✝✞✝ እንኩዋን ለእናታችን "ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ ገዳማዊት" ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✝✞✝
+*" ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ "*+
=>ቅድስቷ እናታችን በነገድ እሥራኤላዊ ስትሆን የተወለደችው ኢየሩሳሌም ውስጥ በ5ኛው መቶ ክ/ዘመን አካባቢ ነው:: ወላጆቿ ክርስቲያኖች በመሆናቸው በሚገባው ፈሊጥ አሳድገው ወደ ትምሕርት አስገቧት::
+አስተማሪዋ ገዳማዊ መነኮስ ነበርና ከተማ ውስጥ አያድርም:: አስተምሯት ዕለቱኑ ወደ በዓቱ ይመለስ ነበር እንጂ:: ዓመተ ክርስቶስ ብሉይ ከሐዲስ ጠንቅቃ ተማረች::
+አንድ ቀን እንደ ልማዷ ልትማር ብትጠብቀውም መምሕሯ ሊመጣ አልቻለም:: ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ መነኮሱን ልትጠይቅ : አንድም ልትማር ወደ በዓቱ ሔደች::
+በሩ ላይ ደርሳ ብታንኩዋኩዋም መልስም : የሚከፍትም አልነበረም:: ከውስጥ ግን ምርር ያለ የለቅሶ ድምጽ ተሰማት:: "ጌታ ሆይ! ይቅር በለኝ?" እያለ በተደጋጋሚ ይጮሃል:: ያ ደጉ መነኮስ ነበር::
+ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ በቅጽበት አንድ ሐሳብ መጣላት:: "እርሱ በንጽሕና እየኖረ ስለ ነፍሱ እንዲሕ ከተማጸነ እኔማ እንደምን አይገባኝ!" ብላ ወደ ቤቷ ተመለሰች:: የለበሰችውን ልብስ አልቀየረችም:: ቤተሰቦቿን አልተሰናበተችም:: ከቤቷ አተር በዘንቢል እና ውሃ በትንሽ እቃ ይዛ ወደ ጐልጐታ ገሰገሰች::
+ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር ላይ ወድቃ አለቀሰች:: ጸለየችም:- "ጌታ ሆይ! ነፍሴን ወደ ዕረፍት አድርሳት? ከክፉ ጠላትም ጠብቀኝ? ይሕንን አተርና ውሃ ለእድሜ ዘመን ሁሉ ባርክልኝ::"
+ይሕን ብላ እየፈጠነች ከኢየሩሳሌም ተነስታ በእግሯ ቃዴስን : ሲናይ በርሃን አቁዋርጣ ግብፅ ደረሰች:: ምርጫዋ ብሕትውና ሆኗልና ልምላሜ ከሌለበት : ፀሐዩ እንደ ረመጥ ከሚፋጅበት በርሃ ገባች::
+በዚያም ከያዘችው አተር ለቁመተ ሥጋ እየበላች : ከውሃውም በጥርኝ እየተጐነጨች : ማንንም ሰው ሳታይ : በፍጹም ተጋድሎ ለ38 ዓመታት ቆየች:: የቀኑ ሐሩር : የሌሊቱ ቁር (ብርድ) ልብሷን ቆራርጦ ቢጨርሰው እግዚአብሔር ፀጉሯን አሳድጐ አካሏን ሸፈነላት::
+ጊዜ ዕረፍቷ ሲደርስ የቅዱሳንን ዜና የሚጽፈው ታላቁ አባ ዳንኤል ወደ እርሷ ደረሰ:: እንዳያት ተከተላት:: እርሷ ግን በተሰነጠቀ አለት ውስጥ ገብታ ተደበቀች:: አባ ዳንኤል በውጪ ሆኖ ተማጸነ:- "እባክህ አባቴ! ውጣና ባርከኝ" አለ:: ሴት መሆኗን አላወቀም ነበርና:: እርሷ ግን "ራቁቴን ነኝና አልወጣም" አለችው::
