዛት የማይታወቅ የቸርቱን ብዛት መርምረን እንወቅ፡፡ ሰው ኹኖ ካዳነን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፭. ተናግሮ የማያስቀር፣ ምሎ የማይከዳ እግዚአብሔር፡- “ከባሕርይህ የተከፈለልጅህ (ክርስቶስን) በዙፋንህ አስቀምጥልሃለሁ” ብሎ ለዳዊት በእውነት ማለለት /መዝ.፻፴፩፡፲፩/፡፡ ዳዊትም ክርስቶስ በሥጋ ከእርሱ እንዲወለድ ባመነ ጊዜ የአካላዊ ቃል ማደርያውን መርምሮ ያውቅ ዘንድ ወደደ፡፡ ቀኖናም ገባ፡፡ ከዚህም በኋላ “ናሁ ሰማዕናሁ በኤፍራታ ወረከብናሁ ውስተ ዖመ ገዳም - በኤፍራታተወልዶ፤ በጎል ተጥሎ፤ በጨርቅ ተጠቅልሎ በግዕዘ ሕፃናት ሲያቅስ ሰማነው”አለ /መዝ.፻፴፩፡፮/፡፡ ይህቺውም እኛን ስለማዳን ይወለድባት ዘንድ የመረጣትቤተ ልሔም፣ ቤተ ኅብስት የተባለች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፡፡ ከሰማይ የወረደው ኅብስት እርሱ ነውና /ዮሐ.፮፡፶፩/፡፡
ከነቢያት አንዱ የሚኾን ሚክያስም ዳግመኛ እንዲህ አላት፡- “አንቺም የኤፍራታ ዕፃ የምትኾኝ ቤተ ኅብስት ቤተ ልሔም እመቤታችን ሆይ! በይሁዳ ከነገሡ ነገሥታት ብትበልጭ እንጂ አታንሺም፡፡ እሥራኤል ዘነፍስን የሚጠብቅ ንጉሥ ባንቺ ይወለዳልና እንዲህ እንደኾንሽ አትቀሪም፡፡ ንጉሥ ይወለድብሻል፤ቅዳሴ መላእክት ይሰማብሻል፤ የብርሃን ድንኳን ይተከልብሻል፤ መቶው ነገደ መላእክት ደጅ ይጠኑብሻል፡፡ አሕዛብ ይገብሩብሻል” ብሏታል /ሚክ.፭፡፪/፡፡ ጀሮም የተባለ ቅዱስ አባት ይህን አንቀጽ ሲተረጕም፡- “ከሰማይ የወረደ ኅብስት /ዮሐ.፮፡፶፩/ የተወለደብሽ ቤተ ኅብስት ሆይ! ሰላምታ ይገባሻል፡፡ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደብሽ ምድረ ፍሬ፣ ምድረ ምውላድ (ኤፍራታ) ሆይ! ሰላምታ ይገባሻል፡፡ በዘመነ ብሉይ ሚክያስ ነቢይ ስለ አንቺ ሲናገር እንዲህ ብሎ ተናግሮ ነበርና፡- ‘ወአንቲኒ ቤተ ልሔም ምድረ ኤፍራታ ኢትቴሕቲ እም ነገሥተ ይሁዳ - አንቺም የኤፍራታ ዕፃ የምትኾኝ ቤተ ልሔም ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሺም /ማቴ.፪፡፮/፡፡ ኢይወጽእ ምስፍና ወምልክና እምአባሉ ለይሁዳ - በትረ መንግሥት ከይሁዳ አይጠፋም እንዲል /ዘፍ.፵፱፡፲/ ከባሕርይ አባቱ ከአብ ጋር ቅድመ ዓለም የነበረ፣ ከዲያብሎስ አስቀድሞ ቀዳማዊ የኾነ እሥራኤል ዘነፍስን የሚጠብቅ ንጉሥ ከአንቺ ይወጣል (ይወለዳልና)” ብሏል /St. Jerome, Letter 108:10/፡፡
ወዮ! ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ ከአብ ከባሕርይ አባቱ ከመንፈስ ቅዱስ ከባሕርይ ሕይወቱ ጋራ ክብር ይግባውና በአንድ በመንፈስ ቅዱስተገልጾላቸው የክርስቶስን ነገር የተናገሩ ሚክያስና ዳዊት የተናገሩት ነገር ምን ይረቅ? ምን ይጠልቅ? አንድም ሚክያስና ዳዊት ለተናገሩት ነገር አንክሮ ይገባል፡፡ከአብ ከባሕርይ አባቱ ከመንፈስ ቅዱስ ከባሕርይ ሕይወቱ ጋር ክብር ከሚገባው ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣን ለምኚልን፡፡

