††† እንኳን ለካህኑ ሰማዕት አባ ኦሪ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። †††
††† በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! †††
††† ቅዱስ አባ ኦሪ ቀሲስ †††
††† ይህ ቅዱስ አባት የዘመነ ሰማዕታት ፍሬ ነው:: በዘመኑ (በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን) ክርስቲያን መሆን ብቻውን ለሞት እንደሚያበቃ ወንጀል ይቆጠር ነበር:: በጊዜው ክርስቲያን ከመሆን በባሰ መንገድ እረኛ ካህን ሆኖ መገኘት በጣም ከባድ ነበር::
ከመነሻውም ያን ጊዜ ክህነት የሚሰጠው በሕዝቡና በሊቀ ጳጳሱ ምርጫ ነበር እንጂ እንደ ዘንድሮ "እኔን ሹሙኝ" ማለት ልማድ አልነበረም:: ምዕመናንም እረኛቸውን ሲመርጡ በጉቦ: በዝምድና አይደለም:: በርትቶ የሚያበረታቸውን: ለመንጋው ራሱን አሳልፎ የሚሰጠውን ይመርጣሉ እንጂ::
ያልሆነ ሰው ለክህነት ቢመረጥ አንድም ክዶ ያስክዳል: ሲቀጥልም ለሕዝቡ መሰናክል መሆኑ አይቀርም:: በጊዜው (በዘመነ ሰማዕታት) የነበሩ ካህናት የቤት ሥራቸውም ማስተማር ብቻ አልነበረም:: በድፍረት በምዕመናን ፊት አንገታቸውን ለሰይፍ መስጠት ይጠበቅባቸው ነበር እንጂ::
ይህንን በገሃድ መፈጸም ከቻሉ አበው አንዱ ደግሞ አባ ኦሪ ቀሲስ ናቸው:: ቅዱሱ ተወልደው ባደጉባት ሃገረ ስጥኑፍ (የግብፅ አውራጃ ናት) መጻሕፍትን የተማሩ: ተወዳጅ እና ደግ ሰው ነበሩ::
አባ ኦሪ ገና ከወጣትነት ቀዳሚ ግብራቸው መንኖ ጥሪት (ምናኔ) ነበር:: በንጽሕናቸው ደስ የተሰኙ ምዕመናንም "ቅስና ተሹመህ ምራን: አስተምረን::" ቢሏቸው አበው ውዳሴ ከንቱን አይፈልጉምና "አይሆንም" አሉ::
ነገሩ ፈቃደ እግዚአብሔር ነበረና አባ ኦሪ ቅስናን ተሹመው ያገለግሉ ገቡ:: ሕዝቡን በማስተማር: በመምከር: ደካማውን በማጽናት ብዙ ደክመዋል::
ከቅድስናቸው የተነሳ ቅዳሴ ሊቀድሱ ሲገቡ ጌታችን በገሃድ ይገለጥላቸው ነበር:: ሠራዊተ መላእክትም ከበው ይነጋገሯቸው ነበር::
ሥጋውን ደሙን በማቀበልም ተግተው ዘመናት አለፉ:: ቆይቶ ግን ያ በዜና ይሰሙት የነበረ መከራ (ሰማዕትነት) በደጃቸው ደረሰ:: በጊዜው ብዙ ሰው በሰማዕትነት አለፈ:: አባ ኦሪም ወደ ቤተ እግዚአብሔር ገብተው ስለ ራሳቸውና ሕዝቡ ጽናትን: ደኅንነትን ለመኑና ከቤተ ክርስቲያን ወጡ::
በቀጥታ የሔዱትም ወደ ዐውደ ስምዕ (የምሥክርነት አደባባይ) ነበር:: በመኮንኑ ፊት ቀርበው "ክርስቶስ አምላክ: ፈጣሪ: የሁሉ ጌታ ነው:: የእናንተ ጣዖት ግን ጠፊ: ረጋፊ: ወርቅ: ብር: እንጨትና ድንጋይ ነው::" ሲሉ በድፍረት ተናገሩ::
መኮንኑም ከአነጋገራቸው የተነሳ ተቆጥቶ ሥቃይን አዘዘባቸው:: ወታደሮቹ ይሆናል ያሉትን ማሰቃያ ሁሉ አባ ኦሪ ላይ ሞከሩ:: በኋላም ወደ ጨለማ እሥር ቤት ወስደው ጣሏቸው:: በእሥር ቤት ውስጥም ድውያንን ፈወሱ: ተአምራትን ሠሩ::
ይሕንን ዜና የሰሙ አሕዛብ ብዙ ድውያንን ሰብስበው መጡ:: ቅዱሱም ሁሉን በጸሎታቸው ፈወሱ:: በዚህ ምክንያትም ብዙ አሕዛብ ወደ ክርስትና መጥተዋል:: በክርስቶስ አምነውም ለክብር በቅተዋል::
ቅዱሱንም ከእሥር ቤት አውጥተው ብዙ ካሰቃዩዋቸው በኋላ በዚህች ቀን ገድለዋቸው ሰማዕትነትን አግኝተዋል:: በአክሊለ ጽድቅ ላይ አክሊለ ካህናትን: በአክሊለ ካህናትም ላይ አክሊለ ሰማዕታትን ደርበዋል::
††† አምላከ ቅዱሳን በአባቶቻችን ጽናት ያጽናን:: ጸጋ በረከታቸውንም ይክፈለን::
††† ነሐሴ 9 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አባ ኦሪ ቀሲስ (ሰማዕት)
2.አባ ጲላጦስ ሊቀ ጳጳሳት
††† ወርኀዊ በዓላት
1.አባ በርሱማ ሶርያዊ (ለሶርያ መነኮሳት ሁሉ አባት)
2.አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ (ኢትዮጵያዊ)
3.ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ቅዱሳን ሊቃውንት (ርቱዐነ ሃይማኖት ዘኒቅያ)
4.የብሔረ ብፁዐን ጻድቃን
5.አባ መልከ ጼዴቅ ዘሚዳ (ኢትዮጵያዊ)
6.ቅዱስ ዞሲማስ ጻድቅ (ዓለመ ብፁዐንን ያየ አባት)
††† "ስለዚሕ ወንድሞቼ ሆይ ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ:: ልባሞች እንደመሆናችሁ እላለሁ:: በምለው ነገር እናንተ ፍረዱ:: የምንባርከው የበረከት ጽዋ ከክርስቶስ ደም ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? የምንቆርሰውስ እንጀራ ከክርስቶስ ሥጋ ጋር ኅብረት ያለው አይደለምን? . . . እኛ ብዙዎች ስንሆን አንድ ሥጋ ነን:: ሁላችን ያን አንዱን እንጀራ እንካፈላለንና::" †††
(፩ቆሮ. ፲፥፲፬-፲፰)
††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ::" /ማቴ ፫:፫/
ዝክረ ቅዱሳንን ተማሩ ብለን እንለምናችኋለን!!
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
✝ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together
https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━━━
Comments
Post a Comment