† ✝️ቅዱስ ዳዊት ልበ አምላክ✝️ †
=>ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- "እግዚአብሔር ለዳዊት በእውነት ማለ: አይጸጸትም::" (መዝ. 131:11) አሁን በእግዚአብሔር መጸጸት ኑሮበት አይደለም:: ቅዱስ ዳዊት የማያጸጽት ፍጹም ወዳጅ መሆኑን ሲገልጥ ነው እንጂ:: ጌታ ቅዱስ ዳዊትን "እንደ ልቤ የሆነ: ፈቃዴን የሚፈጽም: ባሪያየን ዳዊትን አገኘሁት" (መዝ. 88:20) ብሎ ሲናገር ሰምተን እጅግ አደነቅን::
+እንደ አምላክ ልብ ሆኖ መገኘት ምን ይረቅ?! ምንስ ይደንቅ?! ለዚህ አንክሮ ይገባል !! ጌታ ይቀጥልና ደግሞ "ዳዊትን እንዳልዋሸው አንድ ጊዜ በቅዱስነቴ ማልሁ" (መዝ. 88:35) ይላል:: አቤት አባታችን ዳዊት ክብር: የክብር ክብር: ውዳሴና ስግደትም ላንተ በጸጋ ይገባል እንላለን::
+ነቢየ ጽድቅ ቅዱስ ዳዊት 7 ሃብታት ሲኖሩት:-
1.ሃብተ ትንቢት
2.ሃብተ መንግስት
3.ሃብተ ክህነት
4.ሃብተ በገና (መዝሙር)
5.ሃብተ ፈውስ
6.ሃብተ መዊዕ (ድል መንሳት)
7.ሃብተ ኃይል ተብለው ይታወቃሉ::
+በ7ቱ ስሞቹም:-
1.ጻድቅ
2.የዋህ
3.ንጹሕ
4.ብእሴ እግዚአብሔር
5.ነቢየ ጽድቅ
6.መዘምር እና
7.ልበ አምላክ ተብሎ ይጠራል::
+"+ ልደት +"+
=>ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ስለ ልደቱ ሲናገር "እስመ ናሁ በኃጢአት ተጸነስኩ-በኃጢአት ተጸነስኩ" ይላል (መዝ. 50:5) አበው እንደ ነገሩን የቅዱስ ዳዊት አባት ደጉ እሴይ ከነገደ ይሁዳ የኢዮቤድ ልጅ ነው::
+ሚስቱን ሰሊብን አንድ ጐልማሳ በዝሙት ዐይን ሲፈልጋት ተመልክቶ ነበር:: አንድ ቀንም መንገድ ሔድኩ ብሎ ግን ያንን ጐልማሳ መስሎ ተመልሶ አብሯት አድሯል:: በዚያች ሌሊትም ቅዱስ ዳዊት ተጸንሷልና እንዲህ ብሏል::
+"+ ዕድገት +"+
=>ቅዱስ ዳዊት ከሕጻንነቱ ጀምሮ ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ያደረበት ነበር:: ሕጸን ሳለ በእረኝነት በጐቹን አያስነካም ነበር:: አንበሳውን በጡጫ: ድቡን በእርግጫ: ነብሩን በሩጫ የያዙትን ያስጥላቸው ነበር:: በጥቂቱ በበግ እረኝነት ስለ ታመነ ለእሥራኤል እረኛ ሊሆን ተመርጧል::
+"+ መቀባት +"+
+እግዚአብሔር ሳዖልን ከናቀው በሁዋላ ከእሴይ ልጆች መካከል "እንደ ልቤ የሆነውን ቀብተህ አንግስልኝ" ቢለው ነቢዩ ሳሙኤል ቤተ ልሔም ገብቷል::
+በዚያም ከኤልያብ እስከ አሚናዳብ: 7ቱን የእሴይን ልጆች ቢፈትን አልሆነም:: በቅዱስ ሚካኤል ጠቁዋሚነት ግን ከእረኝነቱ ዳዊት ተጠራ:: ገና ከርቀት ሲመጣ የዘይት ቀርኑ ቦግ ብሎ ተከፈተ::
+በቅዱስ ዳዊት ራስ ላይም እንደ እሳት ፈላ:: በአምላክ ምርጫም በ12 ዓመቱ ንጉሥ ተባለ::
+"+ ዳዊትና ጐልያድ ++
=>ኢሎፍላውያን በጠላትነት በተነሱባቸው ጊዜም ጐልያድ የሚሉት የጌት ሰው እሥራኤልን ሲያስጨንቅ ለ40 ቀናት ቆይቶ ነበር:: ለአምላኩ ስምና ክብር የሚቀና ቅዱስ ዳዊት ግን በድፍረት ገጥሞ በፈጣሪው ኃይል: በጠጠር ጥሎታል:: ከእሥራኤልም ሽሙጥን አርቁዋል:: ግን ቅዱሱ ብላቴና: ጐልያድ ደግሞ 6 ክንድ (3 ሜትር) የሚረዝም ሰው ነበር::
+"+ ስደት +"+
=>ቅዱስ ዳዊት ንጉሥ እንዲሆን ተቀብቶ ዙፋን አልጠበቀውም:: ጠላታቸውን ጥሎ ስላዳናቸው ፈንታ: ሳዖልን በገና እየደረደረ ስለ ፈወሰው ፈንታም ሊገደል ተፈለገ:: ፈጣሪው ከእርሱ ጋር ባይሆንም ይገድሉት ነበር::