፮. ለእሥራኤል የነገሠ ዳዊት ኢሎፍላውያን በጠላትነት በተነሡበት ጊዜ ከቤተ ልሔም ምንጭ ውሃ ይጠጣ ዘንድ ወደደ፡፡ ዳዊት ታመመ፤ ቢታመም ዘመዶቹቀሳ አወጡት፡፡ ኢሎፍላውያን ይህን ሰምተው ቤተ ልሔምን አልፈው ሰፈሩ፡፡ዳዊትም “ከቤተ ልሔም ምንጭ ውሃ ማን ባመጣልኝ?” አለ፡፡ ከእናንተ መካከል፡- “ስለምን ከቤተ ልሔም የተቀዳ ውሀ ይጠጣ ዘንድ ወደደ?” የሚል ሊኖር ይችላል፡፡ እኛም እንዲህ ብለን እንመልስለታለን፡- ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርነው ታምሞ ስለነበር የቤተ ልሔም ውሀ ደግሞ ማየ ፈውስ ናትና /፪ኛ ነገ.፳፫፡፲፭-፲፯፣ አንድምታውን ይመልከቱ/፡፡
ስለኾነም የጭፍራ አለቆች አዲኖን ኢያቡስቴ ኤልያናም አፋ አፋቸውን ታጥቀው፣ ዘገራቸውን ነጥቀው፣ ራዋታቸውን ጭነው “የማን ጌታ በውሃ ጥም ይሞታል?” ብለው ፈጥነው ተነሡ፡፡ በኢሎፍላውያን ከተማ ተዋጉለት፡፡ ይጠጣ ዘንድ የወደደውንም ውሀ አመጡለት፡፡ ብጹዕ ዳዊት ግን ስለ ርሱ ሰውታቸውንለሞት አሳልፈው እንደ ሰጡ በየ ጊዜ የራዋቱን ውሀ አፈሰሰው፡፡ በማለፊያው ቀድተው የሰጡትን አልጠጣም፡፡ “የናንተን ደም መጠጣት ነው” ብሎ አፍሶታል፡፡ አንድም ውሀውን መሥዋዕት አድርጐ ለእግዚአብሔር አፈሰሰው፡፡ ከእናንተ መካከል፡- “ዳዊት ንጉሥ ሲኾን መሥዋዕት የሚኾን ላም በግ አጥቶ ነውን?” ብሎ የሚጠይቅ ሊኖር ይችላል፡፡ በፍጹም! እግዚአብሔር የወደዱትን ቢተዉለት ስለሚወድ ነው እንጂ /መዝ.፶፬፡፮፣ ዝኒ ከማሁ፣ ገጽ ፻፵፭/፡፡
ዳዊት የወደደውን ውሀ ስለ እግዚአብሔር ብሎ ስላፈሰሰውም ጽድቅ ኾኖተነገረለት፡፡ አዲኖን፣ ኢያቡስቴ፣ ኤልያና ስለ ዳዊት ብለው ጣዕመ ዓለምን እንደናቁ፤ ዳዊትም ስለነርሱ አንድም ስለ እግዚአብሔር ብሎ ጣዕመ ማይን እንደናቀ ሰማዕታት ጣዕመ ዓለምን ናቁ፡፡ አዲኖን፣ ኢያቡስቴ፣ ኤልያና ዳዊትን ብለው ደማቸውን እናፍስ እንዳሉ፤ ዳዊትም ውሀውን እንዳፈሰሰ፤ ሰማዕታትስለ እግዚአብሔር ብለው ደማቸውን አፈሰሱ፡፡ አዲኖን፣ ኢያቡስቴ፣ ኤልያናስለ ዳዊት ብለው መራራ ሞትን እንታገሥ እንዳሉ፡ ዳዊትም ጽምዓ ማይን ልታገሥ እንዳለ ሰማዕታት መራራ ሞትን ታገሡ፡፡ ቸር አባት ሆይ! እኛስ እንደሰማዕታት ከዓላውያን ነገሥታት፣ ከዓላውያን መኳንንት ገብተን መከራውን ታግሠን ተቀብለን፤ እንደ ምዕመናንም ከፍትወታት ከእኩያት ኃጣውእ ተዋግተንድል ነሥተን መዳን አይቻለንምና እንደ ቸርነትህ ብዛት ይቅር በለን፡፡ ቸርና ይቅር ባይ ከሚባል ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣ ለምኚልን፡፡
፯. ከሦስቱ አካል አንዱ አካል በእግረ አጋንንት መረገጣችንን መጠቅጠቃችንንአየና ባሕርዩን ዝቅ አድርጎ
ሰው ኹኖ በድንግል ማኅፀን አደረ /ኢሳ.፶፱፡፮/፡፡ ባሕየ መላእክትን ባሕይ አላደረገም፤ ባሕርየ ሰብእን ባሕርይ አድርጎ በድንግል ማኅፀን አደረ እንጂ /ዕብ.፪፡፲፮/፡፡ ከብቻዋ ከኃጢአት በቀርም እንደኛ ሰው ኾነ /ዕብ.፬፡፲፬/፡፡ ሚክያስና ዳዊት በቤተ ልሔም ይወለዳል ብለው እንደ ተናገሩ በቤተ ልሔም ተወለደ፡፡ “ይሙት ቤዛነ በትስብእቱ ወየሀበነ መድኃኒተ ዘከመ መለኮቱ” እንዲልም እንደአምላክነቱ አዳነን እንደ ሰውነቱም ቤዛ ኾነን /ኤፌ.፩፡፯/፡፡ ዳግመኛም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “እናንተ አስቀድሞ በሥጋ አሕዛብ የነበራችሁ፥ በሥጋ በእጅ የተገረዙ በተባሉት ያልተገረዙ የተባላችሁ፥ ይህን አስቡ፤ በዚያ ዘመን ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ኾናችሁ በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ ከእግዚአብሔርም ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ። አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ኾናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል” /ኤፌ.፪፡፲፩-፲፫/ እንዲል ወገኖቹ ያልነበርንእኛን ወገኖቹ አደረገን፡፡ ወገኖቹ ካደረገን ልጅሽ ጽንዕት በድንግልና ሥርጉት በቅድስና እመቤታችን ጸጋውን ክብሩን እንዳይነሣ ለምኚልን፡፡
ይኸን ሲጨርስ በያዘችው መስቀለ ብርሃን ባርካው ወደ ሰማይ ታርጋለች፡፡ እርሱም ተባርኮ እጅ ነሥቶ ይቀራል፡፡

አነሣሥቶ ላስጀመረን አስጀምሮም ላስጨረሰን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባው አሜን!!!

"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ::"    /ማቴ ፫:፫/

ዝክረ ቅዱሳንን ተማሩ ብለን እንለምናችኋለን!!
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
✝ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together
https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━━━

Comments