#መጻጒዕ
የዐቢይ ጾም አራተኛ ሳምንት
«ተንሥዕ ንሣዕ ዓራተከ ወሑር፤ ተነስተህ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ» 《ዮሐ.5፡8》
የዐብይ ፆም አራተኛው ሳምንት መጻጉዕ ይባላል፡፡ ይህ ዕለት አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድውያንን መፈወሱ የሚዘከርበት ሳምንት ነው፡፡
«ተነስተህ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ» ያለው ሠላሳ ስምንት ዓመት በአልጋ ላይ ሰውነቱ ልምሾ ሆኖ ታሞ የነበረውን ሰው ነበር፡፡ ይህ ሰው የህመሙ ዘመን ስለረዘመ ዘመዶቹ ሁሉ እየሰለቹ የማስታመሙን ነገር ችላ ብለው ጥለውት ሄደዋል፡፡ ህመምተኛው ዘመዶቹ በተውት ቦታ በቤተሳይዳ መጠመቂያ ፀበል አጠገብ ተኝቶ ነበር፡፡
ጌታችንም ብዙ ዘመን ተኝቶ እንደኖረ አውቆ «ልትድን ትወዳለህን?» አለው፡፡ እርሱም መጠቂያው ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም በማለት መልስ ሰጠ፡፡ ፀበሉን አንዳንድ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ድንገት ሲያናውፀው ቀድሞ ወደ ፀበሉ የገባ ይድን ስለነበር፤ መልሱ የሚያመለክተው ከሁሉ ቀድሞ እኔን ተሸክሞ ወደ ፀበል ሊያስገባኝ የሚችል ዘመድ ስለሌለኝ እንዴት እድናለሁ ነበር፡፡
ነገር ግን ጌታችን የሁሉም መድኃኒት በመሆኑ ወዲያው «ተነስተህ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ» ሲለው ድኖ አልጋውን ተሸክሞ ሄደ፡፡ አይሁድ ማን አልጋውን ተሸክሞ እንዲሄድ እንደፈቀደለት ቢጠይቁት ለጊዜው ጌታችንን ባያውቀውም፤ በሌላ ጊዜ ጌታችን ሲያገኘው «እነሆ! ድነሃል ግን ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ዳግመኛ እንዳትበድል ዕወቅ» በአለው ጊዜ ይህ ሰው ከሰላሳ ስምንት ዓመት የአልጋ ቁራኝነት በኋላ ከተጣበቀበት አልጋ ያላቀቀውን አምላክ ረስቶ ለአይሁድ ሊጠቁመው ሮጦ ሄደ፡፡ እንዳሰበውም ነገራቸው እነሱም ሊያሳድዱት ሊገሉትም ይሹ ነበር፡፡
ከዚህ የፈውስ ታሪክ ፈርጀ ብዙ ነገር እንረዳለን፡፡ ለአብነት ያህል ጥቂቶቹን እንመልከት፡-
1. እግዚአብሔር ሕሙማንን በምሕረቱ ይጐበኛቸዋል፤ ከደዌአቸውም ፈውሶ ጤንነታቸውን ሊመልስላቸው ይችላል፡፡
ከታሪኩ እንደተመለከትነው
ሠላሳ ስምንት ዓመት የተኛውን ከደዌው፣
ከእናቱ ማህፀን ያለዓይን የተወለደውን ከዓይነ ስውርነት፣
አስራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈሳት የነበረችውን ከሕመሟ፣
ከሞተ አራት ቀን የሆነውን አልአዛርን ከሞት፣
የመቶ አለቃውን ልጅ ባለበት ሆኖ ከሞት ወዘተ አድኗቸዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው እምነታችን ካለንና እግዚአብሔር ከፈለገ ማዳን እንደሚቻለው ነው፡፡
2. የዳነ ሰውም ያዳነው አምላኩን በማወቅ፤ ውለታውን በሃይማኖት ጸንቶ በደግ ሥራ መመለስ ይገባዋል፡፡ በመጻጉዕ ታሪክ ላይ ግን የምናገኘው እንዲህ አይደለም፡፡
ከተጣበቀበት የአልጋ ቁራኛነት እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ቢያድነው፤ ለአይሁድ አለቆች ባዳነው ሰውነቱና እግሮቹ ሮጦ ሄዶ ሰብቅ ሠራ፡፡ ምስክር ይሆንበት ዘንድ «እነሆ ድነሃል ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ» በማለት እየተናገረው ሳለ «በሰንበት ያዳነኝ ኢየሱስ ነው» በማለት ያዳነውን በመክሰስ አሳልፎ ሰጠው፡፡
የሰውየውን ማንነት ስንመለከት ልቡ ያልዳነ፤ ያዳነውን ሊረዳ ያልቻለ፣ ክፉና ደጉን ማገናዘብ የተሳነው ሰው ነው፡፡ ዛሬስ ለተደረገልን መልካም ነገር ተገቢውን መልካም ምላሽ በበጐነት የመለሰን ስንቶቻችን ነን?