+እርሱ ግን ለ18 ዓመታት በትእግስት ተሰደደ:: ከአንዴም ሁለት ሦስቴ ጠላቱን ሳዖልን አሳቻ ሥፍራ ላይ አግኝቶ በምሕረት ተወው:: በዚህ የዋሕነቱም በብሉይ ሆኖ "ጠላቶቻችሁን ውደዱ" የምትለውን ሕግ ፈጸማት:: (ማቴ. 7:45, መዝ. 16:4)
+"+ ንግሥና +"+
=>ቅዱስ ዳዊት የስደት ዘመኑ ሲፈጸም ሳዖል ሞተ:: ምን ጠላቱ ቢሆን 'የሳዖል ገዳይ ነኝ' ያለውን ተበቀለ:: ስለ ጠላቱም አለቀሰ:: 30 ዓመት ሲሆነው ነግሦ ለ7 ዓመታት በኬብሮን: ለ33 ዓመታት በኢየሩሳሌም (ጽዮን) ሕዝበ እግዚአብሔርን ጠብቁዋል::
+በዘመኑም ጠላቶቹን ሁሉ ድል አድርጉዋል:: በልጁ አቤሴሎም እጅ መሰደድን: በሳሚ ወልደ ጌራ መሰደብንም ታግሷል::
+"+ ንስሃ +"+
=>ቅዱሱ ንጉሥ ሁሉ ነገር የተሰጠው አባት ነው:: ሁሉ ሕይወቱም ለእኛ ት/ቤት ነው:: ሰው ነውና የኦርዮን ሚስት ቀምቶ: ኦርዮን አስገድሎ ነበር:: ጉዳዩን ነቢዩ ናታን በምሳሌ ሲነግረው ፍጹም ተጸጸተ::
+ማቅ ለብሶ: አመድ ነስንሶ አለቀሰ:: መሬትንም በእንባው ክንድ አራሳት:: ሐረግ እስከ ማብቀልም ደረሰ:: እግዚአብሔርም ንስሃውን ተቀብሎ ከፍ ከፍ አደረገው:: በንስሃ ለምትገኝ ጸጋም ምሳሌ ሆነ::
+"+ ነቢይነት +"+
=>በቤተ ክርስቲያን ትምሕርት ቅዱስ ዳዊትን የሚያህል ነቢይ (ምሥጢር የበዛለት) አልተገኘም:: 'ከዓለም በፊት እንዲህ ነበረ' ብሎ: ከዚያ ከስነ ፍጥረት እስከ ዳግም ምጽዓት የተናገረ እርሱ ነው::
+ስለ መላእክት: ነቢያት: ሐዋርያት: ጻድቃን: ሰማዕታት: ደናግልና መነኮሳት ሁሉ መናገሩ ይደነቃል:: ስለ ድንግል ማርያምና ስለ መድኃኒታችን ክርስቶስም አምልቶ: አስፍቶ ተናግሯል:: 150 ምዕራፎች ባሉት መጽሐፈ ትንቢቱ ኃላፍያትንና መጻዕያትን ተመልክቷል::
+ስለዚህም አበው:-
"አልቦ ምስጢር ወአልቦ ትንቢት:
ዘኢተናገረ አቡነ ዳዊት" ይላሉ::
+"+ መዝሙር +"+
=>ቅዱሱ ነቢይና ንጉሥ በጣም የሚታወቀው በዝማሬው ነው:: ለራሱ ባለ 10 አውታር : ለመዘምራኑ ደግሞ ባለ 8 አውታር በገናን አዘጋጅቶ ፈጣሪውን ያመሰግን ነበር:: 24 ሰዓት ሙሉ ስብሐተ እግዚአብሔር እንዳይቁዋረጥ 288 መዘምራንን በአሳፍ መሪነት መድቦ ነበር::
+ራሱም በፍጹም ተመስጦ: ማር ማር እያለው እግዚአብሔርን ያመሰግነው ነበር:: "ቃልህ ለጉረሮየ ጣፋጭ ነው" እንዲል:: (መዝ. 118:103) የዳዊት መዝሙሩ ለአጋንንት ትልቅ ጠላት ነው:: ቅዱሳን መላእክትም በዳዊት መዝሙር ይዘምራሉ::
"በዘቦቱ ይሴብሑ ሰማያውያን ወምድራውያን" እንዲል::
+"+ #ዳዊትና ጽዮን +"+
=>ቅዱስ ዳዊት ጽዮንን አንጾ ጽላተ ኪዳኑን አመጣ:: ለአምላከ ያዕቆብ ማደሪያን ሊፈልግም ዐይኑ ከእንቅልፍ ተከለከለ:: (መዝ. 131:2) የፈጣሪውን ፈቃድ ሊጠይቅ ሱባኤ ቢገባ "አኮ አንተ ዘትነድቅ ሊተ ቤተ - አንተ ሳትሆን የሚሠራልኝ ልጅህ ነው" አለው::
*አያይዞም የምሥጢረ ሥጋዌን ነገር ቢገልጥለት "ናሁ ሰማዕናሁ በኤፍራታ - እነሆ በኤፍራታ ሰማነው" ሲል ተናግሯል:: (መዝ. 131:6) የኪዳኑ ጽላት (ጽዮን) ከአቢዳራ ቤት ስትመጣ ከዙፋኑ ወርዶ: ከተራው ሕዝብ ጋርም ተቀላቅሎ በበገናና በመሰንቆ ተጫወተ::
