✞✞✞✝ እንኳን ለታላቁ ክርስቲያናዊ ንጉሥ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ዓመታዊ የንግሥ በዓል በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን። ✞✞✞✝
✞✞✞ ✝በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን! ✞✞✞✝
✞✞✞✝ ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ✝ ✞✞✞
✞✞✞ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ ለቤተ ክርስቲያን የፈፀመውን መልካም ተግባር ያሕል መሥራት የቻለ ንጉሥ በሐዲስ ኪዳን የለም:: ጻድቁ ንጉሥ ከቅድስት እናቱ እሌኒ እና ከአባቱ ቁንስጣ በበራንጥያ ተወለደ::
ዘመኑ ዘመነ ዐጸባ (የመከራ ጊዜ) ወይም የሰማዕታት ዘመን በመሆኑ ክርስቲያኖች በግፍ የሚጨፈጨፉበት ወቅት ነበር::
ክርስቲያኖችን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት በተደረገው የአርባ ዓመታት ዘመቻ አብያተ-መቃድስና መጻሕፍት ተቃጠሉ:: ብዙዎቹ በየበርሃው ተሰደዱ:: ሚሊየኖች በግፍ አለቁ::
የዚሕን ዘመን መከራ በውል ያልተረዳ ሰው ቅዱስ ቆንጠንጢኖስን ሊያከብር አይችልም:: ምክንያቱም ይህን የመከራ ዘመን በፈቃደ እግዚአብሔር አስቁሞ: ቀርነ ሃይማኖት የቆመው: ብዙ ሥርዓት የተሠራው: ቤተ ክርስቲያንም ያበራችው በዘመኑ ነውና::
ይህች ዕለት ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ የነገሠባት ናት::
ይህስ እንደ ምን ነው ቢሉ:- በ312 ዓ/ም ዓለምን አስጨንቀው ሲገዙ ከነበሩ ነገሥታት አንዱ የሮሙ ቄሣር መክስምያኖስ ነበር:: ክርስቲያኖችን ከግዛቱ ያጠፋ ዘንድ ብዙ ጊዜ ሞክሯል::
በሰይጣን ምክር አብያተ ክርስቲያናትን ዘግቷል: መጻሕፍትን አቃጥሏል: ምዕመናንንም ጨፍጭፏል:: ነገር ግን ሰማዕታት አንዱ ሲሰዋ አንድ ሺውን እየተካ (በእምነት እየወለደ) ነውና እንኳን ሊጠፉ በየቀኑ ይበዙ ነበር::
ምንም የሚሊየኖችን ደም ቢያፈስም ክርስቲያኖች ከጽናታቸው የሚነቃነቁ አልሆኑም:: በዚህም ስለ ተበሳጨ ከክርስቲያኖች አልፎ በአሕዛብም ላይ ግፍን ጀመረ:: በዚህ ጊዜ ደግሞ የበራንጥያው ንጉሥ ቁንስጣ ዐርፎ ልጁ ቆስጠንጢኖስ ነግሦ ነበርና የሮም ሰዎች ዝናውን ሰሙ::
በእርሱ መንግስት ፍርድ አይጓደልም: ደሃ አይበደልም: ግፍም አይፈጸምም ነበርና ይህንን ያወቁ የሮም ሰዎች መልዕክተኛ ልከው ከአውሬው መክስምያኖስ እንዲያድናቸው ተማጸኑት:: እርሱም ነገሩን ሲሰማ አዝኖ: ከመከራ ሊታደጋቸውም ወዶ: ሠራዊቱን አስከትቶ ተነሳ::
ወደ ጦርነት እየሔደ ካረፈበት ወንዝ ዳር በመንፈቀ መዓልት (ስድስት ሰዓት ላይ) ድንገት ከሰማይ ግሩም ተአምርን ተመለከተ:: የብርሃን መስቀል በከዋክብት አጊጦ: ሰማይንም ሞልቶ: ብርሃኑ ፀሐይን ሲበዘብዛት: በላዩ ላይም "ኒኮስጣጣን" የሚል ጽሑፍ ተስሎበት አየ::
"ምንድን ነው?" ብሎ ቢጠይቅ አንድ ደፋር ክርስቲያን ወታደር (አውስግንዮስ ይባላል:: አርጅቶ በመቶ አሥር ዓመቱ ሰማዕት ሆኗል::) ወደ ንጉሡ ቀርቦ "ይሔማ አዳኝ ሕይወት የሆነ መስቀለ ክርስቶስ ነው::" ብሎታል::
ይሕንን እያደነቀ ሳለም በሌሊት ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ወደ እርሱ መጥቶ ነገሩን ገለጠለት: ምሥጢሩንም ተረጐመለት:: "ኒኮስጣጣን ማለት 'በዝየ ትመውዕ ጸረከ-በዚህ መስቀል ጠላትህን ድል ታደርጋለህ' ማለት ነው::" አለው::