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስረዳን አምላክ ላደረገላቸው ፈውስ ዘመናቸውን በበጐ ምግባር የፈፀሙ አያሌ ቅዱሳን አሉ፡፡
ለምሳሌ ክፉ መናፍስት አደረውባት የነበረችና በኋላ ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምህረት እጁ የጎበኛትን መግደላዊት ማርያምን መጥቀስ ተገቢ ነው፡፡
ይህች ሴት ሰባት አጋንንት የወጣላት ሴት ስትሆን ጌታችን በሚያስተምርበት እየዞረች ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን በጉልበቷና በገንዘቧ ለጌታችንና ለሐዋርያት የሚያስፈልጋቸውን በማቅረብ ታገለግል ነበር፡፡ 《ሉቃ. 8÷2-3》፡፡
በትንሣኤው ቀን ማለዳ ከሁሉ ቀድማ ተገኝታለች፤እያለቀሰችም ጌታችንን ትሻው ነበር፡፡ ለዚህም ልዩ ትጋቷ ጌታችን ከሌሎቹ ይልቅ ትንሣኤውን ለማየት የመጀመሪያዋ አድርጓታል፡፡ የምስራቹን ለሐዋርያት በማድረስ በኩል የክብር መልእክተኛ ሆናለች ከዚህ የበለጠ ምን መታደል አለ፡፡《ዮሐ. 10.1-18》
ከነቢያት አንዱ ነቢዩ ኢሳይያስን ብንመለከት ሐብተ ትንቢቱ ተነስቶት ከንፈሮቹ በለምፅ ነደው እያዘነ ይኖር ነበር፡፡ ኦዝያን በሞተበት ወራት እግዚአብሔር በታላቅ ዙፋን ተቀምጦ ታይቶት፤ ምስጋና ከሚያቀርቡት መላእክት አንዱ ሱራፌል እየበረረ መጥቶ በጉጠት ፍም አፉን ዳሶት «በደልህ ከአንተ ተወገደ፣ ኃጢአትህም ተሰረየልህ» ብሎት ከለምጹ አንጽቶት ኃጢአቱ እንደተሰረየለት ነግሮት ሄዷል፡፡
ነቢዩ ስለተደረገለት ፈውስ የጌታ ድምፅ ማንን እልካለሁ? ሲል እነሆ እኔ አለሁ ብሎ ትንቢት በመናገር፣ ሕዝቡን በማስተማር በመጋዝ እስከ መሠንጠቅ ድረስ እራሱን ለእግዚአብሔር ሰጥቷል፡፡
ከላይ ያየናቸውን ሠላሳ ስምንት ዓመት በአልጋ ላይ የተኛውን መፃጉንና መግደላዊት ማርያምን እንዲሁም ነቢዩ ኢሳይያስን ስናወዳድር በተገቢው ምላሽ ያልሰጠው መፃጉዕ ነው፡፡《ት.ኢሳ.6÷1-8》፡፡
እኛስ በየደቂቃው በኃጢአት ሳለን እንኳ ጥበቃው የማይለየን እግዚአብሔር ያደረገልንን በማሰብ አሁን በዚህ ሰዓት ምን እየሰራን ይሆን ? ወደፊትስ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ምን ለመሥራት አስበናል? ለባሮቹ ፈውስን ሰጥቶ በጐ ምላሽን በማከናወን ያፀናቸው አምላክ እኛንም ይረዳን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡ ይቆየን!
††† ወስብሐት ለእግዚአብሔር †††
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
✝ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together
https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━⊱✿⊰━━
Comments
Post a Comment