+ልብሱን አውጥቶ ሰጥቷት ወጥታ ተጨዋወቱ:: በፈቃደ እግዚአብሔር ዜናዋን ሁሉ አወቀ:: ወደ በዓቷ ዘወር ሲል በዘንቢል የሞላ አተር ተመለከተ:: ለ38 ዓመታት ተበልቶ ዛሬም ሙሉ ነው:: አባ ዳንኤል ይፈትነው ዘንድ ከአተሩ በደንብ በላለት:: ከውሃውም ጠጣለት:: ግን ሊጐድል አልቻለም::
+እያደነቀ "እናቴ ሆይ! ልብሴን ውሰጂው" ቢላት "ሌላ አዲስ አምጣልኝ" አለችው:: ይዞላት በመጣ ቀን ግን ተሠውራለችና አላገኛትም::
+አንድ ቀን ግን (ማለትም ግንቦት 28) አረጋውያን መነኮሳት መጥተው የገጠማቸውን ነገር ነገሩት:: እንዲሕ ሲሉ:- "ሰው ተመልክተን ወደ በዓቱ ስንገባ አተር በዘንቢልና ውሃ በመንቀል አገኘን:: ስንበላው ወዲያው አለቀ::" አባ ዳንኤል ነገሩን ገና ሳይጨርሱለት አለቀሰ::
+አተሩ አለቀ ማለት ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ አርፋለች ማለት ነውና:: አረጋውያኑ ግን ቀጠሉ:- "ከበዓቱ ስንወጣ በጸጉሯ አካሏ ተሸፍኖ ወደ ምሥራቅ ሰግዳ አርፋ አግኝተን ከሥጋዋም ተባርከን ቀበርናት" አሉ:: አባ ዳንኤል ዜናዋን ጽፎላት ዛሬ ቤተ ክርስቲያን ታከብራታለች::
=>አምላካችን በቅድስት ዓመተ ክርስቶስ ጸሎት ይማረን:: ከበረከቷም ያድለን::
=>ግንቦት 28 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅድስት ዓመተ ክርስቶስ ተጋዳሊት (ገዳማዊት)
2.ቅዱስ ኤዺፋንዮስ ሊቅ (ሥጋው ቆዽሮስ የደረሰበት)
3.አባ መርቆሬዎስ ገዳማዊ
4.አባ ጌርሎስ (ጻድቅና ሰማዕት)
5."45" ሰማዕታት (የአባ ጌርሎስ ደቀ መዛሙርት)
6.ቅዱስ አጋቦስ ሰማዕት
=>ወርኀዊ በዓላት
1.አማኑኤል ቸር አምላካችን
2.ቅዱሳን አበው (አብርሃም : ይስሐቅና ያዕቆብ)
3.ቅዱስ እንድራኒቆስና ሚስቱ ቅድስት አትናስያ
4.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ (ሰማዕት)
=>+"+ ለእናንተም ጠጉርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጐናጸፍ በውጭ የሆነ ሽልማት አይሁንላችሁ:: ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ:: +"+ (1ዼጥ. 3:3)
<<< ወስብሐት ለእግዚአብሔር >>>
"ፍቅር ያጌብረኒ ከመ እንግር ዜናሆሙ ለቅዱሳን"የቅዱሳንን ዜና(ታሪክ)እንድመሰክር ፍቅር ያስገድደኛል::አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈሚስጥር
🔊ሁሉም እንዲያነበው invite shareያርጉ
መንፈሳዊ ፅሁፎች፣ስእሎች ካሎት
@FasilKFCይላኩልን
✝ኦርቶዶክስ ለዘላለም ትኑር
Join Us Today And Lets learn Together
https://gondarmaheber.blogspot.com
https://t.me/Be_ente_semoa_le_mareyam
━━━━━━━༺✞༻━━━━━
Comments
Post a Comment