በነጋ ጊዜም ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ በሁሉም የጦር እቃ (በወታደሩ: በጦሩ: በፈረሱ: በጋሻው . . .) ላይ የመስቀል ምልክትን ሠርቶ መክስምያኖስን ገጠመው:: በኃይለ መስቀሉም ድል አድርጐ ማረከው:: የተረፈው የአሕዛብ ሠራዊትም እሸሻለሁ ሲል ድልድይ ተሰብሮበት ወንዝ ውስጥ ገብቶ አለቀ::
✞✞✞ ቅዱሱ ንጉሥም በኃይለ መስቀሉ ሮሜን እጅ አደረጋት::
"ሃይማኖተ ክርስቶስ ነሢኦ ወዘመስቀሉ ትርጓሜ:
ቆስጠንጢኖስ ዮም ነግሠ በሮሜ:
ዘመክስምያኖስ ዕልው ድኅረ ኀልቀ ዕድሜ::" እንዲል::
ቅዱሱ ንጉሥ ድል አድርጐ በዚህች ቀን ወደ ሮም ሲገባ ከመከራና ሞት የተረፉ ክርስቲያኖች ዕፀ መስቀሉን ይዘው በዝማሬ ተቀብለውታል:: እርሱም በዚህች ቀን በ312 ዓ/ም በሮም ግዛት ሁሉ ላይ ነግሦ ለሰባት ቀናት በዓለ መስቀልን በድምቀት አክብሯል:: በዘመኑ ሁሉም ቅዱስ ሚካኤል አልተለየውምና ወዳጁ ሲባልም ይኖራል::
ቅዱሱ ንጉሥ ለሁሉም ነቢያት: ሐዋርያት እና ሰማዕታት አብያተ ክርስቲያናትን ራሱ በመሠረታት በቁስጥንጥንያ አንጿል:: በዘመኑ ቤተ ክርስቲያን በሰላም ኖራለት: በኃይለ መስቀሉ ጠላት ጠፍቶለት ኑሮ አርፏል::
"ቆስጠንጢኖስ" ማለት "ሐመልማል" ማለት ነው::
✞✞✞ ጌትነት ያለው አምላካችን በይቅርታው ይጐብኘን:: ደግ መሪ: መልካም አስተዳዳሪን ያድለን:: ከቅዱሱ ንጉሥም በረከትን ያሳትፈን::
✞✞✞ ነሐሴ 12 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ታላቁ ቅዱስ ቆስጠንጢኖስ (ጻድቅ ንጉሥ)
2.ቅዱስ ዕፀ መስቀል
✞✞✞ ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት
2.ቅዱስ ላሊበላ ጻድቅ (ንጉሠ ኢትዮጵያ)
3.ቅዱስ ማቴዎስ ሐዋርያ
4.ቅዱስ ድሜጥሮስ
5.ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
6.ቅዱስ ቴዎድሮስ ምሥራቃዊ (ሰማዕት)
7.ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ
8.አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ
✞✞✞ "እንግዲህ እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ: ጸጥና ዝግ ብለን እንድንኖር: ልመናና ጸሎት: ምልጃም: ምስጋናም ስለ ሰዎች ሁሉ: ስለ ነገሥታትና መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ:: ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው::" ✞✞✞
(፩ጢሞ. ፪፥፩-፬)
✞✞✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞✞✞
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ::" /ማቴ ፫:፫/
ዝክረ ቅዱሳንን ተማሩ ብለን እንለምናችኋለን!!
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
✝ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together
https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━━━
Comments
Post a Comment