*ስለ ፈጣሪው ክብሩን ተወ:: ከዳን እስከ ቤርሳቤህ የሚገዛ ኃያል ንጉሥ ነበርና:: በጽዮን ፊት እየወደቀ: እየተነሳ: እየታጠቀ: እየፈታ ሲዘምርም ሚስቱ ሜልኮል ናቀችው:: እግዚአብሔር ግን ከፍ ከፍ አደረገው:: (ሳሙ. 6:16)
+"+ ክብረ #ዳዊት +"+
=>እግዚአብሔር ስለ ዳዊት ሲል ኢየሩሳሌምን ብዙ ጊዜ ታድጉዋል:: ሰሎሞንና ሕዝቅያስን (ነገሥታቱን) ይቅር ያላቸው ስለ ባለሟሉ ስለ ዳዊት ነው::
*የሐዲስ ኪዳን የመጀመሪያዋ ቃል "የዳዊት ልጅ . . . " የምትል ናት:: (ማቴ. 1:1) ጌታችን "ወልደ ዳዊት" መባልን ወዷልና:: እንዲያውም ራሱ "እኔ የእሴይ ሥርና የዳዊት ዘር ነኝ" ሲል ተናግሯል:: (ራዕ. 22:16)
+"+ ዕረፍት +"+=>ነቢየ ጽድቅ: ልበ አምላክ ቅዱስ #ዳዊት እሥራኤልን ለ40 ዓመታት መርቶ አረጀ:: 'ምነው ያ ኃያል የእግዚአብሔር ሰው ቶሎ አረጀ?' ቢሉ ከገድሉ ጽናት ሰውነቱ ተቀጥቅጦ ነበርና::
*በዚያውም ላይ አንድ ቀን ስለ ሕዝበ አሥራኤል ቤዛ ይሆናቸው ዘንድ በቀሳፊ መልአክ ፊት ቆሞ ነበርና (ዜና. 21:16) ሰውነቱ ደከመ:: በዚህ ጊዜም ልጁን ሰሎሞንን አንግሦ በ70 ዓመቱ ከክርስቶስ ልደት ሺህ ዓመት በፊት ዐርፏል::
+"+ #ዳዊት በሰማይ +"+
=>በራዕየ ጐርጐርዮስ እንደ ተጻፈው ቅዱስ ዳዊትን በሰማይ 99ኙ ነገደ መላእክት ከበውት ያመሰግናል:: ከርሱ ዝማሬ ግርማ የተነሳ የሰማያት ግዘፋቸው ይናወጻል:: በገድለ አቡነ ኪሮስ እንደ ተጻፈው ደግሞ ቅዱሳን ነፍሳቸው ከሥጋቸው የምትለየው በዳዊት በገና ጣዕመ ዝማሬ ነው::
*በነገረ ማርያም ትምሕርት ደግሞ የቅዱስ ዳዊት ቤቱ ከልዑል አምላክ መንበር ሥር ነው::
*እንግዲህ ምን እላለሁ! ስለ ቅዱስ ዳዊት ከዚህም በላይ መጻሕፍት ብዙ ይላሉ:: ክብሩ ታላቅ ነውና::
<< በእውነት . . . በእውነት . . . በእውነት . . . ያለ ሐሰት ለዳዊት ክብርና ምስጋና ይገባል >>
=>+"+ እንግዲህ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎንና ስለ ባርቅ: ስለ ሶምሶንም: ስለ ዮፍታሔም: ስለ ዳዊትና ስለ ሳሙኤልም: ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛልና::
እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ:: ጽድቅን አደረጉ:: የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ:: የአንበሶችን አፍ ዘጉ:: የእሳትን ኃይል አጠፉ:: ከሰይፍ ስለት አመለጡ:: ከድካማቸው በረቱ:: በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ:: የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ:: +"+ (ዕብ. 11:32-35
✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞
✞ ወለወላዲቱ ድንግል ✞
✞ ወለመስቀሉ ክቡር አሜን ✞
"መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ::" /ማቴ
ዝክረ ቅዱሳንን ተማሩ ብለን እንለምናችኋለን!!።
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together.https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━━━
Comments
Post a Comment